በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓመፀኝነት መላቀቅ የቻልኩበት መንገድ

ከዓመፀኝነት መላቀቅ የቻልኩበት መንገድ

ከዓመፀኝነት መላቀቅ የቻልኩበት መንገድ

ጆሴ አንቶንዮ ኔብሬራ እንደተናገረው

አንድን ሰው ዓመፀኛ እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው? ከልጅነቴ ጀምሮ በደል ይደርስብኝ ስለነበር ስለ ዓመፅ ብዙ አውቃለሁ። አባቴ ጥብቅ ወታደራዊ ሥርዓት የሚከተለው የስፔን ሲቪል ዘብ አባል ነበር። አባቱ ብዙ ጊዜ ይገርፈው ስለነበር እሱም ልክ እንደዛው እኔን ይገርፈኝ ጀመር። አባቴ አብዛኛውን ጊዜ የሚገርፈኝ በወፍራም ቀበቶው ነበር። ይባስ ብሎም ለታናሽ እህቴ ከፍተኛ ፍቅር እያሳየ እኔን ግን በተደጋጋሚ ጊዜ ደደብ እያለ ይሰድበኝ ነበር። የአባቴን ቁጣ የምትፈራው እናቴም ብትሆን አባቴ በሚያደርስብኝ በደል የተነሳ የሚሰማኝን ብስጭት ለማብረድ ወይም የሚያስፈልገኝን ፍቅር ለመስጠት እምብዛም ያደረገችው ነገር አልነበረም።

በትምህርት ቤት ከሌሎች ልጆች ጋር ስሆን በጣም ደስተኛ ሆኜ ለመታየት እሞክር ነበር። እርግጥ ነው፣ ለሚመለከተኝ ሰው ደስተኛና ብሩሕ አመለካከት ያለኝ እመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ ደስታዬ የውሸት ነበር። በውስጤ ያለው ፍርሃትና ቁጣ እንዳይታወቅብኝ ስል የማደርገው ነበር። ወደ ቤት ማዝገም ስጀምር ግን ይህ ሁሉ ይቀርና የሚጠብቀኝን ስድብና ድብደባ እያሰብኩ በፍርሃት መራድ እጀምራለሁ።

ከዚህ ፍቅር የጠፋበት የቤተሰብ ሕይወት ለመሸሽ ስል በ13 ዓመቴ የካቶሊኮች አዳሪ ትምህርት ቤት ገባሁ። ለተወሰነ ጊዜ፣ ቄስ ለመሆን አስብ ነበር። ይሁን እንጂ የትምህርት ቤቱ ሕይወትም ቢሆን ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲኖረኝ አልረዳኝም። ከሌሊቱ 11 ሰዓት ተነስተን በቀዝቃዛ ውኃ ገላችንን መታጠብ ነበረብን። ሙሉውን ቀን የምናሳልፈው በጥናት፣ በጸሎትና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች ላይ በመካፈል ነበር፤ ፕሮግራሙ ምንም ውልፍት የማያደርግ ከመሆኑም ሌላ እረፍታችን በጣም አጭር ነበር።

ምንም እንኳን ተማሪዎች ስለ “ቅዱሳን” የሚገልጹ ታሪኮችን ማንበብ ይጠበቅባቸው የነበረ ቢሆንም በጥናታችን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ተካትቶ አያውቅም። በትምህርት ቤቱ የነበረው ብቸኛው መጽሐፍ ቅዱስም በመስታወት ሣጥን ውስጥ የተቀመጠ ሲሆን እሱን ለማንበብ ልዩ ፈቃድ ማግኘት ያስፈልገን ነበር።

አዳሪ ትምህርት ቤት በገባሁ በሦስተኛው ዓመት ላይ “መንፈሳዊ እንቅስቃሴ” ተብሎ የሚጠራው ራስን የመቅጣት ደንብ ከምንፈጽማቸው ጥብቅ ሃይማኖታዊ ልማዶች አንዱ ሆነ። ራሴን ለሕመም ብዳርግ ከዚህ ጣጣ እንደምገላገል ስላሰብኩ ቁንጣን እስኪይዘኝ ድረስ ለመብላት ሞክሬ ነበር። ይሁን እንጂ የቀየስኩት ዘዴ አላዋጣኝም። ሦስት ዓመት ሊሞላኝ አካባቢ ሁኔታውን መታገሥ ስላቃተኝ ከትምህርት ቤቱ አምልጬ ወደ ቤት ሄድኩ። በዚያን ጊዜ 16 ዓመቴ ነበር።

ጀብደኛ የመሆን ፍላጎት

ወደ ቤት ከተመለስኩ በኋላ የቦክስና የነፃ ትግል ስፖርት ጀመርኩ። ጭካኔ በሚንጸባረቅባቸው በእነዚህ ስፖርቶች ያገኘሁት ስኬት ተፈላጊ ሰው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አደረገኝ፤ ይሁን እንጂ አካላዊ ጥንካሬዬ ልክ እንደ አባቴ የፈለግሁትን ሁሉ ለማግኘት በጉልበት እንድጠቀም የልብ ልብ ሰጠኝ።

በ19 ዓመቴ ግን በሕይወቴ ውስጥ መጠነኛ የርኅራኄ ስሜት እንዳሳይ የሚያደርገኝ አንድ ነገር ተከሰተ። በዚህ ጊዜ ከኢንካርኒታ ጋር የተዋወቅሁ ሲሆን ከዘጠኝ ወር በኋላ ተጋባን። ለሰዉ ጨዋ፣ ደግና ደስተኛ መስዬ ስለምታይ እሷ ያየችው የውጪውን እንጂ ውስጤ የሚታገለኝ ስሜት እንዳለ አልተረዳችም ነበር። የመጀመሪያ ልጃችን ተወልዶ ብዙም ሳይቆይ ወታደራዊ አገልግሎት እንድሰጥ ስጠራ ውስጤ የታመቀው ምሬት ይፋ የሚወጣበት አጋጣሚ ተፈጠረ።

በአንድ በኩል የወታደሮችን የፀጉር አቆራረጥ እጠላው ስለነበር በሌላ በኩል ደግሞ ጀብዱ መሥራት ስለሚያስደስተኝ በባዕድ አገር በተሰማራው የስፔን ክፍለ ጦር ውስጥ ለማገልገል ራሴን በፈቃደኝነት አቀረብኩ። በሞሮኮ በረሃ ሳገለግልና አደገኛ ተልእኮዎችን ስፈጽም ውስጤ ከሚታገለኝ ስሜት ነፃ እንደምሆን ታይቶኝ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ካለብኝ የቤተሰብ ኃላፊነት ማምለጫ መንገድ የማገኝ መስሎኝ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ችግሬ እየተባባሰ መጣ እንጂ ምንም አልተጠቀምኩም።

ብዙም ሳይቆይ አዳዲስ ቅጥረኞችን በማሠቃየት ከሚደሰት አንድ ግዙፍና ጨካኝ መኮንን ጋር ተጋጨሁ። ፍትሕ ሲዛባ መመልከት እጅግ የሚያንገሸግሸኝ ከመሆኑም በላይ ትክክል መስሎ ለታየኝ ነገር ከመታገል ወደኋላ አልልም ነበር። አንድ ቀን ጠዋት በስም ጥሪ ሰዓት አንድ ቀልድ ጣል ሳደርግ መኮንኑ በተሳሳተ መንገድ ተረዳኝ። ሊመታኝ ሲሰነዝር እጁን ጠምዝዤ ወለል ላይ ዘረርኩት። ብለቀው ሽጉጡን ይተኩስብኛል ብዬ ስለፈራሁ እጁን ከመሬት ጋር አጣብቄ ያዝኩት።

በዚህም የተነሳ ቅጣት ከሚቀበሉ ሌሎች ወታደሮች ጋር እንድቀላቀል ተደረግሁ። በአንዲት ትንሽ ወና ክፍል ውስጥ 30 ከሚሆኑ ሰዎች ጋር ለሦስት ወር ቆየሁ። በዚህ ሁሉ ጊዜ ልብሴን እንኳ መቀየር አልቻልኩም። እዚያ የተመደበው መኮንን ሰዎችን እየገረፈ በማሠቃየት የሚደሰት ሰው ነበረ። በአንድ ወቅት ግን ጫፌን ቢነካኝ እንደምገድለው ስዝትበት ቅጣቴን ከ30 ግርፋት ወደ 3 ግርፋት ቀነሰልኝ። እኔም እንደሚያሠቃዩኝ ሰዎች ኃይለኛ እየሆንኩ መጣሁ።

ሚስጥራዊ ተልእኮዎች

በባዕድ አገር በተሰማራው ክፍለ ጦር ውስጥ በሥልጠና ላይ እያለሁ የበለጠ “ጀብዱ” በሚጠይቁ ተልእኮዎች ለመካፈል ምንም ሳላመዛዝን ራሴን አቀረብኩ። በዚህ ጊዜም ቢሆን ይህ ውሳኔዬ ምን ውጤት እንደሚያስከትል የማውቀው ነገር አልነበረም። የኮማንዶ ሥልጠና የተሰጠኝ ሲሆን የተለያዩ ዓይነት የጦር መሣሪያዎችንና ፈንጂዎችን እንዴት መጠቀም እንዳለብኝ ተማርኩ። ኮርሱን ለማጠናቀቅ ቨርጂኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ወደሚገኘው ወደ ላንግሌይ ተላክሁ፤ በዚያም ከሲ አይ ኤ አባላት ጋር ሥልጠና ወሰድኩ።

ብዙም ሳይቆይ ሚስጥራዊ ተልእኮ የሚፈጽም የአንድ የኮማንዶ ቡድን አባል ሆንኩ። በ1960ዎቹ ውስጥ በልዩ ልዩ ሚስጥራዊ ተልእኮዎች ተሳትፌ ነበር። በማዕከላዊና በደቡብ አሜሪካ ዕፅ አዘዋዋሪዎችንና ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ነጋዴዎችን አድኖ ለመያዝ በተደረጉት ጥረቶች ላይ ተካፍያለሁ። እነዚህን ሰዎች ካገኘናቸው “እንድናስወግዳቸው” እንታዘዝ ነበር። እንዲህ በመሰሉት ተልእኮዎች ላይ መሳተፌ በጣም ያሳፍረኛል። መረጃ እንዲያወጡ ለመመርመር ከምንፈልጋቸው ሰዎች በቀር በሕይወት የምናስቀረው አንድም ሰው አልነበረም።

በኋላም የጄኔራል ፍራንኮን አምባገነናዊ አገዛዝ የማይደግፉ የስፔን ወታደራዊ መሪዎች እነማን እንደሆኑ ለማወቅ በእነሱ ላይ ስለላ እንዳካሂድ ተመደብኩ። በተጨማሪም በፈረንሳይ የሚኖሩ የጄነራል ፍራንኮን አገዛዝ የሚቃወሙ ሰዎችን ሰልለናል። የስለላው ዓላማ ቀንደኛ የመንግሥት ተቃዋሚዎችን አፍኖ ወደ ስፔን መውሰድ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም የሚወሰዱት ሊገደሉ ነበር።

የመጨረሻው ተልእኮዬ በአንዲት ትንሽ የአፍሪካ አገር ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ቅጥረኛ ወታደሮችን ማደራጀት ነበር። በዋናው ከተማ ባሉት የጦር ሠፈሮች ላይ ወረራ እንድናካሂድና የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት በቁጥጥር ሥር እንድናውል ታዝዘን ነበር። በታቀደው መሠረት እኩለ ሌሊት ላይ አገሪቱን በመውረር ተልእኳችንን በአራት ሰዓት ውስጥ አጠናቀቅን። በውጊያውም ከእኛ ወገን ሦስት “ከጠላት” ወገን ደግሞ ብዙ ወታደሮች ሞተዋል። እኔም በግድያው ላይ ተካፍያለሁ።

ይህ ዘግናኝ ሁኔታ ሕሊናዬን ያሠቃየኝ ጀመር። ብዙ ጊዜ ቅዠት ስለሚያስቸግረኝ እንቅልፍ አይወስደኝም ነበር። ጠላቶቼን በጨበጣ ውጊያ ስፈጃቸውና ልገድላቸው ስል ፊታቸው ላይ የሚነበበው የፍርሃት ስሜት በሕልሜ ይመጣብኛል።

ከዚያ በኋላ ሌላ ተልእኮ ላለመቀበል ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። ስለዚህ ሰነዶቼን ሁሉ ለጦር ኃይሉ መለስኩኝና መልቀቂያ አገኘሁ። ይሁን እንጂ ከሦስት ወራት በኋላ አለቆቼ ሌላ የስለላ ሥራ እንዳከናውን ጠሩኝ። እኔ ግን ወደ ስዊዘርላንድ ሸሽቼ ሄድኩ፤ በሚስጥራዊ የስለላ ሥራ እካፈል እንደነበር የማታውቀው ባለቤቴ ኢንካርኒታ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ወደ ባስል ከተማ መጥታ አብረን መኖር ጀመርን።

መጥፎ አመል ቶሎ አይለቅም

በጦር ኃይል ውስጥ ባገለገልኩባቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ ኢንካርኒታ በስፔን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር። ስለ አምላክ እውነቱን እንዳወቀች በአድናቆት ስትነግረኝ እኔም የማወቅ ጉጉት አደረብኝ። ጊዜ ሳናጠፋ በስዊዘርላንድ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ፈልገን ካገኘናቸው በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ ማጥናት ጀመርን።

ስለ አምላክ ዓላማዎች ሳውቅ እጅግ ደስ አለኝ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወቴን መምራት ብፈልግም በተለይ የግልፍተኝነት ባሕርዬን መለወጥ ከባድ ሆነብኝ። ያም ሆኖ አዲሱን እምነቴን እወደው ነበር። ለጥቂት ወራት ካጠናሁ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚያደርጉት እኔም ከቤት ወደ ቤት ለመስበክ ዝግጁ እንደሆንኩ እርግጠኛ ሆኜ ነበር።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በይሖዋ እርዳታ ራሴን መግዛት የተማርኩ ሲሆን ቆየት ብሎም እኔም ሆንኩ ኢንካርኒታ ተጠመቅን። በ29 ዓመቴ በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ።

በ1975 ወደ ስፔን ለመመለስ ወሰንን። ይሁን እንጂ የጦር ኃይሉ አልረሳኝም ነበር፤ እናም በአንድ ልዩ ተልእኮ ላይ እንድካፈል ተጠራሁ። ከዚህ ችግር ለማምለጥ እንደገና ወደ ስዊዘርላንድ ሸሸሁ። በ1996 ወደ ስፔን እስከተመለስኩበት ጊዜ ድረስ ቤተሰቤን ይዤ በስዊዘርላንድ ኖርኩ።

በአሁኑ ጊዜ ትዳር የያዙ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ ያሉኝ ሲሆን ሁለት የልጅ ልጆችም አይቻለሁ፤ ሁሉም ይሖዋን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክር ሆኜ ባሳለፍኳቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ ቀደም ሲል በሰሜናዊ ስፔን በሚካሄድ የጎዳና ተቃውሞ ላይ ይካፈል የነበረን አንድ ወጣት ጨምሮ 16 ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ መርዳት ችያለሁ። ይህም ከፍተኛ እርካታ አምጥቶልኛል።

ቀደም ሲል ያሳለፍኩትን በዓመፅ የተሞላ ሕይወት ለመርሳትና እየተመላለሰ ከሚረብሸኝ ቅዠት ለመገላገል በማደርገው ጥረት አምላክ እንዲረዳኝ በተደጋጋሚ ጊዜ ጸልያለሁ። ትክክለኛውን እርምጃ ለመውሰድ ትግል በማደርግበት ጊዜ በ⁠መዝሙር 37:5 ላይ ያለውን “መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል” የሚለውን ምክር ተከትያለሁ። ይሖዋም የገባውን ቃል ጠብቋል። የዓመፀኝነት ባሕርዬን እንዳስተካክል ረድቶኛል። ይህ ደግሞ ለእኔም ሆነ ለቤተሰቤ ትልቅ በረከት ሆኖልናል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ13 ዓመቴ አዳሪ ትምህርት ቤት ስገባ የተነሳሁት

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1968 መልቀቂያ ካገኘሁ በኋላ የጦር ኃይሉን ተሰናብቼ ስወጣ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቴ ከኢንካርኒታ ጋር