በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለእኔ የሚሆኑ ጓደኞች እንዴት ማግኘት እችላለሁ?

ለእኔ የሚሆኑ ጓደኞች እንዴት ማግኘት እችላለሁ?

የወጣቶች ጥያቄ

ለእኔ የሚሆኑ ጓደኞች እንዴት ማግኘት እችላለሁ?

“ዕድሜዬ 21 ዓመት ሲሆን በአካባቢዬ የእኔ እኩያ የሆኑ ወጣቶች እምብዛም የሉም። ስለዚህ ጊዜዬን የማሳልፈው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ከሆኑ ታናናሾቼ ወይም ባለትዳር ከሆኑ ሰዎች ጋር ነው። ተማሪዎቹን የሚያሳስባቸው የፈተና ጉዳይ ሲሆን ባለትዳሮቹን የሚያስጨንቃቸው ደግሞ የቤት ጉዳይ ነው። እነሱን እንቅልፍ የሚነሷቸው ነገሮች እኔን አይመለከቱኝም። ለእኔ የሚሆኑ ጓደኞች ባገኝ በጣም ጥሩ ነበር!”​—ካርሜን *

ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ቢገኝ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይፈልጋል። አንተም እንደዚህ እንደሚሰማህ ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ሰዎች ከነመፈጠርህ ረስተውህ ሲያገሉህና ሲዘጉህ በሌላ አባባል የ15 ዓመቷ ማይኬለ እንደተናገረችው “ዞር ብሎ የሚያይህ ሰው ሲጠፋ” በጣም የምትጎዳው ለዚህ ነው።

እርግጥ ነው፣ ክርስቲያን ከሆንክ “መላው የወንድማማች ማኅበር” ስላለልህ ለአንተ የሚሆን ጓደኛ ማግኘት አያስቸግርህም። (1 ጴጥሮስ 2:17) እንደዚያም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ ከማናቸውም ጋር እንደማትገጥም ይሰማህ ይሆናል። “ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ወደ ቤት ስመለስ መኪና ውስጥ ከኋላ ቁጭ ብዬ አለቅሳለሁ” በማለት የ20 ዓመቷ ሄለና ተናግራለች። “ለእኔ የሚሆን ጓደኛ ለማግኘት በጣርኩ መጠን እንደጠበቅኩት ስለማይሆንልኝ ይበልጥ አዝናለሁ።”

ለአንተ የሚሆን ጓደኛ እንዳጣህ የሚሰማህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት (1) ጓደኛ አይሆኑኝም ብለህ የምታስባቸው ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ እና (2) ከእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር አብረህ ስትሆን አብዛኛውን ጊዜ ምን እንደምታደርግ ለይተን እንወቅ።

ጓደኛ ሊሆኑኝ አይችሉም ብለህ ከምታስባቸው ሰዎች አጠገብ አድርግ።

1. ዕድሜ

□ እኩዮቼ □ ከእኔ ከፍ ያሉ □ ትልልቅ ሰዎች

2. ችሎታ

□ ስፖርተኞች □ ተሰጥኦ ያላቸው □ ምሑራን

3. ባሕርይ

□ በራሳቸው የሚተማመኑ □ ተወዳጅ የሆኑ □ የራሳቸው ቡድን ያላቸው

አሁን ደግሞ ከላይ ምልክት ካደረግክባቸው ሰዎች ጋር ስትሆን አብዛኛውን ጊዜ የምታደርገውን ነገር ከሚገልጸው ዓረፍተ ነገር አጠገብ አድርግ።

□ ከእነሱ ጋር ተመሳሳይ ዝንባሌ ወይም ችሎታ እንዳለኝ አስመስላለሁ።

□ የእነሱን ዝንባሌ ከቁብ ሳልቆጥር የራሴን ብቻ አወራለሁ።

□ ሹልክ ብዬ ለመውጣት አጋጣሚውን እስካገኝ ምንም ትንፍሽ ሳልል እቆያለሁ።

ለጓደኝነት አይመቹኝም የምትላቸው ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑና ከእነሱም ጋር ስትሆን ምን ታደርግ እንደነበር ለይተህ አውቀሃል። አሁን የቀረን አንድ ነገር ነው፤ ይህም ሁኔታውን ለማሻሻል የሚያስችልህን መንገድ መጠቆም ነው። ከዚያ በፊት ግን ልታውቃቸውና ልትጠነቀቅባቸው የሚገቡ ከሌሎች ጋር እንዳትቀላቀል እንቅፋት የሚሆኑብህ መሰናክሎች አሉ።

መሰናክል 1፦ ራስን ማግለል

ችግሩ ምን ይሆን? ከአንተ የተለየ ዝንባሌ ወይም ተሰጥኦ ካላቸው ሰዎች ጋር ስትሆን ከሰው የማትገጥመው አንተ እንደሆንክ ቢሰማህ ምንም አይደንቅም፤ በተለይ ደግሞ ዓይናፋር ከሆንክ እንዲህ ያለ ስሜት ቶሎ ሊያድርብህ ይችላል። “ጨዋታ ማምጣት የሚለውን ነገር ሳስበው ራሱ ያስጠላኛል” በማለት የ18 ዓመቷ አኒታ ትናገራለች። “የማይሆን ነገር ብናገርስ ብዬ እፈራለሁ” ብላለች።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ራሱን የሚያገል ሰው የራስ ወዳድነት ምኞቱን ለማሟላት ይሻል፤ ጥበብንም ሁሉ ይቃወማል።” (ምሳሌ 18:1 NW) ራስን ማግለል ነገሮችን ከማባባስ ውጪ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው። እንዲያውም ራስህን የምታገል ከሆነ ማቆሚያ የሌለው እሽክርክሪት ውስጥ ትገባለህ፦ ብቸኝነት ሲሰማህ ለአንተ የሚሆን ጓደኛ እንደሌለ ታስባለህ፤ በዚህ ጊዜ ከሌሎች መሸሽ ትጀምራለህ። ይህ ደግሞ ብቸኝነት እንዲሰማህ ያደርግሃል፤ ብቸኝነት ሲሰማህ ደግሞ ለአንተ የሚሆን ጓደኛ እንደሌለ ማሰብ ትጀምራለህ፤ . . . አንድ ነገር ካላደረግህ ከዚህ እሽክርክሪት መውጣት አትችልም!

“ሰዎች ልብን ማንበብ አይችሉም። ካልተናገርክ የምትፈልገውን አታገኝም። ከሌሎች ጋር የማትቀላቀል ከሆነ ምንም ጓደኛ ማፍራት አትችልም። የተወሰነ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። እንዲህ ማድረግ የሌላው ሰው ኃላፊነት እንደሆነ ማሰብ ትክክል አይደለም። ጓደኝነት ሲባል መቀበል ብቻ ሳይሆን መስጠትንም ይጠይቃል።”​ሜሊንደ፣ 19

መሰናክል 2፦ መጓጓት

ችግሩ ምን ይሆን? አንዳንድ ሰዎች ጓደኛ ለማግኘት ካላቸው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ያለ ጓደኛ ከመቅረት ከተገኘው ጋር ጓደኛ መሆን ይሻላል በሚል ከማይሆኑ ሰዎች ጋር ይገጥማሉ። “በትምህርት ቤት ውስጥ ታዋቂ ከሆነ አንድ ቡድን ጋር መቀላቀል ባለመቻሌ በጣም ይሰማኝ ስለነበር ችግር ውስጥ ገብቼም ቢሆን በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት እስከ መመኘት ደርሼ ነበር” በማለት የ15 ዓመቷ ረኔ ትናገራለች።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የተላሎች ባልንጀራ . . . ጕዳት ያገኘዋል” ወይም አዲስ ዓለም ትርጉም እንዳስቀመጠው “ከሞኞች ጋር የሚቀራረብ . . . ጉዳት ይደርስበታል።” (ምሳሌ 13:20) በዚህ ጥቅስ ላይ “ተላሎች” ወይም “ሞኞች” የተባሉት ቃል በቃል ምንም የማያውቁ እንደሆኑ አድርገህ አታስብ። እንዲያውም በጣም ጎበዝ ተማሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ደንታ ቢስ ከሆኑ በአምላክ ዓይን ሞኞች ናቸው። ከእነሱ ጋር ለመቀላቀል ስትል እንደ እስስት የምትለዋወጥ ከሆነ ትርፉ ራስህን መጉዳት ብቻ ነው።​—1 ቆሮንቶስ 15:33

“የተገኘው ሁሉ ጥሩ ጓደኛ ይሆናል ማለት አይደለም። ከእነሱ ጋር ስትሆን ማንነትህን መለወጥ እንዳለብህ እንዲሰማህ ከሚያደርጉ ጋር ጓደኛ መሆን አትፈልግም። ጓደኛ ማድረግ የምትፈልገው ከልብ የሚወዱህንና በችግርህ ጊዜ ከጎንህ የሚሆኑትን ነው።”​—ፖላ፣ 21

ቅድሚያውን ውሰድ

ሌሎች ወደ አንተ መጥተው ከእነሱ ጋር እንድትቀላቀል እስኪጋብዙህ ድረስ አትጠብቅ። የ21 ዓመቱ ጂን “ሁልጊዜ ሰዎች ቅድሚያውን ወስደው ከእኛ ጋር እንዲተዋወቁ መጠበቅ የለብንም” ብሏል። “እኛ ራሳችን ሌሎችን ለመቅረብ ጥረት ማድረግ አለብን።” ቀጥሎ የቀረቡት ሁለት የመፍትሔ ሐሳቦች ይህን እንድታደርግ ይረዱሃል፦

ከአንተ የዕድሜ ክልል ውጪ ያሉ ሰዎችን ለማየት ዓይንህን ክፈት። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ዮናታንና ዳዊት በመካከላቸው ወደ 30 ዓመት የሚጠጋ የዕድሜ ልዩነት የነበራቸው ይመስላል፤ ያም ሆኖ ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን እንዳስቀመጠው ዳዊትና ዮናታን “በጣም የሚዋደዱ ጓደኛሞች” * ነበሩ። (1 ሳሙኤል 18:1) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ከትልልቅ ሰዎችም ጋር ጓደኛ መሆን ይቻላል! እስቲ አስበው፣ በአንተ ዕድሜ ላይ የሚገኙትን ካልሆነ በስተቀር ማንንም ጓደኛ ላለማድረግ ራስህን ገድበህ ስታበቃ ጓደኛ አላገኘሁም ብለህ ብታማርር ምን ይባላል? የሚበሉ ዓሦች የሞሉበት ባሕር በከበበው በረሃማ ደሴት ላይ ሆነህ በረሃብ እንደ መሞት ነው! እውነቱን ለመናገር ጓደኛ ሊሆኑህ የሚችሉ ጥሩ ሰዎች በዙሪያህ አሉ። እንደነዚህ ያሉ ጓደኞችን ለማግኘት የሚያስችልህ አንዱ መንገድ ከአንተ የዕድሜ ክልል ውጪ ያሉ ሰዎችን ለማየት ዓይንህን መክፈት ነው።

“እናቴ በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ ትልልቅ ሰዎች ጋር ጭውውት ለመጀመር ጥረት እንዳደርግ አበረታታችኝ። ላወራቸው የምችለው ብዙ ነገር እንዳለኝ ሳውቅ እንደምገረም ነገረችኝ። እናቴ ልክ ነበረች፤ አሁን ብዙ ጓደኞች አሉኝ!”​—ሄለና፣ 20

ተግባቢ ለመሆን ጥረት አድርግ። በተለይ ዓይናፋር ከሆንክ ከሌሎች ጋር መጨዋወት ጥረት ይጠይቅብሃል። ይሁን እንጂ ልታደርገው ትችላለህ። ለዚህ ቁልፉ (1) ማዳመጥ፣ (2) ጥያቄ መጠየቅ እና (3) ልባዊ አሳቢነት ማሳየት ነው።

“ከማውራት ይልቅ አዳማጭ ለመሆን እጥራለሁ። ስናገር ደግሞ ስለ ራሴ ላለማውራት ወይም ስለ ሌሎች አፍራሽ ነገር ላለመናገር እሞክራለሁ።”​—ሴሬና፣ 18

“አንድ ሰው እኔ ስለማላውቀው ነገር ማውራት ከጀመረ አንዳንድ ነገሮችን እንዲያብራራልኝ እጠይቀዋለሁ፤ ይህ ደግሞ የበለጠ እንዲያወራልኝ ያነሳሳዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።”​—ጃረድ፣ 21

ምናልባት በተፈጥሮህ ቁጥብ ልትሆን ትችላለህ፤ ይህ በራሱ ምንም ችግር የለውም። ሲናገር አፍ የሚያስከፍት ዓይነት ሰው መሆን አያስፈልግህም! ይሁን እንጂ ከሌሎች ጋር መቀላቀል እንደሚከብድህ ከተሰማህ በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡትን የመፍትሔ ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር። አንተም እንደ ሊያ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ብላለች፦ “ዓይናፋር ስለሆንኩ ጭውውት ለመጀመር ራሴን ማስገደድ አለብኝ። ነገር ግን ጓደኞች ለማፍራት ተግባቢ መሆን አለብህ። ስለዚህ የግዴን አወራ ጀመር።”

www.watchtower.org/​ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.29 ዳዊት ከዮናታን ጋር ጓደኝነት ሲጀምር በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ወጣት ሳይሆን አይቀርም።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

“በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስገኝ ያን ያህል ከማልቀርባቸው መካከል ቢያንስ አንዱን ለማነጋገር እሞክራለሁ። ሰላምታ መስጠት በራሱ ወዳጅነት ለመመሥረት በር እንደሚከፍት ተገንዝቤያለሁ!”

“ለመቀራረብ ምንም ጥረት ሳያደርጉ ‘ሰዎች ስለማይወዱኝ ከእነሱ ጋር መቀላቀል አልችልም’ ብሎ ማሰብ ቀላል ነው። ችግሩን ለመፍታት ግን ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። አንድ ሰው ቀዳሚ ሆኖ እርምጃ መውሰዱ የኋላ ኋላ የሚክሰው ሲሆን መንፈሰ ጠንካራ እንዲሆንም ይረዳዋል።”

“ቀስ በቀስ ከአዋቂዎች ጋር መጨዋወት ጀመርኩ። መጀመሪያ ላይ ጭንቅ ይለኝ ነበር! ዞሮ ዞሮ ግን የተጠቀምኩት እኔ ነኝ፤ ምክንያቱም ገና በወጣትነቴ ምንጊዜም በችግሬ የሚደርሱልኝ የዕድሜ ልክ ጓደኞች ማፍራት ችያለሁ።”

[ሥዕሎች]

ሎረን

ሬዮን

ካሪሰ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ወላጆችህን ለምን አትጠይቃቸውም?

በእኔ ዕድሜ ሳላችሁ የሚስማማችሁን ጓደኛ ማግኘት ይቸግራችሁ ነበር? ጓደኛ ለማድረግ የሚከብዷችሁ እንዴት ያሉ ሰዎች ነበሩ? ችግሩን ለመፍታት ምን አደረጋችሁ?

․․․․․

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዠ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ማቆሚያ የሌለው የብቸኝነት እሽክርክሪት

ብቸኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል፤ ይህ ደግሞ . . .

. . . ከሰዎች እንደተገለልኩ እንዲሰማኝ ያደርገኛል፤ ይህ ደግሞ . . .

. . . ከሌሎች እንድሸሽ ያደርገኛል፤ በዚህ ጊዜ . . .