በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስደናቂ ውበትና ግርማ ሞገስ

አስደናቂ ውበትና ግርማ ሞገስ

አስደናቂ ውበትና ግርማ ሞገስ

“ፈረሶችን ገና ሳያቸው ነው የወደድኳቸው። በጣም ውብ ከመሆናቸውም ሌላ ለየት ያለ ግርማ ሞገስ አላቸው።”​—ቶማሽ፣ የፈረስ እርባታ ባለሙያ

ብዙዎች፣ ፈረሶች በውበታቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው እንስሳት እንደሆኑ ይሰማቸዋል። የፊት እግሮቻቸውን አንስተው በኋላ እግሮቻቸው ሲቆሙ፣ በኮቴያቸው መሬቱን ሲጎደፍሩ፣ በኩራት ሲያናፉና ደረታቸውን ነፍተው በልበ ሙሉነት ሲጋልቡ የሚታየው የታመቀ ኃይልና ግርማ ሞገሳቸው ተወዳጅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በእርግጥም ፈረሶች በጣም የሚያምሩ እንስሳት ናቸው።

ባለፉት ዘመናት ሁሉ በተለያዩ የአየር ሁኔታዎችና መልክዓ ምድሮች በርካታ የፈረስ ዝርያዎችን ማስገኘት ተችሏል። ከሌላ ዝርያ ጋር ያልተዳቀለው የአረብ ፈረስ በውበታቸው ተወዳዳሪ ከሌላቸው ዝርያዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይታመናል። ይህ የፈረስ ዝርያ ከፍተኛ ጉልበት፣ ፍጥነት፣ ጥንካሬና ማስተዋል ስላለው ለስፖርት ተመራጭ ነው።

የሚገርመው ነገር፣ በማዕከላዊ አውሮፓ የምትገኘው ፖላንድ የአረብ ፈረስ ዝርያዎችን በማራባት ረገድ የረጅም ዘመን ታሪክ አላት። ፈረስ አርቢዎችና በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ እጅግ ተፈላጊ ከሆኑትና ምርጥ ዝርያ ካላቸው የአረብ ፈረሶች መካከል አንዳንዶቹ ከፖላንድ የተገኙ እንደሆኑ ያምናሉ። እንዲህ የሚሉት ለምንድን ነው? ይህንን እና ሌሎች መሰል ጥያቄዎችን ለፈረስ አርቢዎችና በመስኩ ለተሰማሩ ባለሙያዎች አቅርበንላቸው ነበር።

ፈረስ አፍቃሪዎች ስለዚህ ዝርያ ምን ይሰማቸዋል?

እስቲ በመጀመሪያ ከሌላ ዝርያ ጋር ያልተዳቀለውን የአረብን ፈረስ በተመለከተ ትንሽ እናውራ። ይህ ዝርያ የሚነሳው ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ተያይዞ ነው። የፈረስ እርባታ ባለሙያ የሆነው ቶማሽ እንዲህ ይላል፦ “የበደዊን ጎሣዎች ለበርካታ ዘመናት ምርጥ የሆኑትን የአረብ ፈረሶች እየለዩ ያራቡ ከመሆኑም ባሻገር ዝርያቸው ከሌላ ጋር ሳይዳቀል ተጠብቆ እንዲቆይ አድርገዋል። እነዚህ ጎሣዎች የሚያራቧቸውን ፈረሶች በከፍተኛ ጥንቃቄ በመምረጥና ጥሩ አድርገው በመንከባከብ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን የአረብ ፈረስ ዝርያ ማስገኘት ችለዋል። የፈረሶቹ ቀለም አብዛኛውን ጊዜ ግራጫና ቀይ ቡኒ ሲሆን አልፎ አልፎ ደግሞ ጥቁር ሊሆን ይችላል።”

የአረብ ፈረስ ዝርያ አርቢ የሆነችው ሻኔታ እንደገለጸችው “እነዚህ ፈረሶች እጅግ በጣም ውብ ከመሆናቸውም ባሻገር ከሌላ ዘር ጋር ጨርሶ ያልተዳቀሉና ከፈረስ ዝርያዎች ሁሉ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ እንደሆኑ ይታሰባል።” ከኃይለኝነታቸው በተጨማሪ በድፍረታቸውና በጥንካሬያቸው የታወቁ ናቸው። የአረብ ፈረስ ዝርያዎች ሰፊ ደረትና ጠንካራ ሳንባ ያላቸው በመሆኑ ረጅም ርቀት ለመጓዝ ተመራጭ ሊሆኑ ችለዋል።

ከአረብ አገር ወደ ፖላንድ

በፖላንድ ፈረስ አርቢ የሆነውን ቶማሽን “የአረብ ፈረሶች ወደ ፖላንድ እንዴት ሊመጡ ቻሉ?” ብለን ጠየቅነው። “ፈረሶቹን መጀመሪያ ያመጣቸው በ16ኛው መቶ ዘመን በስታምቡል ወደነበረው ሱልጣን ቤተ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ይመላለስ የነበረ አንድ የንጉሡ መልእክተኛ ሊሆን ይችላል” በማለት ገለጸልን። “በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ነገር በፖላንድ ከ18ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ጀምሮ [የፈረስ] እርባታ ፕሮግራም የነበረ መሆኑን ነው።” ኢዛቤላ ፓቬሌትስዛቫትስካ የተባለች የአረብ ፈረስ ዝርያ እርባታ ባለሙያ፣ ቫትስዋፍ ዠቩስኪ የተባሉ መስፍን በዚህ ረገድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበረ ትናገራለች። እኚህ መስፍን የሩቅ ምሥራቅ አገሮችን ባሕል ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው “ከአረብ ፈረሶችን ለማምጣት የተደረጉትን ጉዞዎች ከመምራትም አልፈው አደራጅተዋል።” መስፍኑ ከሌላ ዘር ጋር ያልተዳቀሉ 137 ፈረሶችን ወደ አውሮፓ አምጥተዋል።

ዠቩስኪ በጽናትና በትጋት ያከናወኑት ሥራ በ1817 በምሥራቅ ፖላንድ በምትገኘው በያኑፍ ፖድላስኪ፣ የመጀመሪያው የፖላንድ የአረብ ፈረሶች ማራቢያ ማዕከል እንዲቋቋም አስችሏል። ቶማሽ “አጀማመሩ ተስፋ ሰጪ ነበር። ጥሩ ችሎታ ያላቸው አርቢዎች ለፈረሶቹ እንክብካቤ ያደርጉ ነበር” ብሏል። “ይሁን እንጂ ማዕከላዊውን አውሮፓ ያናወጡት ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በፖላንድ በነበሩት የፈረስ እርባታ ማዕከሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሱ። አብዛኞቹ ፈረሶች ሞቱ፣ ማዕከሉን ትተው ተሰደዱ አሊያም ተሰረቁ።” ይሁንና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙም ሳይቆይ የፈረስ እርባታው ፕሮግራም እንደገና ተጀመረ።

በአሁኑ ጊዜ በፖላንድ ቢያንስ 30 የሚሆኑ የአረብ ፈረሶች ማራቢያ ማዕከሎች አሉ። በፖላንድ ሁለት መቶ ዓመታት ያስቆጠረ ፈረስ የማርባት ልማድ መኖሩ ጥራት ያላቸው ፈረሶች እንዲገኙ አድርጓል። በዚህም ምክንያት ፖላንድ ከዋና ዋናዎቹ የአረብ ፈረስ ዝርያዎች ማራቢያ ማዕከላት አንዷ ለመሆን በቅታለች። በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለሙያዎችና ፈረስ አድናቂዎች በዚህ አገር በሚደረጉት ታዋቂ የሆኑ ዓመታዊ የፈረስ ትርዒቶችና ጨረታዎች ላይ ለመገኘት ከመላው ዓለም ይጎርፋሉ።

ለአረብ ፈረሶች የሚደረገው ዕለታዊ እንክብካቤ

ከሌሎች ዝርያዎች ጋር ያልተዳቀሉና ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ፈረሶችን ለማርባት እንስሳቱ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማቅረብ ያስፈልጋል። ማውጎርዣታ የተባለች የፈረስ ማራቢያ ባለቤት እንዲህ ብላለች፦ “የአረብ ዝርያ የሆኑ ፈረሶች ከፍተኛ እንክብካቤ ይፈልጋሉ። ኃይለኛ የሆነው ይህ የፈረስ ዝርያ ምንጊዜም ጥሩ የአካል ብቃትና ቁመና እንዲኖረው የተመጣጠነ የአመጋገብ ፕሮግራም ማዘጋጀት ያስፈልገናል። የደረሱ እርጉዝ ባዝራዎች ልዩ ትኩረት ይፈልጋሉ።” * ለአረብ የፈረስ ዝርያ ተስማሚ የሆነው ምግብ እንዴት ያለ ነው?

ማውጎርዣታ በመቀጠል እንዲህ ብላለች፦ “ማለዳ ላይ ለፈረሶቹ ድርቆሽ እንሰጣቸዋለን፤ ድርቆሹ አስፈላጊ የሆኑ ቪታሚኖችንና ማዕድናትን ጨምሮ ፈረሶቹ የሚያስፈልጓቸውን ንጥረ ነገሮች በሙሉ እንዲያገኙ ያደርጋል። ከገለባ ጋር የተደባለቀ ሲናር በጣም ገንቢ ሲሆን የገብስና የስንዴ ፍሩሽካም ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ ፈረሶቹ የሚመርጡት ለምለም ሣር ወይም አልፋልፋ ሲሆን ድንች፣ ካሮትና ቀይ ሥርም ይወዳሉ። በአብዛኛው በቅዝቃዜው ወቅት አርቢዎች ለፈረሶቹ በፕሮቲን የበለጸገ የተዘጋጀ መኖ ይገዙላቸዋል። የአረብ ዝርያ የሆኑ ፈረሶች ከሚሰጣቸው ምግብ በተጨማሪ ጨው መላስ ያስፈልጋቸዋል፤ ማዕድናትና ዕፅዋት ያለበት ጨው ኃይለኝነታቸውን ለማብረድ ይረዳል። ይሁን እንጂ ምርጥ የሆነው ድርቆሽ ወይም የእንስሳት መኖ እንኳ ለምለም ሣር ከመጋጥ ጋር ሊወዳደር አይችልም። በመጨረሻም ፈረሶቹ ሁልጊዜ ንጹሕ ውኃ ማግኘት አለባቸው፤ ቆሻሻ ውኃ ንክች አያደርጉም።”

ለአረብ የፈረስ ዝርያዎች ተገቢ እንክብካቤ ማድረግ ለቆዳቸውና ለፀጉራቸው ትኩረት መስጠትንም ያካትታል። ይህም ቆዳቸውን በጥንቃቄ ማጽዳትን፣ ልዩ በሆኑ ብሩሾች ቀስ አድርጎ መቦረሽን እንዲሁም በእጅ መደባበስን ይጠይቃል። ቶማሽ ሌላም የሚያስፈልግ ነገር እንዳለ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በየቀኑ ኮቴያቸውን ማጽዳት በጣም አስፈላጊ ነው፤ እንዲህ ማድረጋችን ካንሰርን ጨምሮ ብዙ ዓይነት በሽታዎችን ለማስወገድ ያስችላል። በተለይ የፈረሶቹን ዓይን፣ አፍንጫ፣ ከንፈርና ጆሮ በትኩረት መከታተል አስፈላጊ ነው።” ሻኔታ በማከል እንዲህ ብላለች፦ “ፈረሶቹ ጥሩ የአካል ብቃት እንዲኖራቸውና ቁመናቸው እንዲያምር የሚሮጡበት ቦታ እንዲሁም የሚንከባለሉበት አሸዋ፣ ጭቃ ወይም ሣር ያስፈልጋቸዋል። አንድ ፈረስ ከጋለበ በኋላ ሲያልበው መጀመሪያ በብርድ ልብስ ይሸፈንና ከዚያም ይጸዳል።”

ባለሙያዎች እያንዳንዱ ፈረስ የሚያስፈልገውን ነገር መከታተል አስፈላጊ እንደሆነ አጥብቀው ይገልጻሉ። ማውጎርዣታ እንዲህ ብላለች፦ “የአረብ ዝርያዎች ስድስተኛ የስሜት ሕዋስ እንዳላቸው ይታመናል፤ ሰዎች ሲቀርቧቸው፣ ሲደባብሷቸውና እቅፍ ሲያደርጓቸው በጣም ደስ ይላቸዋል። ለፈረሶቹ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማድረግ ፈረሱ በጋላቢው ሙሉ በሙሉ እንዲተማመንና ለእሱ ፍጹም ታዛዥ እንዲሆን ያደርገዋል። ፈረሶች ሰዎች ፈገግ ሲሉላቸው፣ ሲያቅፏቸው አሊያም እንደ ካሮት ወይም ስኳር የመሰለ ልዩ ምግብ ሲሰጧቸው በደስታ ያሽካካሉ። ፈረሶችን የሚወዱ ሁሉ እነሱን መንከባከብ በጣም ያስደስታቸዋል።” ቶማሽ ለፈረሶች ያለውን ፍቅር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ፈረሶችን ገና ሳያቸው ነው የወደድኳቸው። በጣም ውብ ከመሆናቸውም ሌላ ለየት ያለ ግርማ ሞገስ አላቸው። ይሁን እንጂ አመኔታቸውን ማግኘት ቀላል አይደለም። እኔ ብዙ ዓመት ፈጅቶብኛል።”

የፈረሶች የወደፊት ዕጣ

ሰዎች ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የፈረሶች በተለይም የአረብ ዝርያ ያላቸው ፈረሶች ውበት፣ ፍጥነት፣ ቅልጥፍና፣ ጥንካሬና ማስተዋል በጣም የሚያስደንቃቸው ከመሆኑም ሌላ ከፈረሶች ጋር ልዩ የሆነ ወዳጅነት መሥርተዋል። የሚያሳዝነው ግን ሰዎች ይህን ወዳጅነት አግባብ ባልሆነ መንገድ መጠቀማቸው በጦርነት ላይ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ፈረሶች ሞት ምክንያት ሆኗል። ይሁን እንጂ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሰው ልጆች በፈረስ የሚገለገሉት ለተከበረ ዓላማ ብቻ ይሆናል፤ ይህም ለፈጣሪያቸው ለይሖዋ አምላክ ውዳሴ ያመጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 አርቢው ባዝራዋ የምታረግዝበትን ጊዜ ሊወስን ይችላል። ባዝራዋ አብዛኛውን ጊዜ በየዓመቱ መውለድ የምትችል ቢሆንም ይህ ሲባል በየዓመቱ ትወልዳለች ማለት አይደለም። አንዲት ባዝራ ከ25 እስከ 30 ዓመት የምትኖር ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ15 እስከ 18 ግልገሎችን ትወልዳለች።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባዝራ ከግልገሏ ጋር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአረብ ፈረሶች የሚደረግ የዕለት ተዕለት እንክብካቤ

1. ቆዳውንና ፀጉሩን በጥንቃቄ መቦረሽ

2. ኮቴዎቹን ማጽዳት

3. ፍቅር ማሳየት

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ድንጉላ ፈረሶች በረዶ ላይ ሲጫወቱ