በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስደናቂ የሆነው የወሊድ ሂደት

አስደናቂ የሆነው የወሊድ ሂደት

አስደናቂ የሆነው የወሊድ ሂደት

ዘጠነኛው ወር ስለሞላ በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው ሕፃን ሊወለድ ነው። * ሽሉ ከእናቱ ማህፀን ያለ ጊዜው እንዳይወጣ የማህፀኗ አንገት በጥብቅ ተዘግቶ ቆይቷል። አሁን ግን የማህፀኗ አንገት መሳሳት፣ መላላትና መለጠጥ ጀምሯል። በዚህ ወቅት አንደ ተአምር የሚቆጠረው የወሊድ ሂደት ሀ ብሎ ይጀምራል።

ከዚህ አስደናቂ ሂደት በስተጀርባ ያለው ምንድን ነው? በርካታ ነገሮችን መጥቀስ ቢቻልም በተለይ ሁለቱ ምክንያቶች በጣም አስደናቂ ናቸው። የመጀመሪያው አስደናቂ ነገር በአንጎል ውስጥ የሚመረተው ኦክሲቶሲን የሚባለው ሆርሞን የሚለቀቅ መሆኑ ነው። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ይህን ሆርሞን የሚያመነጩ ቢሆንም አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ምጥ ሲጀምራት ግን ይህ ሆርሞን በከፍተኛ መጠን ይመረታል፤ ይህም የማህፀኗ አንገት እንዲለጠጥ ማህፀኗ ደግሞ እንዲኮማተር ያደርጋል።

ልትወልድ በደረሰች ሴት አንጎል ውስጥ ያለው ፒቱታሪ ዕጢ ይህን ሆርሞን መልቀቅ ያለበት ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ የሚያውቅበት መንገድ አሁንም ድረስ እንቆቅልሽ ነው። ኢንክሪደብል ቮዬጅ—ኤክስፕሎሪንግ ዘ ሂዩማን ቦዲ የተሰኘው መጽሐፍ ‘አንጎሏ የእርግዝናው ወቅት ማብቃቱንና ጠንካራ የሆኑት የማህፀን ጡንቻዎች ለአጭር ጊዜም ቢሆን በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ የሚጀምሩበት ሰዓት መድረሱን በሆነ መንገድ ያውቃል’ በማለት ይናገራል።

ሁለተኛው አስደናቂ ነገር ደግሞ የእንግዴ ልጁ ፕሮጀስትሮን የሚባለውን ሆርሞን ማምረቱን በማቆም የሚጫወተው ሚና ነው። ይህ ሆርሞን በእርግዝና ወቅት ኃይለኛ የማህፀን መኮማተር እንዳይፈጠር ይከላከላል። አሁን ግን ፕሮጀስትሮን ስለማይመረት ማህፀን መኮማተር ይጀምራል። በጥቅሉ ሲታይ ከ8 እስከ 13 ሰዓት ከሚቆይ ምጥ በኋላ ሕፃኑ፣ ተለጥጦ በሰፋው የማህፀን አንገት በኩል ተገፍቶ ይወጣል። ከዚያ በኋላ ደግሞ እንግዴ ልጁ ይወጣል።

በዚህ ጊዜ አዲስ የተወለደው ሕፃን በእናቱ ሆድ ውስጥ ከነበረው ሁኔታ በጣም ከሚለዩት አዳዲስ ሁኔታዎች ጋር በፍጥነት መላመድ ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ሽሉ በማህፀን ውስጥ እያለ ሳንባዎቹ በእንሽርት ውኃ ተሞልተው የሚቆዩ ቢሆንም ሕፃኑ በእናቱ ማህፀን አንገት በኩል በሚያልፍበት ጊዜ ግን ይህ ፈሳሽ ተጨምቆ ይወጣል። አሁን መተንፈስ እንዲጀምር ሳንባዎቹ በአየር መሞላት አለባቸው፤ አብዛኛውን ጊዜ ሕፃኑ መተንፈስ እንደጀመረ የሚታወቀው ከማህፀን እንደወጣ በሚያሰማው ለቅሶ ነው። በልቡና በደም ዝውውር ሥርዓቱ ላይም ከፍተኛ ለውጥ ይካሄዳል። ደሙ በሕፃኑ ሳንባዎች በኩል በማለፍ ኦክሲጅን እንዲያገኝ ለማስቻል ሁለቱን የልብ ደም ተቀባይ ገንዳዎች የሚያገናኘው የደም ቧንቧ እና በሳንባ በኩል የሚያልፈው የደም ሥር ይዘጋሉ። ሕፃኑ በዚህ ፍጥነት የውጪውን ዓለም መላመዱ እጅግ ያስደንቃል።

ጠቅላላው የምጥና የወሊድ ሂደት “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው” የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ያስታውሰናል። ይህም “ለመወለድ ጊዜ አለው” የሚለውን ይጨምራል። (መክብብ 3:1, 2) በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በሆርሞንና በአካል ላይ የሚከሰቱት እነዚህ ተከታታይ ለውጦች፣ መጽሐፍ ቅዱስ “የሕይወት ምንጭ” በማለት የሚጠራውን የፈጣሪያችንን ንድፍ የማውጣት ችሎታ ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ ቢባል አትስማማም?—መዝሙር 36:9፤ መክብብ 11:5

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 እርግዝና በአብዛኛው የሚቆየው ከ37 እስከ 42 ሳምንት ነው።

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]

የወሊድ ሂደት

1 ሽሉ ከምጥ በፊት የሚኖረው አቀማመጥ

2 ሽሉ ወደ ማህፀን አንገት ሲጠጋ

3 የማህፀን አንገት ይለጠጣል

4 ሽሉ ከማህፀን ሲወጣ

[ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

1

የእንግዴ ልጅ

ብልት

የማህፀን አንገት

2

3

4