በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማይግሬን እንዳይነሳብህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ማይግሬን እንዳይነሳብህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ማይግሬን እንዳይነሳብህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ፍልቅልቅ የሆነችው ጆይስ የምትሠራው በቢሮ ውስጥ ነው፤ አንድን ሰነድ በትኩረት እየተመለከተች እያለ በድንገት ገጹ ላይ ያሉት አንዳንዶቹ ነገሮች አልታይ አሏት። ከዚያም ዓይኗን ያጥበረብራት፣ ብዥ ይልባት እንዲሁም የሚንቀሳቀሱ ነገሮች ይታዩአት ጀመር። ብዙም ሳይቆይ ጆይስ ማየት አስቸገራት። ጆይስ እነዚህ ነገሮች የምን ምልክት እንደሆኑ ስለገባት ጊዜ ሳታጠፋ ለዚህ ዓይነቱ ድንገተኛ ሕመም ተብሎ የተዘጋጀውን ትንሽ እንክብል ዋጠች።

ጆይስ፣ ማይግሬን ወይም በጣም ኃይለኛ የሆነ ራስ ምታት አለባት፤ ይህን ሕመም ከተለመደው ራስ ምታት የሚለዩት የተለያዩ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አልፎ አልፎ ከሚያጋጥመው ራስ ምታት በተለየ መልኩ ማይግሬን የመደጋገም ባሕርይ አለው። በተጨማሪም ይህ ዓይነቱ ራስ ምታት ታማሚው የዘወትር እንቅስቃሴውን ማከናወን እስኪያቅተው ድረስ በጣም ኃይለኛ ነው።

የማይግሬን ምልክቶች ምንድን ናቸው? ይህ ሕመም ያለባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ራሳቸውን ከፍሎ የሚያማቸው ሲሆን ጭንቅላታቸው ውስጥ የሚነዝር ስሜት ይሰማቸዋል። በተጨማሪም የማቅለሽለሽ ስሜት ሊኖራቸውና ኃይለኛ ብርሃን ማየት ሊከብዳቸው ይችላል። ሕመሙ ለተወሰኑ ሰዓታት ወይም ለብዙ ቀናት ሊቆይ ይችላል።

አብዛኞቹ ሰዎች አልፎ አልፎ የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥማቸው ራሳቸውን ቢያማቸውም ማይግሬን የሚባለው ከባድ ራስ ምታት የሚያሠቃየው ከ10 ሰዎች ውስጥ አንዱን ብቻ ነው። ይህ ሕመም ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን ይበልጥ ያጠቃል። ሥቃዩ በአንዳንዶች ላይ የሚበረታ ሲሆን ማይግሬን ያለባቸው አብዛኞቹ ሰዎች በዓመት ውስጥ ብዙ ቀናት ከሥራ ይቀራሉ። ይህ ሕመም ገቢ እንዲቀንስ ሊያደርግ እንዲሁም በቤተሰብና በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በመሆኑም የዓለም ጤና ድርጅት ይህንን ሕመም በዓለም ላይ ካሉት እንቅስቃሴን የሚገድቡ 20 ዋና ዋና ሕመሞች መካከል መድቦታል።

አንዳንድ የማይግሬን ሕመምተኞች ራስ ምታቱ ከመጀመሩ ትንሽ ቀደም ብሎ እጃቸው ይቀዘቅዛል፣ ሰውነታቸው ይዝላል፣ ይርባቸዋል ወይም ስሜታቸው ይለዋወጣል። ልክ ራስ ምታቱ ሊጀምር ሲል የማዞር ስሜት ይሰማቸዋል፣ ጆሯቸው ጭው ይልባቸዋል፣ ሰውነት ሲደነዝዝ የሚኖረው ዓይነት ስሜት ይኖራቸዋል፣ ነገሮች ድርብ ሆነው ይታዩአቸዋል፣ መናገር ያስቸግራቸዋል ወይም ጡንቻቸው ይዝልባቸዋል።

የማይግሬን መንስኤ ሙሉ በሙሉ ባይታወቅም በጭንቅላት ውስጥ ያሉ የደም ሥሮችን የሚያጠቃ የነርቭ ሥርዓት እክል እንደሆነ ይታሰባል። ሕመምተኞቹን የሚያሠቃያቸው የሚነዝር ስሜት የሚፈጠረው ደም በተቆጡ የደም ሥሮች በኩል ሲያልፍ ሳይሆን አይቀርም። ኢመርጀንሲ ሜድስን የተሰኘው መጽሔት እንዲህ ይላል፦ “ማይግሬን ያለባቸው ሰዎች በቀላሉ የሚታወክ የነርቭ ሥርዓት በዘር የወረሱ ሲሆን እንደ እንቅልፍ ማጣት፣ ኃይለኛ ሽታ፣ ጉዞ፣ ምግብ ሳይበሉ መቆየት፣ ውጥረትና የሆርሞን መጠን መለዋወጥ ያሉት ነገሮች በነርቭ ሥርዓታቸው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላል።” ማይግሬን ያለባቸው ሰዎች በሆድ ዕቃ መታወክና በመንፈስ ጭንቀት የመጠቃታቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው።

ማይግሬን እንዳይነሳብህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ከወላጆችህ የወረስከውን የነርቭ ሥርዓት መለወጥ አትችልም። ይሁን እንጂ የማይግሬን ሕመም እንዳይነሳብህ መከላከል ትችል ይሆናል። አንዳንዶች የየዕለት ውሏቸውን በማስታወሻ በመመዝገብ ሕመሙን የሚቀሰቅሱባቸውን የምግብ ዓይነቶች ወይም ሁኔታዎች ለይተው ማወቅ ችለዋል።

የእያንዳንዱ ሰው ሁኔታ የተለያየ ነው። ሎራን፣ ማይግሬን የሚነሳባት በወር አበባዋ ጊዜ እንደሆነ ተገነዘበች። እንዲህ ብላለች፦ “በወር አበባዬ ዑደት አጋማሽ አካባቢ ከወትሮው የበለጠ እንቅስቃሴ ካደረግሁ ወይም የሚያነቃቃ ነገር ካጋጠመኝ ኃይለኛ ራስ ምታት ሊነሳብኝ ይችላል፤ ለምሳሌ ከባድ ሥራ፣ ሙቀት ወይም ቅዝቃዜ፣ ከፍተኛ ድምፅ ሌላው ቀርቶ ቅመም የበዛበት ምግብም እንኳ ሳይቀር ራስ ምታቱን ይቀሰቅስብኛል። በመሆኑም በዚህ ጊዜ ለመረጋጋትና ሁሉን ነገር በልክ ለማድረግ እጥራለሁ።” ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት በማይግሬን ስትሠቃይ የኖረችው ጆይስ “ብርቱካን፣ አናናስና ቀይ ወይን ወዲያውኑ ከባድ ራስ ምታት እንደሚያስነሱብኝ ስለተገነዘብኩ ከእነዚህ ነገሮች እርቃለሁ” በማለት ትናገራለች።

ብዙውን ጊዜ የማይግሬን ሕመምን የሚቀሰቅሱት በርካታ ነገሮች አንድ ላይ ተደማምረው ስለሚሆን መነሻውን ለይቶ ማወቅ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ቸኮሌት በልተህ ምንም ላትሆን ትችላለህ፤ በሌላ ጊዜ ግን ቸኮሌት ከመብላትህ በተጨማሪ ሌላ ነገር ሲታከልበት ማይግሬንህ ሊነሳብህ ይችላል።

ማይግሬንህን የሚቀሰቅሱብህን ነገሮች ለይተህ ማወቅ ወይም ከእነዚህ ነገሮች መራቅ ባትችል እንኳ በተቻለ መጠን ሕመሙ እንዳይነሳብህ ማድረግ የምትችልባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ። ባለሙያዎች ሳምንቱን ሙሉ ቋሚ የእንቅልፍ ሰዓት እንዲኖርህ ይመክራሉ። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አርፍደህ መነሳት የምትፈልግ ከሆነ ደግሞ በወትሮው ሰዓት ተነስተህ ለጥቂት ደቂቃዎች የሆነ ነገር ካከናወንክ በኋላ ተመልሰህ እንድትተኛ ያበረታታሉ። ካፌይን የሚባለውን ንጥረ ነገር የምትወስድበት መጠን መለወጡም ኃይለኛ ራስ ምታት እንዲነሳብህ ሊያደርግ ስለሚችል በቀን ውስጥ ከሁለት ስኒ ቡና በላይ አትጠጣ፤ እንደ ኮካ ያሉ ካፌይን ያላቸው ለስላሳ መጠጦችንም ቢሆን ከሁለት በላይ አትጠጣ። ረሃብ ማይግሬንን ሊቀሰቅስ ስለሚችል ምግብ ሳትበላ ብዙ አትቆይ። ብዙ ጊዜ ማይግሬንን የሚቀሰቅሰውን ውጥረትን ማስወገድ ቀላል ባይሆንም ፕሮግራምህን በማስተካከል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ ወይም ለስለስ ያለ ሙዚቃ በማዳመጥ ራስህን ዘና ማድረግ ትችል ይሆናል።

ማይግሬን ሕክምና አለው?

ማይግሬንን ለማስታገስ የሚረዱ የተለያዩ አማራጮች አሉ። * ለምሳሌ ያህል፣ ፍቱን ከሚባሉት መድኃኒቶች አንዱ እንቅልፍ ነው። የሐኪም ትእዛዝ የማያስፈልጋቸው የሥቃይ ማስታገሻ መድኃኒቶችም ሕመምተኛው ትንሽ ቀለል ብሎት እንቅልፍ እንዲወስደው ሊረዱት ይችላሉ።

በ1993 ለማይግሬን ታስበው የተዘጋጁ ትሪፕታን የሚባሉ በሐኪም ትእዛዝ የሚሰጡ አዲስ ዓይነት መድኃኒቶች ተሠሩ። ዘ ሜዲካል ጆርናል ኦቭ አውስትራሊያ የዚህ መድኃኒት መገኘት “በሕክምናው መስክ ትልቅ እድገት” እንደሆነ ገልጿል። መጽሔቱ አክሎም “የትሪፕታን . . . መሠራት ማይግሬንንና ሌሎች የራስ ምታት ሕመሞችን በማከም ረገድ የሚኖረው ሚና በባክቴሪያ የሚመጡ በሽታዎችን በማከም ረገድ ፔኒሲሊን ካስገኘው ውጤት ጋር የሚመጣጠን ነው!” ብሏል።

ማይግሬን ለሕይወት የሚያሰጋ ሕመም አይደለም። በመሆኑም ለማይግሬን የሚወሰደው መድኃኒት በባክቴሪያ ምክንያት ለሚመጡ በሽታዎች እንደሚሰጠው ፔኒሲሊን የሰዎችን ሕይወት የሚያድን አይደለም። ይሁን እንጂ ትሪፕታን የሚባሉት መድኃኒቶች ለብዙ ዓመታት በማይግሬን ሲሠቃዩ ለኖሩ ሰዎች ትልቅ እፎይታ አምጥተዋል። እርግጥ ነው፣ ማይግሬን ያለባቸው ሰዎች ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ለውጦች ማድረግ ያስፈልጋቸዋል፤ ያም ሆኖ አንዳንዶቹ ሕመምተኞች ትሪፕታን የተባሉት መድኃኒቶች ተአምር እንደሠሩላቸው ይሰማቸዋል።

ይሁንና ማንኛውም መድኃኒት ቢሆን ጥቅምና ጉዳት አለው። ትሪፕታን የተባሉት መድኃኒቶች ምን ጉዳት አላቸው? መጀመሪያ ነገር፣ የእያንዳንዱ የትሪፕታን እንክብል ዋጋ በአንድ ጥሩ ምግብ ቤት ስትመገብ የምታወጣውን ወጪ ያህል ነው፤ በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ በዚህ መድኃኒት የሚጠቀሙት ከመካከለኛ እስከ ከባድ የማይግሬን ሕመም ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። በተጨማሪም ትሪፕታን እፎይታ የሚያስገኙት ለሁሉም ሰው አይደለም፤ እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች እነዚህን መድኃኒቶች መሞከር እንኳ እንዳይችሉ የሚያደርጋቸው የጤና እክል አለባቸው። በማይግሬን ሕመም የሚሠቃዩ ሰዎች ከወላጆቻቸው የወረሱትን እክል ማስተካከል የሚቻልበት የሚታወቅ ሕክምና ባይኖርም ኢመርጀንሲ ሜድስን እንደገለጸው “አዳዲስና የተሻሻሉ የማይግሬን መድኃኒቶች ስላሉ ሕመምተኞች እየተሠቃዩ የሚኖሩበት ምንም ምክንያት የለም።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 ንቁ! አንድን የሕክምና ዓይነት ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም። እያንዳንዱ ግለሰብ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ መመዘን ይኖርበታል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንዶች የየዕለት ውሏቸውን በማስታወሻ በመመዝገብ ሕመሙን የሚቀሰቅሱባቸውን የምግብ ዓይነቶች ወይም ሁኔታዎች ለይተው ለማወቅ ችለዋል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙውን ጊዜ ማይግሬንን የሚቀሰቅሰውን ውጥረትን ለመቀነስ ለስለስ ያለ ሙዚቃ ማዳመጥ ሊረዳህ ይችላል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማይግሬን እንቅስቃሴን የሚገድብ በዘር የሚተላለፍ ሕመም ሲሆን ብዙውን ጊዜ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ይቻላል