በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኢስታንቡል ትንንሽ ፎቅ ቤቶች

የኢስታንቡል ትንንሽ ፎቅ ቤቶች

የኢስታንቡል ትንንሽ ፎቅ ቤቶች

● በብዙ የዓለም ክፍሎች ከእንጨት የተሠሩ የወፍ ቤቶችን መመልከት የተለመደ ነው። እነዚህ ቤቶች ወፎች የሚመገቡባቸው፣ ሙቀት የሚያገኙባቸው፣ ጎጇቸውን የሚሠሩባቸው፣ ጫጩቶቻቸውን የሚያሳድጉባቸው ብሎም ከሚያድኗቸው እንስሳትና ከሌሎች ነገሮች ጥበቃ የሚያገኙባቸው ተስማሚ ቦታዎች ናቸው። በኢስታንቡል የወፍ ቤቶች የሚሠሩት እውነተኛ ቤቶችን እንዲመስሉ ተደርገው ነው። አንዳንዶቹ ፎቅ ቤቶች የሚመስሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ መስጊድ ወይም ቤተ መንግሥት ይመስላሉ። * እነሱም የርግብ መኖሪያዎች፣ የወፍ ፎቅ ቤቶች አልፎ ተርፎም የድንቢጥ ቤተ መንግሥቶች በመባል ይታወቃሉ።

ከእነዚህ የወፍ ቤቶች ውስጥ በጣም ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩት ቢያንስ ቢያንስ በ15ኛው መቶ ዘመን የተሠሩ ሲሆን በኦቶማን ግዛት የነበረውን የሕንፃ ንድፍ የተከተሉ ናቸው። በዚያን ወቅት ቀለል ባለ መንገድ ይሠሩ የነበረ ቢሆንም ከ18ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ግን በጣም ትልልቅና የተንቆጠቆጡ መኖሪያ ቤቶችን እንዲመስሉ ተደርገው መሠራት ጀመሩ። አንዳንዶቹ ለወፎቹ የምግብና የውኃ ማስቀመጫ፣ የሚተላለፉበት መንገድ ሌላው ቀርቶ አካባቢውን የሚቃኙ ይመስል ሰገነትም ይሠራላቸው ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ፀሐይ በብዛት የሚያገኘውን፣ ነፋስ የማያጠቃውን እንዲሁም ድመቶች፣ ውሾችና ሰዎች በቀላሉ የማይደርሱበትን የመኖሪያ ሕንፃቸውን ክፍል ይመርጡና የወፍ ቤቶቹን ያስቀምጧቸዋል። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ የወፍ ቤቶች የሚሠሩት ለወፎቹ ተብሎ ብቻ ሳይሆን የመኖሪያ ሕንፃዎቹን አጠቃላይ ንድፍ ለማስዋብ ጭምር ነበር። የወፍ ቤቶችን በትላልቅና በትናንሽ መስጊዶች ላይ አልፎ ተርፎም መንገደኛ ሰው ከፈለገ እንዲጠጣበት ተብለው በተዘጋጁ ንጹሕ ውኃ በሚፈስባቸው ቦታዎች፣ በቤተ መጻሕፍት፣ በድልድዮችና በግል ቤቶች ላይ ማየት የተለመደ ነበር።

የሚያሳዝነው ነገር፣ ከእነዚህ ትንንሽ ፎቅ ቤቶች ብዙዎቹ ለረጅም ጊዜ በተፈራረቀባቸው ነፋስ፣ ዝናብና ፀሐይ የተበላሹ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ዋጋማነታቸውን ባልተገነዘቡ ሰዎች ጠፍተዋል። የወፎቹ ቤቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መጥተዋል። ይሁን እንጂ ኢስታንቡልን የመጎብኘት አጋጣሚ ካገኘህና ታሪካዊ የሆኑ የሕንፃ ንድፎችን ማየት የሚያስደስትህ ከሆነ እነዚህን ውብ ትንንሽ ሕንፃዎች በጣራ ክፈፎች ላይ ለማግኘት ጥረት አድርግ። አሁን የእነዚህን ትንንሽ ፎቅ ቤቶች ምንነት ስለተረዳህ እነሱንም በማየት በከተማይቱ የምታደርገውን ጉብኝት የበለጠ ጣዕም እንዲኖረው ማድረግ ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 እነዚህ የወፍ ቤቶች የእውነተኛ ቤት ቅርጽ ያላቸው ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ የአንድን ሕንፃ ሞዴል በመኮረጅ የተሠሩ አይደሉም።