በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች

ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች

አንዳንድ ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች መጥፎ ነገር የሚናገሩት ለምንድን ነው?

ብዙዎቹ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳተ መረጃ አላቸው። ሌሎች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ አይወዱትም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ሥራ የሚያከናውኑት ለሰዎች ባላቸው ፍቅር በመገፋፋት ነው፤ ‘የሚድኑት የይሖዋን ስም የሚጠሩ ሰዎች’ እንደሆኑ ማወቃቸው ለሌሎች እንዲሰብኩ ያነሳሳቸዋል።—ሮም 10:13

የይሖዋ ምሥክሮች ፕሮቴስታንቶች አሊያም አክራሪዎች ወይም መናፍቃን ናቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያኖች ቢሆኑም ከካቶሊኮችና ከኦርቶዶክሶች እንደሚለዩ ሁሉ ከፕሮቴስታንቶችም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም፤ ምክንያቱም እነዚህ ሃይማኖቶች የሚያስተምሯቸው አንዳንድ ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንደሌላቸው ይገነዘባሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንደሆነ የተገለጸው አምላክ ሰዎችን በገሃነመ እሳት ለዘላለም ያሠቃያል ብሎ አያስተምርም። በተጨማሪም ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ሰዎች የማትሞት ነፍስ እንዳለቻቸው ብሎም ክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባት እንዳለባቸው አያስተምሩም።—ሕዝቅኤል 18:4፤ ዮሐንስ 15:19፤ 17:14፤ ሮም 6:23 *

“ሃይማኖታዊ አክራሪነት፣ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች በስፋት ያካሄዱት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ነው” በማለት ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ይናገራል። ከእነዚህ አክራሪ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ውስጥ አንዳንዶቹ “በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ የሚወስዱት አቋም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ቃል በቃል በመረዳት ላይ የተመሠረተ ነው።” ይህ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮችን አቋም አይገልጽም። ቀደም ብለን እንደጠቀስነው የይሖዋ ምሥክሮች ፖለቲካ ውስጥ የማይገቡ ከመሆኑም ሌላ በፖለቲካም ሆነ በሌላ በምንም ዓይነት መንገድ ተጠቅመው አመለካከታቸውን ሌሎች ሰዎች እንዲቀበሉ ለማስገደድ አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ ያነጋግራሉ።—የሐዋርያት ሥራ 19:8

ኑፋቄ የሚባለው ደግሞ በአንድ ሃይማኖት ውስጥ ሆኖ የተለየ እምነት የሚያራምድ ወይም ተገንጥሎ አንድ አዲስ ሃይማኖት የሚያቋቁም ቡድን ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ግን ከየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ተገንጥለው የወጡ ሃይማኖታዊ ቡድን አይደሉም። ስለዚህ መናፍቃን አይደሉም።

የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ የሚከናወነው እንዴት ነው?

በስብሰባዎቻቸው ላይ ማንኛውም ሰው መገኘት ይችላል፤ በስብሰባዎቹ ላይ የሚከናወነው ዋናው ነገር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲሆን ተሰብሳቢዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ከሳምንታዊ ስብሰባዎቻቸው አንዱ የሆነው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የጉባኤ አባላቱን የማስተማር፣ የማንበብና ምርምር የማድረግ ችሎታዎችን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። ሌላው ስብሰባ ደግሞ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችን ይበልጥ የሚጠቅም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የ30 ደቂቃ ንግግር ነው። ከዚያም በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሉ። ስብሰባዎቹ የሚጀመሩትም ሆነ የሚደመደሙት በመዝሙርና በጸሎት ሲሆን ከተሰብሳቢዎቹ ገንዘብ የመጠየቅ ልማድ የለም፤ እንዲሁም ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም።—2 ቆሮንቶስ 8:12

የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ገንዘብ የሚያገኘው እንዴት ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ የሚደገፈው በፈቃደኝነት በሚደረግ መዋጮ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥምቀት፣ ለሠርግ፣ ለቀብር ሥነ ሥርዓት ወይም ለሌላ ሃይማኖታዊ አገልግሎት ገንዘብ አያስከፍሉም። አሥራትም አያወጡም። መዋጮ ማድረግ የፈለገ ማንኛውም ሰው መንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚቀመጠው መዋጮ ሣጥን ውስጥ ገንዘብ መክተት ይችላል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ የሚጠቀሙባቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ራሳቸው የሚያዘጋጁ ሲሆን ይህም ወጪ ይቀንስላቸዋል፤ እንዲሁም የመንግሥት አዳራሾቻቸውና ቅርንጫፍ ቢሮዎቻቸው በአብዛኛው የሚገነቡት በፈቃደኛ ሠራተኞች ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች የሕክምና እርዳታ ይቀበላሉ?

አዎን ይቀበላሉ። እንዲያውም የይሖዋ ምሥክሮች እነሱም ሆኑ የቤተሰቦቻቸው አባላት ከሁሉ የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ ይፈልጋሉ። ከዚህም በላይ ነርስ፣ ፓራሜዲክ፣ ዶክተርና የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ሆነው የሚሠሩ በሕክምናው መስክ የተሠማሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ደም በመውሰድ የሚደረግ ሕክምናን አይቀበሉም። መጽሐፍ ቅዱስ “ከደም . . . ራቁ” በማለት ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29) የሚገርመው ነገር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የሕክምና ባለሙያዎች ያለ ደም የሚደረገውን ሕክምና “ቁጥር አንድ” እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል፤ ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ ሕክምና ደም ከመጠቀም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ብዙ የጤና ችግሮችን ያስወግዳል።

^ አን.5 እነዚህንና ሌሎች በርካታ ዓበይት ርዕሰ ጉዳዮችን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።