በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች በቀላሉ ማግኘት ስለሚቻል የሚያምኑት ነገር ለማንም ሚስጥር አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያምኑባቸው ዋና ዋና መሠረተ ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።

1. መጽሐፍ ቅዱስ፦

የይሖዋ ምሥክሮች “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ” እንደሆነ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) የሃይማኖታዊ ጥናቶች ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄሰን ቤዱን “[የይሖዋ ምሥክሮች] የሚያምኑበትም ሆነ የሚያደርጉት ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው እንጂ የሚያምኑበት ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖሩን ሳያጣሩ አስቀድመው አይወስኑም” በማለት ጽፈዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ለማጣጣም ይጥራሉ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ለራሳቸው እንደሚመች አድርገው አይተረጉሙትም። እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈው ነገር ሁሉ ቃል በቃል መወሰድ እንደሌለበት ይገነዘባሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሰባቱ የፍጥረት ቀናት ረዘም ያለ ጊዜን የሚያመለክቱ ምሳሌያዊ ቀናት ናቸው።—ዘፍጥረት 1:31፤ 2:4

2. ፈጣሪ፦

እውነተኛው አምላክ፣ ይሖዋ (የሮም ካቶሊክ ጀሩሳሌም ባይብል እና አዲሱ መደበኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተሠራበት እንዲሁም አንዳንድ ዘመናዊ ምሑራን የሚመርጡት ያህዌ የሚለውን ነው) የሚል የግል ስም ለራሱ አውጥቷል፤ ይህም እውነተኛውን አምላክ ከሐሰት አማልክት ይለየዋል። * (ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም) ጥንት በነበሩት ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ መለኮታዊው ስም በዕብራይስጥ ቋንቋ 7,000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። ኢየሱስ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ላይ “ስምህ ይቀደስ” በማለት የዚህን ስም አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ማቴዎስ 6:9) አምላክ ለእሱ ብቻ አምልኮ እንዲቀርብለት የመጠየቅ መብት አለው። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ለአምልኮ ምንም ዓይነት ሥዕል ሆነ ምስል አይጠቀሙም።—1 ዮሐንስ 5:21

“አብ ከእኔ ይበልጣል።”—ዮሐንስ 14:28

3. ኢየሱስ ክርስቶስ፦

አዳኝ፣ “የአምላክ ልጅ” እና “የፍጥረት ሁሉ በኩር” ነው። (ዮሐንስ 1:34፤ ቆላስይስ 1:15፤ የሐዋርያት ሥራ 5:31) ኢየሱስ የሥላሴ ክፍል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በአምላክ የተፈጠረ ነው። እሱ ራሱ “አብ ከእኔ ይበልጣል” ብሏል። (ዮሐንስ 14:28) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ይኖር የነበረ ሲሆን ለእኛ መሥዋዕት በመሆን ከሞተና ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ  ተመልሷል። “[በእሱ] በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።”—ዮሐንስ 14:6

4. የአምላክ መንግሥት፦

ይህ መንግሥት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ የሆነለትና ‘ከምድር የተዋጁ’ 144,000 ተባባሪ ገዥዎች ያሉት በሰማይ የሚገኝ እውን መስተዳድር ነው። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3, 4፤ ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14) ኢየሱስና ተባባሪ ገዥዎቹ፣ ወደፊት ከክፋት ሁሉ ጸድታ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩባት ምድር ላይ ይገዛሉ።—ምሳሌ 2:21, 22

5. ምድር፦

መክብብ 1:4 “ምድር . . . ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች” ይላል። ክፉዎች ከጠፉ በኋላ ምድር ወደ ገነትነት ትለወጥና ለዘላለም የጻድቃን መኖሪያ ትሆናለች። (መዝሙር 37:10, 11, 29) ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ ‘ፈቃድህ በምድር ትሁን’ በማለት የተናገራቸው ቃላት በዚያን ጊዜ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።—ማቴዎስ 6:10 አ.መ.ት

6.

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት፦ ‘አምላክ ሊዋሽ አይችልም።’ (ቲቶ 1:2) በመሆኑም የዚህን ዓለም መጨረሻ አስመልክቶ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጨምሮ አምላክ የሚናገራቸው ትንቢቶች በሙሉ ምንጊዜም ይፈጸማሉ። (ኢሳይያስ 55:11፤ ማቴዎስ 24:3-14) ከሚመጣው ጥፋት የሚተርፉት እነማን ናቸው? አንደኛ ዮሐንስ 2:17 “የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ . . . ለዘላለም ይኖራል” ይላል።

7. ሰብዓዊ ባለሥልጣናት፦

ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ” ብሏል። (ማርቆስ 12:17) በዚህም ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ ሕግ ጋር እስካልተጋጨ ድረስ የአገሪቱን ሕግ ይታዘዛሉ።—የሐዋርያት ሥራ 5:29፤ ሮም 13:1-3

“ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14

8. የስብከቱ ሥራ፦

ኢየሱስ የዚህ ዓለም መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት “የመንግሥቱ ምሥራች” በምድር ዙሪያ እንደሚሰበክ ትንቢት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ሕይወት አድን ሥራ መካፈል መቻላቸውን እንደ ክብር ይቆጥሩታል። እርግጥ ነው፣ ምሥራቹን መስማት ወይም አለመስማታቸው የሰዎቹ ምርጫ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ” ይላል።—ራእይ 22:17

9. ጥምቀት፦

የይሖዋ ምሥክሮች የሚያጠምቁት መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት አጥንተው ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ በመሆን አምላክን ለማገልገል የሚፈልጉ ሰዎችን ብቻ ነው። (ዕብራውያን 12:1) ሰዎቹ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ መጠመቃቸው ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን ያሳያል።—ማቴዎስ 3:13, 16፤ 28:19

10. የቀሳውስትና የምእመናን ልዩነት፦

ኢየሱስ ተከታዮቹን “እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 23:8) መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉትን ጨምሮ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የቀሳውስት ቡድን አልነበራቸውም። የይሖዋ ምሥክሮች የጥንቶቹን ክርስቲያኖች ምሳሌ ይከተላሉ።

^ စာပိုဒ်၊ 4 “ይሖዋ” የሚለውን ስም የፈጠሩት የይሖዋ ምሥክሮች አይደሉም። ለምሳሌ የ1879 ትርጉም ይህን ስም ተጠቅሟል። ከዚህም በላይ እንደ እንግሊዝኛና ጀርመንኛ ያሉ ቋንቋዎች ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት “ጀሆቫ” የሚለውን ስም ይጠቀሙ ነበር። የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መለኮታዊውን ስም “አምላክ” እና “ጌታ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች በመተካት ለመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት አክብሮት እንደሌላቸው አሳይተዋል።