በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ልጆች ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ?

ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ልጆች ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ?

ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ልጆች ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ?

ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ከሚከተሉት ሁለት ሁኔታዎች ይበልጥ የሚያስጨንቃችሁ የትኛው ነው? ልጃችሁ በርከት ያለ ገንዘብ ይዞ ገበያ መውጣቱ ነው? ወይስ ያለ ምንም ቁጥጥር ኢንተርኔት እንደሚጠቀም ማወቃችሁ? ሁለቱም ሁኔታዎች በተወሰነ መጠን ለአደጋ ያጋልጣሉ። እንዲሁም በሁለቱም ሁኔታዎች ልጁ ኃላፊነት የሚሰማው ዓይነት ሰው መሆን አለበት። ወላጆች፣ ልጆቻቸው ጨርሶ ገበያ እንዳይወጡ ሊከለክሏቸው አይችሉም፤ ሆኖም ገበያ ሲወጡ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ሊያስተምሯቸው ይችላሉ። ኢንተርኔት በመጠቀም ረገድም ብዙ ወላጆች ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ። ከዚህ በታች የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጠቃሚ መመሪያ ይሰጣሉ።

“አስተዋይ ሰው ሥራውን በዕውቀት ያከናውናል።” (ምሳሌ 13:16) ወላጆች፣ ልጆቻቸው ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ከሆነ ስለ ኢንተርኔት መሠረታዊ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል፤ እንዲሁም ልጆቻቸው ፈጣን መልእክቶችን ሲለዋወጡ፣ የተለያዩ ድረ ገጾችን ሲያነቡ ወይም በሌላ መንገድ ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ምን እያደረጉ እንዳሉ ሊያውቁ ይገባል። ማርሼ የተባለች የሁለት ልጆች እናት “‘ዕድሜዬ ገፍቷል’ ወይም ‘ብዙም እውቀት የለኝም’ ብላችሁ አትደምድሙ፤ በቴክኖሎጂው መስክ በየጊዜው የሚደረጉትን ለውጦች ለማወቅ ጥረት አድርጉ” ብላለች።

“ከጣራው ላይ ሰው [እንዳይወድቅ] . . . በጣራው ዙሪያ መከታ አብጅለት።” (ዘዳግም 22:8) የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ተገቢ ያልሆኑ መልእክቶችንና ምስሎችን አጣርቶ የሚያስቀር እንዲሁም ልጆች መጥፎ ድረ ገጾችን እንዳይመለከቱ የሚከለክል “መከታ” ያዘጋጃሉ፤ እንዲህ ለማድረግ የሚረዱ የተለያዩ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችም አሉ። እንዲያውም አንዳንድ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ልጆች ስማቸውን፣ አድራሻቸውን ወይም እነዚህን የመሳሰሉ የግል መረጃዎችን እንዳይሰጡ ሊያግዷቸው ይችላሉ። ይህ ሲባል ግን ወላጆች በእነዚህ መከላከያዎች በመጠቀም ሁሉንም ዓይነት መጥፎ ነገር ሙሉ በሙሉ ማገድ ይችላሉ ማለት አይደለም። ከዚህም በላይ ኮምፒውተር መጠቀም የሚችሉ በዕድሜ ከፍ ያሉ ብዙ ልጆች እነዚህን መከላከያዎች እንዴት ማለፍ እንደሚቻል ያውቃሉ።

“መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።” (ምሳሌ 18:1 የ1954 ትርጉም) በታላቋ ብሪታንያ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው ዕድሜያቸው ከ9 እስከ 19 ዓመት ከሆኑ 5 ወጣቶች መካከል አንዱ መኝታ ቤቱ ውስጥ ሆኖ ኢንተርኔት መጠቀም ይችላል። ወላጆች ኮምፒውተሩን በቤት ውስጥ ሰው ሊያየው በሚችል ቦታ ማስቀመጣቸው ልጆቻቸው በኢንተርኔት ምን እየሠሩ እንዳሉ ለማወቅ ያስችላቸዋል፤ ልጆቹም ተገቢ ያልሆኑ ድረ ገጾችን እንዳይከፍቱ ሊያደርጋቸው ይችላል።

“ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ።” (ኤፌሶን 5:15, 16) ልጆቻችሁ ኢንተርኔት መጠቀም የሚችሉት መቼና ለምን ያህል ሰዓት እንደሆነ እንዲሁም መመልከት የሚችሏቸውና የማይችሏቸው ድረ ገጾች የትኞቹ እንደሆኑ ወስኑ። ስላወጣችኋቸው መመሪያዎች ከልጆቻችሁ ጋር ተወያዩ፤ መመሪያውን በትክክል መረዳት እንዲችሉም እርዷቸው።

ልጆቻችሁ ከቤት ውጪ በሚሆኑበት ጊዜ የሚያደርጉትን ነገር መቆጣጠር እንደማትችሉ ግልጽ ነው። በመሆኑም እናንተ አብራችኋቸው በማትሆኑበት ጊዜ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ማድረግ እንዲችሉ ጥሩ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን በልባቸው ውስጥ መቅረጻችሁ አስፈላጊ ነው። * (ፊልጵስዩስ 2:12) ከኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ያወጣችሁትን መመሪያ መጣስ ምን እንደሚያስከትልባቸው ለልጆቻችሁ በግልጽ ንገሯቸው። መመሪያውን ከጣሱ የተናገራችሁትን ከመፈጸም ወደኋላ አትበሉ።

“[አስተዋይ እናት] የቤተ ሰዎቿን ጕዳይ በትጋት ትከታተላለች።” (ምሳሌ 31:27) የልጆቻችሁን ኢንተርኔት አጠቃቀም ተከታተሉ፤ እንዲህ እንደምታደርጉም ንገሯቸው። ይህ ነፃነታቸውን እንደተጋፋችሁ ተደርጎ ሊታይ አይችልም። ኢንተርኔት ሁሉም ሰው ሊያየው የሚችል ነገር መሆኑን አትዘንጉ። የዩናይትድ ስቴትስ የፌዴራል የምርመራ ቢሮ እንደገለጸው ወላጆች፣ ልጆቻቸው በኢንተርኔት ላይ የሚያደረጉትን ነገር እንዳያውቁ ሊያግዳቸው የሚችል ምንም ነገር መኖር የለበትም፤ እንዲሁም የኢ-ሜይል መልእክቶቻቸውንና የተመለከቷቸውን ድረ ገጾች አልፎ አልፎ ማየታቸው ጥሩ እንደሆነም ገልጿል።

“የመለየት ችሎታ ይጋርድሃል፤ ማስተዋልም ይጠብቅሃል። ጥበብ ንግግራቸው ጠማማ ከሆነ ሰዎች፣ ከክፉዎችም መንገድ ታድንሃለች።” (ምሳሌ 2:11, 12) ወላጆች የልጆቻቸውን የኢንተርኔት አጠቃቀም በመከታተል ሊያከናውኑ የሚችሉት ነገር ውስን ነው። ልጆቻችሁን ኢንተርኔት ከሚያስከትለው አደጋ ለመጠበቅ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት የምታስተምሯቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶችና የእናንተ ምሳሌነት ናቸው። እንግዲያው ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ምን ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ለልጆቻችሁ ንገሯቸው። ኢንተርኔት የሚያስከትለውን አደጋ ለመከላከል ከሁሉ የተሻለው መንገድ ስለ ጉዳዩ ከልጆቻችሁ ጋር በግልጽ መወያየት ነው። ቶም የተባለ አንድ ክርስቲያን እንዲህ ብሏል፦ “ለሁለቱም ወንዶች ልጆቻችን ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ ‘መጥፎ’ ሰዎች ነግረናቸዋል። በተጨማሪም የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ምን እንደሆኑ፣ እነዚህን ነገሮች ለምን መመልከት እንደሌለባቸው እንዲሁም ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር ፈጽሞ መጻጻፍ የሌለባቸው ለምን እንደሆነ አስረድተናቸዋል።”

ልጆቻችሁን ከአደጋ መጠበቅ ትችላላችሁ

ልጆቻችሁን በኢንተርኔት ሊያጋጥም ከሚችል አደጋ መጠበቅ ጥረት ይጠይቃል፤ ከዚህም በላይ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ በየጊዜው ይለወጣል። በቴክኖሎጂው መስክ የሚታየው እድገት አንዳንድ ጥቅሞችን ሊያስገኝ ቢችልም ልጆቻችሁን ባላሰባችሁት መንገድ ለአደጋ ሊያጋልጣቸው ይችላል። ታዲያ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደፊት ሊያጋጥሟቸው ለሚችሉ አደጋዎች ሊያስታጥቋቸው የሚችሉት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው” ይላል።—መክብብ 7:12

ልጆቻችሁ ጥበበኞች እንዲሆኑ እርዷቸው። በተጨማሪም ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ሊያጋጥሟቸው ከሚችሉ አደጋዎች ራሳቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ አስተምሯቸው፤ እንዲሁም ኃላፊነት እንደሚሰማቸው በሚያሳይ መንገድ ኢንተርኔትን እንዲጠቀሙ አሠልጥኗቸው። እንዲህ ካደረጋችሁ የልጆቻችሁ ደኅንነት አደጋ ላይ ሳይወድቅ በኢንተርኔት እንዲጠቀሙ ልትረዷቸው ትችላላችሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 በርካታ ወጣቶች በሞባይል ስልኮች፣ በእጅ በሚያዙ ትናንሽ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሌላው ቀርቶ በአንዳንድ የቪዲዮ መጫወቻዎች አማካኝነት ኢንተርኔት መጠቀም እንደሚችሉ ወላጆች ማስታወስ ይኖርባቸዋል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በታላቋ ብሪታንያ በየሳምንቱ ኢንተርኔት ከሚጠቀሙ ከ9 እስከ 19 ዓመት ባለው ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 57 በመቶ የሚሆኑት የብልግና ምስሎችን ተመልክተው ያውቃሉ፤ ሆኖም ልጆቻቸው የብልግና ምስሎች አይተው እንደሚያውቁ የሚሰማቸው 16 በመቶ የሚሆኑት ወላጆች ብቻ ናቸው

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ልጆችን ለማጥመድ የሚፈልጉ እስከ 750,000 የሚደርሱ ሰዎች በየዕለቱ ቻት ሩሞችንና ተቃራኒ ጾታ ያላቸውን ሰዎች የሚያገናኙ ድረ ገጾችን ይቃኛሉ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በዩናይትድ ስቴትስ ከሚኖሩ ከ12 እስከ 17 ዓመት ባለው ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 93 በመቶ የሚሆኑት ኢንተርኔት ይጠቀማሉ

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጃችሁ ኃላፊነት እንደሚሰማው በሚያሳይ መንገድ ኢንተርኔትን እንዲጠቀም ልታሠለጥኑት ትችላላችሁ?