በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሰው ልጅ ችግሮች መፍትሔው በጎ አድራጎት ነው?

ለሰው ልጅ ችግሮች መፍትሔው በጎ አድራጎት ነው?

ለሰው ልጅ ችግሮች መፍትሔው በጎ አድራጎት ነው?

አብዛኛውን ጊዜ የዜና ማሰራጫዎች ስለ ተፈጥሮ አደጋዎች፣ ስለ ድህነት፣ ስለ ረሀብ፣ ስለ በሽታና ስለ ሌሎች አካባቢያዊ ችግሮች የሚዘግቡ ቢሆንም ሰዎች የሚያሳዩት የለጋስነት መንፈስ እየጨመረ መጥቷል። ሀብታም የሆኑ ግለሰቦች ለአንዳንድ ጠቃሚ ነገሮች በመቶ ሚሊዮን አንዳንዴም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መለገሳቸውን የሚገልጽ ዜና አልፎ አልፎ ይደመጣል። በመዝናኛው ዓለም ታዋቂ የሆኑ ግለሰቦች ዝናቸውን በመጠቀም ሰዎች አሳሳቢ ለሆኑ ችግሮች ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ ይጥራሉ። መጠነኛ ገቢ ያላቸው ሰዎችም ሳይቀሩ ለተለያዩ ጠቃሚ ነገሮች ገንዘብ ይለግሳሉ። ይሁንና የገንዘብ ልግስና ብቻውን የሰው ልጅ ችግሮችን ለዘለቄታው ማስወገድ ይችላል?

ለጋሾች የበዙበት ዘመን

በአንዳንድ አገሮች ልግስና የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ይህንን አስመልክቶ አንድ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ገልጿል:- “ከ21ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ ብዙ ካፒታል ያላቸው በርካታ የእርዳታ ድርጅቶች በብዙ አገሮች ውስጥ ተቋቁመዋል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ከዚህ ቀደም ታይቶ አይታወቅም።” ሀብታሞች እየበዙ በሄዱ መጠን የልግስና መንፈስ እንደሚጨምር ይጠበቃል። ይህም የሆነው ሰዎች የሚሰጡት ገንዘብ ስለሚኖራቸው ብቻ ሳይሆን አንድ ሀብታም በሚሞትበትና ውርሱን ለሌላ ሰው በሚያስተላልፍበት ወቅት ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚለገሰው ገንዘብ ስለሚጨምር ነው። ዚ ኢኮኖሚስት የተባለው የብሪታንያ የዜና መጽሔት፣ ያለንበትን ጊዜ “ለጋሾች የበዙበት ዘመን” ብሎ መጥራቱ የተገባ ነው።

ሰዎች የልግስና መንፈስ እንዲኖራቸው ከሚገፋፏቸው ምክንያቶች አንዱ መንግሥታት አጣዳፊ ለሆኑ ዓለም አቀፋዊ ችግሮች እልባት መስጠት አለመቻላቸው ነው። በአፍሪካ የተባበሩት መንግሥታት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ልዩ መልእክተኛ የሆኑ አንድ ግለሰብ፣ ዝነኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች በዓለም ዙሪያ በሚታዩት ችግሮች ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ ያደረጋቸው አንዱ ምክንያት “በፖለቲካ አመራር ላይ የሚታየው ክፍተት” እንደሆነ ተናግረዋል። ጆኤል ፍለሽ ማን የተባሉ አንድ ሰው ዘ ፋውንዴሽን:- ኤ ግሬት አሜሪካን ሴክሬት—ሃው ፕራይቬት ዌልዝ ኢዝ ቼንጂንግ ዘ ወርልድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት ችግሩ የተያያዘው ከድህነትም ይሁን ከጤና፣ ከትምህርትም ይሁን ከፍትሕ አሊያም ከአካባቢ ሁኔታ ጋር “መንግሥታትና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቾች እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያደጉት ጥረት በቂ አለመሆኑ” በተለይ የሀብታም ሰዎችን ትዕግሥት እንዲሟጠጥ አድርጓል። አንዳንድ ሀብታም የሆኑ ለጋሾች ዛሬ የሚታዩትን ችግሮች ለማስተካከል ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ በንግዱ ዓለም ውጤታማ የሆኑበትን መንገድ ለመከተል ይጥራሉ።

ለጋሾች ያላቸው ኃይል

ልግስና ከ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ በሰፊው የሚታወቅ ድርጊት ነው። አንድሩ ካርኒጌንና ጆን ሮክ ፌለርን የመሳሰሉ ታዋቂ የንግድ ሰዎች፣ ባካበቱት ሀብት ድሆችን ለመርዳት ወስነዋል። እነዚህ ለጋሾች በልምድ የሚደረገው ልግስና፣ የተራቡ ሰዎችን ከመመገብ ወይም የታመሙ ልጆችን ከመንከባከብ ባለፈ በችግሩ መንስኤ ላይ ያተኮረ አለመሆኑን አስተውለዋል። እነዚህ ሰዎች እርዳታውን በተደራጀ መልኩ መስጠት እንዳለባቸው ስለተሰማቸው ማኅበራዊ ለውጥን የሚያበረታቱ እንዲሁም የችግሮቹን መንስኤ ለማስወገድ የሚደረጉ ጥናቶችን በገንዘብ የሚደግፉ ተቋማትንና ድርጅቶችን አቋቁመዋል። ከእነዚህ ዓመታት ጀምሮ በዓለም ዙሪያ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ እንዲህ ያሉ ድርጅቶች የተቋቋሙ ሲሆን ከ50 በላይ የሚሆኑት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ካፒታል አላቸው።

እነዚህ ድርጅቶች ብዙ መልካም ነገሮችን እንዳደረጉ አይካድም። በእርዳታ የተገነቡት በርካታ ትምህርት ቤቶች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ መናፈሻ ቦታዎችና ሙዚየሞች ለዚህ ምሥክር ናቸው። በተመሳሳይም የእህል ምርት እንዲጨምር የሚያደርጉ ፕሮግራሞች መነደፋቸው ድህነት ባጠቃቸው አገሮች ጥሩ ምርት እንዲገኝ ረድቷል። በሕክምናው ዘርፍ ለሚደረገው ምርምር የሚሰጠው እርዳታም የተሻለ ሕክምና ማግኘት እንዲቻል በር ከፍቷል። እንዲሁም በተወሰኑ አካባቢዎች እንደ ቢጫ ወባ ያሉ አንዳንድ በሽታዎችን ለማጥፋት ተችሏል።

በዛሬው ጊዜ፣ ሰዎች በዓለም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አፋጣኝ እርምጃዎችን እየወሰዱና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ ይገኛሉ። በመሆኑም ብዙዎች በዚህ ረገድ ጥሩ ውጤት እንደሚገኝ ይጠብቃሉ። አንድ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት በ2006 ተሰብስበው ለነበሩ ለጋሾች ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ግለሰቦችም ሆኑ የግል ድርጅቶች የሰዎችን ችግር ለመቅረፍ ያደረጉትን ልግስና አቅልለን የምንመለከተው አይደለም።”

ይሁንና ብዙዎች ይህን በተመለከተ የተለየ አመለካከት አላቸው። ዓለም አቀፍ የጤና አጠባበቅ ባለሙያ የሆኑት ሎሪ ጋሬት እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “አንድ ሰው በእጃችን የሚገኘውን ገንዘብ ሲመለከት በዓለም ላይ የሚታዩት በርካታ ችግሮች በቅርቡ እንደሚወገዱ ይሰማው ይሆናል፤ እውነታው ግን ይህ አይደለም።” ለምን? ለዚህ እንደ ችግር አድርገው ከጠቀሷቸው ነገሮች መካከል ቢሮክራሲ፣ ሙስና፣ የተቀናጀ ጥረት አለመኖር እንዲሁም ለጋሾች ገንዘባቸው ለአንድ ችግር ብቻ ለምሳሌ ያህል ለኤድስ እንዲውል ብለው መስጠታቸው ይገኙበታል።

የተቀናጀ ጥረት አለመኖሩ እንዲሁም ገንዘቡ “በአብዛኛው የሚውለው በስፋት ለሚታወቁ በሽታዎች ብቻ መሆኑ፣ በዛሬው ጊዜ የሚደረገው ልግስና የታሰበለትን ዓላማ እንዳያሳካ ብሎም ችግሮቹ ይበልጥ እንዲባባሱ አድርጓል” ሲሉ ጋሬት የተሰማቸውን ተናግረዋል።

ገንዘብ ብቻውን መፍትሔ የማያመጣው ለምንድን ነው?

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ዓላማ ምንም ይሁን ምን የሚያስገኙት ውጤት ውስን ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ገንዘብም ሆነ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ትምህርት እንደ ስግብግብነት፣ ጭፍን ጥላቻ፣ ብሔርተኝነት፣ ጎሰኝነት እንዲሁም የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች የመሳሰሉ ነገሮችን ሊያስወግዱ አለመቻላቸው ነው። እነዚህ ነገሮች የሰው ልጆችን ችግሮች ያባባሱ ቢሆንም ዛሬ ላለው ሥቃይና መከራ ዋነኛ መንስኤ አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ልጆች ላይ እየደረሱ ላሉት ችግሮች መንስኤ አድርጎ የሚጠቅሳቸው ሌሎች መሠረታዊ ነገሮች አሉ።

ከእነዚህ መሠረታዊ ነገሮች መካከል አንዱ ሰዎች አለፍጽምናን መውረሳቸው ነው። (ሮሜ 3:23፤ 5:12) ፍጹም ባለመሆናችን መጥፎ ነገሮችን ማሰብ እንዲሁም ማድረግ ይቀናናል። ዘፍጥረት 8:21 “ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ” እንደሆነ ይናገራል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለዚህ መጥፎ ዝንባሌ በመሸነፍ የጾታ ብልግና ሲፈጽሙና አደገኛ ዕፆችን ሲወስዱ ይታያሉ። እነዚህ ድርጊቶች ደግሞ ኤድስን ጨምሮ በርካታ በሽታዎች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆነዋል።—ሮሜ 1:26, 27

የሰው ልጆች እየደረሰባቸው ላለው ሥቃይ ሌላው መንስኤ ደግሞ ራሳችንን በተሻለ መንገድ መምራት አለመቻላችን ነው። ኤርምያስ 10:23 ሰው “አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል” ይናገራል። የግብረ ሰናይ ድርጅቶች የመንግሥታትን እገዛ ሳይፈልጉ ሌሎችን ለመርዳት የሚነሳሱበት አንዱ ምክንያት ከላይ እንደተጠቀሰው ‘በፖለቲካ አመራር ላይ ክፍተት’ መኖሩ ነው። ሰዎች ገዢያቸው አድርገው ሊመለከቱት የሚገባው ፈጣሪን እንጂ እንደ እነሱ ያለ ሰብዓዊ ፍጡርን እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ኢሳይያስ 33:22

ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ የሰው ልጆችን እያሠቃዩ ያሉትን ችግሮች በሙሉ ለማስወገድ ቃል እንደገባ ይናገራል። እንዲያውም ይህን ከግብ ለማድረስ ወሳኝ እርምጃዎችን ወስዷል።

ተወዳዳሪ የማይገኝለት ለጋሽ

ልግስና ተብሎ የተተረጎመው “ፊልአንትሮፒ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ሰውን መውደድ” የሚል ፍቺ ካለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው። ከፈጣሪያችን የበለጠ ለሰው ዘር ፍቅር ያለው አካል ማንም የለም። ዮሐንስ 3:16 እንዲህ ይላል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል።” አዎን፣ ይሖዋ ሰዎችን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ለማውጣት ከገንዘብ እጅግ የላቀ ዋጋ ከፍሏል። ውድ የሆነውን ልጁን “ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ” ሰጥቷል። (ማቴዎስ 20:28) ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በእንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቍስል እናንተ ተፈውሳችኋል።”—1 ጴጥሮስ 2:24

በተጨማሪም ይሖዋ በአገዛዝ ረገድ የሚታየውን ችግር ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። ይህንንም ከግብ ለማድረስ መላዋን ምድር የሚገዛ መንግሥት አቋቁሟል። በሰማይ ሆኖ የሚገዛው ይህ መንግሥት ክፉዎችን በሙሉ ከምድር ጠራርጎ በማስወገድ በምድር ላይ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ያደርጋል።—መዝሙር 37:10, 11፤ ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14

አምላክ ለመከራና ሥቃይ ዋነኛ መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን በማስወገድ ሰዎች በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ ሊፈጽሟቸው ያልቻሏቸውን ነገሮች ያከናውናል። የይሖዋ ምሥክሮች የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ከማቋቋም ይልቅ የኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን ‘የአምላክን መንግሥት ወንጌል’ ለመስበክ ያውሉታል።—ማቴዎስ 24:14፤ ሉቃስ 4:43

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል’

የይሖዋ ምሥክሮች በ2 ቆሮንቶስ 9:7 ላይ የሚገኙትን እነዚህን ቃላት ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራሉ። ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ሌሎችን ለመርዳት በሚያውሉበት ጊዜ “በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ” የሚለውን ምክር ይከተላሉ።—1 ዮሐንስ 3:18

የይሖዋ ምሥክሮች፣ የተፈጥሮ አደጋን የመሳሰሉ አንዳንድ ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት ሌሎችን መርዳት እንደ ትልቅ መብት ይቆጥሩታል። ለምሳሌ ያህል፣ ካትሪና፣ ሪታ እና ዊልማ የተባሉት ከባድ አውሎ ነፋሶች የዩናይትድ ስቴትስን ደቡባዊ ክፍል በመቱበት ወቅት በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ ለመስጠትና የግንባታ ሥራ ለማከናወን ችግሩ ወደደረሰበት ሥፍራ በፈቃደኝነት ሄደዋል። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች በአካባቢው በተቋቋሙት የእርዳታ ኮሚቴዎች ሥር ሆነው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ከ5,600 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች የመኖሪያ ቤቶችን እንዲሁም 90 የመንግሥት አዳራሾችን መጠገንና መገንባት ችለዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች አሥራት አያወጡም ወይም የእርዳታ ገንዘብ አይለምኑም፤ ከዚህ ይልቅ ሥራቸው ሙሉ በሙሉ የሚደገፈው በፈቃደኝነት በሚሰጥ መዋጮ ነው።—ማቴዎስ 6:3, 4፤ 2 ቆሮንቶስ 8:12

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገንዘብ፣ ለሰው ልጆች ሕመምና ሥቃይ መንስኤ የሆኑትን መሠረታዊ ነገሮች ማስወገድ አይችልም

[ምንጭ]

© Chris de Bode/Panos Pictures