በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ ትክክለኛነት የሚደግፉ በርካታ ሳይንሳዊ ማስረጃዎች አሉ፤ እነዚህ ማስረጃዎች ሐቁን በዓይን የምናየውን ያህል እውን የሚያደርጉና ስለ ሕይወት ያለንን እውቀት የሚያሳድጉ ናቸው።”—ሊቀ ጳጳስ ቤነዲክት 16ኛ

“በዩናይትድ ስቴትስ በሚኒያፖሊስ [ሚኒሶታ] ውስጥ 40 ዓመታት ያስቆጠረ አንድ ትልቅ ድልድይ የትራፊክ እንቅስቃሴ በሚበዛበት ሰዓት ላይ በድንገት ተደርምሶ 18 ሜትር ጥልቀት ወዳለው ሚሲሲፒ ወንዝ ውስጥ በመግባቱ ምክንያት [13 ሰዎችን] ከገደለ በኋላ ባለ ሥልጣናቱ ‘የአሠራር ጉድለት ያለባቸውን’ 74,000 ድልድዮች ለመገምገምና ለመጠገን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት . . . ደፋ ቀና እያሉ ነው።”—ዘ ዊክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ብዙኃኑ ሕግ ይጥሳሉ

ታይምስ የተሰኘ አንድ የለንደን ጋዜጣ “‘ብዙኃኑ ሕግ አክባሪ ነው’ የሚለው አስተሳሰብ መሠረተ ቢስ ነው” በማለት ዘግቧል። አክሎም “አብዛኞቹ ብሪታንያውያን የሚታዘዙት የፈለጉትን ሕግ ብቻ ያውም ደስ ካላቸው እንደሆነ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል” ብሏል። ለንደን ውስጥ በኪንግስ ኮሌጅ የሚገኘው የወንጀልና የፍትሕ ምርምር ማዕከል ያካሄደው አንድ ጥናት እንዳመለከተው ሕግ ከሚጥሱ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ “የተከበረ” ከሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል የመጡ ናቸው። ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከቀረጥ ለማምለጥ ሲሉ ለሠራተኞቻቸው በካሽ እንደሚከፍሉ፣ አንድ ሦስተኛ የሚያህሉት ትርፍ ገንዘብ ሲመለስላቸው ለራሳቸው እንደሚያስቀሩ፣ አንድ አምስተኛ የሚያህሉት ደግሞ ከመሥሪያ ቤታቸው አንዳንድ ነገሮችን እንደሚሰርቁ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ጥናቱን ያካሄዱት ሰዎች በመደምደሚያቸው ላይ እንደገለጹት እንዲህ ያሉት ባሕርያት “ምናልባትም በጎዳና ላይ ከሚፈጸሙት ወንጀሎች በላይ የኅብረተሰቡ የሥነ ምግባር አቋም መውረዱን የሚያመለክቱ” ናቸው።

የኑክሌር መሣሪያዎች በእርግጥ “በአምላክ እጅ ውስጥ” ናቸው?

የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ በሩሲያ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ወንዶችና ሴቶች ለሚያከናውኑት ተግባር ቡራኬ ሰጠች። ክራስናያ ዝቪዝደ የተሰኘው ጋዜጣ ሞስኮ በሚገኝ አዳኙ ክርስቶስ በሚባል ካቴድራል ውስጥ በተደረገ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ የተነበበውን መልእክት ጠቅሶ እንደዘገበው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ የሆኑት ዳግማዊ አሌክሲስ “በእናንተ የተፈጠሩትና በአደራ የተሰጧችሁ የኑክሌር መሣሪያዎች ምንጊዜም በአምላክ እጅ ውስጥ እንዲቆዩና ሌሎችን ለማስፈራራት እንዲሁም ለመበቀል ብቻ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች እንዲሆኑ . . . ወደ አምላክ ጸሎት አቀርባለሁ” ብለዋል።

ማር በጥንቷ እስራኤል

“መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤል ‘ወተትና ማር የምታፈስ ምድር’ (ወይም ቢያንስ ማር የምታፈስ) እንደነበረች የሚናገረው ሐሳብ ትክክል መሆኑን የሚያሳይ አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ ተገኘ” ሲል ኢየሩሳሌም የሚገኘው የሒብሩ ዩኒቨርሲቲ አርኪኦሎጂ ተቋም ገልጿል። በእስራኤል ቤት ሺአን ሸለቆ ውስጥ ቴል ሬኮቭ በተባለ ቦታ ከተገኙት ነገሮች መካከል በሦስት ረድፍ መደዳውን የተደረደሩ ከሸክላ የተሠሩ ቀፎዎች ይገኙበታል፤ እያንዳንዱ ቀፎ ሞላላ ቅርጽ ያለው ሲሆን ሦስት ደረጃዎች አሉት። ዘገባው እንደገለጸው ቀፎዎቹ ለንብ እርባታ ያገለገሉት “ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ10ኛው እስከ 9ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ” አካባቢ ሲሆን በቦታው “ወደ 100 የሚጠጉ ቀፎዎች” እንደነበሩ ተገምቷል። ንብ አርቢዎች በየዓመቱ “እስከ ግማሽ ቶን የሚደርስ ማር” ይመረት እንደነበረ ገምተዋል።

የቤት እንስሳት ይበልጡባቸዋል

በኢንተርኔት በተደረገ አንድ ጥናት መሠረት “ከአራት አውስትራሊያውያን መካከል አንዱ፣ የቤት እንስሳውን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የቤተሰቡ አባል አድርጎ እንደሚመለከተው እንዲያውም ከትዳር ጓደኛው ወይም ከወላጆቹ እንኳ አስበልጦ እንደሚወደው ይናገራል” በማለት ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ በኢንተርኔት ባሰራጨው ዜና አማካኝነት ዘግቧል። ገንዘብ አያያዝን በሚመለከት የምክር አገልግሎት የሚሰጥ አንድ የአውስትራሊያ ኩባንያ ባደረገው ጥናት ላይ ከተካፈሉ ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት “ለራሳቸው ሕክምና ከሚያውሉት ጊዜና ገንዘብ ይልቅ ለቤት እንስሳቸው” የሚያጠፉት ይበልጣል። ለቤት እንስሳቱ ከሚታዘዙላቸው የሕክምና ዓይነቶች መካከል አጥንት መቀጠል፣ ኬሞቴራፒ፣ የአካል ክፍሎችን ለመቀየር የሚደረግ ቀዶ ሕክምና፣ ሽንጥ ወይም ዳሌ መተካት አልፎ ተርፎም የአንጎል ቀዶ ሕክምና ይገኙበታል።