በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ልማድ ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

ይህን ልማድ ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ይህን ልማድ ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

“ማስተርቤሽን መፈጸም ስጀምር የስምንት ዓመት ልጅ ነበርኩ። ከጊዜ በኋላ አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት ተማርኩ። በዚህ ልማድ በተሸነፍኩ ቁጥር በጣም አዝናለሁ። ‘አምላክ እንደ እኔ ያለውን ሰው እንዴት ሊወድ ይችላል?’ እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር እንደማልበቃ ይሰማኝ ነበር።”—ሉዊዝ *

አንተም እንደ ሉዊዝ የማስተርቤሽን (ስሜትን ለማርካት ተብሎ የጾታ ብልትን የማሻሸት) ልማድ ተጠናውቶህ ይሆናል። ይህን ድርጊት እንድትፈጽም የሚገፋፋህን ኃይለኛ ስሜት የምትቋቋምና የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆነውን ራስን የመግዛት ባሕርይ የምታሳይ ከሆነ ይሖዋ በአንተ እንደሚደሰት ታውቃለህ። (ገላትያ 5:22, 23፤ 2 ጴጥሮስ 1:5, 6) ሆኖም አንዳንድ ጊዜ በዚህ ልማድ ትሸነፍ ይሆናል። ይህ ልማድ ባገረሸብህ ቁጥር ልትለወጥና ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተህ ልትኖር እንደማትችል አድርገህ ታስባለህ።

ፔድሮ የተባለ ወጣት ይሰማው የነበረው ልክ እንደዚህ ነበር። እንዲህ ይላል:- “ልማዱ ሲያገረሽብኝ በጣም አዝናለሁ። ለሠራሁት ስህተት ፈጽሞ ይቅርታ ሊደረግልኝ እንደማይችል ይሰማኛል። መጸለይ እንኳ ይከብደኛል። ‘ይሖዋ ጸሎቴን ትሰማ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፣ ግን . . .’ በማለት ጸሎቴን እጀምራለሁ።” አንድሬ የተባለ ወጣትም የሚከተለውን ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥቷል:- “ግብዝ እንደሆንኩ ይሰማኛል። የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዬን ለማከናወን ጠዋት ከአልጋ መነሳት ትግል ነበር። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ወይም በአገልግሎት መካፈል አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር።”

አንተም እንደ ሉዊዝ፣ ፔድሮ ወይም አንድሬ ዓይነት ስሜት የሚሰማህ ከሆነ አይዞህ። ይህ ችግር ያለብህ አንተ ብቻ እንደሆንክ እንዲሁም ልትለወጥ እንደማትችል አድርገህ አታስብ! በርካታ ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች ይህን ልማድ ታግለው ማሸነፍ ችለዋል። አንተም ልታሸንፈው ትችላለህ። *

የጥፋተኝነትን ስሜት ማሸነፍ

ከላይ እንዳየነው ማስተርቤሽን የመፈጸም ልማድ ያላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ በጥፋተኝነት ስሜት ይሠቃያሉ። ‘እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሐዘን’ ይህን ልማድ ለማሸነፍ ኃይል ሊሰጥህ እንደሚችል ምንም አያጠራጥርም። (2 ቆሮንቶስ 7:11) ሆኖም ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ተስፋ ስለሚያስቆርጥህ ይህን ልማድ ለማሸነፍ የምታደርገውን ጥረት እርግፍ አድርገህ እንድትተው ሊያደርግህ ይችላል።—ምሳሌ 24:10

ስለዚህ ስለ ጉዳዩ ትክክለኛ ግንዛቤ ሊኖርህ ይገባል። ማስተርቤሽን ርኩስ ድርጊት ነው። “ለተለያየ ምኞትና ምቾት ባሪያ” እንድትሆን ከማድረጉም በላይ አእምሮን ሊያቆሽሹ ለሚችሉ መጥፎ ዝንባሌዎች ያጋልጥሃል። (ቲቶ 3:3) ሆኖም ስሜትን ለማርካት ተብሎ የራስን የጾታ ብልት ማሻሸት እንደ ዝሙት ያለ ከባድ የጾታ ብልግና አይደለም። (ኤፌሶን 4:19) በመሆኑም ይህ ችግር ካለብህ ይቅር የማይባል ኃጢአት ሠርቻለሁ ብለህ አትደምድም። ችግሩን ለማሸነፍ ቁልፉ ይህን ድርጊት እንድትፈጽም የሚገፋፋህን ኃይለኛ ስሜት መቋቋምና ፈጽሞ ጥረትህን አለማቆምህ ነው!

አንዳንድ ጊዜ ልማዱ ሲያገረሽብህ በቀላሉ ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ። በዚህ ጊዜ በምሳሌ 24:16 ላይ የሚገኘውን “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣልና፤ ክፉዎች ግን በጥፋት ይወድቃሉ” የሚለውን ጥቅስ አስታውስ። ለተወሰነ ጊዜ ይህ ልማድ ስላገረሸብህ ክፉ ሰው ነህ ማለት አይደለም። በመሆኑም ተስፋ አትቁረጥ። ከዚህ ይልቅ ይህ ልማድ እንዲያገረሽብህ ያደረገውን ነገር ለማወቅና ያንን ደግመህ ላለማድረግ ጥረት አድርግ።

ነጋ ጠባ ስላለብህ ችግር እያሰብክ ራስህን ከመውቀስ ይልቅ በይሖዋ ፍቅርና ምሕረት ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መድብ። በሥነ ምግባር ድክመት ተሸንፎ የነበረው መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል። እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።” (መዝሙር 103:13, 14) አዎን፣ ይሖዋ ፍጹማን አለመሆናችንን ግምት ውስጥ የሚያስገባ ከመሆኑም ሌላ ስህተት በምንሠራበት ጊዜ “ይቅር” ለማለት ዝግጁ ነው። (መዝሙር 86:5) በሌላው በኩል ግን ለመሻሻል ጥረት እንድናደርግም ይፈልጋል።

ይህን ልማድ ለማሸነፍ እንድትችልና ችግሩ እንዳያገረሽብህ ለማድረግ የሚረዱ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ?

ሌሎችን ማማከር ያለው ጥቅም

በበርካታ አገሮች ስለ ጾታ ግንኙነት በሰፊው የሚነገር ቢሆንም ብዙ ሰዎች በቁም ነገርና ክብር ባለው መንገድ ስለዚህ ጉዳይ ማውራት ይከብዳቸዋል። አንተም ብትሆን ለምትቀርበው ሰው እንኳ ይህንን ጉዳይ አንስቶ ማውራት ያሳፍርህ ይሆናል። ለብዙ ዓመታት ይህን ልማድ ለማሸነፍ ሲታገል የቆየ አንድ ክርስቲያን እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ወጣት ሳለሁ ስለዚህ ጉዳይ ከአንድ ሰው ጋር ለመወያየት የሚያስችል ድፍረት በነበረኝ ኖሮ እላለሁ! ለብዙ ዓመታት በጥፋተኝነት ስሜት ስሠቃይ የኖርኩ ከመሆኑም በላይ ይህ ችግር ከሌሎች ጋርና ከሁሉም በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና በእጅጉ ጎድቶታል።”

ታዲያ ሁኔታውን ለማን ማወያየት ትችላለህ? በመንፈሳዊ ለጎለመሰ ሰው ቢቻል ለወላጅ ማማከር ከሁሉ የተሻለ አማራጭ ነው። ምናልባት እንዲህ ብለህ መጀመር ትችላለህ:- “በጣም እያስጨነቀኝ ስላለ አንድ ችግር ላወያይህ/ሽ እችላለሁ?”

ማርዮ አባቱን ለማነጋገር ወሰነ፤ አባቱም የልጁን ስሜትና ችግሩን በሚገባ ተረዳለት። እንዲያውም እርሱ ራሱ ወጣት ሳለ ይህንን ልማድ ለማሸነፍ መታገል አስፈልጎት እንደነበረ ገለጸለት። ማሪዮ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “የአባቴ ሐቀኝነትና ሊረዳኝ ከልቡ መፈለጉ በእጅጉ አበረታታኝ። እርሱ ይህን ልማድ ማሸነፍ ከቻለ እኔም የማልችልበት ምንም ምክንያት የለም ብዬ አሰብኩ። የአባቴ አመለካከት ልቤን ስለነካው ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ አለቀስኩ።”

አንድሬም በድፍረት ለአንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ችግሩን ያማከረ ሲሆን እንዲህ በማድረጉም ተደስቷል። * አንድሬ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ሽማግሌው እኔን በሚያዳምጥበት ጊዜ ዓይኑ እንባ አቀረረ። ተናግሬ እንደጨረስኩ፣ ይሖዋ እንደሚወደኝ ያረጋገጠልኝ ከመሆኑም ሌላ ያለብኝ ችግር ብዙ ሰዎችን የሚያጋጥም እንደሆነ ነገረኝ። የማደርገውንም ለውጥ እንደሚከታተልና ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ላይ ይህን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን እንደሚያመጣልኝ ቃል ገባልኝ። ከእርሱ ጋር መነጋገሬ ችግሩ በሌላ ጊዜ ቢያገረሽብኝ እንኳ በማደርገው ትግል ለመቀጠል እንድቆርጥ አድርጎኛል።”

ልክ እንደ ማሪዮና አንድሬ አንተም ብትሆን የማስተርቤሽንን ልማድ ለማሸነፍ በምታደርገው ጥረት እርዳታ ማግኘት ትችላለህ። “ይህን ልማድ ለማሸነፍ እርምጃ ውሰድ!” የሚለው ሣጥን ውስጥ የሚገኘውን ምክር ለመከተል ጥረት አድርግ። በትግሉ ማሸነፍ እንደምትችል እርግጠኛ ሁን!

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.6 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ወንዶች ቢሆኑም ከማስተርቤሽን ልማድ ለመላቀቅ የሚታገሉ በርካታ ሴቶችም አሉ። በመሆኑም የተሰጠው ምክር ለሁለቱም ጾታዎች ይሠራል። በተጨማሪም ይህ ርዕስ የሚያብራራው ስሜትን ለማርካት ብሎ የራስን የጾታ ብልት ስለማሻሸት ነው። የትዳር ጓደኛ ካልሆነ ሰው ጋር ይህን ድርጊት መፈጸም በአምላክ ዓይን ከባድ ኃጢአት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙት ብሎ በሚጠራው ድርጊት ውስጥ ይካተታል። በነሐሴ 2004 ንቁ! መጽሔት ገጽ ከ10-12 ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምን ስህተት አለው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.17 አንዲት ወጣት ሴት እናቷን ወይም በጉባኤ የምትገኝ የጎለመሰች ክርስቲያን እህትን ለማወያየት ትፈልግ ይሆናል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ይሖዋ “ይቅር” ለማለት ዝግጁ መሆኑን ማስታወሱ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?—መዝሙር 86:5

▪ የማስተርቤሽንን ልማድ ለማሸነፍ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ?

▪ እርዳታ ለመጠየቅ ማፈር የሌለብህ ለምንድን ነው?

▪ አእምሮህ ንጹሕ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ልማዱ ስላገረሸብህ በትግሉ ተሸንፈሃል ማለት አይደለም!

‘አልሆነልኝም፤ ስለዚህ ከናካቴው ብተወው ይሻለኛል’ ብሎ ማሰብ እንዴት ቀላል ነው። እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት አስወግድ። ለጊዜው ወይም በተደጋጋሚ ጊዜያት ችግሩ ቢያገረሽብህም፣ ይህ በትግሉ እንድትሸነፍ ሊያደርግህ አይገባም።

አንድ ምሳሌ ተመልከት:- አንድ ፎቅ በደረጃ እየወጣህ ሳለ ተደናቅፈህ አንድ ወይም ሁለት ደረጃ ወደኋላ ተመለስክ እንበል፣ ‘እንደገና ተመልሼ ከመጀመሪያው ደረጃ መጀመር አለብኝ’ ብለህ ታስባለህ? እንዲህ እንደማታስብ የታወቀ ነው! ታዲያ መጥፎ ልማድህን ለማሸነፍ በምታደርገው ትግልስ ለምን እንደዚህ ታስባለህ?

ልማዱ ሲያገረሽብህ በአብዛኛው የጥፋተኝነት ስሜት መኖሩ አይቀርም። ይህ ዓይነቱ የጥፋተኝነት ስሜት የማትረባ፣ ደካማና ምንም ጥሩ ነገር የማይገባህ ሰው እንደሆንክ በማሰብ ወደ ሌላኛው ጽንፍ እንድትሄድ ሊያደርግህ ይችላል። እንዲህ ባለ የተጋነነ የጥፋተኝነት ስሜት መዋጥ የለብህም። እንዲህ ያለው ስሜት በትግሉ ለመቀጠል የሚያስችልህን ኃይል ያሟጥጥብሃል። በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰዎችን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ሊቤዥ እንደመጣ ማስታወስ ያስፈልጋል። ስለሆነም ማናችንም ብንሆን በአሁኑ ጊዜ ነገሮችን ፍጹም ትክክል በሆነ መንገድ ማከናወን አንችልም።—ከሚያዝያ 8, 1991 ንቁ! መጽሔት ገጽ 15 (እንግሊዝኛ) የተወሰደ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ይህን ልማድ ለማሸነፍ እርምጃ ውሰድ!

▪ አእምሮህ በሌሎች ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አስገድደው።ፊልጵስዩስ 4:8

▪ ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶች እንዲያቆጠቁጡ የሚያደርጉ ነገሮችን ከመመልከት ተቆጠብ።—መዝሙር 119:37

▪ “እጅግ ታላቅ ኀይል” ለማግኘት ጸልይ።—2 ቆሮንቶስ 4:7

▪ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ራስህን አስጠምድ።—1 ቆሮንቶስ 15:58

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ተጨማሪ እርዳታ

የማስተርቤሽንን ልማድ ለማሸነፍ የሚረዳ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት፣ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና—ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የሚለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 25 እና 26 ተመልከት።