በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዛሬዎቹ ወጣቶች የሚሆን እርዳታ

ለዛሬዎቹ ወጣቶች የሚሆን እርዳታ

ለዛሬዎቹ ወጣቶች የሚሆን እርዳታ

በዛሬው ጊዜ ወጣቶች የሚያድጉበት ዓለም አንዳንድ ጊዜ የሚያስፈራ ሆኖ ሊታያቸው ይችላል። አንዳንዶቹ ወላጆቻቸው ሲለያዩ ወይም ሲፋቱ ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸው በዝምታ ይመለከታሉ። ሌሎች ደግሞ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው በአደገኛ ዕፅና በወንጀል ተጠምደው ወደ አዘቅት ሲወርዱ ያያሉ። ብዙዎቹ በወሲባዊ ድርጊት እንዲካፈሉ ከተቃራኒም ሆነ ከተመሳሳይ ጾታ እኩዮቻቸው ጫና ይደረግባቸዋል። እንዲሁም ሁሉም ማለት ይቻላል አልፎ አልፎ የብቸኝነት፣ የጭንቀትና የሚረዳቸው ሰው የማጣት ችግር ይደርስባቸዋል።

ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም ምን ያስፈልጋቸዋል? ዶክተር ሮበርት ሾው “ልጆች ጠንካራ የሥነ ምግባር ደንብ ይኸውም ጥሩ ጓደኛ እንዲመርጡ፣ ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያደርጉና ለሌሎች አዛኝ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ዘላቂ መመሪያ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ ጽፈዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የፈጣሪ ቃል የሰፈረበት መጽሐፍ በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን ጠንካራና ዘላቂ መመሪያ ይዟል። ይህን አስጨናቂ ዘመን ለመቋቋም የሚያስፈልገን ምን እንደሆነ ከይሖዋ አምላክ የበለጠ ማን ሊያውቅ ይችላል?

ተጨባጭና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጨባጭና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። ወጣቶችን ወደ ጉልምስና ዕድሜ በሚያደርሰው መንገድ ለመምራት ለሚፈልጉ ወላጆችና ሌሎች ሰዎች በጣም ጠቃሚ ናቸው።

ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል”፤ ወይም ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን እንደሚለው “ልጆች በተፈጥሮአቸው የግዴለሽነትና የሞኝነት ሥራ ይሠራሉ” በማለት ያለውን እውነታ አምኖ ይቀበላል። (ምሳሌ 22:15) አንዳንድ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ከዕድሜያቸው ቀድመው የበሰሉ ቢመስሉም ገና በቂ ተሞክሮ ያላገኙ ወጣቶች መሆናቸው አልቀረም። በመሆኑም የእድገት ክፍል ለሆኑት ያለመረጋጋት፣ ግራ የመጋባት፣ የመረበሽ ስሜቶችና የወጣትነት ፍላጎቶች የተጋለጡ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) ታዲያ እነዚህን ወጣቶች እንዴት መርዳት ይቻላል?

መጽሐፍ ቅዱስ በወላጆችና በልጆች መካከል የማይቋረጥ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖር ያበረታታል። ወላጆችን፣ የአምላክን ሥርዓቶች “ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር” ሲል ያዛል። (ዘዳግም 6:6, 7) እንዲህ ያለው ጭውውት ሁለት ጥቅም አለው። በመጀመሪያ ልጆች የአምላክን መንገዶች እንዲማሩ ያስችላል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ሁለተኛ፣ ወላጆችና ልጆች የሚነጋገሩበት አጋጣሚ ይሰጣል። በተለይ ልጆች ብቸኛ መሆንና ከሰው መራቅ የሚፈልጉበት የጉርምስና ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ይህ በጣም አስፈላጊ ይሆናል።

እርግጥ አብዛኞቹ ወጣቶች አልፎ አልፎ ብቸኝነት ይሰማቸዋል፤ አንዳንዶች ግን እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ለረዥም ጊዜ ይጠናወታቸዋል። አንድ ስለ ወጣቶች የተዘጋጀ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “እንደነዚህ ያሉት ወጣቶች በትምህርት ቤት ጓደኛ ማግኘት እንዳስቸገራቸው፣ የሚያናግራቸው ሰው እንደሌለ፣ ብቸኝነት እንደሚሰማቸው፣ ሌሎች ልጆች እንዲቀርቧቸው ማድረግ እንዳስቸገራቸው እንዲሁም ችግር ሲያጋጥማቸው እርዳኝ ብለው የሚጠይቁት ሰው እንደሌላቸው ይናገራሉ” ይላል። *

ወላጆችና ጉዳዩ የሚያሳስባቸው ትላልቅ ሰዎች ቅድሚያውን ወስደው ወጣቶች ችግሮቻቸውን እንዲቋቋሙ መርዳት ይችላሉ። እንዴት? የአንድ የወጣቶች መጽሔት ዋና አዘጋጅ “በወጣቶቹ አእምሮ ውስጥ ምን እየተጉላላ እንዳለ ማወቅ የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ እነርሱኑ መጠየቅ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። ወጣቶች በልባቸው ያለውን የሚያሳስባቸውንና የሚያስጨንቃቸውን ነገር አውጥተው እንዲናገሩ ለማድረግ ጊዜና ትዕግሥት እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ከሚገኘው ጥቅም አንጻር ሲታይ ጥረቱና ድካሙ አያስቆጭም።—ምሳሌ 20:5

ምክንያታዊ ገደብ ማበጀት

ወጣቶች ከጥሩ የሐሳብ ግንኙነት በተጨማሪ ምክንያታዊ የሆኑ ገደቦች ያስፈልጓቸዋል። እነርሱም ቢሆኑ ይህንኑ ይፈልጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “መረን የተለቀቀ ልጅ . . . እናቱን ያሳፍራል” ይላል። (ምሳሌ 29:15) ሊቃውንት እንደሚናገሩት የወጣቶች ምግባረ ብልሹነት ዋነኛ መንስኤ ግልጽ የሆኑ ገደቦች አለመኖር ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዶክተር ሾው “አንድ ሕፃን ያደገው የጠየቀው ሁሉ እየተደረገለት ተሞላቅቆ ወይም ‘አይቻልም’ የሚል ቃል ሳይሰማ አሊያም ምንም ዓይነት ገደብ ሳይደረግበት ከሆነ ሌሎች ሰዎች የራሳቸው ሕይወት፣ ስሜት፣ ፍላጎትና ፈቃድ እንዳላቸው ሊማር አይችልም። ራሱን በሌሎች ቦታ አድርጎ የማየት ባሕርይ ካላዳበረ ለሌሎች ፍቅር ሊኖረው አይችልም።”

ለበርካታ ዓመታት፣ ችግር ያጋጠማቸውን ወጣቶች ሲረዱ የቆዩት ዶክተር ስታንተን ሴምናው ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥተዋል። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አንዳንድ ወላጆች ልጆች እንደፈለጋቸው መኖር አለባቸው ብለው ያምናሉ። በእነርሱ ላይ ግዳጅ ወይም ኃላፊነት መጫን ተገቢ ያልሆነ ጫና ያሳድርባቸዋል እንዲሁም ልጅነታቸውን ያሳጥርባቸዋል የሚል ጭፍን አስተሳሰብ አላቸው። ይሁን እንጂ ገደብ አለማበጀታቸው በጣም አደገኛ ውጤት ያስከትላል። ተግሣጽ ወይም እርማት ሳያገኝ ያደገ ልጅ ራሱን መገሠጽና መቆጣጠር እንደሚያስቸግረው አይገነዘቡም።”

ታዲያ እንዲህ ሲባል ወላጆች በጣም ጥብቅ መሆን አለባቸው ማለት ነው? በፍጹም አይደለም። ገደብ ማበጀት የጥሩ አስተዳደግ አንድ ዘርፍ ነው። ቁጥጥሩ በጣም ጠንክሮ የማያፈናፍን ሕግ ከወጣ ቤቱ ውጥረት የሰፈነበት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “አባቶች ሆይ፤ ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው” ይላል።—ቈላስይስ 3:21፤ ኤፌሶን 6:4

ስለዚህ ወላጆች በተለይ ልጆቻቸው በዕድሜ እያደጉና እየበሰሉ ሲሄዱ የመመሪያና የተግሣጽ አሰጣጥ ዘዴያቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ መገምገም ይኖርባቸዋል። የልጁ ኃላፊነት የመሸከም አቅም እየታየ አንዳንድ መመሪያዎችን ወይም ገደቦችን ላላ ማድረግ ወይም ማሻሻል ይቻል ይሆናል።—ፊልጵስዩስ 4:5

ጠንካራ ትስስር መገንባት

በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው አምላክ ጣልቃ ገብቶ ከዓለም ላይ ክፋትን ከማጥፋቱ በፊት “የሚያስጨንቅ ጊዜ” እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮአል። የምንኖረው በዚህ አምላክ የለሽ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ዘመን’ ውስጥ እንደሆነ ማስረጃዎች ያመለክታሉ። ወጣቶችም እንደ አዋቂዎች “ራሳቸውን የሚወዱ . . . ፍቅር የሌላቸው፣ . . . ራሳቸውን የማይገዙ” ሰዎች የበዙበትን ይህን ዓለም መቋቋም ይኖርባቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 *

ከጎረምሳ ልጃቸው በጣም እንደተራራቁ የሚሰማቸው ወላጆች አንዳንድ እርምጃዎችን በመውሰድና በመነጋገር በመካከላቸው ያለውን ትስስር ሊያጠነክሩ ይችላሉ። ብዙ ወላጆች በልጆቻቸው ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳደርና የተቀራረበ ዝምድና ለመመሥረት ጥረት የሚያደርጉ መሆናቸው የሚያስመሰግን ነው።

በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ጠቃሚ መሣሪያ ነው። ብዙ ወላጆች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ወጣቶች ደግሞ አደገኛ ወጥመድ ውስጥ ከመውደቅ እንዲጠበቁ አስችሏል። (ዘዳግም 6:6-9፤ መዝሙር 119:9) መጽሐፍ ቅዱስ ከፈጣሪያችን ከይሖዋ አምላክ የመጣ በመሆኑ ለዛሬዎቹ ወጣቶች የሚሰጠው እርዳታ ተወዳዳሪ የሌለው እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ አልፎ አልፎ የብቸኝነት ስሜት ከሚሰማው ወጣት ይልቅ ስር የሰደደ የብቸኝነት ስሜት ያለበት ወጣት አብዛኛውን ጊዜና ለረዥም ጊዜ ራሱን ከሰዎች እንደሚያገል ጠቁሟል። “ጓደኛ ማጣት የማይለወጥ፣ መቆጣጠር የማይቻልና በራሱ ውስጣዊ ጉድለት የሚመጣ” እንዲሁም ሁኔታው “አሁንም ሆነ ወደፊት ሊለወጥ የማይችል እንደሆነ ያምናል።”

^ አን.18 የይሖዋ ምሥክሮች፣ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት 39 ምዕራፎች አሳሳቢ ጥያቄዎችን ያብራራሉ። አንዳንዶቹ ርዕሶች የሚከተሉት ናቸው:- “እውነተኛ ጓደኞች ላፈራ የምችለው እንዴት ነው?” “የእኩዮችን ግፊት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” “የብቸኝነት ስሜት እንዲለቀኝ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?” “ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠርኩ ለመጫወት ደርሻለሁን?” “አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ እምቢ መባል የሚኖርበት ለምንድን ነው?” “ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ቢፈጸም ምናለበት?”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚያሳስቡህን ነገሮች አሳቢ ከሆነ ሰው ጋር ተወያይ