በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሻለ ጤና ለማግኘት የተደረገ የዘመናት ትግል

የተሻለ ጤና ለማግኘት የተደረገ የዘመናት ትግል

 የተሻለ ጤና ለማግኘት የተደረገ የዘመናት ትግል

በኒው ዮርክ ትኖር የነበረችው ጆዋን ሳንባ ነቀርሳ ያዛት። ይሁን እንጂ የያዛት ሳንባ ነቀርሳ የተለመደው ዓይነት አልነበረም። አሉ የሚባሉትን መድኃኒቶች በሙሉ መቋቋም የሚችልና ከያዛቸው ሕመምተኞች መካከል ከግማሽ የሚበልጡትን የሚገድል ነበር። ይሁን እንጂ ጆዋን ሕክምናዋን በሥርዓት አልተከታተለችም። በመሆኑም ቢያንስ ለተወሰኑ ሰዎች በሽታዋን አጋብታለች። በሁኔታዋ የተበሳጨው ሐኪሟ ‘ታስራ መቀመጥ ነበረባት’ ብሏል።

ሳንባ ነቀርሳ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ቀሳፊ በሽታ ነው። በዚህ በሽታ የተሰቃዩና የሞቱ ሰዎች በሚሊዮን ይቆጠራሉ። በጥንቷ ግብጽና ፔሩ እንዳይፈራርሱ ተጠብቀው በቆዩ አስከሬኖች ላይ የበሽታው ምልክት ታይቷል። ዛሬ ደግሞ በአዲስ መልክ አገርሽቶ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎችን በመግደል ላይ ነው።

በአፍሪካ በአንድ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ አነስተኛ አልጋ ላይ ተኝቶ የሚቃትተው ካርሊቶስ ላቡ ግንባሩ ላይ ችፍ ብሏል። በወባ በሽታ ምክንያት ማልቀስ እንኳን እስኪያቅተው ድረስ ተዳክሟል። ግራ የተጋቡት ወላጆቹ መድኃኒት የሚገዙበት ገንዘብ የሌላቸው ከመሆኑም በላይ ልጃቸውን የሚያሳክሙበት ክሊኒክ በአቅራቢያቸው የለም። ትኩሳቱ እየባሰበት ሄዶ በ48 ሰዓት ውስጥ ሞተ።

ወባ በየዓመቱ እንደ ካርሊቶስ ያሉ አንድ ሚሊዮን የሚያክሉ ሕፃናትን ሕይወት ይቀጥፋል። በምሥራቅ አፍሪካ መንደሮች አንድ ልጅ በአማካይ በአንድ ወር ውስጥ ከ50 እስከ 80 ጊዜ ድረስ ወባ ተሸካሚ በሆኑ ትንኞች ይነደፋል። ትንኞቹ ቀድሞ ወዳልነበሩባቸው አዳዲስ አካባቢዎች እየተዛመቱ ከመሆኑም በላይ ፀረ ወባ መድኃኒቶች ፈዋሽነታቸው እየቀነሰ መጥቷል። በየዓመቱ 300 ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች አጣዳፊ በሆነ የወባ በሽታ እንደሚሰቃዩ ይገመታል።

በሳን ፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርኒያ የሚኖረው የ30 ዓመቱ ኬነት ዶክተሩ ዘንድ ለሕክምና የቀረበው በ1980 ነበር። ተቅማጥና ድካም እንደሚያስቸግረው ተናገረ። ከአንድ ዓመት በኋላ ሕይወቱ አለፈች። እውቅ የሆኑ ሐኪሞች ክትትል ያደረጉለት ቢሆንም ሰውነቱ እየመነመነ ሄዶ በመጨረሻ በሳንባ ምች ሕይወቱን አጣ።

ከሁለት ዓመት በኋላ ከሳን ፍራንሲስኮ 16,000 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኘው የሰሜናዊ ታንዛኒያ መንደር አንዲት ወጣት ሴት ተመሳሳይ ሕመም ይሰማት ጀመር። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ መራመድ እንኳን አቃታትና ብዙም ሳትቆይ ሞተች። የመንደሩ ሰዎች ለዚህ እንግዳ የሆነ በሽታ የጁልያና በሽታ የሚል ስም አወጡለት። ይህን ስያሜ ያወጡለት በዚህች ወጣትና በሌሎች የመንደሩ ሴቶች ላይ በሽታውን ያጋባው ጁልያና የሚል ስም የተጻፈባቸውን ልብሶች ይሸጥ የነበረ ሰው ስለሆነ ነው።

የኬነትም ሆነ የታንዛኒያዊቷ ሴት በሽታ ኤድስ ነበር። የሕክምና ሳይንስ በጣም አደገኛ የሆኑትን በሽታ አምጪ ረቂቅ ተሕዋስያን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገ መስሎ በታየበት በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ይህ ተዛማች በሽታ ብቅ ብሎ የሰው ልጆችን ማወክ ጀመረ። በሁለት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ብቻ በኤድስ የተቀሰፉት ሰዎች ብዛት በአሥራ አራተኛው መቶ ዘመን አውሮፓንና እስያን ከጠራረገውና ምንጊዜም ከአውሮፓውያን ሕሊና ከማይጠፋው ዘግናኝ የሆነ ወረርሽኝ የማይተናነስ ሆነ።

ጥቁሩ ሞት

ጥቁሩ ሞት የተባለው ወረርሽኝ የፈነዳው ከክሪሚያ የመጣ መርከብ በሲስሊ ደሴት በምትገኘው መሲና የተባለች  የወደብ ከተማ መልሕቅ በጣለበት በ1347 ነበር። መርከቡ ይዞት ከመጣው መደበኛ ጭነት በተጨማሪ ወረርሽኝም አምጥቶ ነበር። * ወዲያው ጥቁሩ ሞት መላይቱን ኢጣሊያ አዳረሰ።

በቀጣዩ ዓመት የሲዬና፣ ኢጣሊያ ተወላጅ የሆነው አኞሎ ዲ ቱራ የከተማውን ሰዎች ሰቆቃ እንደሚከተለው በማለት ገልጿል:- ‘በሲዬና ሰዎች መሞት የጀመሩት በግንቦት ወር ነበር። በጣም የሚዘገንንና የሚያስጨንቅ ሁኔታ ነበር። በበሽታው የተለከፉ ሰዎች ሳይውሉ ሳያድሩ ወዲያው ይሞታሉ። ቀን ከሌት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይረግፋሉ።’ በመቀጠል ‘አምስት ልጆቼን በገዛ እጄ ቆፍሬ ቀበርኩ። ተመሳሳይ ዕጣ የገጠማቸው ብዙዎች ናቸው። ሁሉም ሰው ከዛሬ ነገ እሞታለሁ ብሎ ይጠብቅ ስለነበር ምንም ያህል ዘመድ ቢሞትበት የሚያለቅስ ሰው አልነበረም። ሰዎች እንደ ቅጠል ይረግፉ ስለነበረ ሰው ሁሉ የዓለም ፍጻሜ የቀረበ መስሎት ነበር’ ብሏል።

አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚሉት ወረርሽኙ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ መላዋን አውሮፓ ሲያዳርስ ከጠቅላላው ሕዝብ ሲሶ የሚሆነው፣ ምናልባት ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ሞተዋል። ሰው እምብዛም የማይደርስባት አይስላንድ እንኳ ሳትቀር ብዙ ሕዝብ አልቆባታል። በሩቅ ምሥራቅ በ13ኛው መቶ ዘመን 123 ሚሊዮን ይደርስ የነበረው የቻይና ሕዝብ ቁጥር በ14ኛው መቶ ዘመን ላይ ወደ 65 ሚሊዮን ወርዶ ነበር። የሕዝቡ ብዛት ይህን ያህል ሊቀንስ የቻለው በወረርሽኙና ወረርሽኙን ተከትሎ በመጣው ረሃብ ምክንያት ነው።

 ከዚያ በፊት ይህን የሚያክል መከራና ሥቃይ ያስከተለ ወረርሽኝ፣ ጦርነት ወይም ረሃብ አልነበረም። ማን ኤንድ ማይክሮብስ የተባለው መጽሐፍ “በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ አቻ ያልተገኘለት እልቂት ነበር” ብሏል። “በአውሮፓ፣ በሰሜን አፍሪካና በአንዳንድ የእስያ አገሮች ይኖሩ ከነበሩት ሰዎች መካከል ከአንድ አራተኛ እስከ ግማሽ የሚሆኑት አልቀዋል።”

የአሜሪካ አገሮች ከቀረው ዓለም ተነጥለው የሚገኙ በመሆናቸው ከጥቁር ሞት እልቂት አምልጠዋል። ይሁን እንጂ መርከበኞች ውቅያኖስ አቋርጠው መጓዝ ሲጀምሩ ሁኔታው ተለወጠ። በ16ኛው መቶ ዘመን ከጥቁር ሞት የከፋ የወረርሽኝ ሰደድ አዲሱን ዓለም መመንጠር ጀመረ።

ፈንጣጣ የአሜሪካን አገሮች ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ

ኮለምበስ በ1492 ዌስት ኢንዲስ ደሴቶች በደረሰ ጊዜ የአገሬው ሰዎች ‘የሚያምር መልክ፣ ጥሩ ቁመና፣ ፈርጠም ያለ ጡንቻና መካከለኛ ቁመት ያላቸው’ እንደሆኑ ገልጾ ነበር። ብርቱና ጠንካራ መስሎ ይታይ የነበረው ቁመናቸው ግን የምሥራቁን ንፍቀ ክበብ በሽታዎች ሊቋቋምላቸው አልቻለም።

በ1518 በሂስፓንዮላ ደሴት የፈንጣጣ ወረርሽኝ ተከሰተ። የአገሬው ተወላጆች ፈንጣጣ ነክቷቸው የማያውቁ በመሆናቸው ከፍተኛ እልቂት ደረሰባቸው። የስፔይን ተወላጅ የሆነ አንድ የዓይን ምሥክር በዚህች ደሴት በሕይወት የተረፉት አንድ ሺህ የሚያክሉ ሰዎች ብቻ እንደነበሩ ተናግሯል። ወረርሽኙ ወዲያው ወደ ሜክሲኮና ፔሩ ተዛመተና ተመሳሳይ እልቂት አስከተለ።

በቀጣዩ መቶ ዘመን እንግሊዛውያን ሰፋሪዎች በሰሜን አሜሪካ ወደምትገኘው ወደ ማሳቹሴትስ ሲደርሱ ፈንጣጣ የአገሩን ሕዝብ ፈጅቶት ነበር። ጆን ዊንትሮፕ የተባሉት የሰፋሪዎቹ መሪ “የአገሬው ሰዎች በፈንጣጣ ምክንያት ሙሉ በሙሉ አልቀዋል ለማለት ይቻላል” ሲሉ ጽፈዋል።

ፈንጣጣን ተከትለው ሌሎች ወረርሽኞችም ተከሰቱ። አንድ መረጃ እንደሚያመለክተው ኮለምበስ አሜሪካን በረገጠ በአንድ መቶ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከውጭ የገቡ ወረርሽኝ በሽታዎች 90 በመቶ የሚያክለውን የአዲሱ ዓለም ነዋሪ ጠራርገውት ነበር። የሜክሲኮ ሕዝብ ብዛት ከ30 ሚሊዮን ወደ 3 ሚሊዮን ያሽቆለቆለ ሲሆን የፔሩ ደግሞ ከስምንት ሚሊዮን ወደ አንድ ሚሊዮን ወርዶ ነበር። እርግጥ በፈንጣጣ ያለቁት የአሜሪካ ተወላጆች ብቻ አልነበሩም። ስከርጅ፣ ዚ ዋንስ ኤንድ ፊውቸር ትሬት ኦቭ ስሞልፖክስ የተባለው መጽሐፍ “በሰው ልጅ የታሪክ ዘመናት ፈንጣጣ የገደላቸው ሰዎች ብዛት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሲሆን . . . በሃያኛው መቶ ዘመን የተከሰቱት ወረርሽኞችና ጦርነቶች የጨረሷቸው ሰዎች ቁጥር አንድ ላይ ቢደመር እንኳን አይተካከሉትም” ብሏል።

አሁንም ድል አልተገኘም

ዛሬ የተለያዩ ወረርሽኞችና ፈንጣጣ ያደረሱት አሰቃቂ እልቂት በታሪክ አምዶች ብቻ የሚዘከር ያለፈ ነገር መስሎ ሊታይ ይችላል። በሃያኛው መቶ ዘመን የሰው ልጅ፣ በተለይ በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮች፣ ከተዛማች በሽታዎች ጋር ባደረገው ጦርነት ብዙ ድል ተቀዳጅቷል። ዶክተሮች የአብዛኛዎቹን በሽታዎች መንስኤም ሆነ መድኃኒት አግኝተዋል። (በሚቀጥለው ገጽ ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) አዳዲስ ክትባቶችና አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች አሻፈረኝ ብለው የቆዩ  በሽታዎችን ሳይቀር ማጥፋት የሚችሉ ተአምረኛ መሣሪያዎች መስለው ነበር።

ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ የአለርጂና የተዛማች በሽታዎች ብሔራዊ ተቋም ዳይሬክተር የነበሩት ሪቻርድ ክራውዜ እንዳመለከቱት “ወረርሽኝ እንደሞትና እንደግብር ልናመልጥ ከማንችላቸው ነገሮች አንዱ ሆኗል።” ሳንባ ነቀርሳንና ወባን ማጥፋት አልተቻለም። በቅርቡ የተከሰተው የኤድስ ወረርሽኝ ደግሞ የወረርሽኝ ጥላ ከዓለማችን ሊወገድ አለመቻሉን እንድንገነዘብ አስገድዶናል። ማን ኤንድ ማይክሮብስ የተባለው መጽሐፍ “በዓለማችን ላይ የብዙዎቹን ሕይወት እየቀጠፉ ያሉት ተዛማች በሽታዎች ሲሆኑ በመጪዎቹ በርካታ ዓመታትም ቢሆን በዋነኛ ቀሳፊነታቸው ይቀጥላሉ” ይላል።

አንዳንድ ዶክተሮች ከበሽታዎች ጋር በተደረገው ትግል አስደናቂ ውጤት ሊገኝ የቻለ ቢሆንም ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት የተገኙት ውጤቶች በአጭሩ ተቀጭተው የሚቀሩ ይሆናሉ ብለው ይሰጋሉ። “የተዛማች በሽታዎች አደገኛነት እየተባባሰ መጣ እንጂ ጋብ እንኳን አላለም” በማለት ሮበርት ሾፕ የተባሉት ኤፒዲሚዮሎጂስት ተናግረዋል። ይህ የሆነበትን ምክንያት የሚቀጥለው ርዕስ ያብራራልናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 ወረርሽኙ የቡቦኒክና የሳንባ ምች ወረርሽኝን ጨምሮ የተለያየ መልክ ነበረው። ቡቦኒክ የተባለው ወረርሽኝ ይዛመት የነበረው አይጦች ላይ በሰፈሩ ቁንጫዎች አማካኝነት ሲሆን የሳንባ ምቹ ደግሞ በሽተኞች ሲያስነጥሱና ሲስሉ በሚሠራጩት ተሕዋስያን ምክንያት ነው።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሁለት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ብቻ በኤድስ የተቀሰፉት ሰዎች ብዛት በአሥራ አራተኛው መቶ ዘመን አውሮፓንና እስያን ከጠራረገው ወረርሽኝ አይተናነስም

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እውቀትና አጉል እምነት

በ14ኛው መቶ ዘመን ጥቁሩ ሞት በአቪኞ የነበሩትን ሊቀ ጳጳሳት ቤተሰብ ያምስ በነበረበት ጊዜ ሐኪማቸው ይህ ቸነፈር የተከሰተው ሳተርን፣ ጁፒተርና ማርስ የተባሉት ሦስት ፕላኔቶች አክዋርየስ በተባለው የከዋክብት ጭፍራ ቅርጽ ስለተቀናጁ ነው ብለዋቸው ነበር።

ከአራት መቶ ዓመታት ያህል በኋላ ደግሞ ጆርጅ ዋሽንግተን ጉሮሯቸውን አመማቸውና ተኙ። ሦስት ታዋቂ ዶክተሮች ሁለት ሊትር የሚያክል ደም በዋግምት እየመጠጡ በማውጣት ሊያድኗቸው ብዙ ጣሩ። ታካሚው በጥቂት ሰዓት ውስጥ አረፉ። ገላን በመብጣት በበሽታ የተበከለን ደም መጦ ማውጣት ከሂፖክራተስ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ድረስ ለ2,500 ዓመታት የቆየ መደበኛ የሕክምና ዘዴ ነበር።

አጉል እምነትና ወግ ለሕክምና ሳይንስ እድገት ትልቅ ጋሬጣ ሆኖ ቢቆይም ታታሪ ዶክተሮች የተዛማች በሽታዎችን መንስኤ ለማወቅና ለእነዚህ በሽታዎች መድኃኒት ለማግኘት ብዙ ጥረዋል። ከደረሱባቸው ትላልቅ ግኝቶች አንዳንዶቹ ከታች ተዘርዝረዋል።

ፈንጣጣ። በ1798 ኤድዋርድ ጄነር ለፈንጣጣ ፍቱን የሆነ ክትባት ፈለሰፈ። በ20ኛው መቶ ዘመን ክትባቶች እንደ ፖሊዮ፣ ቢጫ ወባና ኩፍኝ የመሳሰሉትን ተዛማች በሽታዎች በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስገኝተዋል።

ሳንባ ነቀርሳ። በ1882 ሮበርት ኮኽ የሳንባ ነቀርሳን ባክቴሪያ ነጥሎ ከማሳወቁም በላይ በሽታው መኖሩን መርምሮ ለማግኘት የሚያስችል ዘዴ ፈለሰፈ። ከ60 ዓመት በኋላ ስትሬፕቶማይሲን የተባለው ሳንባ ነቀርሳን ፈጽሞ ሊያድን የሚችል አንቲባዮቲክ መድኃኒት ተፈለሰፈ። ይህ መድኃኒት ቡቦኒክ ቸነፈርን ጭምር ለማከም ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል።

ወባ። ከ17ኛው መቶ ዘመን ወዲህ ሲንቾና ከተባለው ዛፍ ቅርፊት የተገኘው ክዋይነን የተባለ መድኃኒት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የወባ ታማሚዎችን ሕይወት ታድጓል። ሮናልድ ሮስ በ1897 ወባ የምታዛምተው አኖፊለስ የምትባለው ትንኝ መሆኗን አሳወቀ። በዚህም ምክንያት ትንኞችን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት በቆላማ አካባቢዎች በወባ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ አስችሏል።

[ሥዕሎች]

የዞዲያክ ሰንጠረዥ (ከላይ) እና ገላን መብጣት

[ምንጭ]

ሁለቱም:- Biblioteca Histórica “Marqués de Valdecilla”

[በገጽ 3 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዛሬ፣ በአዲስ መልክ ያገረሸው ሳንባ ነቀርሳ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎችን ይቀስፋል

[ምንጮች]

ኤክስሬይ:- New Jersey Medical School–National Tuberculosis Center; ሰው:- ፎቶ:- WHO/Thierry Falise

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1500 አካባቢ የተሠራ ነው ተብሎ የሚታሰበው የጀርመን ቅርጽ አንድ ዶክተር ጥቁሩ ሞት እንዳይዘው ለመከላከል ጭንብል እንዳደረገ ያሳያል። በጭንብሉ ጫፍ ላይ ሽቶ ይደረግ ነበር

[ምንጭ]

Godo-Foto

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቡቦኒክ በሽታ የሚያስይዘው ባክቴሪያ

[ምንጭ]

© Gary Gaugler/Visuals Unlimited