በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብዙ ሰዎች በአለርጂ የሚሰቃዩት ለምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች በአለርጂ የሚሰቃዩት ለምንድን ነው?

 ብዙ ሰዎች በአለርጂ የሚሰቃዩት ለምንድን ነው?

ስፔይን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ዓይንህን ይበላሃል፣ እንባህ ይፈስሳል፣ ቀኑን ሙሉ ያስነጥስሃል፣ ከአፍንጫህ ውኃ መሰል ንፍጥ ያለማቋረጥ ይዝረበረባል እንዲሁም እንደልብ መተንፈስም ያስቸግርሃል። ምን ሆነህ ነው? ጉንፋን ይዞህ ይሆናል። እነዚህ ምልክቶች በተደጋጋሚ የሚታዩብህ የሚበኑ ነገሮች አጠገብ ስትሆን ከሆነ አለርጂ አለብህ ማለት ነው። ከሆነ አንተ ብቻ ሳትሆን በዚህ ሕመም የሚሰቃዩ ብዙ ሰዎች አሉ። ተመርምረው አለርጂ እንዳለባቸው የሚነገራቸው ሰዎች ቁጥር በያመቱ እየጨመረ ይሄዳል።

“አለርጂ ማለት ሰውነታችን ጎጂ እንደሆኑ አድርጎ ለሚያስባቸው ነገሮች ያለውን ከልክ ያለፈ ጥላቻ የሚገልጽበት መንገድ ነው” በማለት የዛሬዋ ሴት የሚል ትርጉም በያዘ ርዕስ የሚዘጋጀው መጽሔት ይዘግባል። “አለርጂ ያለባቸው ሰዎች በሽታን የሚከላከሉት የሰውነታቸው ሕዋሳት የአበባ ዱቄትን ጨምሮ እንደ ባዕድ የሚቆጥሯቸውን ነገሮች በሙሉ ይቃወማሉ። እነዚህን ነገሮች የሚጠሏቸው ግን ጎጂ ስለሆኑ አይደለም።” እነዚህ ነገሮች በሽታ ተከላካይ የሆኑትን የሰውነታችንን ሕዋሳት ሲያስቆጧቸው በመግቢያው ላይ የተገለጹት የሚረብሹ የሕመም ምልክቶች ይታያሉ።።

በ1819 አለርጂ ምን እንደሆነ የገለጹት እንግሊዛዊው ሐኪም ጆን ቦስቶክ ነበሩ። የዚህን የሕመም ምልክት ምንነት ለማስረዳት የመጀመሪያው ሐኪም ናቸው። ቦስቶክ ወቅት እየለየ የሚመጣባቸውን የራሳቸውን የሕመም ምልክት ዘርዝረዋል። እነዚህ ምልክቶች አዲስ በታጨደ ድርቆሽ ምክንያት የሚመጡ ናቸው ብለው ያምኑ ነበር። የኋላ ኋላ ግን ለአለርጂ መንስኤዎች ብዙ ዓይነት ብናኞች እንደሆኑ ተደርሶበታል። በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ቦስቶክ በመላው እንግሊዝ ያገኙአቸው የአለርጂ ተጠቂዎች በጣም ጥቂት ነበሩ።

በዛሬው ጊዜ ግን በአለርጂ የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር በጣም ብዙ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? በማድሪድ፣ ስፔይን የአስምና የአለርጂ በሽታዎች ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ካቪየር ሱቢሳ የተባሉ ሰው በተመራማሪዎች እየተጠኑ ያሉ ሁለት መላ ምቶችን ይጠቅሳሉ። አንዱ መላ ምት ተወቃሽ የሚያደርገው በናፍጣ የሚሠሩ ሞተሮችን ነው። ናፍጣ ሲቃጠል የሚያወጣቸው ቅንጣቶች ለአለርጂ ሕመሞች መንስኤ የሆነውን ነገር ሁሉ ይቀሰቅሳሉ። የአለርጂ ሕመም ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ክዋን ኮትኔ እንደሚሉት ከሆነ “በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች አለርጂ ከጠቅላላው ሕዝብ 20 በመቶ የሚሆነውን የሚያጠቃ ሲሆን በብዛት የሚታየው በከተሞች ነው።”

እንደ ተመራማሪዎቹ መላ ምት ከሆነ ለአለርጂ ሕመም ሁለተኛው መንስኤ ከልክ በላይ ጤናንና ንጽሕናን ለመጠበቅ የሚደረገው ጥረት ነው። ‘የተወለድነው ጀርሞችን ለማጥፋት ብዙ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ በሚውሉበት የማዋለጃ ክፍል ውስጥ ነው። የምንመገበውም ምግብ ቢሆን ባክቴሪያዎችን ለማጥፋት ኬሚካል ይጨመርበታል። የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል ሲባል ብዙ ክትባቶችን እንወስዳለን። ካመመን ደግሞ ወዲያውኑ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን እንወስዳለን። በመሆኑም በሽታን የሚከላከሉት የሰውነታችን ሕዋሳት ከተወለድንበት ጊዜ አንስቶ ለብዙ ነገሮች አለርጂክ የመሆን ባሕርይ ያዳብራሉ’ በማለት ዶክተር ሱቢሳ ያስረዳሉ።

በአለርጂ የምትሰቃይ ከሆንክ ተስፋ አትቁረጥ! የሕመሙ ምልክቶች ምንነት ታውቆ ሕክምና ከተደረገ የዚህን ሕመም በተደጋጋሚ መከሰትና ያለውን ኃይል መቆጣጠር አሊያም መቀነስ ይቻላል።