በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የውኃ ኮዳዎች አያያዝ

በካናዳው የካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ አንድ ጥናት “ሳይታጠቡ ውኃ በሚያዝባቸው ኮዳዎች ውስጥ አስደንጋጭ ብዛት ያላቸው ባክቴሪያዎች” እንደሚገኙ አመልክቷል ሲል ቤተር ሆምስ ኤንድ ጋርደንስ የተሰኘው መጽሔት ዘግቧል። የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ከሚጠቀሙባቸው የውኃ ኮዳዎች ውስጥ ከ13 በመቶ በላይ የሚሆኑት የተገኘባቸው የባክቴሪያ ብዛት ለጤና አያሰጋም ከሚባለው መጠን ያለፈ እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል። የተገኘው ባክቴሪያ በዓይነ ምድር ውስጥ የሚገኙትን የሚጨምር ሲሆን ይህ ሊሆን የቻለው ተማሪዎቹ እጃቸውን በደንብ ስለማይታጠቡ ሳይሆን አይቀርም። አንዲት ተመራማሪ የውኃ ኮዳዎች እንደገና ውኃ ከመሞላታቸው በፊት በፈላ ውኃና በሣሙና ታጥበው እንዲደርቁ መደረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኒኮቲን ሱስ

ናሽናል ፖስት የተባለው የካናዳ ጋዜጣ “ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳበ ሲጋራ አንድን ወጣት ሱሰኛ ሊያደርግ ይችላል” ሲል ዘግቧል። “የጥናቱ ውጤት አንድ ሰው የኒኮቲን ሱሰኛ የሚሆነው ለተወሰኑ ዓመታት ካጨሰ በኋላ ነው የሚለውን እስካሁን ተቀባይነት አግኝቶ የቆየ አመለካከት ውድቅ የሚያደርግ ነው።” በ1,200 ወጣቶች ላይ በተደረገ የስድስት ዓመት ጥናት ተመራማሪዎች “አልፎ አልፎ የሚያጨሱ ወጣቶች እንኳን ከእኩዮች ተጽዕኖ የበለጠ ግፊት የሚያሳድርባቸው ነገር ያደረባቸው ሱስ” እንደሆነ ደርሰውበታል ሲል ጋዜጣው ገልጿል። በጥናቱ መሠረት “የኒኮቲን ሱስ ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጋራ ከተጨሰበት ወቅት አንስቶ በየቀኑ ማጨስ እስከተጀመረበት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።” ተመራማሪዎቹ ፀረ ማጨስ ዘመቻዎች ወጣቶች እንዲያጨሱ የሚደረግባቸውን ተጽዕኖ እንዲቋቋሙ ብቻ ሳይሆን ማጨስ የጀመሩትም ሱሱን እንዲያሸንፉ ለመርዳት በሚያስችል መንገድ መቃኘት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

የመኪና አደጋ ሰለባዎች

በየዓመቱ በአሰቃቂ ወንጀሎች ከሚገደሉት ሰዎች ይልቅ በመኪና አደጋ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በሺህ የሚቆጠር ብልጫ ያሳያል” በማለት ኤል ፔይስ የተሰኘው የስፔይን ጋዜጣ ዘግቧል። በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በጎዳና ላይ የመኪና አደጋ ከሚደርስባቸው ውስጥ 55,000 የሚሆኑት የሚሞቱ ሲሆን 3.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ይደርስባቸዋል። በስፔይን በጎዳና ላይ በሚደርሱት የመኪና አደጋዎች ለሕልፈተ ሕይወት ከሚዳረጉት ሰዎች መካከል 35 በመቶ የሚሆኑት ከ15 እስከ 29 ዓመት ዕድሜ ያላቸው በመሆኑ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች ዋናው የሞት መንስኤ የመኪና አደጋ ሆኗል። በመንገድ ላይ የሚደርሰውን የመኪና አደጋ ለመቀነስ የተቋቋመው ላ ሊግ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ቃል አቀባይ የሆኑት ዣን ፒካርድ ማሆ የተባሉ ሴት “የመኪና አደጋ ከሁሉ የከፋ የሕዝብ ጤና ጠንቅ ሆኗል። ካላመናችሁኝ በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ ምን ያህል የመኪና አደጋ ሰለባዎችን እንደሚቀበሉ የድንገተኛ ክፍል ሐኪሞችን ጠይቁ” ሲሉ ተናግረዋል። ላ ሊግና በአውሮፓ የተቋቋሙ ሌሎች ሁለት ቡድኖች በመንገድ ላይ የሚደርሰውን የመኪና አደጋ ለመቀነስ በማሰብ መኪና አምራች ፋብሪካዎች ፍጥነትን የሚገድቡ መሣሪያዎችን እንዲሁም ተሽከርካሪዎችን ለአደጋ የዳረገውን ምክንያት የሚጠቁም ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ (ጥቁር ሣጥን) በመኪኖች ላይ እንዲገጥሙ ጥያቄ አቅርበዋል።

ስለላ በተንቀሳቃሽ ስልክ

በውስጣቸው የተገጠመ ካሜራ ያላቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮች በምስጢር መያዝ ያለባቸውን የንግድ ጉዳዮች አደጋ ላይ እየጣሉ መሆኑን ፍራንክፈርተር አልጌማይነ ጻይቱንግ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። ካሜራዎቹ በአንድ ወቅት ሽያጭን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚያስችሉ ዕቃዎች ተደርገው ይታዩ የነበረ ቢሆንም በዘመናዊዎቹ ተንቀሳቃሽ ስልኮች አማካኝነት የሚነሱት ዲጂታል ፎቶዎች ዝርዝር ጉዳዮችን የመያዝ አቅማቸው በእጅጉ ስለተሻሻለ በብዙ ኩባንያዎች የደኅንነት ባለ ሥልጣናት ዘንድ እንደ ችግር እየታዩ ነው። የስልክ ካሜራዎቹ በቀላሉ የማይታዩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ከቀድሞዎቹ ካሜራዎች በተለየ መልኩ ምስሉን ወዲያውኑ ማስተላለፍ መቻላቸው ለኢንዱስትሪ ስለላ የተመቹ መሣሪያዎች ያደርጋቸዋል። ሰላዩ ቢደረስበት እንኳን ምስሉ አስቀድሞ ለሌላ ወገን ተላልፎ ሊሆን ስለሚችል ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። በዚህም ምክንያት በበርካታ ኩባንያዎች ውስጥ የዲዛይን ክፍሎችንና አዳዲስ ሞዴሎች የሚፈተሹባቸውን ቦታዎች ጨምሮ የጥበቃ ሥራ በተጠናከረባቸው አካባቢዎች በውስጣቸው የተገጠመ ካሜራ ያላቸውን ስልኮች መጠቀም በጥብቅ የተከለከለ ነው።

ከመጠን በላይ ለንጽሕና መጨነቅ ጉዳት ሊኖረው ይችላል?

ብዙ ሰዎች የዕለት ተግባራቸውን ከጨረሱ በኋላ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ገላቸውን ሞቅ ባለ ውኃ መታጠብ ያስደስታቸዋል። ይሁን እንጂ “ከመጠን በላይ ሰውነትን አጥርቶ መታጠብ ብዙ ዓይነት የቆዳ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል” ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ የተባለው የአውስትራሊያ ጋዜጣ አስጠንቅቋል። “ብዙ ሰዎች ከሚገባ በላይ ቶሎ ቶሎና ለረዥም ጊዜ ጥሩ ባልሆኑ ሣሙናዎች ይታጠባሉ።” ዶክተር ሜገን አንድሩስ የተባሉት የቆዳ ሐኪም “ሁላችንም እጅግ በጣም ንጹሕ እንደሆን እንዲሰማን እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ በቆዳችን ላይ ጉዳት እያደረስን ሊሆን ይችላል። . . . ሰዎች ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ሲሉ በራሳቸው ላይ ጉዳት ያደርሳሉ።” ለምን? ከልክ ያለፈ ገላን የመታጠብ ልማድ በቆዳ ላይ የሚገኘውን “የተፈጥሮ ዘይት ሊያጠፋ፣ የጀርም ተከላካይ ሽፋኖችን ሊያስወግድና በቆዳችን ላይ ትናንሽ ጠባሳና ስንጥቅ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።” አንድሩስ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ለአጭር ጊዜ መታጠብ እንደሚበቃ ይመክራሉ።

አደገኛ ምክር

“እስከ 1970ዎቹ ዓመታት ድረስ በባንግላዴሽና በምዕራብ ቤንጋል [ሕንድ] የሚገኙ አብዛኞቹ መንደርተኞች ውኃ የሚቀዱት በእጅ ከሚቆፈሩ ጥልቅ ያልሆኑ ጉድጓዶች ወይም ከወንዞች አሊያም ከኩሬዎች ስለነበረ ብዙ ጊዜ በኮሌራ፣ በአንጀት ተስቦና በሌሎች ውኃ ወለድ በሽታዎች ይሰቃዩ ነበር” በማለት ዘ ጋርዲያን ዊክሊ የተባለው ጋዜጣ ይገልጻል። “በኋላ ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥልቅ ጉድጓዶችን እንዲቆፍሩና በምድር ውስጥ ከሚገኙ ውኃ ያዘሉ ዓለቶች በሽታ የማያመጣ ንጹሕ ውኃ በቧንቧ እንዲያወጡ መምከር ጀመረ።” በባንግላዴሽ፣ በቬትናም፣ በላኦስ፣ በበርማ (አሁን ማያንማር)፣ በታይላንድ፣ በኔፓል፣ በቻይና፣ በፓኪስታን፣ በካምቦዲያና ሕንድ ውስጥ በምትገኘው በምዕራብ ቤንጋል እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ጥልቅ ጉድጓዶች ተቆፈሩ። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ጥልቅ ጉድጓዶች ከሥራቸው አርሴኒክ አዘል ዝቃጮች ነበሯቸው። በዚህ ሳቢያ ብዙ ሰዎች በአርሴኒክ በመመረዛቸው የዓለም ጤና ድርጅት “በታሪክ ዘመናት ይህን ያህል ብዛት ያለው ሕዝብ የተመረዘበት ወቅት ታይቶ አያውቅም” ሲል ሁኔታውን ገልጾታል። ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት 150 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ይህን የተበከለ ውኃ ሲጠጡ ቆይተዋል። በባንግላዴሽ ብቻ 15,000 ሰዎች በከባድ ሁኔታ በአርሴኒክ ተመርዘዋል። በአካባቢው የሚገኙ ድርጅቶች፣ መንግሥታትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማራጭ ለማግኘት ብርቱ ጥረት ቢያደርጉም እስከአሁን ሁኔታውን ለማስወገድ የሚያስችል ዘዴ አልተገኘም።

የልጆች ራስን የመግደል ዛቻ

ሚሌኞ የተባለው የሜክሲኮ ሲቲ ጋዜጣ “ራስን የመግደል ሙከራ ከሚያደርጉ ወይም ራሳቸውን ከሚገድሉ ልጆች መካከል ሰማንያ በመቶ የሚሆኑት ይህን ሐሳባቸውን ከቀናት ወይም ከወራት በፊት በቃል ወይም በጽሑፍ ያስታውቃሉ” ሲል ዘግቧል። ትናንሽ ልጆች መኖር እንዲያስጠላቸው ከሚያደርጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል በደል (አካላዊ ወይም ስሜታዊ)፣ በፆታ መነወር፣ የቤተሰብ መፈራረስና ከትምህርት ቤት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ይገኙበታል። በሜክሲኮ ማህበራዊ ደኅንነት የሥነ አእምሮ ስፔሽያሊስት የሆኑ ሆሴ ሉዊስ ቫስኬዝ እንደሚሉት ሞት በቴሌቪዥንና በፊልሞች፣ በቪዲዮ ጨዋታዎችና በመጻሕፍት በጣም የተለመደና ተዘውትሮ የሚታይ ነገር በመሆኑ ልጆች ስለ ሕይወት ዋጋማነት የተሳሳተ አስተሳሰብ ሊያድርባቸው ችሏል። በማከልም ከስምንት እስከ አሥር ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ከሚገኙ 100 ልጆች መካከል 15 የሚሆኑት ራሳቸውን የመግደል ሐሳብ ሲኖራቸው ከእነዚህ መካከል 5 በመቶ የሚሆኑት ራሳቸውን እስከማጥፋት ይደርሳሉ ብለዋል። ጋዜጣው ልጆች ራሳቸውን ስለመግደል ሲናገሩ ለማስፈራራት ወይም ትኩረት ለመሳብ ሲሉ ነው ብሎ ነገሩን ችላ ከማለት ትኩረት ሰጥቶ መከታተል እንደሚገባ ይመክራል። በተጨማሪም “ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አብሮ መሆንና መጫወት፣ ሐሳብ ለሐሳብ መለዋወጥ እንዲሁም ሁልጊዜ ፍቅር ማሳየት ይኖርባቸዋል” ይላል።

ንዴት ይጎዳሃል

በጣሊያን የፓዱዋ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና መምህርት የሆኑት ቫሌንቲና ዱርሶ እንደሚሉት “ንዴት በኅብረተሰባችን ውስጥ በጣም እየተስፋፋ የመጣ ክስተት ይሁን እንጂ በሰውነታችን ላይ ጉዳት ያስከትላል።” ጡንቻዎች ይኮማተራሉ፣ የልብ ምት ይጨምራል፣ ትንፋሽ ቁርጥ ቁርጥ ይላል እንዲሁም መላው ሰውነት ከባድ ውጥረት ውስጥ ይገባል። በተጨማሪም ንዴት የአንድን ሰው የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ ያዛባል፣ እንዲሁም የሚያደርጋቸውን ነገሮች እንዳይቆጣጠር ተጽዕኖ ያሳድርበታል። “ሊያናድዱ ለሚችሉ ሁኔታዎች ራሳችንን አስቀድመን የማዘጋጀት ልማድ ይኑረን። . . . በረጋ መንፈስ ፊት ለፊት ‘በዚህ ነገር አልስማማም’ ማለት ብንችል የተሻለ ኑሮ እንኖራለን” በማለት ዱርሶ ይመክራሉ።

በውጥረት ውስጥ የሚገኙ ዶክተሮች

የካናዳ ሕክምና ማኅበር በቅርቡ በአገሪቱ 2,251 ዶክተሮች ላይ ጥናት ካደረገ በኋላ “45.7 በመቶ የሚሆኑት መንፈሳቸው እንዲዝል፣ እንዲሰላቹና ሥራቸውን በአግባቡ ለመወጣት ብቃት እንደሚጎድላቸው እንዲሰማቸው የሚያደርግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ድካም እንደሚታይባቸው መረጋገጡን” ቫንኩቨር ሰን የተባለው ጋዜጣ ገልጿል። የብሪቲሽ ኮሎምቢያ የሐኪሞች መርጃ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ፖል ፋርናን እንደሚሉት ለብዙ ዶክተሮች ውጥረት ምክንያት የሆነው እረፍት ለመውሰድ በሚፈልጉበት ጊዜ የሚተካቸው ሰው ለማግኘት አለመቻላቸው፣ ሁልጊዜ ለሚደረግላቸው ጥሪ ዝግጁ ሆነው እንዲጠባበቁ መደረጉና በጣም ብዙ የሆነ የወረቀት ሥራ እንዲሠሩ መገደዳቸው እንደሆነ ገልጸዋል። ዶክተር ፋርናን ውጥረት ያለባቸው ዶክተሮች ከቤተሰባቸው ጋር ጊዜ በማሳለፍ እንዲሁም ስሜታዊና መንፈሳዊ እርካታ በሚያስገኝ እንቅስቃሴ በመሳተፍ አኗኗራቸውን ሚዛናዊ እንዲያደርጉ መክረዋል።