በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንግግር የማቅረብ ችሎታ ማዳበር የምችለው እንዴት ነው?

ንግግር የማቅረብ ችሎታ ማዳበር የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ንግግር የማቅረብ ችሎታ ማዳበር የምችለው እንዴት ነው?

“አድማጮች የምሠራቸውን ስህተቶች አንድ በአንድ የሚያዩብኝና መፍራቴን የሚያውቁብኝ መሰለኝ። ሐሳቤን ሰብስቤ መናገር አቃተኝ። በሆዳቸው የሚስቁብኝ ሆኖ ተሰማኝ።”—ሳንዲ *

የትምህርት ቤቱ አዳራሽ ጢም ብሎ ሞልቷል። ንግግር እንድትሰጥ ወደ መድረኩ ስትጋበዝ ወዲያው የሁሉም ትኩረት በአንተ ላይ ያርፋል። ጥቂት ተራምደህ የምትደርስበት አትራኖስ በጣም ሩቅ መስሎ ታየህ። ውስጥ እጅህን ያልብህና እግርህ ይብረከረክ ጀመር፤ እንዲሁም ምክንያቱ ባይታወቅም አፍህ ደረቀ። ከዚያም ለመጥረግ ፋታ እንኳ ሳታገኝ ላብህ በጉንጭህ ላይ ኩልል ብሎ ወረደ። እንዴት ያሳፍራል! መሣሪያ የደገነብህ ሰው እንደሌለ ታውቃለህ፤ ሆኖም ከውስጥ የሚሰማህ ስሜት ከዚህ የተለየ አይደለም።

ግልጹን ለመናገር፣ አብዛኞቻችን በሰዎች ፊት ቆመን ንግግር ማቅረብ በጣም ያስፈራናል። (ኤርምያስ 1:5, 6) እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች ከሞት ይልቅ ሕዝብ ፊት ቆሞ ንግግር ማቅረብ እንደሚያስፈራቸው ይናገራሉ! አንተ በግል የሚሰማህ ስሜት ምንም ይሁን ምን ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንድትሰጥ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ቀጥሎ አንዳንዶቹን ምክንያቶች የምናይ ከመሆኑም ሌላ እንዴት የተዋጣልህ ተናጋሪ መሆን እንደምትችል እንመለከታለን።

ንግግር እንድታቀርብ ስትጋበዝ

ጥሩ ተናጋሪ ለመሆን የሚሰጥ ሥልጠናን በተመለከተ የወጣ አንድ ማስታወቂያ “በሰዎች ፊት ንግግር ማቅረብ ሁሉም ሰው ሊያዳብረው የሚገባ ችሎታ ነው” ይላል። አዎን፣ ይዋል ይደር እንጂ አንድ ቀን ሰዎች በተሰበሰቡበት ንግግር ማቅረብህ አይቀርም። አንደኛ ነገር በበርካታ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች በሌሎች ፊት ንግግር እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ። ታቲያና የተባለች አንዲት ወጣት “የክፍል ጓደኞቼ ፊት ወጥቼ ንግግር እንዳቀርብ የተጠየቅሁባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ” በማለት ታስታውሳለች። ተማሪዎች ንግግር ለመስጠት ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያስገድዱ በርካታ አጋጣሚዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የቃል ሪፖርት ማቅረብ፣ በአንድ መጽሐፍ ላይ አስተያየት መስጠት፣ በሚዲያ የተለያዩ ዝግጅቶችን ማቅረብ እንዲሁም በክርክር መሳተፍ አንዳንዶቹ ናቸው።

ትምህርት ጨርሰህ ወደ ሥራው ዓለም ከገባህ በኋላ ደግሞ ለሥራ ባልደረቦችህ ሥልጠና እንድትሰጥ፣ ለደንበኞች ገለጻ እንድታደርግ ወይም ለሥራ አመራር ቦርድ የሒሳብ ሪፖርት እንድታቀርብ ልትጠየቅ ትችላለህ። እንዲያውም ንግግር የማቅረብ ችሎታ ጋዜጠኝነትን፣ የአስተዳደር ሥራን፣ የሕዝብ ግንኙነትንና ሽያጭን ጨምሮ ለበርካታ ሥራዎች በጣም ጠቃሚ ነው።

ይሁን እንጂ የሥራ ምርጫህ የጉልበት ሥራ ወይም ጸሐፊነት ቢሆንስ? በዚህ ጊዜም ቢሆን ለቃል ፈተና በምትቀርብበት ጊዜ ጥሩ አድርገህ ሐሳብን መግለጽ መቻልህ ሥራ ማግኘት አለማግኘትህን ይወስናል። ሥራ ከያዝክ በኋላም ቢሆን ጥሩ አድርገህ ሐሳብህን መግለጽ መቻልህ ይጠቅምሃል። ካሪን ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ለሦስት ዓመታት ያህል በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ አስተናጋጅ ሆና ሠርታለች። “ጥሩ የመናገር ችሎታ ካላችሁ ሰዎች በአእምሮ የበሰላችሁና ተጨማሪ ኃላፊነት የመሸከም አቅም ያላችሁ አድርገው ይመለከቷችኋል። ከዚህም በላይ የተሻለ ሥራ፣ የደመወዝ ጭማሪ ወይም ቢያንስ ቢያንስ ከበፊቱ የበለጠ አክብሮት እንድታገኙ ያስችላችኋል” ብላለች።

በሌላ በኩል ደግሞ ወጣት ክርስቲያኖች ከአምልኮታቸው ጋር በተያያዘ በሌሎች ፊት ቀርበው የመናገር ብዙ አጋጣሚ አላቸው። (ዕብራውያን 10:23) ታኒሸ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበክ መብት ያለን በመሆኑ አንድ ሰው ሐሳቡን በሚገባ መግለጽ መቻሉ በጣም አስፈላጊ ነው” ትላለች። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በጉባኤም ሆነ በአገልግሎት ላይ ወጣት ክርስቲያኖች ‘ያዩትንና የሰሙትን ከመናገር ወደ ኋላ’ አይሉም።—የሐዋርያት ሥራ 4:20፤ ዕብራውያን 13:15

በመሆኑም ጥሩ የንግግር ችሎታ ማዳበር በርካታ ጥቅሞች አሉት። ይሁንና አድማጮች ፊት ቆሞ መናገር የሚለው ሐሳብ ራሱ ሊያስጨንቅህ ይችላል። ፍርሃትህን ለማሸነፍ ማድረግ የምትችለው ነገር ይኖራል? አዎን፣ አለ።

የሚሰማህን ፍርሃት ማሸነፍ

ከጭንቀት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑትና ንግግር የመስጠት ጥሩ ችሎታ ያላቸው ዶክተር ሞርተን ኦርመን እንዲህ ብለዋል:- “በዚህ ረገድ እንዲሳካልህ ልዩ ችሎታ ማዳበር ወይም ፍጹም ሰው መሆን አያስፈልግህም። በሰዎች ፊት ንግግር የምታቀርብበት ዋናው ዓላማ ለአድማጮች አንድ ቁምነገር ማካፈል ነው።” በሌላ አባባል በምታቀርበው መልእክት ላይ ትኩረት አድርግ እንጂ ስለ ራስህ ወይም በውስጥህ ስለሚሰማህ ጭንቀት አታስብ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሐዋርያው ጳውሎስ ንግግር የማቅረብ ችሎታው ደካማ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ሆኖም ምንጊዜም ቢሆን የሚናገረው ጠቃሚ ነገር ስለነበረው የተነሳበትን ዓላማ ዳር ማድረስ ችሏል። (2 ቆሮንቶስ 11:6) በተመሳሳይ ለአድማጮች የሚጠቅም አንድ ቁምነገር እንዳዘጋጀህ እርግጠኛ ከሆንክ የሚያድርብህ የፍርሃት ስሜት ወዲያውኑ ይቀንሳል።

ጥሩ የመናገር ችሎታ ያላቸውና በመስኩ አስተማሪ የሆኑት ራን ሳትሆፍ ደግሞ እንዲህ ይላሉ:- የምታቀርበውን ንግግር እንደ ሥራ አድርገህ አትቁጠረው። ንግግር ስታቀርብ ከአንድ ሰው ጋር እንደምታወራ አድርገህ ለማሰብ ሞክር። ከአንድ ሰው ጋር ስትነጋገር ከምታደርገው ባልተለየ ከአድማጮችህ ጋር በጥቅሉ ሳይሆን ከአንድ ግለሰብ ጋር የምትነጋገር ያህል ግንኙነት ለመፍጠር ሞክር። ለአድማጮችህ በግለሰብ ደረጃ ልባዊ አሳቢነት አሳይ እንዲሁም ወትሮ በምትናገርበት መንገድ ሐሳብህን ግለጽ። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4) ንግግርህን ከአንድ ሰው ጋር እንደምትነጋገር አድርገህ ባቀረብከው መጠን ይበልጥ ዘና ማለት ትችላለህ።

ሌላው ለጭንቀት መንስኤ የሚሆነው ጉዳይ፣ ያልሆነ ነገር ብናገር ወይም ባደርግ ምን ይውጠኛል አሊያም አድማጮች ይተቹኛል የሚለው ስሜት ነው። ሌኒ ላስኮውስኪ የተባሉት ጥሩ ችሎታ ያላቸው ተናጋሪና የንግግር ችሎታ አስተማሪ አድማጮች እያንዳንዱን ንግግር የሚከታተሉት ቀና አመለካከት ይዘው እንደሆነ ተናግረዋል። “አድማጮችህ እንዲሳካልህ እንጂ እንዲበላሽብህ አይፈልጉም” ብለዋል። በመሆኑም አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። የሚቻል ከሆነ ንግግሩን ለማዳመጥ የሚመጡትን አንዳንድ ሰዎች አስቀድመህ ሰላም ለማለት ጥረት አድርግ። እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወዳጅ ተመልከታቸው።

በተጨማሪም የፍርሃት ስሜት ሙሉ በሙሉ መጥፎ ነው ማለት እንደማይቻል አስታውስ። አንድ ባለሙያ “ብዙዎች አይመስላቸውም እንጂ የፍርሃት ስሜት ለአንተም ሆነ ለምታቀርበው ንግግር ጥሩ ነው” ብለዋል። እንዴት? ምክንያቱም መጠነኛ የፍርሃት ስሜት አቅምህን እንደምታውቅ የሚያሳይ በመሆኑና ከልክ በላይ በራስህ እንዳትታመን ሊያደርግህ ስለሚችል ነው። (ምሳሌ 11:2) ብዙ ስፖርተኞች፣ ሙዚቀኞችና የፊልም ተዋናዮች ፍርሃት ሲሰማቸው የሚኖራቸው ንቃት የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። በሰዎች ፊት ንግግር ማቅረብን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች

አንዳንድ ወጣት ክርስቲያኖች እነዚህንና ሌሎች ሐሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ በተወሰነ መጠን ልምድ ያገኙ ከመሆኑም ሌላ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታቸውና በጉባኤ ጥሩ ንግግር ማቅረብ ችለዋል። ከሰጡት ሐሳብ መካከል የሚጠቅምህን ነጥብ ለማግኘት ሞክር።

ጄድ:- “ንግግሩን በራስህ አባባል ለመግለጽ ሞክር። የምታቀርበው ትምህርት ጠቃሚ እንደሆነ ራስህን አሳምን። አስፈላጊ መልእክት እንደያዝክ ካመንክ አድማጮችህም ተመሳሳይ ስሜት ያድርባቸዋል።”

ሮሼል:- “ንግግሩን ስለማመድ በቪዲዮ መቀረጹን ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ጉድለቶችህን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይህ ቢሆንም እንኳ ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም የምትወደውን ርዕስ ምረጥ። እንዲህ ካደረግህ በአቀራረብህ ላይ በግልጽ ይታያል።”

ማርግሬት:- “እያንዳንዱን ነገር ጽፌ ከምናገር ይልቅ አስተዋጽኦ ይዤ ንግግር ሳቀርብ ዘና ብዬ የምናገር ከመሆኑም ሌላ በውይይት መልክ ለማቅረብ ያስችለኛል። ከዚህ በተጨማሪ መናገር ከመጀመሬ በፊት አየር በደንብ መሳብ እንድረጋጋ ይረዳኛል።”

ከሪን:- “ስህተት ስትሠራ በራስህ ላይ ሳቅ። ደግሞም ሁሉም ሰው ይሳሳታል። አቅምህ ከሚፈቅደው በላይ እንድታደርግ አይጠበቅብህም።”

ስፖርት፣ ቲያትር ወይም ሙዚቃን ጨምሮ በማንኛውም መስክ ልምድ ማዳበርንና ደጋግሞ መለማመድን የሚተካ ነገር እንደሌለ የታወቀ ነው። ታቲያና ልምምድ ማድረግ የምትችልበት በቂ ጊዜ እንድታገኝ ንግግሩን አስቀድሞ አዘጋጅቶ ማጠናቀቅ ጠቃሚ መሆኑን ትናገራለች። እንዲሁም በቀላሉ ተስፋ አትቁረጥ። “በሌሎች ፊት በተደጋጋሚ ንግግር ባቀረብኩ ቁጥር የዚያኑ ያህል ንግግር ማቅረብ እየቀለለኝ መጣ” ብላለች። ይሁንና ልትዘነጋው የማይገባ አንድ ተጨማሪ የእርዳታ ምንጭ አለ፤ በተለይ ደግሞ እውነተኛውን አምልኮ ደግፎ የመናገር አጋጣሚ ስታገኝ በዚህ እርዳታ መታመንህ አስፈላጊ ነው።

የላቀ የማስተማር ችሎታ ካለው ፈጣሪ እርዳታ ማግኘት

ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ከመሆኑ በፊት ገና ወጣት እያለ “በአነጋገሩ አስተዋይ” ነው የሚል መልካም ስም አትርፎ ነበር። (1 ሳሙኤል 16:18) ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? መስክ ላይ በጎች እየጠበቀ ረጅም ሰዓት ያሳልፍ ነበር። በዚህ ጊዜ ዳዊት የላቀ የማስተማር ችሎታ ካለው ከይሖዋ አምላክ ጋር በጸሎት የጠበቀ ዝምድና መመሥረት ችሎ እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። (መዝሙር 65:2) ይህም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንኳ ሳይቀር ሐሳቡን በግልጽ፣ በእርግጠኝነትና አሳማኝ በሆነ መንገድ የመግለጽ ችሎታ እንዲያዳብር አስችሎታል።—1 ሳሙኤል 17:34-37, 45-47

አምልኮህን ለማከናወን በምታደርገው ጥረት አምላክ ዳዊትን እንደረዳው ሁሉ አንተም አሳማኝ በሆነ መንገድ የመናገር ችሎታ እንዲኖርህ “የተባ አንደበት” ሊሰጥህ እንደሚችል እርግጠኛ ሁን። (ኢሳይያስ 50:4፤ ማቴዎስ 10:18-20) አዎን፣ ንግግር የመስጠት ችሎታህን እንድታሻሽል የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች በተጠቀምክባቸው መጠን ሰዎች በተሰበሰቡበት ጥሩ አድርጐ የመናገር ችሎታ ታዳብራለህ!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጥሩ ተናጋሪ ለመሆን የሚያስችል ሥልጠና

በምድር ዙሪያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በሚባል ፕሮግራም አማካኝነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት የሚቀርብበት ሳምንታዊ ስብሰባ አለ። ተማሪዎች በውይይት በሚቀርቡ ክፍሎች ይሳተፋሉ፣ በጉባኤ ፊት ንግግር ያቀርባሉ እንዲሁም እድገት እንዲያደርጉ የሚረዳ ምክር በግል ይሰጣቸዋል። ይህ ፕሮግራም ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል? የ19 ዓመቱ ክሪስ የራሱን ተሞክሮ ሲነግራችሁ አድምጡ።

እንዲህ ይላል:- “በትምህርት ቤቱ መሳተፍ ከመጀመሬ በፊት ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ስሆን በጣም ይጨንቀኝ ነበር። አንድ ቀን ንግግር ለማቅረብ መድረክ ላይ እወጣለሁ የሚል ሐሳብ ፈጽሞ አልነበረኝም። ሆኖም በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ንግግሬን እየተንተባተብኩ ባቀርብም እንኳ የተሰጠኝን ክፍል ለማቅረብ የማደርገውን ጥረት ስለሚገነዘቡ በንግግሩ በጣም እንደተደሰቱ በመግለጽ ያበረታቱኝ ነበር። ከዚያም ንግግር ባቀረብኩ ቁጥር ያመሰግኑኛል። ይህ በጣም ረድቶኛል።”

ክሪስ በትምህርት ቤቱ ለአምስት ዓመታት ሲሳተፍ ከቆየ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የ45 ደቂቃ ንግግር ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ይገኛል። አንተስ ከዚህ ዝግጅት የተሟላ ጥቅም እያገኘህ ነው?

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሐሳብህን በሚገባ የመግለጽ ችሎታ ማዳበርህ በማንኛውም የሕይወት መስክ ይጠቅምሃል