በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማኅበራዊ እሴቶች እያሽቆለቆሉ ነውን?

ማኅበራዊ እሴቶች እያሽቆለቆሉ ነውን?

ማኅበራዊ እሴቶች እያሽቆለቆሉ ነውን?

ወላጆች ለልጆቻቸው ሊሰጡ ከሚገባቸው ታላላቅ ስጦታዎች መካከል ገደብ የሌለው ፍቅርና ወላጆች በቃል ብቻ የሚናገሯቸው ሳይሆኑ ራሳቸው የሚያከብሯቸው ማኅበራዊ እሴቶች ይገኙበታል።

ትክክለኛ ማኅበራዊ እሴት ከሌለ ሕይወት አሰልቺ ውጣ ውረድ ከመሆን አያልፍም። ማኅበራዊ እሴቶች ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን ያደርጉልናል። ለየትኞቹ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን መመሪያ ይሰጡናል። የሥነ ምግባር ድንበሮችንና የጥሩ ባሕርይ ሕጎችን ይወስኑልናል።

ይሁን እንጂ የታወቁና ጸንተው የኖሩ ብዙ ማኅበራዊ እሴቶች በፍጥነት እየተለወጡ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ፕሮፌሰር ሮናልድ ኢንግልሃርት “ማኅበረሰባችን ግለሰቦች የፆታ ሥነ ምግባርን በተመለከተ በራሳቸው ፍላጎት እንዲሄዱና የፈቀዱትን እንዲያደርጉ የሚያበረታታ አመለካከትን በማስፋፋት ላይ ነው” ብለዋል። በ16 አገሮች የሕዝብ አስተያየት ያሰባሰበ በ1997 የተካሄደ አንድ ጥናት ከጋብቻ ውጭ ስለሚወለዱ ልጆች ምን ዓይነት አስተያየት እንዳላቸው ሰዎችን ጠይቆ ነበር። አጥኚዎቹ “90 በመቶ የሚሆኑ የምዕራብ አውሮፓ ነዋሪዎች፣ 15 በመቶ የሚደርሱ የሲንጋፖርና የሕንድ ነዋሪዎች ከጋብቻ ውጭ ልጅ መውለድ ተቀባይነት እንዳለው መናገራቸውን” ዘግበዋል።

እንዲያውም አንዳንዶች ይህን አዲስ የወሲብ ነጻነት አወድሰው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ዘ ራይዝ ኦቭ ገቨርንመንት ኤንድ ዘ ዲክላይን ኦቭ ሞራሊቲ የተባለውን ቡክሌት የጻፉት ጀምስ ኤ ዶርን “ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ልጆች ቁጥር መጨመሩ” እና “የቤተሰብ መፈራረስ የሥነ ምግባር ዝቅጠት መኖሩን የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው” ብለዋል።

ሌሎች እያሽቆለቆሉ የመጡ እሴቶች

ሌሎች ለብዙ ዘመናት ጸንተው የኖሩ ማኅበራዊ እሴቶችም እያሽቆለቆሉ መጥተዋል። በፕሮፌሰር ኢንግልሃርት የተመራው የዓለም እሴቶች ጥናት በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች “ለባለ ሥልጣናት አክብሮት ማሳየት እየቀረ መጥቷል” ብሏል።

ሌላው ለብዙ ዘመናት ጸንቶ የኖረው ማኅበራዊ እሴት ደግሞ የሥራ ክቡርነት ነው። ይህም ቢሆን እያሽቆለቆለ እንደመጣ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። ናሽናል ፌዴሬሽን ኦቭ ኢንዲፔንደንት ቢዝነስ የተባለው ድርጅት በዩናይትድ ስቴትስ ከግማሽ ሚልዮን በሚበልጡ አሠሪዎች ላይ ጥናት አካሂዶ ነበር። “ጥያቄ ከቀረበላቸው አሠሪዎች መካከል 31 በመቶ የሚሆኑት ለክፍት የሥራ ቦታዎች ብቁ ሠራተኛ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነባቸውና 21 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የሠራተኞች ጥራት በአጠቃላይ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።” አንድ አሠሪ “ከአንድ ቀን በላይ ሰዓት አክብረውና ሳይሰክሩ ሥራ የሚገቡ ሠራተኞች ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል” ብለዋል።

ይህን የመሰለ ማሽቆልቆል የኖረው ኢኮኖሚውን በተቆጣጠሩት ባለ ሃብቶች ምክንያት ሊሆን ይችላል። አሠሪዎች ያገኙ የነበረው ትርፍ ሲቀንስባቸው ሠራተኞችን ይቀንሳሉ ወይም አንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞችን ያስቀራሉ። ኤቲክስ ኤንድ ቢሄቭየር የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “በአሠሪዎቻቸው ቁርጠኝነትና አስተማማኝነት መታመን ያቃታቸው ሠራተኞች በተራቸው ለአሠሪዎቻቸው አሉታዊ ባሕርይ ማሳየት ይጀምራሉ። ሠራተኛው ነገ ከሥራ ሊወጣ እንደሚችል ስለሚያውቅ ሙሉ ጉልበቱን በሥራ ላይ የማዋል ፍላጎት አይኖረውም።”

ማኅበራዊ እሴቶች ያሽቆለቆሉበት ሌላም የኑሮ መስክ አለ። ጨዋነትና ግብረገብነት በእጅጉ አሽቆልቁሏል። በአውስትራሊያ የተካሄደ አንድ ጥናት “ከ87.7 በመቶ የሚበልጡ ሠራተኞች በመሥሪያ ቤታቸው የሚታየው የጨዋነትና የግብረገብነት መጥፋት የሠራተኞችን ሞራል እየነካ ነው እንዳሉ” አረጋግጧል። በዩናይትድ ስቴትስ በከፍተኛ የንግድ ድርጅቶች ባለሞያዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት “ጥያቄ ከቀረበላቸው መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በመሥሪያ ቤቶች ጨዋነትና አክብሮት እየጠፋ ሄዷል እንዳሉ” ዘግቧል። የሲ ኤን ኤን ዜና ወኪል እንደሚከተለው ብሏል:- “ደንበኞችን በአግባቡ አለማስተናገድ በጣም እየተስፋፋ በመምጣቱ ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት በዓመቱ ውስጥ በአግባቡ ባለመስተናገዳቸው ምክንያት ሱቁን ጥለው የወጡበት ጊዜ እንዳለ ተናግረዋል። ግማሽ ያህል የሚሆኑት ደግሞ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ከመጠን በላይ ጮክ ብለው ወይም ሌሎችን በሚያበሳጭ መንገድ የሚነጋገሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ እንዳጋጠሟቸው ተናግረዋል። ከአሥር አሽከርካሪዎች መካከል 6 የሚሆኑት ደግሞ በአደገኛ ሁኔታ ወይም በግድየለሽነት የሚያሽከረክሩ ሰዎችን አዘውትረው እንደሚመለከቱ ተናግረዋል።”

የሰው ሕይወት ምን ያህል ክቡር ነው?

አንዳንድ ሰዎች የተወሰኑ ‘ማኅበራዊ እሴቶችን’ እንደሚቀበሉ ይናገሩ እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የሚናገሩት ነገር ከድርጊታቸው ጋር አይጣጣምም። ለምሳሌ ያህል ግሎባል ኤቲክስ የተባለ አንድ ተቋም የ40 አገር ተወካዮችን አስተያየት አሰባስቦ ነበር። አርባ በመቶ የሚሆኑት ትልቅ ቦታ ከሚሰጧቸው አምስት ማኅበራዊ እሴቶች መካከል አንዱ “የሕይወት ክቡርነት” እንደሆነ ተናግረዋል። *

በተግባር ሲታይ ግን ሁኔታው ምን ይመስላል? በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮች በሰው ላይ የሚደርሱትን ብዙዎቹን ሥቃዮች ለማስወገድ የሚያስችል አቅም እንዳላቸው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ካሮል ቢላሚ በ1998 የጻፉት መጽሐፍ “በታዳጊ አገሮች አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ከሚሞቱት 12 ሚልዮን ሕፃናት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚሞቱት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሲሆን ይህ እልቂት በ14ኛው መቶ ዘመን አውሮፓን ካጨደው ጥቁር ሞት ተብሎ ከሚታወቀው ወረርሽኝ ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ነው” ይላል። እንዲህ ያለው ዘገባ ለሰው ሕይወት አክብሮት ላለው ማንኛውም ሰው በጣም አስደንጋጭ ነው። “ይሁን እንጂ” ይላሉ ቢላሚ “የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ዓለም አቀፋዊ ችግር እንደሆነ በበቂ ሳይንሳዊ መረጃ የተረጋገጠና እየከፋ ያለ ችግር መሆኑ ቢታወቅም ብዙ ሰዎችን የሚያስደነግጥ ሆኖ አልተገኘም። የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከሚያስከትለው መጠነ ሰፊ ጉዳት ወይም የተመጣጠነ ምግብ ከሚያስገኘው ጥቅም ይልቅ ብዙ ትኩረት የሚሰጠው በዓለም የአክሲዮን ገበያዎች ላይ ለሚታየው ውጣ ውረድ ነው።”

በሕክምናው መስክም ቢሆን ለሕይወት የተዛባ አመለካከት እንዳለ ይታያል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማለትም እስከ 1970ዎቹ ዓመታት ድረስ አንድ ጽንስ ጊዜው ሳይደርስ በ23 ሳምንቱ ቢወለድ በሕይወት የመኖር ዕድሉ በጣም የመነመነ ነበር። ዛሬ ግን እንዲህ ካሉት ሕፃናት መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በሕይወት መኖር ይችላሉ። ይህን ስንመለከት በመላው ዓለም በየዓመቱ ከ40 እስከ 60 ሚልዮን የሚደርሱ ውርጃዎች መፈጸማቸው እንዴት ያለ እንግዳ ክስተት ነው! ከእነዚህ ውርጃዎች መካከል አብዛኞቹ የሚፈጸሙት ዶክተሮች በሕይወት ለማቆየት ከሚደክሙላቸው ሕፃናት በዕድሜያቸው ብዙም የማያንሱ ናቸው። ታዲያ ይህ ሁኔታ ከባድ የሥነ ምግባር ግራ መጋባት መኖሩን አያመለክትም?

የሥነ ምግባር መመሪያ ያስፈልጋል

የሕዝብ አስተያየት አሰባሳቢዎች “በሕይወት ውስጥ ያን ያህል የማያሳስብህ ጉዳይ ምንድን ነው?” በማለት ላቀረቡት ጥያቄ ሁለት መልስ የተሰጠ ሲሆን ከሁለቱ መካከል በአስፈላጊነቱ የመጨረሻውን ደረጃ የያዘው “ሃይማኖትን አጥብቆ መያዝ” የሚለው ሆኗል። በእርግጥም ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መሄዱ የሚያስደንቅ አይደለም። ፕሮፌሰር ኢንግልሃርት በምዕራባውያን አገሮች የተገኘው ብልጽግና “ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ መጠን ሥጋት የሌለበት ኑሮ በማስገኘቱ ከሃይማኖት ይገኝ የነበረው የመረጋጋትና የመተማመን ስሜት አስፈላጊነት በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጓል” ብለዋል።

ሰዎች በታወቁ ሃይማኖቶች ላይ የነበራቸው እምነት እየተዳከመ በሄደ መጠን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የነበራቸውም እምነት በዚያው መጠን ቀንሷል። አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት ሰዎች በሥነ ምግባር ረገድ ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን መወሰን በሚያስፈልጋቸው ጊዜ መመሪያ የሚያገኙት ከምን ወይም ከማን እንደሆነ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። አብዛኞቹ ከግል ተሞክሯቸው እንደሆነ ተናግረዋል። “የአምላክ ቃል በከፍተኛ ርቀት በሁለተኛነት ይከተላል” በማለት የጥናቱ ውጤት ዘግቧል።

ማኅበራዊ እሴቶች ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆሉ መሄዳቸው አያስደንቅም። ቁሳዊ ግቦችን ማሳደድና ለራስ ብቻ የመኖር ዝንባሌ መስፋፋቱ ለሥነ ምግባር መመሪያ የሚሆን ነገር ካለመኖሩ ጋር ተዳምሮ ስግብግብነትና ለሌሎች ስሜት ደንታ ቢስ የመሆን ባሕል እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ለውጦች አስፈላጊ የሆኑ ምን ነገሮች እንዲጠፉ አድርገዋል?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ50 ዓመት በፊት የሰብዓዊ መብቶችን ድንጋጌ አጽድቋል። ይህ ድንጋጌ በአንቀጽ 1 ላይ “ሁሉም ሰዎች ነጻ ሆነው የተወለዱ ሲሆን በክብርና በመብት ረገድም እኩል ናቸው” ይላል።

[በገጽ 22 እና 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የቤተሰብ መፈራረስ፣ ጥሩ ያልሆነ የሥራ ሥነ ምግባርና ጨዋነት የጎደለው ጠባይ እያሽቆለቆሉ የመጡ የዘመናችን እሴቶች መለያ ባሕርይ ሆነዋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በየዓመቱ ከዚህ አለቀኑ ከተወለደ ሕፃን በጥቂት ሳምንት ብቻ የሚያንሱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት በውርጃ ይገደላሉ