በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማኅበራዊ እሴቶች እየተለወጡ የመጡት ለምንድን ነው?

ማኅበራዊ እሴቶች እየተለወጡ የመጡት ለምንድን ነው?

ማኅበራዊ እሴቶች እየተለወጡ የመጡት ለምንድን ነው?

“በሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ምንድን ነው?”

ይህ ጥያቄ በ60 አገሮች ለሚኖሩ 50, 000 ሰዎች ቀርቦ ነበር። የሕዝብ አስተያየት ሰብሳቢዎቹ ከሁሉም የዓለም ክፍሎች ማለት ይቻላል በብዛት የተገኘው መልስ “ደስተኛ ቤተሰብ መመሥረት” እና “ጥሩ ጤና” የሚለው እንደሆነ ዘግበዋል።

ላይ ላዩን ሲታይ የዓለም ሕዝቦች በሙሉ ተመሳሳይ የሆኑ ታላላቅ ማኅበራዊ እሴቶች ያሏቸው ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ እውነታው ያን ያህል ብሩሕ አይደለም። በቀደሙት ዘመናት የሰዎች እሴቶች በታወቁ ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ሕግጋት ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። ይሁን እንጂ ሁኔታዎች በፍጥነት እየተለዋወጡ መጥተዋል። ማሪሳ ፈራሪ ኦክዮኔሮ የተባሉት ተመራማሪ ስለ ኢጣሊያ ሲናገሩ “ወጣቶች ወላጆቻቸው ከነበሯቸው ባሕላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች በጣም እየራቁ መጥተዋል” ብለዋል። በመላው ዓለም ስለሚኖሩ ወጣቶችም ሆነ አረጋውያን ተመሳሳይ ነገር መናገር ይቻላል።

ወርልድ ቫልዩስ ሰርቨይ የተባለው የምርምር ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሮናልድ ኢንግልሃርት “በዓለም አመለካከት ላይ ሥር ነቀል ለውጥ እየተካሄደ መሆኑን የሚያመለክቱ ብዙ ማስረጃዎች አሉ” ብለዋል። ይህን ለውጥ ያመጣው ምንድን ነው? ኢንግልሃርት “እነዚህ ለውጦች የኢኮኖሚያዊና የቴክኖሎጂያዊ ለውጥ ነጸብራቅ ናቸው” ይላሉ።

ለምሳሌ ያህል በሕዝብ አስተያየት ጥናቱ መሠረት በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች በጣም ከሚያሳስቧቸው ነገሮች መካከል ሥራ ማግኘት “ከመጨረሻዎቹ ረድፎች” የሚመደብ ሆኗል። በታዳጊ አገሮች ግን ሥራ ማግኘት ከመጀመሪያዎቹ ረድፎች የሚመደብ ነው። አዎን፣ ሰዎች ድሆች በሚሆኑበት ጊዜ ከሁሉ በላይ ቅድሚያ የሚሰጡት ነገር የዕለት ጉርስ ማግኘት ይሆናል። አገሮች በኢኮኖሚ እያደጉ ሲሄዱ ግን ጤናን፣ ደስታ የሰፈነበት ቤተሰብንና ስሜትን አውጥቶ መግለጽን ለመሰሉ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት ይጀምራሉ።

የቴክኖሎጂ እድገት እየተስፋፋ ሲሄድ እነዚህ አዳዲስ ማኅበራዊ እሴቶች በታዳጊ አገሮች ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም። ዘ ፊውቸሪስት የተባለው መጽሔት “እምነቶቻችንና እሴቶቻችን የሚቀረጹት በምንመለከታቸውና በምንሰማቸው ነገሮች ነው” ብሏል። ስለሆነም መገናኛ ብዙኃን በምዕራባውያን እሴቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። “እነዚህ መገናኛ ብዙኃን መላውን ዓለም ማዳረስ ጀምረዋል” ይላል ዘ ፊውቸሪስት።

ታዲያ በአመለካከትና በባሕርይ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ እየተካሄደ ነው? እነዚህስ ለውጦች አንተንና ቤተሰብህን የሚነኩት እንዴት ነው?