በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላካዊ እሴቶችን የሚያስከብር መንግሥት

አምላካዊ እሴቶችን የሚያስከብር መንግሥት

 አምላካዊ እሴቶችን የሚያስከብር መንግሥት

ሁሉንም የምድር ቋንቋ ተናጋሪዎችና ዘሮች የሚያስተዳድር በምድር ላይ አንድ መንግሥት ብቻ ይኖራል ብትባል ምን ይሰማሃል? ጦርነትን፣ ጥላቻን፣ ወንጀልን፣ ድህነትን፣ የአየር ብክለትን፣ በሽታንና ሞትን አጥፍቶ በምትኩ በጣም ክቡር የሆኑ እሴቶችን የሚያስጠብቅ መንግሥት ይመጣል ብትባል ምን ትላለህ?

 ‘አይሆንም እንጂ ቢሆንማ በጣም ጥሩ ነበር’ ትል ይሆናል። የማይሆን ነገር አይደለም። እንዲያውም እንዲህ ያለው መንግሥት እንደሚመጣ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ያለ መንግሥት እንደሚቋቋም ቃል ገብቷል። ተከታዮቹንም ይህ መንግሥት እንዲመጣ እንዲጸልዩ አስተምሯል። “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 6:​9, 10

በመላው ዓለም የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ጸሎት ስለሚያውቁትና ስለ ጸሎቱም ቢያንስ መስማታቸው ስለማይቀር አንተም እነዚህን ቃላት አሳምረህ ታውቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ የእነዚህ ቃላት ትርጉም ምንድን ነው ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ይህ መንግሥት የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ከመሆኑ ጋር የተቆራኘ መሆኑን አስተውል። ታዲያ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? አምላክ ለምድር ያለው ፈቃድስ ምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት ይሖዋ አምላክ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን የሚያረጋግጥበት መሣሪያ ነው። በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የበላይነት የሚተዳደር ንጉሣዊ መስተዳድር ነው። አምላክ ለምድር ያለው ፈቃድም በመዝሙር 37:​10, 11 ላይ በግልጽ ተቀምጧል:- “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”

ስለዚህ የዚህ ዓለም የሥነ ምግባር እሴቶች እያሽቆለቆሉ በመሄዳቸው ተስፋ ቆርጠህ ከሆነ አይዞህ። በቅርቡ የዓለም ሁኔታዎችና የሥነ ምግባር እሴቶች ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚካሄድባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ገብቷል። የአምላክ መንግሥት በቅርቡ መላዋን ምድር በማስተዳደር የአምላክን የሥነ ምግባር እሴቶች እንደሚያስከብር የተሰጠው ተስፋ ጠንካራ መሠረት ያለው ነው።

የአምላክ መንግሥት በሚያመጣቸው ተስፋዎች ላይ መታመናችን ያለ ሥጋት እንድንኖር ያስችለናል። የዚህ መንግሥት አስተዳደር የሚያስከብራቸውን እሴቶች ተመልከት:- “የእግዚአብሔርን ሥራ፣ በምድር ያደረገውንም ተአምራት እንድታዩ ኑ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፤ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቈርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።” (መዝሙር 46:​8, 9) ሰላምና ደህንነት እንደሚሰፍን የሚያረጋግጥ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው!

መዝሙር 72:​12-14 ስለ አምላክ መንግሥት ንጉሥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚናገረው ትንቢት ላይ እንዲህ ይላል:- “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው በፊቱ ክቡር ነው።”

የመጽሐፍ ቅዱስ እሴቶች

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የሥነ ምግባር እሴቶች መካከል አንዳንዶቹን ተመልከት:- “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው።” (ማቴዎስ 5:​3) ሌላው ደግሞ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” ይላል።​—⁠ምሳሌ 3:​5, 6

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም ለመከተል ስለመረጥነው የሥነ ምግባር እሴት ተጠያቂዎች እንደምንሆን ያስተምራል። መክብብ 11:​9 እንዲህ ይላል:- “አንተ ጐበዝ፣ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፣ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፣ በልብህም መንገድ ዓይኖችህም በሚያዩት ሂድ፤ ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ እወቅ።” ስለምናደርጋቸው ነገሮች ተጠያቂዎች መሆናችን በምሳሌ 2:​21, 22 ላይ በቀጥታ ተገልጿል:- “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።”

ጽድቅ የሰፈነበት መንግሥት እንደሚመጣ የሚገልጽ ይህን የመሰለ የሚያበረታታ ተስፋ ካገኘን ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረታችን ምንኛ ጠቃሚ ነው! የአምላክ መንግሥት ተገዥዎች የመሆን ፍላጎት ካላቸው ጋር መተባበራችንና መወዳጀታችን የክብራማ መንግሥቱ አገዛዝ ከሚያስገኛቸው ፍሬዎችና መንግሥቱ ከሚያስፋፋቸው አስደናቂ እሴቶች ተካፋይ እንድንሆን ያዘጋጀናል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”​—⁠መዝሙር 37:​11