በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁኔታዎች የሚሻሻሉበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

ሁኔታዎች የሚሻሻሉበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

 ሁኔታዎች የሚሻሻሉበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

በአሁኑ ጊዜ የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ሌሎች ድርጅቶች የበሽታ ክትትልና ቁጥጥር ፕሮግራም በማካሄድ ላይ ናቸው። አዳዲስ የቁጥጥር ዘዴዎችን የሚያስፋፉና አዳዲስ መድኃኒቶችን ለማግኘት የሚደረጉ ምርምሮችን የሚያግዙ በርካታ ድርጅቶች አሉ። ይህ ሁሉ የሚደረገው እየጨመረ የሄደውን በነፍሳት የሚተላለፉ በሽታዎችን ችግር ለመቋቋም ነው። ግለሰቦችና ማኅበረሰቦችም ተጨማሪ እውቀት ለማግኘትና ራሳቸውን ለመጠበቅ ሊያደርጉ የሚችሉት ብዙ ነገር አለ። ሆኖም ለግለሰቦች ጥበቃ ማድረግና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽታዎችን መቆጣጠር የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

በበሽታዎች ላይ የሚደረግ ቁጥጥር የተሳካ ውጤት እንዲያስገኝ ከተፈለገ ዓለም አቀፋዊ ትብብርና መተማመን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ብዙ ሊቃውንት ይስማማሉ። የፑሊትሰር ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ጋዜጠኛ ሎሪ ጋረት ዘ ካሚንግ ፕሌግ ​—⁠ኒውሊ ኢመርጅንግ ዲዚዝስ ኢን ኤ ወርልድ አውት ኦቭ ባላንስ በተባለው መጽሐፋቸው “የሰዎችና የአገሮች መቀራረብ እየተፋጠነና እየተቀላጠፈ መሄዱ ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው አልፈው ጎረቤቶቻቸውን፣ ከተሞቻቸውን፣ አገራቸውንና ከዚያም አልፈው ንፍቀ ዓለማቸውን እንዲመለከቱ ያስገድዳቸዋል” ብለዋል። “ረቂቅ ተህዋሲያንና በሽታ ተሸካሚ ነፍሳት ሰዎች  ያቆሟቸውን ሰው ሠራሽ ድንበሮች አያከብሩም።” በአንድ አገር የተነሣ ወረርሽኝ አጎራባች አገሮችን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም ሥጋት ላይ ይጥላል።

አንዳንድ መንግሥታትና ሕዝቦች ከድንበራቸው ውጭ የሚመጣውን ጣልቃ ገብነት በሙሉ፣ የበሽታ መከላከያ ፕሮግራሞችን ሳይቀር በጥርጣሬ ዓይን ይመለከታሉ። በተጨማሪም ፖለቲካዊ ጠባብነትና የንግድ ስስት የተባበረ ዓለም አቀፋዊ ጥረት እንዳይደረግ እንቅፋት ይሆናል። በሰው ልጅና በበሽታ መካከል በሚደረገው ግብ ግብ ረቂቅ ተህዋሲያን አሸናፊዎች ይሆኑ ይሆን? አዎን የሚል አመለካከት ያላቸው ደራሲው ዩጂን ሊንደን “ጊዜው አልፎብናል” ይላሉ።

የተስፋ ጭላንጭል

ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ እድገቶች ከበሽታዎች ስርጭት ፍጥነት ጋር እኩል ሊሄዱ አልቻሉም። በተጨማሪም በነፍሳት የሚተላለፉ በሽታዎች ችግር በሰው ልጅ ጤንነት ላይ ከተጋረጡት በርካታ አደጋዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ተስፋ የምናደርግበት ምክንያት አለን። ሳይንቲስቶች በሕያዋን ፍጥረታት መካከል ያለውን የተወሳሰበ ቅንጅት ገና መረዳት መጀመራቸው ቢሆንም ምድር ራሷን የማደስና የመጠገን ችሎታ እንዳላት ያምናሉ። ፕላኔታችን የተፈጥሮ ሥርዓቶች ሚዛናቸው እንዲጠበቅ የሚያደርጉ አሠራሮች አሏት። በአንድ ወቅት ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች በደን ይሸፈናሉ። በዚህም ምክንያት በጥቃቅን ተህዋሲያን፣ በነፍሳትና በእንስሳት መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ በኋላ ሚዛኑን የጠበቀ ይሆናል።

ከዚህም በላይ ውስብስብ የሆነው የተፈጥሮ አሠራር ከመጀመሪያ የምድርን አሠራሮች ያቋቋመ አንድ ፈጣሪ እንዳለ ያረጋግጣል። ብዙ ሳይንቲስቶች ምድርን የፈጠረ አንድ ታላቅ ጥበበኛ መኖር እንዳለበት ያምናሉ። አዎን፣ በእርግጥ አስተዋይ የሆኑ ሰዎች የአምላክን መኖር መካድ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ሁሉን የሚችልና አፍቃሪ እንደሆነ ይገልጻል። ደስተኞች ሆነን እንድንኖር ይፈልጋል።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ሰው አውቆና ፈቅዶ በፈጸመው ኃጢአት ምክንያት የሰው ልጅ አለፍጽምናን፣ በሽታንና ሞትን እንደወረሰ ይገልጻል። ታዲያ ይህ ማለት ከዚህ መከራ መውጣት አንችልም ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም! አምላክ ምድርን የሰው ልጆች ከሌሎች ትናንሽና ትላልቅ ፍጥረታት ጋር ተስማምተው የሚኖሩባት ገነት የማድረግ ዓላማ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ግዙፍ አራዊትም ሆኑ ትናንሽ ነፍሳት ሰዎችን የማይጎዱበት ዓለም እንደሚመጣ ይተነብያል።​—⁠ኢሳይያስ 11:​6-9

እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለው ሁኔታ ተጠብቆ እንዲኖር የሰው ልጅ የሚያከናውነው ማኅበረሰባዊም ሆነ ሥነ ምሕዳራዊ ሥራ ይኖረዋል። ሰው ምድርን ‘እንዲጠብቅ’ አምላክ ኃላፊነት ሰጥቶታል። (ዘፍጥረት 2:​15) በሚመጣው ገነት የሰው ልጅ ፈጣሪው የሚሰጠውን መመሪያ በመከተል ይህን ተግባሩን ፍጹም በሆነ ሁኔታ ይወጣል። ስለዚህ “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም” የሚለው ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ይህን መጪ ዓለም በጉጉት መጠባበቅ እንችላለን።​—⁠ኢሳያያስ 33:​24