በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመናገር ነጻነትን የሚደግፍ ብይን ሰጠ

ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመናገር ነጻነትን የሚደግፍ ብይን ሰጠ

ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመናገር ነጻነትን የሚደግፍ ብይን ሰጠ

ወሳኝ የሆነው ቀን ሰኔ 17, 2002 ደረሰ። ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የጽሑፍ አስተያየቱን ይፋ አደረገ። ብይኑ ምን ነበር? ብዙ ጋዜጦች በየአምዶቻቸው ላይ ሙሉውን ታሪክ አስፍረዋል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ጉብኝት ላይ የተጣለውን እንቅፋት አስወገደ” ብሏል። የኦሃዮው ዘ ኮለምበስ ዲስፓች “ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፈቃድ አውጡ የሚለውን ድንጋጌ ውድቅ አደረገ” ብሏል። የክሌቭላንድ ኦሃዮው ዘ ፕሌይን ዲለር በአጭሩ “ድጋፍ ሰብሰቢዎች የማዘጋጃ ቤቱን ፈቃድ ማግኘት አያስፈልጋቸውም” ብሏል። ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ በርዕሰ አንቀጽ አምዱ ላይ “የመናገር ነጻነት ድል አደረገ” ብሏል።

የበታች ፍርድ ቤቶች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የወሰኑት ብይን የተገለበጠው 8 ለ1 በሆነ የድምፅ ብልጫ ነበር። የፍርድ ቤቱን ባለ 18 ገጽ ሐተታ ያዘጋጁት ዳኛ ጆን ፖል ስቲቨንስ ነበሩ። ውሳኔው በመጀመሪያው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ጥበቃ ያገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ሕዝባዊ አገልግሎት አረጋግጧል። ፍርድ ቤቱ በሰጠው አስተያየት ምሥክሮቹ ፈቃድ እንዲሰጣቸው የማያመለክቱት “የመስበክ ሥልጣን ያገኘነው ከቅዱሳን ጽሑፎች ነው” ስለሚሉ ነው። ከዚያም ፍርድ ቤቱ ምሥክሮቹ ካቀረቡት የጽሑፍ አቤቱታ በመጥቀስ “ለእኛ ከማንኛውም ማዘጋጃ ቤት የመስበክ ፈቃድ እንዲሰጠን መጠየቅ አምላክን እንደመሳደብ ያስቆጥርብናል” ብሏል።

የፍርድ ቤቱ ሐተታ “ይህ ፍርድ ቤት ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ከቤት ወደ ቤት በመዘዋወርና ትናንሽ ጽሑፎችን በማደል ሥራ ላይ የሚጣለውን ገደብ ሁሉ ውድቅ ሲያደርግ ቆይቷል። እነዚህ አንደኛውን ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የሚመለከቱ አቤቱታዎች በአብዛኛው የቀረቡት በይሖዋ ምሥክሮች ሲሆን ይህም የሆነው በአጋጣሚ ሳይሆን ሃይማኖታቸው ከቤት ወደ ቤት እንዲሄዱ ስለሚጠይቅባቸው ነው። በከሳሽ መርዶክና በተከሳሽ ፔንሲልቫኒያ ጉዳይ እንዳመለከትነው . . . (1943 ) የይሖዋ ምሥክሮች ‘የጳውሎስን አርዓያ በመከተል “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት እናስተምራለን” ይላሉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:⁠20) “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” የሚለውን ትእዛዝ የሚረዱት ቃል በቃል ነው። (ማርቆስ 16:​15) ይህንንም ማድረጋቸው የአምላክን ትእዛዝ መጠበቃቸው እንደሆነ ያምናሉ’” ብሏል።

የፍርድ ቤቱ ትችት አሁንም በመቀጠል የ1943ቱን መዝገብ ጠቅሷል። “ይህ ዓይነቱ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በመጀመሪያው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ በአብያተ ክርስቲያናት ከሚከናወነው አምልኮና ከመስበኪያ ሰገነት ከሚቀርብ ስብከት የማይተናነስ እውቅና ተሰጥቶታል። ሠፊ ተቀባይነት ካገኙት ባሕላዊ የሃይማኖት ተግባራት የማይተናነስ ጥበቃ የማግኘት መብት አለው።” ትችቱ በ1939 ቀርቦ የነበረ አንድ መዝገብ በመጥቀስ “ፈቃድ የመጠየቅ ግዴታ በመጣል በነጻነትና አላንዳች እንቅፋት ጽሑፎችን የማደል መብትን መጋፋት ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን መንፈግ ነው” ብሏል።

ከዚያም ፍርድ ቤቱ ትልቅ ግምት የሚሰጠው አስተያየት ሰንዝሯል። “የይሖዋ ምሥክሮች በመናገር ነጻነት ላይ ገደብ ለመጣል የተደረገውን ሙከራ በሙሉ የተቃወሙት የራሳቸውን መብት ብቻ ለማስከበር ብለው እንዳልሆነ ከጉዳዮቹ መረዳት ይቻላል።” “እንደመንደሩ ባሉት ድንጋጌዎች አፋቸው የሚዘጋባቸው ‘አናሳ ወገኖች’ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ አይደሉም” በማለት አብራርቷል።

የፍርድ ቤቱ ትችት በመቀጠል “አንድ ዜጋ ጎረቤቶቹን ለማነጋገር አስቀድሞ ከመንግሥት ፈቃድ ይጠይቅ ማለት በአንደኛው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የተረጋገጡትን መብቶች ብቻ ሳይሆን የአንድን ነጻ ማኅበረሰብ ጽንሰ ሐሳብ መዳፈር ነው። . . . ይህን የመሰለውን ጭውውት ለማድረግ ፈቃድ መጠየቅ ያስፈልጋል የሚል ሕግ ከብሔራዊ ቅርሳችንና ከሕገ መንግሥታዊ ባሕላችን ፈጽሞ የራቀ ነው” ይላል። በተጨማሪም “ይህ ዓይነቱ ፈቃድ መጠየቅን የሚደነግግ ሕግ ስለሚያስከትለው ጉዳት” ተናግሯል።

የወንጀል ሥጋት

ፈቃድ ማውጣት ቤት ሰብረው ከሚዘርፉና ከሌሎች ወንጀለኞች ይከላከላል ስለሚለው ሐሳብስ ምን ለማለት ይቻላል? ፍርድ ቤቱ የሚከተለውን ክርክር አቅርቧል:- “ይህ ዓይነቱ ስጋት ተገቢ ቢሆንም ወንጀልን ለመከላከል ተብለው የሚወጡ ሕጎች በአንደኛው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የተረጋገጡትን መብቶች መጋፋት እንደማይኖርባቸው ካሁን በፊት የቀረቡልን ጉዳዮች በግልጽ ያሳያሉ።”

የፍርድ ቤቱ ትችት አሁንም በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ፈቃድ ይዞ አለመገኘት ወንጀለኞችን ቤት ከማንኳኳትና በሕጉ ባልተካተቱ ጉዳዮች ላይ ከመነጋገር ያግዳል ማለት የማይመስል ነገር ነው። ለምሳሌ መንገድ እንዲያሳዩአቸው ወይም ስልክ እንዲያስደውሏቸው ሊጠይቁ . . . አለበለዚያም የውሸት ስም አስመዝግበው ከተጠያቂነት ሊያመልጡ ይችላሉ።”

ፍርድ ቤቱ ወደኋላ መለስ ብሎ በ1940ዎቹ በዚሁ ፍርድ ቤት ተሰጥቶ የነበረ ውሳኔ በመጥቀስ እንደሚከተለው ብሏል:- “በሁለተኛው የዓለም ጦርነት [የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር] አባላትን ከጥቃቅን ስደቶች ለመጠበቅ የተሰጡት የፍርድ አስተያየቶች ፍርድ ቤቱ ከዚህ ካሁኑ ጉዳይ ጋር የቅርብ ተዛምዶ ስላለው የሕገ መንግሥቱ የመጀመሪያ ማሻሻያ ያለውን አመለካከት በግልጽ ያሳያሉ።”

የፍርድ ቤቱ መደምደሚያ ምን ነበር? “የመጀመሪያው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ተሽሮ መዝገቡ ወደዚሁ ፍርድ ቤት እንዲመለስ ወስነናል” ብሏል።

በዚህ መንገድ በመጨረሻ ቺካጎ ሳን-ታይምስ እንዳለው “ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮችን ደግፏል።” ያውም 8 ለ1 በሆነ የድምፅ ብልጫ።

ለወደፊቱስ?

በስትራተን መንደር አጠገብ በሚገኘው በዌልስቪል ጉባኤ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችስ ይህን በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘውን ድል እንዴት ተመለከቱት? በስትራተን ነዋሪዎች ላይ የሚፎክሩበት ምንም ምክንያት እንደሌላቸው የታወቀ ነው። ምሥክሮቹ ደግ በሆኑት የመንደሩ ነዋሪዎች ላይ ምንም ዓይነት ቅሬታ የላቸውም። በአካባቢው ከሚኖሩት ምሥክሮች አንዱ የሆነው ግሪጎሪ ኩሃር “እዚህ የፍርድ ቤት ሙግት ውስጥ የገባነው ፈልገነው ሳይሆን ድንጋጌው አግባብ ባለመሆኑ ብቻ ነው። ይህን ያደረግነውም ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካውያን ሁሉ ነው።”

የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው የሚኖሩ ሰዎችን ላለማስቆጣት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ጂን ኩንዝ የተባለው ሌላ ምሥክር ደግሞ “ለመጨረሻ ጊዜ በስትራተን የሰበክነው መጋቢት 7, 1998 ነበር። ከአራት ዓመት በፊት መሆኑ ነው። እንደምታሰር ተነገረኝ። ባለፉት ዓመታት በሙሉ ፖሊሶች እንደሚያስሩን መዛታቸውን የሚገልጹ በርካታ ሪፖርቶች ደርሰውናል። የድንጋጌው ቅጂ በጽሑፍ እንዲሰጠን ስንጠይቅ ግን መልስ አላገኘንም።”

ኩንዝ በመቀጠል “የእኛ ምርጫ ሁልጊዜም ከአካባቢያችን ሰዎች ጋር በጥሩ ጉርብትና መኖር ነው። እቤታቸው እንዳንሄድ የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ አንደርስባቸውም። እንድንጠይቃቸው የሚፈልጉና ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ለማድረግ የሚፈልጉ ደግሞ አሉ” ብሏል።

ግሪጎሪ ኩሃር እንደሚከተለው በማለት ያብራራል:- “በዚህ ሙግት የገፋንበት የስትራተንን ነዋሪዎች ለማስቆጣት አይደለም። በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠልንን የመናገር ነጻነታችንን በሕጋዊ መንገድ ለማስጠበቅ ስለፈለግን ብቻ ነው።”

በመቀጠልም “ከጊዜ በኋላ ወደ ስትራተን ለመመለስ ተስፋ እናደርጋለን። ስንመለስም የመጀመሪያውን በር የማንኳኳው እኔ ብሆን በጣም ደስ ይለኛል። ከዚህ ሁሉ እንቅፋት በኋላ የክርስቶስን ትእዛዝ ለመፈጸም መመለስ ይኖርብናል” ብሏል።

“በከሳሽ ዎችታወርና በተከሳሽ የስትራተን መንደር” መካከል የተነሳውን ውዝግብ በተመለከተ የተላለፈው ብይን ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ ከሰሙ በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የማዘጋጃ ቤት ባለ ሥልጣናት የራስን ደንብ በማውጣት የይሖዋ ምሥክሮችን የወንጌላዊነት ሥራ ማስቆም እንደማይቻል ተገንዝበዋል። እስከ አሁን ድረስ በዩናይትድ ስቴትስ 90 በሚያህሉ መንደሮች ውስጥ ከቤት ወደ ቤት ከሚደረገው ስብከት ጋር በተያያዘ ተነስተው የነበሩ ችግሮች ተወግደዋል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የይሖዋ ምሥክሮች አሁንም እንደገና ድል አደረጉ”

በአንደኛው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማዕከል የትምህርት ፕሮግራሞች ዲሬክተርና ከፍተኛ ምሁር የሆኑት ቻርልስ ሲ ሄይንስ ከላይ የተጠቀሱትን ቃላት ፍሪደም ፎረም ዌብ ሳይት ላይ “የእምነት ነጻነት” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ አስፍረዋል። ሄይንስ ጽሑፋቸውን በመቀጠል “የይሖዋ ምሥክሮች ባለፈው ሳምንት ለመላው የአሜሪካ ሕዝብ በአንደኛው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሥር የሚካተቱ በርካታ መብቶችን ካረጋገጡላቸው በርካታ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ድሎች መካከል 48ኛውን ድል አስመዝግበዋል” ብለዋል። “ይህን አንድ ቁም ነገር መዘንጋት የለብንም” በማለት ያስጠነቅቃሉ። “መንግሥት የአንድን እምነት ነጻነት መገደብ ከቻለ የማንኛውንም ወይም የሁሉንም እምነት ነጻነት የመገደብ ሥልጣን ይኖረዋል ማለት ነው። . . . ማንም ሰው ያለማዳመጥ፣ በሩን የመዝጋት መብት አለው። መንግሥት ግን ማንኳኳት የሚችለውንና የማይችለውን ሰው የመወሰን ሥልጣን ሊኖረው አይገባም። ስለዚህ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታላቅ ምስጋና ሊሰጠው ይገባል።”

ሄይንስ ሲደመድሙ “የይሖዋ ምሥክሮች ለሁላችንም ባለውለታዎቻችን ናቸው። ምንም ያህል ጊዜ ቢሰደቡ፣ ከከተሞች ቢባረሩና ቢደበደቡ እንኳን ለራሳቸውም ሆነ (ለእኛ) መብቶች መታገላቸውን አላቆሙም። እነርሱ ድል ነሱ ማለት እኛም ድል ነሳን ማለት ነው” ብለዋል።

[በገጽ 10, 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስላሳለፈው ውሳኔ ጋዜጦች ምን አሉ?

“ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮችን ደገፈ፤ ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት ፈቃድ ማግኘት አያስፈልገውም።

የይሖዋ ምሥክሮች ቤት እያንኳኩ በሚያከናውኑት አገልግሎታቸው ሁልጊዜም አምላክ ከእነርሱ ጋር እንደሆነ ያምናሉ። አሁን ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከእነርሱ ጋር ሆኗል።”​—⁠ቺካጎ ሳን ታይምስ፣ ሰኔ 18, 2002

“የንግግር ነጻነት ድል አደረገ

የይሖዋ ምሥክሮች እበራችሁ መጥተው ከገበታ ቢያስነሷችሁ እንኳ ልታመሰግኗቸው ይገባል። ለሃይማኖታዊ መመሪያዎቻቸው በድፍረት በመቆማቸው እነዚህ በዩናይትድ ስቴትስ አንድ ሚልዮን የማይሞሉና ብዙም ያልታወቁ ሃይማኖተኞች ከማንኛውም ድርጅት ይበልጥ ለግለሰብ አሜሪካውያን የመናገር ነጻነት ለማስገኘት ጥረት አድርገዋል። . . .

“ምሥክሮቹ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ሲያቀርቡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ባለፉት ከ65 የሚበልጡ ዓመታት ባቀረቧቸው ከሁለት ደርዘን የሚበልጡ አቤቱታዎች ብዙሐኑ የጫኑባቸውን ጭቆና በጥሩ ሁኔታ ተዋግተው ድል ማግኘት ችለዋል።”​—⁠ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ፣ ሰኔ 18, 2002

▪ “በየቤቱ እየሄዱ ሰዎችን ማነጋገር በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠ መብት ነው ተባለ። ይህ የይሖዋ ምሥክሮችን ድል ያቀዳጀ ውሳኔ ነው።

ፖለቲከኞች፣ ሃይማኖታዊ ቡድኖች፣ ገርል ስካውት ተብለው የሚታወቁት የልጃገረዶች ማኅበርና ሌሎች ከአካባቢ ባለ ሥልጣኖች ፈቃድ ማግኘት ሳያስፈልጋቸው የሰዎችን በር የማንኳኳት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰኞ ዕለት ወሰነ።”​—⁠ሳን ፍራንሲስኮ ክሮኒክል፣ ሰኔ 18, 2002

“ጠቅላይ ፍርድ ቤት:- የይሖዋ ምሥክሮችንም ሆነ ገርል ስካውት ተብለው የሚታወቁትን የልጃገረዶችን ማኅበር ቤት እንዳያንኳኩ መከልከል አትችሉም

ዋሽንግተን​—⁠ሕገ መንግሥቱ ሚስዮናውያን፣ ፖለቲከኞችና ሌሎች ከአካባቢ ባለ ሥልጣኖች ፈቃድ ማግኘት ሳያስፈልጋቸው የሰዎችን በር የማንኳኳት መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል ሲል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰነ። . . .

“ፍርድ ቤቱ 8 ለ1 በሆነ የድምፅ ብልጫ በአንደኛው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የተረጋገጠው የመናገር ነጻነት አንድን መልእክት ለማድረስ የሰዎችን ቤት ማንኳኳትን ይጨምራል በማለት ወስኗል።”​—⁠ስታር ትሪብዩን፣ ሚንያፖሊስ፣ ሰኔ 18, 2002

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳኛ ስቲቨንስ

[ምንጭ]

ስቲቨንስ:- Collection, The Supreme Court Historical Society/Joseph Bailey