በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሞባይል ስልክ “ሱስ”

የሞባይል ስልክ “ሱስ”

የሞባይል ስልክ “ሱስ”

ጃፓን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ዴይሊ ዮሚዩሪ የተሰኘው የጃፓን ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ ላይ “ሰዎች በሞባይል ስልክ መጠቀም ሱስ እየሆነባቸው መጥቷል” በማለት ተናግሯል። ሱስ? ትሉ ይሆናል። ጋዜጣው በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “ወጣቶች የሞባይል ስልካቸውን እንደ አካላቸው ክፍል አድርገው እስከመመልከት ደርሰዋል፤ ስልካቸውን ካልያዙ በጭንቀት ይዋጣሉ።” ብዙዎች ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዳይቋረጥ በመፍራት በሄዱበት ሁሉ ሞባይል ስልካቸውን ይዘው ይዞራሉ። “ካልተደወለላቸው ይጨነቃሉ፣ ይነጫነጫሉ እንዲሁም ፈላጊ እንደሌላቸው ሆኖ ይሰማቸዋል።” በዚህም ምክንያት መልስ መስጠት ባያስፈልጋቸውም እንኳን ለማንኛውም ጥሪ ወዲያው ምላሽ ይሰጣሉ።

እርግጥ ነው፣ ሞባይል ስልክ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፤ እንዲያውም ድንገተኛ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በአግባቡ እስከሆነ ድረስ በሞባይል ስልክ መጠቀም በራሱ ምንም ስህተት የለውም። ሆኖም አንዳንድ ባለሥልጣናት እንደሚሉት የሞባይል ስልክ “ሱስ” የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታችንን ሊያዳክምብን ይችላል። ጋዜጣው እንደገለጸው በኦሳካ የሚኖሩ አንዲት የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር በሞባይል ስልክ ምክንያት “ልጆች የፊት መግለጫዎችን፣ የሌሎች ሰዎችን ባሕርይና የድምፅ ቃናን የመረዳት ችሎታቸውን እያጡ እንዳሉ” ተናግረዋል። “ይህም ልጆች ግልፍተኛና ለሌሎች ስሜት ግድ የሌላቸው እንዲሆኑ አድርጓል።”

ዘገባው ሲደመድም እንዲህ ብሏል:- “ወደፊትም ቢሆን በልጆች ላይ የሚታየው ይህ ዓይነቱ አዝማሚያ እንዳይባባስ ማድረግ የሚቻል አይመስልም። ይህ ሁኔታ የሚያስከትለውን ጎጂ ተጽዕኖ መቀነስ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ትላልቅ ሰዎች በሞባይል ስልክ አጠቃቀም ረገድ ለልጆች ጥሩ ምሳሌ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።”