በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጀመሪያው እንቅፋት—በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተደረገ የቃል ክርክር

የመጀመሪያው እንቅፋት—በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተደረገ የቃል ክርክር

የመጀመሪያው እንቅፋት—በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተደረገ የቃል ክርክር

በመሐል ዳኛው በዊልያም ሬንኪስትና በስምንቱ ተባባሪ ዳኞች ፊት የሚደረገው የቃል ክርክር የተቀጠረው ለየካቲት 26, 2002 ነበር። የይሖዋ ምሥክሮችን ወክለው የቀረቡት አራት ጠበቆች ነበሩ።

የምሥክሮቹ ተቀዳሚ ጠበቃ ክርክሩን የጀመሩት በሚከተለው ትኩረት የሚስብ መግቢያ ነበር:- “ዕለቱ ቅዳሜ ጠዋት 5:​00 ሰዓት፣ ቦታው የስትራተን መንደር ነው። [ከዚያም ማይክሮፉኑን እየመቱ ሦስት ጊዜ አንኳኩ።] ‘ጤና ይስጥልኝ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጸሙ ካሉት ነገሮች አኳያ ነቢዩ ኢሳይያስ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ስለተናገረው ቃል ላነጋግርዎት ቤትዎ ድረስ መጥቼአለሁ። ክርስቶስ ኢየሱስም ስለዚህ ምሥራች ተናግሯል። ይህም የአምላክ መንግሥት ምሥራች ነው።’ ”

በመቀጠል እንዲህ አሉ:- “በስትራተን መንደር በቅድሚያ ፈቃድ ካልተገኘ በቀር ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ይህን መልእክት ማድረስ ወንጀል ነው።”

‘ገንዘብ አትጠይቁም?’

ስቲፈን ጂ ብሪየር የተባሉት ዳኛ ለምሥክሮቹ አንድ አግባብነት ያለው ጥያቄ አቀረቡ። በየቤቱ የሚሄዱት ሰዎች “ምንም ገንዘብ፣ አንዲትም ሳንቲም እንኳን አይጠይቁም፣ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ነገር አይሸጡም፣ ‘ስለ ሃይማኖት ላነጋግርህ እፈልጋለሁ’ ከማለት ሌላ ምንም ነገር አያደርጉም ማለት ነው?”

የምሥክሮቹ ጠበቃ እንዲህ በማለት መለሱ:- “ክቡር ሆይ! በዚህ ረገድ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም። በስትራተን መንደር የይሖዋ ምሥክሮች ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዲሰጣቸው አልጠየቁም። በሌሎች አካባቢዎችም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ የፈቃደኝነት መዋጮ መስጠት እንደሚቻል ከመናገር በቀር ገንዘብ አይጠይቁም። . . . ገንዘብ ለመሰብሰብ የተሰማራን ሰዎች አይደለንም። ፍላጎታችን ለሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መናገር ነው።”

ከመንግሥት ፈቃድ ማግኘት አስፈላጊ ነው?

“አቋማችሁ አስፈላጊ ስለሆነ ጉዳይ ከጎረቤት ጋር ለመነጋገር የከንቲባውን ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልገንም የሚል ነው። አይደለም?” በማለት ዳኛ አንቶኒን ስካልያ የአስተዋይነት ጥያቄ አቀረቡ። የምሥክሮቹ ጠበቃ ሲመልሱ “አንድ ዜጋ ሌላውን ዜጋ በቤቱ ለማነጋገር ፈቃድ ማውጣት አለበት በማለት መስተዳድሩ ያወጣውን ድንጋጌ ፍርድ ቤቱ መደገፍ ይገባዋል ብለን አናምንም” አሉ።

የክርክሩ አቀራረብ ተለወጠ

አሁን የስትራተን መንደር ክርክሩን የሚያቀርብበት ተራ ደረሰ። ተቀዳሚ ጠበቃው የስትራተንን ድንጋጌ ሲያብራሩ እንዲህ አሉ:- “የስትራተን መንደር የነዋሪዎቹን ሰላም ሲያስከብር፣ ወንጀል ለመከላከል ጥረት ሲያደርግ የሕዝብን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታውን እየተወጣ ነው። በየግል ቤቶች እየተዘዋወሩ ዕቃ መሸጥንና ድጋፍ ማሰባሰብን የሚከለክለው ድንጋጌ በቅድሚያ መመዝገብንና ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው እንቅስቃሴ ወቅት ፈቃድ ይዞ መገኘትን የሚጠይቅ ብቻ ነው።”

ዳኛ ስካልያ ወዲያው ወደ ጉዳዩ እምብርት በመግባት እንደሚከተለው በማለት ጠየቁ:- “ፍርድ ቤታችን ይህን የመሰለ ስፋት ባለው ጉዳይ ላይ ማለትም ድጋፍ ማሰባሰብን ወይም ገንዘብ አለመጠየቅንም ሆነ ዕቃ አለመሸጥን በሚመለከት ወይም ‘ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወይም የአካባቢ ደህንነት ጥበቃን በተመለከተ ላነጋግር እፈልጋለሁ’ ስለ ማለት ብይን ሰጥቶ ያውቅ እንደሆነ የምታስታውሱት ነገር አለ? እንዲህ ያለ ጉዳይ ቀርቦ ያውቃል?”

ዳኛ ስካልያ በመቀጠል “ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት እንኳን ቀርቦ አያውቅም” አሉ። የመሃል ዳኛው ሬንኪስት “ያን የሚያህል ዓመት እንኳ አልኖርክም” ብለው በቀልድ መለሱ። በችሎቱ የነበሩ ሁሉ ሳቁ። ዳኛ ስካልያ አሁንም ነጥባቸውን ሳይለቁ “ይህ ጉዳይ ይህን ያህል ከባድ የሆነበት ምክንያት ፈጽሞ አይታየኝም” አሉ።

አግባብ ነው ትላላችሁ?

ዳኛ አንቶኒ ኤም ኬኔዲ ቀጥተኛ የሆነ ጥያቄ አቀረቡ:- “ከምኖርበት አካባቢ ትንሽ ራቅ ብዬ የማላውቃቸውን ሰዎች ቆሻሻ በጊዜው አለመሰብሰቡ ወይም የምክር ቤት ተወካያችን ጉዳይ አሳስቦኛልና ላነጋግራችሁ እፈልጋለሁ ለማለት መንግሥት ፈቃድ እንዲሰጠኝ መጠየቅ ቢኖርብኝ አግባብ ነው ትላላችሁ? በእርግጥ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለማከናወን የመንግሥት ፈቃድ መጠየቅ ይኖርብኛል? በጣም የሚያስገርም ነገር ነው” አሉ።

ከዚያም ዳኛ ሳንድራ ዴይ ኦኮነር የክርክሩ ተካፋይ በመሆን “በአንዳንድ የበዓል ቀናት እየዘፈኑ በየቤቱ ስለሚዞሩት ልጆችስ ምን ለማለት ይቻላል?” ሲሉ ጠየቁ። “እነርሱም ፈቃድ መጠየቅ ሊኖርባቸው ነው?” ዳኛ ኦኮነርና ስካልያ በዚሁ የክርክር አቅጣጫ በመቀጠል ሌላ የክርክር ነጥብ አቀረቡ። “ከጎረቤት አንድ ስኒ ስኳር ለመበደርስ? ጎረቤቴን ስኳር እንዲያበድረኝ ከመጠየቄ በፊት ፈቃድ መጠየቅ ሊኖርብኝ ነው?”

ምሥክሮቹ እየዞሩ ድጋፍ የሚያሰባስቡ ሰዎች ናቸው?

ዳኛ ዴቪድ ኤች ሱተር “ይህ ድንጋጌ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚመለከት የሆነው ለምንድን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ድጋፍ ለማሰባሰብ ወይም አንድ ዓይነት ሸቀጥ ለመሸጥ ወይም አገልግሎት ለመስጠት የሚዘዋወሩ ወይም ሱቅ በደረቴዎች ወይም ሸቃጮች ናቸው? አይደሉም” አሉ። የመንደሩ ጠበቆች ድንጋጌውን በዝርዝር ከጠቀሱ በኋላ የበታች ፍርድ ቤቶች የይሖዋ ምሥክሮች ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚዘዋወሩ (canvasser) ናቸው ብለው እንደበየኑ ተናገሩ። ዳኛ ሱተር ለዚህም ሲመልሱ “የይሖዋ ምሥክሮች ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚዘዋወሩ ሰዎች ናቸው ከተባለ ካንቫሰር ለሚለው ቃል በጣም የተለጠጠ ትርጉም ተሰጥቷል ማለት ነው።”

ከዚያም ዳኛ ብሪየር መዝገበ ቃላት ካንቫሰር የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ምን ብሎ እንደሚፈታው ከጠቀሱ በኋላ ይህ ቃል ለይሖዋ ምሥክሮች እንደማይሠራ አመለከቱ። በማከል “በይግባኝ መልሳችሁ ላይ እነዚህ ገንዘብ የመሰብሰብ ወይም ሸቀጥ የመሸጥ ወይም ድምፅ የማሰባሰብ ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች ወደ ከተማው ማዘጋጃ ቤት ሄደው መመዝገባቸው አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት የሚገልጽ ነገር አላነበብኩም። የከተማው መስተዳድር ዓላማ ምንድን ነው?”

ሐሳብ የመግለጽ ነጻነት ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ “ልዩ መብት” ተደርጎ የተቆጠረበት ምክንያት

ከዚያም የመንደሩ ጠበቆች “የከተማው ዓላማ የባለንብረቶችን ፀጥታ ለመጠበቅ ነው” ሲሉ ተከራከሩ። በመቀጠልም ነዋሪዎችን ከአጭበርባሪዎችና ከወንጀለኞች ለመጠበቅ ነው በማለት ምክንያታቸውን አብራሩ። ዳኛ ስካልያ ከድንጋጌው በመጥቀስ ከንቲባው “የተጠየቀው መብት ባሕርይ ምን እንደሆነ በትክክል ለማወቅ” ስለ ፈቃድ ጠያቂውና ስለ ዓላማው ተጨማሪ ጥያቄ ሊያቀርብ እንደሚችል አመለከቱ። ቀጥለውም “ስለ አንድ ጉዳይ ለማሳመን የአገሩን ዜጎች ማነጋገር እንደ ልዩ መብት ተደርጎ መቆጠሩ ሊገባኝ የማይችል ነገር ነው” አሉ።

ዳኛ ስካልያ አሁንም በመቀጠል “ታዲያ የሰው በር ለማንኳኳት የፈለገ ሁሉ ከማንኳኳቱ በፊት ማዘጋጃ ቤት ቀርቦ የእጁን አሻራ እንዲያስነሳ ትጠይቃላችሁ ማለት ነው? ገና ለገና ወንጀል ይፈጸማል ተብሎ የሰው በር የሚያንኳኳ ሁሉ ማዘጋጃ ቤት ቀርቦ መመዝገብ አለበት ይባላል? አይባልም” አሉ።

ለነዋሪዎች ጥበቃ ተደርጎላቸዋል?

የመንደሩ ጠበቃ የተፈቀደላቸው 20 ደቂቃ እንዳለቀ ክርክሩን ለኦሃዮ ግዛት አቃቤ ሕግ ለቀቁ። እየዞሩ መሸቀጥን የሚከለክለው ድንጋጌ ነዋሪዎችን ከእንግዳ ሰዎች፣ “ኑ ሳይባሉ በር ከሚያንኳኩ ሰዎች ይጠብቃል። . . . የመንደሩም አስተዳደር ‘እንደዚህ ያለው እንቅስቃሴ ያሳስበናል’ ማለቱ ተገቢ ይመስለኛል” በማለት ተከራከሩ።

ከዚያም ዳኛ ስካልያ የሚከተለውን አስተያየት ሰጡ:- “የመንደሩ አስተዳደር የይሖዋ ምሥክሮችን ተቀብለው ለማነጋገር የፈለጉ ሰዎችን፣ ብቻቸውን በመሆናቸው ምክንያት የሚያነጋግራቸው ሰው ቢያገኙ ደስ የሚላቸውን ጭምር ለማነጋገር ማዘጋጃ ቤቱ በር የማንኳኳት ፈቃድ እንዲሰጣቸው መጠየቅ አለባቸው ማለቱ ነው።”

“በጣም አነስተኛ የሆነ ገደብ”

በጥያቄና መልሱ ወቅት ዳኛ ስካልያ እንዲህ በማለት አንድ ጠንካራ ነጥብ ጠቅሰዋል:- “ሁላችንም በዓለም ውስጥ የአምባገነን አስተዳደርን ያህል ኅብረተሰቡን ከወንጀል የሚከላከል አስተዳደር የለም ለማለት እንችላለን። በአምባገነን አስተዳደሮች ብዙ ወንጀል አይኖርም። ለነፃነት ከምንከፍለው ዋጋ አንዱ ይነስም ይብዛ ሕገወጥ ለሆኑ እንቅስቃሴዎች መጋለጥ ነው። ጥያቄው ይህ ድንጋጌ ሊያስቀር የሚችለው ሕገወጥ እንቅስቃሴ የሰው በር ለማንኳኳት ፈቃድ ለመጠየቅ መገደድን የሚያህል ዋጋ ሊከፈልበት የሚገባ ነውን?” የሚለው ነው። ከዚያም ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ “ይህ እኮ በጣም አነስተኛ ገደብ ነው” ሲሉ መለሱ። ዳኛ ስካልያ “ይህን የመሰለ ድንጋጌ ያወጣ አንድም ማዘጋጃ ቤት መኖሩ ተሰምቶ አያውቅም። ታዲያ እንዲህ ያለውን ድንጋጌ አነስተኛ ገደብ ነው ማለት እንችላለን? እኔ አይመስለኝም” በማለት ተቃወሙ።

በመጨረሻም ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ከዳኞቹ አንዱ በጣም ስለተጫኗቸው “የሰው ቤት ማንኳኳትን የሚያግድ ሕግ ማውጣት የሚቻል አይመስለኝም” ብለው አመኑ። በዚሁ ክርክሩ አቆመ።

በክርክሩ ወቅት የምሥክሮቹ ጠበቃ ድንጋጌው ፈቃድ ጠያቂው እውነተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥበት መንገድ የሌለው መሆኑን አመለከቱ። “ወደ መንደሩ አስተዳደር ሄጄ ‘እገሌ እባላለሁ’ ብዬ ፈቃድ ልወስድና ከቤት ወደ ቤት ልሄድ እችላለሁ።” በተጨማሪም ከንቲባው የምንም ድርጅት አባል ላልሆነ ሰው ፈቃድ የመከልከል ሥልጣን አላቸው። “በባለ ሥልጣኑ መልካም ፈቃድ ብቻ የሚወሰን ነገር ነው ብለን እናምናለን” ካሉ በኋላ “[የይሖዋ ምሥክሮች] እንቅስቃሴ የተመካው በአንደኛው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ላይ ነው በማለት በአክብሮት እናሳስባለን።”

ብዙም ሳይቆይ የመሐል ዳኛው ሬንኪስት “ጉዳዩን [ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ] እንዲያየው ተወስኗል” በማለት የቃል ክርክሩን ዘጉ። ሙሉው ችሎት ከአንድ ሰዓት በላይ አልቆየም። ይህ ሰዓት ያስገኘው ውጤት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በሰኔ ወር ይፋ የሆነው የጽሑፍ ብይን ያመለክታል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የመሃል ዳኛ ሬንኪስት

ዳኛ ብሪየር

ዳኛ ስካልያ

[ምንጮች]

ሬንኪስት:- Collection, The Supreme Court Historical Society/Dane Penland; ብሪየር:- Collection, The Supreme Court Historical Society/Richard Strauss; ስካልያ:- Collection, The Supreme Court Historical Society/Joseph Lavenburg

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዳኛ ሱተር

ዳኛ ኬኔዲ

ዳኛ ኦኮነር

[ምንጭ]

ኬኔዲ:- Collection, The Supreme Court Historical Society/Robin Reid; ኦኮነር:- Collection, The Supreme Court Historical Society/Richard Strauss; ሱተር:- Collection, The Supreme Court Historical Society/Joseph Bailey

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ችሎቱ የተካሄደበት ክፍል

[ምንጭ]

Photograph by Franz Jantzen, Collection of the Supreme Court of the United States