በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ሆኖም ደጋፊ ያላጡ ወላጆች

የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ሆኖም ደጋፊ ያላጡ ወላጆች

የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ሆኖም ደጋፊ ያላጡ ወላጆች

“ልጆቼ ቤት እንደደረሱ እቅፍ አድርገው ሲስሙኝና እንደሚወዱኝ ሲነግሩኝ እንኳን እናት ሆንኩ እላለሁ።”ዶሪስ፣ ሁለት ልጆችን ያለ አባት የምታሳድግ እናት

የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ወላጆች “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መጽናናትና መበረታታት ይገባቸዋል። (መዝሙር 127:3) ልጆች በአንድ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ መኖራቸው በአምላክ ዘንድ ያላቸውን ተወዳጅነት አይቀንሰውም። ፈጣሪያችን በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች የተሳካላቸው እንዲሆኑ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “አባት የሌለውን ልጅና ባልዋ የሞተባትን ሴት ይረዳል” ይላል። (መዝሙር 146:9 NW) የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ወላጆች አምላክ ሊረዳቸውና ሊደግፋቸው ዝግጁ እንደሆነ እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ።

አንድ ልጅ በአካል፣ በስሜትና በመንፈሳዊ ለማደግ በሚያስችለው ፍቅር፣ ሰላምና መረጋጋት በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ የማደግ መብት አለው። ሕፃኑን አሰልጥኖ ማሳደግ ደግሞ አምላክ ለእያንዳንዱ ወላጅ የሰጠው መብትና ግዴታ ነው።

የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ብዙ ወላጆች የተሳካ ውጤት የሚገኘው በትጋት በመጸለይ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶችን ሥራ ላይ በማዋልና ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ በመመካት እንደሆነ ተገንዝበዋል። ይህም በመዝሙር 55:22 ላይ ከሚገኘው ከሚከተለው ምክር ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል:- “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል።”

አያቶች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያን ወላጆች የትዳር ጓደኛ የሌላት አንዲት ወላጅ የሚያጋጥሟትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድትቋቋም የሚረዱባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። የቅርብ ዘመዶችና የአምልኮ ባልንጀሮች እርዳታ ሊያበረክቱ የሚችሉባቸው በርካታ መንገዶች ይኑሩ እንጂ አምላክ በዋነኛነት ኃላፊነቱን የሰጠው ለልጁ ወላጅ ነው። *

የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ብዙ ወላጆች የሚኖሩበት ሁኔታ ያስከተለባቸውን በርካታ ችግሮች በጽናት ተወጥተው ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ጥሩ ጠባይ ያላቸውና አምላክን የሚፈሩ ልጆች ማሳደግ መቻላቸው በጣም ያስደስታል። የንቁ! ዘጋቢ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን አነጋግሯል። እነዚህ ስኬታማ የሆኑ ወላጆች የሚከተሏቸው የጋራ ባሕርያት ከዚህ ቀጥሎ ተዘርዝረዋል።

የተደራጀና የተቀናጀ የቤተሰብ አስተዳደር። በሚገባ የተደራጁ ለመሆንና ፕሮግራሞቻቸውን ለማቀናጀት ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ። ጥሩ እቅድ ማውጣትና የተደራጁ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የትጉህ አሳብ ወደ ጥጋብ ያደርሳል” ይላል።—ምሳሌ 21:5

ቅድሚያ መስጠት። ለቤተሰባቸው ቅድሚያ ይሰጣሉ። የልጆቻቸውን ፍላጎት ከራሳቸው ፍላጎት ያስቀድማሉ።—1 ጢሞቴዎስ 5:8

ሚዛናዊ አመለካከት። ለችግሮቻቸው መፍትሔ ይፈልጋሉ እንጂ ችግሮቻቸውን አያጋንኑም ወይም አቅልለው አይመለከቱም። ምሬትም ሆነ ቁጭት ሳይሰማቸው ችግሮቻቸውን ተቀብለው ለመወጣት ይሞክራሉ።

ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ። በእነርሱና በልጆቻቸው መካከል ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዲኖር ጥረት ያደርጋሉ። በቤተሰቡ ውስጥ የሐሳብና የስሜት ግልጽነትና አለመደባበቅ እንዲኖር ያበረታታሉ። ልጆቹን ያለ እናት የሚያሳድግ አንድ አባት “ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ አነጋግራቸዋለሁ። ምግብ በምናዘጋጅበት ጊዜ ሞቅ ያለ ጨዋታ እንጫወታለን። የልባቸውን አውጥተው የሚገልጹልኝ በዚህ ጊዜ ነው” ብሏል።

ራስን መጠበቅ። ጊዜያቸውን የሚሻሙባቸው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም ለመንፈሳዊ፣ ለስሜታዊና ለአካላዊ ፍላጎቶቻቸው ተገቢውን ትኩረት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ከባልዋ ተፋትታ ሁለት ልጆችዋን የምታሳድገው ኤተል እንዲህ ትላለች:- “ለራሴ የሚሆን ጊዜ ለማግኘት እሞክራለሁ። ለምሳሌ አንድ ወዳጄ ልጆቼን ሙዚቃ በምታስተምርበት ጊዜ ለራሴ የሚሆን አንድ ሰዓት የሚያክል ጊዜ አገኛለሁ። ቴሌቪዥኑን ሳልከፍት ቁጭ እላለሁ።”

አዎንታዊ አመለካከት። ስለ ወላጅነትም ሆነ ስለ ኑሮ በአጠቃላይ አዎንታዊ የሆነ አመለካከት አላቸው። አስጨናቂ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው እንኳን ብሩሕ ነገር ይታያቸዋል። የትዳር ጓደኛ የሌላት አንዲት እናት “ልጆችን ያለ አባት ማሳደግ ምንም ደስታ የሌለው ሕይወት እንዳልሆነ መገንዘብ ችያለሁ” ብላለች።

የትዳር ጓደኛ ባይኖራቸውም ስኬታማ የሆኑ ወላጆች

እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው መመሪያዎች ውጤታማ ናቸው? ልጆቻቸውን በተሳካ ሁኔታ ማሳደግ የቻሉ የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ወላጆች ታሪክ እንደሚያሳየው ከሆነ ውጤታማ ናቸው። በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው በእንግሊዝ አገር የምትኖረውና ከባሏ የተፋታችው ግሎሪያ ተቀጥራ እየሠራች ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ልጅ አሳድጋለች። ሦስቱም አድገው የሙሉ ጊዜ ክርስቲያን አገልጋዮች በመሆን የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በማስፋፋት ላይ ይገኛሉ። ግሎሪያ እንዲህ ያለ ውጤት ልታገኝ የቻለችው እንዴት እንደሆነ ተጠይቃ ስትመልስ እንዲህ ብላለች:- “መወጣት የነበረብኝ የመጀመሪያው ፈታኝ ሁኔታ ቋሚና አስደሳች የሆነ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ ነው። ልጆቹ ደስተኛ እንዲሆኑ፣ የአእምሮ ሰላም እንዲኖራቸው፣ እርካታ እንዲያገኙና ከብዙ እንቅፋቶችና ወጥመዶች እንዲጠበቁ እፈልግ ነበር። የማታ ሥራ አገኘሁ። ዓላማዬ በተቻለ መጠን ከልጆቼ ጋር መሆን ነበር። ወደ ሥራ ከመሄዴ በፊት አብሬያቸው እጸልይና አስተኛቸዋለሁ። ሥራ ላይ በምሆንበት ጊዜ አክስቴ አብራቸው ትቆይ ነበር።”

ግሎሪያ ልጆቿ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን እንዲያስቀድሙ የረዳቻቸው እንዴት ነበር? እንዲህ በማለት አክላ ተናግራለች:- “ትልቁ ዓላማዬ መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም ነበር። ብዙ ገንዘብ አልነበረንም። ይህንንም ልጆቼ በግልጽ እንዲያውቁ አድርጌያለሁ። እንዲያደርጉ የምጠይቃቸውን ነገሮች በሙሉ እኔም አደርጋለሁ። ሁሉም ይተባበሩኝ ነበር።” በጣም የሚቀራረብና የሚፋቀር ቤተሰብ እንዲኖራት ያስቻላት ምን እንደሆነ መለስ ብላ ስታስታውስ እንዲህ ትላለች:- “ቁልፉ ሥራዎችን አብሮ መሥራት ነው። ወደራሱ ክፍል ሄዶ ብቻውን የሚቀመጥ አልነበረም። ምግብ የምናበስለው፣ ቤት የምናጸዳውና የምናስጌጠው አንድ ላይ ሆነን ነበር። እንቅስቃሴዎቻችን ሚዛናዊ እንዲሆኑ እናደርግ ነበር። ለመዝናኛ የሚሆን ጊዜም እንዳናጣ ሁልጊዜ እጠነቀቅ ነበር።”

ጆሴፍ የሚባለውን ልጅዋን ያለ አባት የምታሳድገው ካሮሊን በልጅዋ አስተዳደግ ደስ ተሰኝታለች። እርሷስ የተጠቀመችበት ዘዴ ምንድን ነው? እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “ከመተኛታችን በፊት መጽሐፍ ቅዱስ አብረን እናነባለን። ከዚያም ከንባቡ ምን ትምህርት እንዳገኘ እጠይቀዋለሁ። በተጨማሪም ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አንዳንድ አንቀጾችን እናነብና ያነበብናቸው ነገሮች በኛ ላይ እንዴት እንደሚሠሩ እንወያያለን። ይህም ጆሴፍ በትምህርት ቤት ጉልበተኞች ሲያስቸግሩትም ሆነ ሌሎች ችግሮች ሲገጥሙት ረድቶታል።” ካሮሊን ኑሮዋ ቀላል እንዳልሆነ ባትክድም ብቻዋን እንደሆነች ሆኖ አይሰማትም። “የማያቋርጥ ትግል ነው። ቢሆንም ይሖዋ እንደረዳኝ ይሰማኛል። በተጨማሪም ከክርስቲያን ጉባኤ ብዙ ማበረታቻ አገኛለሁ” ብላለች።

እንደ ግሎሪያና እንደ ካሮሊን ያሉ በሺህ የሚቆጠሩ ወላጆች የትዳር ጓደኛ ከጎናቸው ሳይኖር ልጆቻቸውን ስኬታማ በሆነ መንገድ ማሳደግ መቻላቸው ዛሬም ወላጆች ጥሩና በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆኑ ልጆች ለማሳደግ በረዥም ዘመናት ተፈትነው ውጤታማነታቸው በተረጋገጠው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ሊታመኑ እንደሚችሉ ያሳያል። (ምሳሌ 22:6) በእርግጥም የተሳካ ውጤት ማግኘት ይቻላል! ልጆችን ያለ አባት ወይም ያለ እናት ማሳደግ በርካታ ፈተናዎችን የሚያስከትል ቢሆንም እነዚህ ፈተናዎች እድገት ለማድረግና ለጋስነት ለማሳየት የሚያስችል በር ሊከፍቱ ይችላሉ። እንዲህ ያለ ኃላፊነት የወደቀባቸው ወላጆች የሚገጥማቸውን ፈታኝ ሁኔታ መወጣት የሚችሉት ሙሉ በሙሉ በአምላክ በመታመንና እርዳታ እንደሚያደርግላቸው እርግጠኛ ሆነው በመኖር ነው።—መዝሙር 121:1-3

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች እንዴት የተሳካላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለ መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የግሎሪያ ሦስት ልጆች የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረጋቸው ክርስቲያን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። ስዕሉ ላይ የሚታየው ባሁኑ ጊዜ ሚስዮናዊ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው ትልቁ ልጅ የላከውን ደብዳቤና ፎቶግራፍ ሲመለከቱ ነው

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካሮሊንና ልጅዋ ጆሴፍ