በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቤልሻዛር የሚለው ስም የተጻፈበት ሸክላ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

የባቢሎኑ ቤልሻዛር ስለነበረው ሥልጣን አርኪኦሎጂ ምን ያረጋግጣል?

ለበርካታ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው ቤልሻዛር በሕይወት የነበረ ሰው አለመሆኑን ይገልጹ ነበር። (ዳን. 5:1) ለዚህ ምክንያት አድርገው የሚጠቅሱት፣ ቤልሻዛር በሕይወት እንደኖረ የሚያሳይ ማስረጃ በአርኪኦሎጂ ጥናት መገኘት አለመቻሉን ነው። ሆኖም በ1854 ይህን የሚቀይር ነገር ተገኘ። ምን?

በዚያ ዓመት፣ ጆን ጆርጅ ቴይለር የተባለው የብሪታንያ ቆንሲል በጥንቷ ዑር ከተማ (በዛሬዋ ኢራቅ ደቡባዊ ክፍል ይገኛል) ፍርስራሽ ላይ ጥናት ማድረግ ጀመረ። በዚያም በአንድ ትልቅ ግንብ ውስጥ የተለያዩ ሞላላ ሸክላዎችን አገኘ። እያንዳንዳቸው 10 ሴንቲ ሜትር ገደማ ርዝመት ባላቸው በእነዚህ ሸክላዎች ላይ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፈ ጽሑፍ ተቀርጾባቸው ነበር። በአንደኛው ሸክላ ላይ ያለው ጽሑፍ፣ ለባቢሎኑ ንጉሥ ለናቦኒደስና ለበኩር ልጁ ለቤልሻዛር ረጅም ዕድሜ ለመለመን የቀረበ ጸሎትን ያካተተ ነው። ተቺዎችም እንኳ ይህ ግኝት ቤልሻዛር በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ለማመን ተገደዋል።

ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ቤልሻዛር በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን ብቻ ሳይሆን ንጉሥ እንደነበረም ይገልጻል። ተቺዎች በዚህ ላይም ጥያቄ ነበራቸው። ለምሳሌ በ19ኛው መቶ ዘመን የኖሩ ዊልያም ቶልበት የተባሉ እንግሊዛዊ የሳይንስ ሊቅ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “አንዳንድ ጸሐፊዎች ብልሳርሱር [ቤልሻዛር] ከአባቱ ከናቦኒደስ ጋር አብሮ ይገዛ እንደነበር ይናገራሉ። ሆኖም . . . ይህን የሚጠቁም አንድም ማስረጃ የለም።”

ይሁን እንጂ ይህ ውዝግብ እልባት አግኝቷል፤ ምክንያቱም የቤልሻዛር አባት የሆነው ናቦኒደስ አንዳንድ ጊዜ ለተወሰኑ ዓመታት ከዋና ከተማዋ ርቆ ይሄድ እንደነበር የሚገልጽ ጽሑፍ በሌሎች ሸክላዎች ላይ ተገኘ። ታዲያ እሱ በሌለበት አገሪቱን የሚያስተዳድረው ማን ነበር? ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “ናቦኒደስ ከአገር ይወጣ በነበረበት ወቅት ዙፋኑን እና የሠራዊቱን ዋነኛ ክፍል ለቤልሻዛር አደራ ይሰጥ ነበር” ይላል። በመሆኑም ቤልሻዛር በእነዚህ ወቅቶች እንደ ንጉሥ ሆኖ ባቢሎንን ያስተዳድር ነበር ማለት ይቻላል። ከዚህ አንጻር፣ የአርኪኦሎጂ ባለሙያና የቋንቋ ምሁር የሆኑት አለን ሚላርድ እንደተናገሩት “የዳንኤል መጽሐፍ ቤልሻዛርን ‘ንጉሥ’ ብሎ መጥራቱ” ተገቢ ነው።

እርግጥ ነው፣ ለአምላክ አገልጋዮች የዳንኤል መጽሐፍ እምነት የሚጣልበትና በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን ዋነኛ ማስረጃ የሚሆናቸው ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።—2 ጢሞ. 3:16