በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑ ሰዎች መማሬ ብዙ በረከት አስገኝቶልኛል

ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑ ሰዎች መማሬ ብዙ በረከት አስገኝቶልኛል

ወጣት እያለሁ አገልግሎት በጣም ይከብደኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ላከናውናቸው እንደማልችል የሚሰሙኝ የተለያዩ ኃላፊነቶች ተሰጥተውኛል። ፍርሃቴን እንዳሸንፍና ለ58 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል ግሩም በረከቶች እንዳገኝ ከረዱኝ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች መካከል ስለ አንዳንዶቹ እስቲ ልንገራችሁ።

የተወለድኩት ፈረንሳይኛ በሚነገርበት የኩዊቤክ ግዛት ውስጥ ባለችው በኩዊቤክ ሲቲ ነው። ሉዊ እና ዚሊያ የተባሉት ወላጆቼ በፍቅር ተንከባክበው አሳድገውኛል። አባቴ በተፈጥሮው ቁጥብ ሰው ሲሆን ማንበብ ይወድ ነበር። እኔ ደግሞ መጻፍ ስለሚያስደስተኝ ሳድግ ጋዜጠኛ ለመሆን እመኝ ነበር።

አሥራ ሁለት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ የአባቴ የሥራ ባልደረባ የሆነ ሩዶልፍ ሱሲ የተባለ ሰው ከጓደኛው ጋር ቤታችን መጣ። እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። በወቅቱ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙም አላውቅም ነበር፤ ስለ ሃይማኖታቸው ለማወቅም ፍላጎት አልነበረኝም። ያም ቢሆን ለጥያቄዎቻችን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ መስጠታቸው አስገርሞኝ ነበር። ወላጆቼም ይህ ስለማረካቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንድናጠና የቀረበልንን ግብዣ ተቀበልን።

በወቅቱ የምማረው በካቶሊክ ትምህርት ቤት ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ላይ ስለምማራቸው ነገሮች አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች ጋር አንዳንድ ጊዜ እወያይ ነበር። ቄሶች የነበሩት አስተማሪዎቻችን ውሎ አድሮ ይህን አወቁ። ከቄሶቹ አንዱ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሞ የተናገርኩት ነገር ስህተት መሆኑን ከማስረዳት ይልቅ ዓመፀኛ እንደሆንኩ በተማሪዎቹ ሁሉ ፊት ተናገረ! ይህ ገጠመኝ አስጨናቂ ቢሆንም ለበጎ ሆነልኝ፤ ምክንያቱም ትምህርት ቤቱ የሚያስተምራቸው ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደማይስማሙ እንድገነዘብ ረድቶኛል። ከዚህ ትምህርት ቤት መውጣት እንዳለብኝ ገባኝ። በመሆኑም ወላጆቼን አስፈቀድኩና ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ተዛወርኩ።

አገልግሎትን መውደድ የቻልኩት እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን ብቀጥልም መንፈሳዊ እድገቴ አዝጋሚ ነበር፤ ምክንያቱም ከቤት ወደ ቤት ማገልገል እፈራ ነበር። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ተሰሚነት የነበራት ሲሆን የስብከቱ ሥራችንን አጥብቃ ትቃወም ነበር። የኩዊቤክ አስተዳዳሪ የሆነው ሞሪስ ዱፕሌሲ ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ነበረው። እሱ ይደግፋቸው የነበሩ ረብሸኛ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ያስቸግሩ አልፎ ተርፎም ጥቃት ይሰነዝሩባቸው ነበር። በዚያ ወቅት በስብከቱ ሥራ መካፈል ትልቅ ድፍረት ይጠይቅ ነበር።

ፍርሃቴን እንዳሸንፍ የረዳኝ፣ ጆን ሬ የተባለ የዘጠነኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት ተመራቂ የሆነ ወንድም ነው። ብዙ ተሞክሮ ያካበተው ይህ ወንድም ገር፣ ትሑትና በቀላሉ የሚቀረብ ነው። በቀጥታ የመከረኝ ከስንት አንዴ ቢሆንም ግሩም ምሳሌነቱ ብዙ አስተምሮኛል። ጆን ፈረንሳይኛ መናገር ስለሚከብደው ብዙ ጊዜ አብሬው አገልግሎት በመውጣት በቋንቋ አግዘው ነበር። ከእሱ ጋር ጊዜ ማሳለፌ በድፍረት ከእውነት ጎን ለመቆም እንድወስን ረድቶኛል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከተገናኘሁ ከአሥር ዓመት በኋላ ይኸውም ግንቦት 26, 1951 ተጠመቅሁ።

ጆን ሬ (ሀ)፣ እኔ (ለ)፤ ጆን ሬ የተወው ግሩም ምሳሌ ከቤት ወደ ቤት ለመስበክ የነበረኝን ፍርሃት እንዳሸንፍ ረድቶኛል

በኩዊቤክ ሲቲ ባለችው ትንሿ ጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች አቅኚዎች ነበሩ። የእነሱ መልካም ምሳሌነት እኔም አቅኚ እንድሆን አነሳሳኝ። በዚያን ጊዜ ከቤት ወደ ቤት ስንሰብክ የምንጠቀመው መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ነበር። ጽሑፎችን ሳንጠቀም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተማር ነበረብን። ይህም ለእውነት ጥብቅና ለመቆም የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እንዳውቅ ረድቶኛል። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስንም እንኳ ቢሆን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ከሌለው ለማንበብ ፈቃደኞች አልነበሩም።

በ1952 ሲሞን ፔትሪ የተባለች በጉባኤያችን ያለች ታማኝ እህት አገባሁ። ከዚያም ወደ ሞንትሪያል የሄድን ሲሆን በተጋባን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊዝ የተባለችውን ልጃችንን ወለድን። ከማግባቴ ከጥቂት ጊዜ በፊት በአቅኚነት ማገልገሌን አቁሜ የነበረ ቢሆንም እኔና ሲሞን ቤተሰባችን በጉባኤ እንቅስቃሴዎች የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ እንዲችል አኗኗራችንን ቀላል ለማድረግ እንጥር ነበር።

አገልግሎቴን ይበልጥ ስለ ማስፋት በቁም ነገር ማሰብ የጀመርኩት ከአሥር ዓመት በኋላ ነበር። በ1962 ካናዳ ቤቴል ውስጥ ለሽማግሌዎች በተዘጋጀውና አንድ ወር በሚቆየው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ተካፈልኩ፤ በዚያ ወቅት እንድኖር የተመደብኩት ከሚል ዋሌት ከተባለ ወንድም ጋር ነበር። ከሚል ለአገልግሎት የነበረው ቅንዓት በጣም አስገረመኝ፤ በተለይ ደግሞ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ሆኖ እንዲህ ያለ ቅንዓት ማሳየቱ የሚገርም ነበር። ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ኩዊቤክ ውስጥ ልጆች እያሳደጉ አቅኚ መሆን ጨርሶ ያልተለመደ ነበር፤ ከሚል ግን ይህን የማድረግ ግብ ነበረው። አብረን በኖርንበት ጊዜ ከሚል ስላለሁበት ሁኔታ እንዳስብበት አበረታታኝ። ከጥቂት ወራት በኋላ፣ እንደገና አቅኚ ሆኜ ለማገልገል ወሰንኩ። አንዳንዶች በውሳኔዬ ላይ ጥያቄ ቢያነሱም እኔ ግን ይሖዋ አገልግሎቴን ለማስፋት የማደርገውን ጥረት እንደሚባርከው በመተማመን በውሳኔዬ ጸናሁ።

ልዩ አቅኚዎች ሆነን ወደ ኩዊቤክ ሲቲ ተመለስን

በ1964 እኔና ሲሞን የትውልድ ከተማችን በሆነችው በኩዊቤክ ሲቲ ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል ተመደብን፤ በዚያም ለዓመታት አገልግለናል። በዚህ ወቅት ከአገልግሎት አንጻር ሁኔታዎች ቢሻሻሉም ተቃውሞ ያጋጥመን ነበር።

አንድ ቅዳሜ ከሰዓት ከኩዊቤክ ሲቲ ብዙም በማትርቅ ሳንት መሪ የተባለች ትንሽ ከተማ ሳገለግል አንድ ፖሊስ ያዘኝ። ፖሊሱ ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ የሰበክሁት ያለፈቃድ እንደሆነ በመግለጽ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስዶ አሰረኝ። ከዚያም ባያርዦን የተባለ የሚያስፈራ ዳኛ ፊት ቀረብኩ። ዳኛው ጠበቃዬ ማን እንደሆነ ጠየቀኝ። የታወቀ የይሖዋ ምሥክሮች ጠበቃ የሆነው ግሌን ሃው * እንደሆነ ስነግረው “ውይ፣ እሱስ ባልሆነ!” ሲል በመረበሽ ስሜት ተናገረ። በዚያ ወቅት ግሌን ሃው ለይሖዋ ምሥክሮች ጥብቅና በመቆም ባስገኛቸው ድሎች ይታወቅ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ፍርድ ቤቱ ክሱ እንደተነሳልኝ ነገረኝ።

በኩዊቤክ በሥራችን ላይ በነበረው ተቃውሞ የተነሳ ተስማሚ የመሰብሰቢያ ቦታዎችን ለመከራየትም እንቸገር ነበር። ለትንሿ ጉባኤያችን ማግኘት የቻልነው የመሰብሰቢያ ቦታ አንድ ያረጀና ማሞቂያ የሌለው መጋዘን ነበር። በጣም በሚበርደው የቅዝቃዜ ወቅት ወንድሞች ክፍሉን ለማሞቅ ትንሽ ማሞቂያ ይጠቀሙ ነበር። ብዙውን ጊዜ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት በማሞቂያዋ ዙሪያ ተሰባስበን የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን በማውራት የተወሰኑ ሰዓታት እናሳልፍ ነበር።

ባለፉት ዓመታት የስብከቱ ሥራ ምን ያህል እያደገ እንደሄደ መመልከቱ አስደሳች ነው። በ1960ዎቹ ዓመታት በኩዊቤክ ሲቲ አካባቢ፣ በኮት ኖርት ክልል እና በጋስፔ ልሳነ ምድር በአጠቃላይ የነበሩት ጥቂት ትናንሽ ጉባኤዎች ብቻ ናቸው። ዛሬ በእነዚህ አካባቢዎች ከሁለት ወረዳ የሚበልጡ አስፋፊዎች የሚገኙ ሲሆን ወንድሞች በሚያማምሩ የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ይሰበሰባሉ።

በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ እንድንካፈል ተጋበዝን

በ1977 ቶሮንቶ፣ ካናዳ ውስጥ ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ተካፍያለሁ

በ1970 እኔና ሲሞን በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ተጋበዝን። ከዚያም በ1973 በአውራጃ ሥራ እንድናገለግል ተመደብን። በእነዚያ ዓመታት ውስጥ፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ከነበሩት እንደ ሎርየ ሶሙየር * እና ዴቪድ ስፕሌን * ካሉ ብቃት ያላቸው ወንድሞች ብዙ ተምሬያለሁ። ከእያንዳንዱ የወረዳ ስብሰባ በኋላ እኔና ዴቪድ የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል ስለምንችልበት መንገድ አንዳንድ ሐሳቦች እንለዋወጥ ነበር። በአንድ ወቅት ዴቪድ እንዲህ እንዳለኝ ትዝ ይለኛል፦ “ሊዮንስ የመደምደሚያ ንግግርህን ወድጄዋለሁ። ጥሩ ነበር፤ እኔ ብሆን ግን በንግግርህ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ሦስት የተለያዩ ንግግሮች አደርገው ነበር!” በንግግሮቼ ውስጥ ብዙ መረጃ የማጨቅ ልማድ ነበረኝ። እጥር ምጥን ያለ ንግግር መስጠትን መማር ነበረብኝ።

በካናዳ ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች አገልግያለሁ

የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች የሚመደቡት የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን እንዲያበረታቱ ነበር። በኩዊቤክ ከነበሩት ከብዙዎቹ አስፋፊዎች ጋር በደንብ እንተዋወቅ ነበር። በመሆኑም ወረዳዎችን በምጎበኝበት ወቅት ብዙውን ጊዜ አብረውኝ ማገልገል ይፈልጋሉ። ከእነሱ ጋር ማገልገል ቢያስደስተኝም ለወረዳ የበላይ ተመልካቹ በቂ ጊዜ እየሰጠሁ አልነበረም። በአንድ ወቅት አንድ አፍቃሪ የወረዳ የበላይ ተመልካች “ለወንድሞች ጊዜ መስጠትህ ጥሩ ነው፤ ሆኖም ይህ የእኔ ሳምንት መሆኑን አትርሳ። እኔም ማበረታቻ ያስፈልገኛል!” አለኝ። ይህ ደግነት የተንጸባረቀበት ምክር ይበልጥ ሚዛናዊ እንድሆን ረድቶኛል።

በ1976 ያልተጠበቀ አሳዛኝ ሁኔታ አጋጠመኝ። ውዷ ባለቤቴ ሲሞን በጠና ታመመችና በሞት አንቀላፋች። የራሷን ጥቅም መሥዋዕት የምታደርግና ይሖዋን የምትወድ በመሆኗ ጥሩ አጋር ሆናኛለች። በአገልግሎት ራሴን ማስጠመዴ፣ እሷን ማጣቴ ያስከተለብኝን ሐዘን ለመቋቋም በጣም ረድቶኛል፤ ይሖዋንም በዚህ ከባድ ጊዜ ላደረገልኝ ፍቅራዊ ድጋፍ በጣም አመሰግነዋለሁ። በኋላ ላይ ካሮሊን ኤሊየት የተባለች እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆነች ቀናተኛ እህት አገባሁ፤ አቅኚ የሆነችው ካሮሊን ወደ ኩዊቤክ የመጣችው ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ነው። ካሮሊን በቀላሉ የምትቀረብና ለሌሎች በተለይም ዓይናፋር ወይም ብቸኛ ለሆኑ ሰዎች ከልብ የምታስብ እህት ናት። በጉብኝት ሥራ ላይ አብራኝ መካፈሏ ትልቅ በረከት ሆኖልኛል።

ወሳኝ ዓመት

ጥር 1978 በኩዊቤክ በተካሄደው የመጀመሪያው የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ እንዳስተምር ተመደብኩ። ትምህርቱ ለተማሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ለእኔም አዲስ በመሆኑ በጣም ተጨንቄ ነበር። ደስ የሚለው ነገር ባስተማርኩት የመጀመሪያ ክፍል ላይ፣ ልምድ ያካበቱ ብዙ አቅኚዎች ነበሩ። አስተማሪ ብሆንም ከተማሪዎቹ ብዙ ተምሬያለሁ!

በ1978 “ድል አድራጊ እምነት” የሚል ብሔራት አቀፍ ስብሰባ በሞንትሪያል ኦሎምፒክ ስታዲየም ተካሄዶ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ከ80,000 የሚበልጡ ሰዎች የተገኙ ሲሆን በኩዊቤክ ከተደረጉ ስብሰባዎች ሁሉ ትልቁ ይህ ነው። በስብሰባው የዜና አገልግሎት ክፍል ውስጥ እንድሠራ ተመድቤ ነበር። ከበርካታ ጋዜጠኞች ጋር የተነጋገርኩ ሲሆን የመገናኛ ብዙኃን አዎንታዊ ነገር በመዘገባቸው ተደስቻለሁ። ስብሰባውን በተመለከተ ከእኛ ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን የያዘ ከ20 ሰዓት የሚበልጥ ፕሮግራም በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ተላልፏል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ርዕሶችም ታትመዋል። በዚህ የተነሳም አስደናቂ ምሥክርነት መስጠት ተችሏል!

ወደ ሌላ ክልል መዛወር

በ1996 ትልቅ ለውጥ አጋጠመኝ። ከተጠመቅኩበት ጊዜ አንስቶ ያገለገልኩት ፈረንሳይኛ በሚነገርበት በኩዊቤክ ነበር፤ በዚህ ዓመት ግን በቶሮንቶ አካባቢ በሚገኝ እንግሊዝኛ የሚነገርበት አውራጃ ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ። ብቃት እንደሌለኝ የተሰማኝ ከመሆኑም ሌላ በተሰባበረ እንግሊዝኛዬ ንግግር መስጠት በጣም አስፈርቶኝ ነበር። አዘውትሬ መጸለይና ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን አስፈልጎኛል።

መለስ ብዬ ሳስበው በቶሮንቶ አካባቢ ስላሳለፍናቸው ሁለት ግሩም ዓመታት ጥሩ ትዝታ አለኝ። ካሮሊን የእንግሊዝኛ ችሎታዬን እንዳሻሽል በትዕግሥት ረድታኛለች፤ ወንድሞችም ቢሆን በጣም ይደግፉኝና ያበረታቱኝ ነበር። በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ወዳጆች አፍርተናል።

ቅዳሜና እሁድ ከሚደረገው ትልቅ ስብሰባ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ሥራዎችን ማከናወንና ለስብሰባው ዝግጅት ማድረግ ቢኖርብኝም ዓርብ ምሽት ላይ ብዙውን ጊዜ ለአንድ ሰዓት ያህል ከቤት ወደ ቤት አገለግል ነበር። አንዳንዶች በሳምንቱ መጨረሻ በሚካሄደው ስብሰባ የተነሳ ፕሮግራሜ የተጣበበ ሆኖ ሳለ አገልግሎት መውጣቴ አስገርሟቸው ይሆናል። ሆኖም በአገልግሎት ጥሩ ውይይት አድርጌ ስመለስ መንፈሴ ይታደስ ነበር። አሁንም ድረስ በመስክ አገልግሎት መካፈል ምንጊዜም በጣም ያስደስተኛል።

በ1998 እኔና ካሮሊን በሞንትሪያል ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል ተመደብን። ለተወሰኑ ዓመታት፣ የተሰጠኝ ምድብ ልዩ የአደባባይ ምሥክርነትን ማደራጀትን እንዲሁም ሕዝቡ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ያለውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያስተካክል ለመርዳት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር መሥራትን ይጨምር ነበር። በአሁኑ ጊዜ እኔና ካሮሊን በቅርቡ ወደ ካናዳ ለመጡ የሌላ አገር ሰዎች እንሰብካለን፤ እነዚህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መማር ያስደስታቸዋል።

ከባለቤቴ ከካሮሊን ጋር

ከተጠመቅኩ አንስቶ ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍኳቸውን 68 ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ በእጅጉ እንደተባረክሁ ይሰማኛል። አገልግሎትን ለመውደድ ጥረት በማድረጌ እንዲሁም በርካታ ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ በመርዳቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ልጄ ሊዝና ባለቤቷ ልጆቻቸውን ካሳደጉ በኋላ የዘወትር አቅኚዎች ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ለአገልግሎት ያላት ቅንዓት ሳይቀዘቅዝ እንደቀጠለ መመልከቴ የደስታ ምንጭ ሆኖልኛል። ግሩም ምሳሌ በመሆንና ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር በመስጠት በመንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ እንዲሁም የተለያዩ ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን መወጣት እንድችል ለረዱኝ የእምነት ባልንጀሮቼ በጣም አመስጋኝ ነኝ። በምድባችን ላይ በታማኝነት መጽናት የምንችለው ኃያል በሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ስንታመን ብቻ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። (መዝ. 51:11) ይሖዋ የእሱን ስም የማወደስ ውድ መብት ስለሰጠኝ እሱን ማመስገኔን እቀጥላለሁ!—መዝ. 54:6

^ አን.16 በሚያዝያ 22, 2000 ንቁ! ከገጽ 18-24 (እንግሊዝኛ) ላይ “ውጊያው የአምላክ እንጂ የእናንተ አይደለም” በሚል ርዕስ የወጣውን የግሌን ሃውን የሕይወት ታሪክ ተመልከት።

^ አን.20 በኅዳር 15, 1976 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ “ብታገልለት የማያስቆጭ ነገር አገኘሁ” በሚል ርዕስ የወጣውን የሎርየ ሶሙየርን የሕይወት ታሪክ ተመልከት።

^ አን.20 ዴቪድ ስፕሌን የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል ሆኖ እያገለገለ ነው።