በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 3

የሰዎችን ሕይወት የሚያሻሽል ጠቃሚ ምክር

የሰዎችን ሕይወት የሚያሻሽል ጠቃሚ ምክር

እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ ለማሰብ ሞክር፤ አንተ ወዳለህበት አካባቢ ተዛውሮ የመጣ አንድ አዲስ ሐኪም አለ። መጀመሪያ ላይ ጥሩ ሐኪም ስለ መሆኑ ትጠራጠር ይሆናል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጓደኞችህ ይህ ሐኪም ባደረገላቸው እርዳታ ጤንነታቸው በሚገርም ሁኔታ ቢሻሻልስ? አንተም ወደዚህ ሐኪም ለመሄድ አትነሳሳም?

ቅዱሳን መጻሕፍትም ከዚህ ሐኪም ጋር የሚመሳሰሉባቸው መንገዶች አሉ። አንዳንድ ሰዎች፣ እነዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት ጠቃሚ ምክር የያዙ መሆናቸውን ይጠራጠራሉ። ይሁን እንጂ በቅዱሳን መጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር በተግባር ላይ ሲያውሉ ሕይወታቸው በሚገርም ሁኔታ ይሻሻላል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።

በትዳር ውስጥ የሚያጋጥምን ችግር መፍታት

ሱሚያቱን የተባለች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ከባለቤቴ ከዱማስ ጋር እንደተጋባን አካባቢ ችላ እንደሚለኝ ይሰማኝ ነበር። ብዙ ጊዜ በብስጭት እጮኽበት፣ ዕቃዎችን እወረውርበት አልፎ ተርፎም እመታው ነበር። አንዳንድ ጊዜ በጣም ከመናደዴ የተነሳ ራሴን ስቼ እወድቅ ነበር።

“ዱማስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጥናት ሲጀምር አሾፍኩበት። ይሁን እንጂ እሱ ሲያጠና ሌላ ክፍል ውስጥ ሆኜ በድብቅ አዳምጥ ነበር። አንድ ቀን አንድ ጥቅስ ሲነበብ ሰማሁ፤ ጥቅሱ ‘ሚስቶች ለጌታ እንደሚገዙ ሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ፤ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር’ ይላል። (ኤፌሶን 5:​22, 33) እነዚህ ቃላት ልቤን ነኩት። በባለቤቴ ላይ ለፈጸምኩት በደል ይቅር እንዲለኝ አምላክን ለመንኩት፤ እንዲሁም ጥሩ ሚስት እንድሆን እንዲረዳኝ ጸለይኩ። ብዙም ሳይቆይ ከዱማስ ጋር ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጥናት ጀመርኩ።”

ዱማስ እና ሱሚያቱን

በተጨማሪም ቅዱሳን መጻሕፍት “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል” ይላሉ። (ኤፌሶን 5:​28) ሱሚያቱን እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ ትምህርቶች በሁለታችንም ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ዱማስ ከሥራ ሲመለስ ሻይ አቀርብለት እንዲሁም በጥሩ መንፈስ አነጋግረው ጀመር። ዱማስም በበኩሉ ከበፊቱ ይበልጥ ፍቅር ያሳየኝ እንዲሁም የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት ያግዘኝ ጀመር። ሁለታችንም ‘አንዳችን ለሌላው ደጎችና ርኅሩኆች ለመሆን ብሎም በነፃ ይቅር ለመባባል’ ጥረት አደረግን። (ኤፌሶን 4:​32) በውጤቱም አንዳችን ለሌላው ያለን ፍቅርና አክብሮት እያደገ ሄደ። አሁን ከ40 ዓመት በላይ አስደሳች የትዳር ሕይወት አሳልፈናል። በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ትዳራችንን ታድጎልናል!”

ቁጣን መቆጣጠር

ታይብ “ቁጡ ነበርኩ” በማለት ይናገራል። “ብዙ ጊዜ እደባደብና ሰዎችን በሽጉጥ አስፈራራ ነበር። በምናደድበት ጊዜ ባለቤቴን ኩስትሪያንም ጭምር እመታትና መሬት ላይ እዘርራት ነበር። ብዙ ሰዎች ይፈሩኝ ነበር።

ኩስትሪያ እና ታይብ ማታ ማታ አብረው ይጸልያሉ

“አንድ ቀን ‘እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ’ የሚለውን ኢየሱስ (ኢሳ) የተናገረውን ጥቅስ አነበብኩ። (ዮሐንስ 13:​34) እነዚህ ቃላት ልቤን በጥልቅ ስለነኩኝ ለውጥ ለማድረግ ቆርጬ ተነሳሁ። ቁጣ ቁጣ ሲለኝ አምላክ እንዲያረጋጋኝ እጸልያለሁ። ንዴቴም ወዲያውኑ ይበርዳል። እኔና ባለቤቴ ‘ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ፤ ዲያብሎስ አጋጣሚ እንዲያገኝ አታድርጉ’ የሚለውን በኤፌሶን 4:​26, 27 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ አደረግን። ሁልጊዜ ማታ ማታ ቅዱሳን መጻሕፍትን አብረን እናነባለን እንዲሁም እንጸልያለን። ይህም በዕለቱ ያጋጠመንን ውጥረት እንድናስወግድና እርስ በርስ እንድንቀራረብ ረድቶናል።

“አሁን የምታወቀው ሰላማዊ ሰው በመሆኔ ነው። ባለቤቴና ልጆቼ ይወዱኛል እንዲሁም ያከብሩኛል። ብዙ ወዳጆች ያሉኝ ሲሆን ወደ አምላክ እንደቀረብኩም ይሰማኛል። በጣም ደስተኛ ነኝ።”

ከዕፅ ሱስ መላቀቅ

ጎይን

“የምውለው ረብሸኛ ከሆኑ ወጣቶች ጋር ነበር፤ እንዲሁም ከባድ አጫሽ የነበርኩ ሲሆን ብዙ ጊዜ ሰክሬ መንገድ ላይ አድር ነበር” ይላል ጎይን። “በተጨማሪም ማሪዋና እና ኤክስታሲ የተባሉ ሕገ ወጥ ዕፆችን በጥይት መከላከያ ሰደርያዬ ውስጥ እየደበቅሁ እጠቀምና እሸጥ ነበር። ሌሎች የሚያስቡኝና እኔም እንዲያዩኝ የምፈልገው ምንም የማይበግረኝ ሰው እንደሆንኩ አድርገው ቢሆንም ሁልጊዜ የምኖረው በፍርሃት ነበር።

“ከዚያም አንድ ሰው ‘ልጄ ሆይ፣ ትምህርቴን አትርሳ፤ . . . ረጅም ዕድሜና የሕይወት ዘመን እንዲሁም ሰላም ያስገኙልሃልና’ የሚለውን ጥቅስ አሳየኝ። (ምሳሌ 3:​1, 2) ረጅም ዕድሜና ሰላማዊ ሕይወት ማግኘት ተመኘሁ! በተጨማሪም ‘እነዚህ ተስፋዎች ስላሉን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እንዲሁም አምላክን በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ’ የሚለውን ጥቅስ አነበብኩ። (2 ቆሮንቶስ 7:⁠1) በመሆኑም ዕፅ መውሰዴን አቆምኩ፤ አብሬያቸው ከምውላቸው ወጣቶች ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋረጥሁ፤ እንዲሁም አምላክን ማገልገል ጀመርኩ።

“ከዕፅ ሱስ ከተላቀቅኩ አሁን ከ17 ዓመት በላይ ሆኖኛል። ጥሩ ጤንነት፣ ደስተኛ ቤተሰብ፣ ጥሩ ጓደኞችና ንጹሕ ሕሊና አለኝ። ደግሞም ሰክሬ በየመንገዱ ከማደር ይልቅ እያንዳንዱን ሌሊት በሰላም አልጋዬ ላይ ተኝቼ አድራለሁ።”

የዘር ጥላቻን ማሸነፍ

ባምባንግ እንዲህ ይላል፦ “በወጣትነቴ ዓመፀኛ ነበርኩ፤ ደግሞም አብዛኛውን ጊዜ ጥቃት የምፈጽመው እጠላቸው በነበሩ አንድ የአናሳ ጎሣ አባላት ላይ ነበር።

“ከጊዜ በኋላ ግን አምላክን መፈለግ ጀመርኩ። በአንድ ወቅት፣ ተሰብስበው ቅዱሳን መጻሕፍትን የሚያጠኑ ሰዎች ወዳሉበት አንድ የእምነት ቡድን ሄድኩ። እዚያም እጠላው የነበረው ጎሣ አባላት የሆኑ ሰዎች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ! በተጨማሪም በዚህ የእምነት ቡድን ውስጥ ያሉት ከተለያዩ ዘሮች የመጡ ሰዎች በነፃነትና በደስታ ተቀላቅለው እየኖሩ እንደሆነ ተመለከትሁ። በጣም ተገረምኩ! ከዚያም ‘አምላክ አያዳላም፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው’ የሚለውን ጥቅስ አስተዋልኩ።​—⁠የሐዋርያት ሥራ 10:​34, 35

“አሁን ልቤ በዘር ጥላቻ የተመረዘ አይደለም። በጣም ከምቀርባቸው ጓደኞቼ አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት እጠላው የነበረው ጎሣ አባላት ናቸው። አምላክ በቅዱስ መጽሐፉ አማካኝነት ፍቅርን አስተምሮኛል።”

ባምባንግ ከተለያየ ዘር የመጡ ጥሩ ጓደኞች አሉት

ዓመፀኝነትን መተው

ጋሮጋ እንዲህ ብሏል፦ “ወጣት ሳለሁ ሦስት ጊዜ ወኅኒ ቤት ገብቼ ነበር፤ ሁለት ጊዜ በስርቆት፣ አንድ ጊዜ ደግሞ ሰውን በጩቤ በመውጋቴ ታስሬ ነበር። በኋላም አንድ ዓማፂ ቡድን ውስጥ ገባሁና ብዙ ሰዎችን ገደልኩ። ግጭቱ ሲያቆም የአንድ ወንጀለኛ ቡድን መሪ በመሆን ቀማኞችንና ነጣቂዎችን ማሰማራት ጀመርኩ። ምንጊዜም የምንቀሳቀሰው የግል ጠባቂዎቼ አጅበውኝ ነበር። በጣም ዓመፀኛና አደገኛ ሰው ነበርኩ።

ጋሮጋ አሁን ዓመፀኛ ሳይሆን በሌሎች ዘንድ የተከበረ የአምላክ ቃል አስተማሪ

“ከዚያም አንድ ቀን እንዲህ የሚለውን ጥቅስ አነበብኩ፦ ‘ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም። ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣ ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣ በቀላሉ አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም።’ (1 ቆሮንቶስ 13:​4, 5) እነዚህ ቃላት ልቤን ነኩት። የመኖሪያ ሰፈር በመቀየር ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጥናት ጀመርኩ፤ እንዲሁም በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን ምክሮች በሕይወቴ ተግባራዊ አደረግሁ።

“አሁን ዓመፀኛ ሰው አይደለሁም። ከዚህ ይልቅ በሌሎች ዘንድ የተከበርኩ የአምላክ ቃል አስተ​ማሪ ነኝ። ሕይወቴ ትርጉም ያለውና አስደሳች ሆኗል።”

የአምላክ ቃል ኃይል አለው

እነዚህና ሌሎች በርካታ ተሞክሮዎች “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ” መሆኑን ያረጋግጣሉ። (ዕብራውያን 4:​12) ምክሩ ቀላል፣ ጠቃሚና ተስፋ ሰጪ ነው።

ቅዱሳን መጻሕፍት አንተንም ሊረዱህ ይችላሉ? አዎ፣ ያጋጠመህ ችግር ምንም ይሁን ምን ሊረዱህ ይችላሉ። “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመገሠጽ ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የአምላክ ሰው ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።”​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17

እንግዲያው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ መሠረታዊ ትምህርቶች እንመልከት።