በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | ትዳር

መጨቃጨቅ ማቆም የምትችሉት እንዴት ነው?

መጨቃጨቅ ማቆም የምትችሉት እንዴት ነው?

ተፈታታኙ ነገር

ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በረጋ መንፈስ መነጋገር ከብዷችኋል? ፈንጂ በተቀበረበትና አንድ እርምጃ ብትራመዱ ሊፈነዳ በሚችልበት ቦታ የምትጓዙ ያህል፣ ‘አንድ ነገር ብናገር ወይም ባደርግ ከትዳር ጓደኛዬ ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ እገባለሁ’ የሚለው ስጋት ያስጨንቃችኋል?

ከሆነ ነገሮች ሊሻሻሉ እንደሚችሉ እርግጠኛ ሁኑ። ሆኖም በመጀመሪያ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ይህን ያህል የምትጨቃጨቁት ለምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋችኋል።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

አለመግባባት።

ጂሊያን * የምትባል አንዲት ባለትዳር እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ለባለቤቴ የሆነ ነገር እነግረዋለሁ፤ ሆኖም የምነግረው ባሰብኩት መንገድ ላይሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ነገሩን ሳልነግረው የነገርኩት የሚመስለኝ ጊዜ አለ፤ ለካስ የነገርኩት በሕልሜ ነው። ይህ በእውነት እኔ ላይ የደረሰ ነገር ነው!”

ልዩነት።

ከትዳር ጓደኛህ ጋር የቱንም ያህል ብትጣጣሙ አንዳንድ ጊዜ አመለካከታችሁ ሊለያይ ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ሁለት ሰዎች ፍጹም አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ሊኖራቸው አይችልም፤ ይህ ልዩነት ትዳር ጣዕም ያለው አሊያም ውጥረት የነገሠበት እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። ለብዙ ባለትዳሮች ግን የአመለካከት ልዩነት ውጥረት ፈጥሮባቸዋል።

የወላጆች መጥፎ ምሳሌነት።

ሬቸል የተባለች አንዲት ባለትዳር እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ብዙ ጊዜ ይጨቃጨቃሉ፤ በዚያ ላይ ደግሞ አንዳቸው ስለሌላው አክብሮት የጎደለው አስተያየት ይሰጣሉ። በመሆኑም እኔም ካገባሁ በኋላ ባለቤቴን የማናግረው እናቴ አባቴን በምታናግርበት መንገድ ነበር። እንዴት አክብሮት ማሳየት እንዳለብኝ አልተማርኩም።”

ከበስተጀርባ ያሉ መንስኤዎች።

ብዙውን ጊዜ ለጦፈ ጭቅጭቅ መንስኤ የሚሆነው ነገር በወቅቱ የተነሳው ጉዳይ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ “ሁልጊዜ እንዳረፈድሽ ነው!” በማለት ክርክር ቢጀመር መንስኤው በጊዜ የመድረስ ጉዳይ ላይሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ አንደኛው የትዳር ጓደኛ ችላ እንደተባለ ተሰምቶት ይሆናል።

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ነጋ ጠባ የምትጨቃጨቁ ከሆነ ጤንነታችሁ ሊቃወስ ይችላል፤ አልፎ ተርፎም ሁኔታው ከጊዜ በኋላ ወደ ፍቺ ሊያመራችሁ ይችላል። ታዲያ መጨቃጨቅ ማቆም የምትችሉት እንዴት ነው?

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ጭቅጭቅን ለመከላከል ቁልፉ ትክክለኛውን መንስኤ ለይቶ ማወቅ ነው። በተረጋጋችሁበት ጊዜ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ሆናችሁ ቀጥሎ የቀረበውን መልመጃ ለመሥራት ሞክሩ።

1. ሁለታችሁም በቅርቡ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር የተጨቃጨቃችሁበትን አንድ ነገር ወረቀት ላይ ጻፉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ባል “ቀኑን ሙሉ ከጓደኞችሽ ጋር ስታሳልፊ የት እንደነበርሽ እንኳ ደውለሽ አልነገርሽኝም” ብሎ ሊጽፍ ይችላል። አንዲት ሚስት ደግሞ “ከጓደኞቼ ጋር ጊዜ በማሳለፌ ተበሳጨህ” ብላ ትጽፍ ይሆናል።

2. አስተሳሰባችሁን ሰፋ በማድረግ በሚከተሉት ነገሮች ላይ ተወያዩ፦ ጉዳዩ በእርግጥ ያን ያህል ከባድ ነበር? ችላ ተብሎ ሊታለፍ ይችል ነበር? አንዳንድ ጊዜ ለሰላም ሲባል በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከት ሊኖረን እንደሚችል አምኖ መቀበሉ እንዲሁም ጉዳዩን በፍቅር መሸፈኑ የተሻለ ይሆናል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 17:9

አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ ጉዳዩ ከቁብ የማይቆጠር ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ከደረሳችሁ ይቅርታ ተጠያየቁ፤ ከዚያም ስለ ጉዳዩ መነጋገርም ሆነ ማብሰልሰል አቁሙ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ቆላስይስ 3:13, 14

ከሁለት አንዳችሁ ጉዳዩ ትንሽ ከበድ ያለ እንደሆነ ከተሰማችሁ ቀጥሎ ያለውን እርምጃ ውሰዱ።

3. በጭቅጭቁ ወቅት ምን እንደተሰማህ ጻፍ፤ የትዳር ጓደኛህም እንድትጽፍ ንገራት። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ባል “ከእኔ ጋር ከመሆን ይልቅ ከጓደኞችሽ ጋር መሆን ያስደስትሻል” ብሎ ሊጽፍ ይችላል። ሚስትየዋ ደግሞ “ሁልጊዜ አባቷን ማስፈቀድ እንዳለባት ሕፃን እንደምትቆጥረኝ ይሰማኛል” ብላ ትጽፍ ይሆናል።

4. ከትዳር ጓደኛህ ጋር ወረቀቶቹን በመለዋወጥ አንዳችሁ ስለ ሌላው የጻፋችሁትን አስተያየት አንብቡ። በጭቅጭቁ ወቅት የትዳር ጓደኛህን በእርግጥ ያሳሰባት ነገር ምንድን ነው? እያንዳንዳችሁ በበኩላችሁ ለጭቅጭቁ ትክክለኛ መንስኤ የሆነውን ነገር በሰላም ለመፍታት ምን ማድረግ ትችሉ እንደነበር ተወያዩ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 29:11

5. ከዚህ መልመጃ ምን ትምህርት እንዳገኛችሁ ተወያዩ። ከመልመጃው ያገኛችሁትን ትምህርት ወደፊት የሚነሱ ጭቅጭቆችን ለመፍታት ወይም ለመከላከል ልትጠቀሙበት የምትችሉት እንዴት ነው?

^ አን.7 ስሞቹ ተቀይረዋል።