በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ፍቅር እርዳታ ለመስጠት ያነሳሳናል

አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ፍቅር እርዳታ ለመስጠት ያነሳሳናል

በአስቸጋሪ ጊዜያት የይሖዋ ምሥክሮች ለእምነት ባልንጀሮቻቸውም ሆነ ለሌሎች ሰዎች እርዳታ ይሰጣሉ። ይህን ለማድረግ የሚያነሳሳቸው፣ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነው ፍቅር ነው።—ዮሐንስ 13:35

የይሖዋ ምሥክሮች፣ እስከ 2012 አጋማሽ ባሉት 12 ወራት ውስጥ በተለያዩ አገራት ከሰጡት እርዳታ መካከል የተወሰነው ከዚህ በታች ተዘርዝሯል። እርዳታ ስንሰጥ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎትም ለማሟላት ምንጊዜም ጥረት እናደርጋለን፤ በእርግጥ ከታች ያለው ዝርዝር በዚህ ረገድ ያደረግነውን ጥረት አይገልጽም። እርዳታውን በአብዛኛው የሚያስተባብሩት፣ ቅርንጫፍ ቢሮዎቻችን ያቋቋሟቸው የእርዳታ ሰጪ ኮሚቴዎች ናቸው። አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙት ጉባኤዎችም እርዳታ በመስጠቱ ሥራ አዘውትረው ይካፈላሉ።

ጃፓን

ጃፓን፦ መጋቢት 11, 2011 የጃፓን ሰሜናዊ ክፍል በምድር መናወጥና ይህን ተከትሎ በተከሰተ ሱናሚ የተመታ ሲሆን አደጋው በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል። በመላው ዓለም የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋው የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም፣ ገንዘብና ቁሳቁሶችን በልግስና የሰጡ ከመሆኑም ሌላ በሙያቸው እገዛ አበርክተዋል።

ብራዚል፦ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በመሬት መንሸራተትና በጭቃ ናዳ የተነሳ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋው ወደተጠቃው አካባቢ 42 ቶን ቶሎ የማይበላሹ ምግቦችን፣ 20,000 ጠርሙስ ውኃ፣ 10 ቶን አልባሳት፣ 5 ቶን የጽዳት ዕቃዎች እንዲሁም መድኃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ልከዋል።

ኮንጎ (ብራዛቪል)፦ በአንድ የጦር መሣሪያዎች ማከማቻ ቦታ ላይ በደረሰ ፍንዳታ የ4 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች የወደሙ ሲሆን የሌሎች 28 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአደጋው ለተጎዱት ምግብና ልብስ ተሰጥቷል፤ እንዲሁም በአካባቢው ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች በቤታቸው ተቀብለዋቸዋል።

ኮንጎ (ኪንሻሳ)፦ በኮሌራ ለተጠቁት መድኃኒት ተከፋፍሏል። ኃይለኛ ዝናብ በመጣሉ የተነሳ የተከሰተው ጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ደግሞ አልባሳት ተሰጥቷል። በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች የሕክምና እርዳታ፣ ለዘር የሚሆን እህል እንዲሁም ብዙ ቶን የሚመዝን ልብስ ተሰጥቷል።

ቬኔዙዌላ፦ ኃይለኛ ዝናብ በመጣሉ የጎርፍ መጥለቅለቅና የጭቃ ናዳ ተከስቷል። የአደጋ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴዎች በአደጋው የተጠቁ 288 የይሖዋ ምሥክሮችን ረድተዋል። ከ50 በላይ አዳዲስ ቤቶች ተሠርተዋል። በተጨማሪም የእርዳታ ኮሚቴዎቹ፣ የቫሌንሲያ ሐይቅ የውኃ መጠን ከፍ እያለ በመምጣቱ ሳቢያ ቤታቸው ለአደጋ የተጋለጠባቸውን ሰዎች እየረዱ ነው።

ፊሊፒንስ

ፊሊፒንስ፦ በኃይለኛ አውሎ ነፋስ ምክንያት የተወሰነው የአገሪቱ ክፍል በጎርፍ ተጥለቀለቀ። ቅርንጫፍ ቢሮው በአደጋው ለተጎዱት ሰዎች ምግብና አልባሳት የላከ ሲሆን በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም የጎርፉ መጠን ከቀነሰ በኋላ አካባቢውን በማጽዳት ሥራ ተካፍለዋል።

ካናዳ፦ በአልበርታ ከተነሳው ኃይለኛ ሰደድ እሳት በኋላ፣ የስሌቭ ሌክ ጉባኤን በጽዳቱ ሥራ ለማገዝ ሲሉ በዚያ አካባቢ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ መጠን ያለው መዋጮ ልከዋል። ጉባኤው የተላከለት ገንዘብ ለሥራው ከሚያስፈልገው በላይ በመሆኑ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ገንዘብ፣ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚገኙ በአደጋ የተጠቁ ሰዎችን ለመርዳት እንዲውል ልኮታል።

ኮት ዲቩዋር፦ በአገሪቱ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት፣ በጦርነት ትታመስ በነበረችበት ወቅት እንዲሁም ከጦርነቱ በኋላ፣ ለተቸገሩት ሰዎች የሚሆን ቁሳቁስ፣ መጠለያ እንዲሁም የሕክምና እርዳታ ተሰጥቷል።

ፊጂ፦ ዶፍ ዝናብ በመጣሉ የተነሳ በተከሰተው ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ 192 የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ፣ የምግብና የገቢ ምንጫቸው የሆነውን እርሻቸውን አጥተዋል። በመሆኑም ምግብ በእርዳታ ተሰጥቷቸዋል።

ጋና፦ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ለሚገኙ በጎርፍ የተጠቁ ሰዎች ምግብና ዘር ተሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም ቤታቸው ለፈረሰባቸው ምትክ የሚሆን መኖሪያ ተዘጋጅቶላቸዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ፦ ውሽንፍር የቀላቀለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ፣ በሦስት ግዛቶች በሚገኙ 66 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን 12 ቤቶች ደግሞ ወድመዋል። አብዛኞቹ ቤቶች ኢንሹራንስ የነበራቸው ቢሆንም የቤቶቹን ባለቤቶች በመልሶ ማቋቋሙ ሥራ ለማገዝ ሲባል የገንዘብ እርዳታ ተሰጥቷል።

አርጀንቲና፦ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች፣ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የሚገኙትን ቤታቸው በእሳተ ጎሞራ አመድ የተጎዳባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ረድተዋቸዋል።

ሞዛምቢክ፦ በድርቅ ለተጎዱ ከ1,000 የሚበልጡ ሰዎች ምግብ ተከፋፍሏል።

ናይጄርያ፦ በከባድ የአውቶቡስ አደጋ ምክንያት ለተጎዱ ከ20 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። በዘርና በሃይማኖት ልዩነት ሳቢያ በተነሳ ብጥብጥ ምክንያት ቤታቸውን ላጡ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙ በርካታ ሰዎችም ድጋፍ ተሰጥቷል።

ቤኒን፦ በከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች መድኃኒት፣ አልባሳት፣ የወባ መከላከያ አጎበርና ንጹሕ ውኃ የተከፋፈለ ከመሆኑም ሌላ መጠለያ ተዘጋጅቶላቸዋል።

ዶሚኒካን ሪፑብሊክ

ዶሚኒካን ሪፑብሊክ፦ በዚያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች፣ አይሪን ተብሎ በተሰየመው ከባድ አውሎ ነፋስ የተጎዱ ቤቶችን በመጠገንና የቁሳቁስ እርዳታ በመስጠቱ ሥራ ተካፍለዋል።

ኢትዮጵያ፦ በድርቅ በተጎዱ ሁለት ቦታዎች እንዲሁም የጎርፍ መጥለቅለቅ በደረሰበት አካባቢ ለሚገኙ በአደጋው የተጠቁ ሰዎች የገንዘብ እርዳታ ተደርጓል።

ኬንያ፦ በድርቅ ለተጎዱ ሰዎች የእርዳታ ገንዘብ ተልኳል።

ማላዊ፦ በዘሌካ የስደተኞች መጠለያ ለሚኖሩት ሰዎች እርዳታ ተደርጓል።

ኔፓል፦ በመሬት መንሸራተት ምክንያት የአንዲት የይሖዋ ምሥክር ቤት ከባድ ጉዳት ደረሰበት። ጊዜያዊ መኖሪያ የተዘጋጀላት ከመሆኑ ሌላ በአካባቢው ያለው ጉባኤ አስፈላጊውን እርዳታ አድርጎላታል።

ፓፑዋ ኒው ጊኒ፦ ዓመፀኛ የሆኑ ሰዎች የስምንት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች አቃጠሉባቸው። ቤቶቹን መልሶ ለመገንባት ዝግጅት ተደርጓል።

ሩማኒያ፦ በጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ የአንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ጉዳት ስለደረሰባቸው ለመልሶ ግንባታው ሥራ እገዛ ተደርጓል።

ማሊ፦ በድርቅ ምክንያት ሰብላቸው ስለተበላሸባቸው ምግብ ለተቸገሩ ሰዎች፣ ጎረቤት አገር ከሆነችው ከሴኔጋል እርዳታ ተልኮላቸዋል።

ሴራ ሊዮን፦ ቀደም ሲል ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከፈረንሳይ የመጡ በሕክምና ሙያ ላይ የተሰማሩ የይሖዋ ምሥክሮች የሕክምና እርዳታ አድርገውላቸዋል።

ታይላንድ፦ ኃይለኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ በበርካታ ግዛቶች ውስጥ ከባድ ጉዳት አድርሷል። የእርዳታ ቡድኖች 100 ቤቶችንና 6 የመሰብሰቢያ አዳራሾችን በመጠገኑ እንዲሁም በማጽዳቱ ሥራ ተካፍለዋል።

ቼክ ሪፑብሊክ፦ በጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ የተወሰኑ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በአቅራቢያ ባለችው ስሎቫኪያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በእርዳታው ሥራ ተካፍለዋል።

ስሪ ላንካ፦ ሱናሚ ካደረሰው ጉዳት ጋር በተያያዘ የሚያስፈልገው አብዛኛው የእርዳታ ሥራ ተጠናቅቋል።

ሱዳን፦ በአገሪቱ በተነሳው ውጊያ ምክንያት ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉት የይሖዋ ምሥክሮች ምግብ፣ አልባሳት፣ ጫማዎችና የፕላስቲክ መሸፈኛዎች ተልኮላቸዋል።

ታንዛንያ፦ በደረሰው ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ 14 ቤተሰቦች ንብረታቸውን አጥተዋል። በአካባቢው የሚገኙት ጉባኤዎች አልባሳትና የቤት ውስጥ ዕቃዎችን ለግሰዋል። አንድ መኖሪያ ቤትም እንደገና ተገንብቷል።

ዚምባብዌ፦ በአገሪቱ ውስጥ በአንድ አካባቢ በድርቅ ሳቢያ ረሃብ ተከስቷል። በድርቅ ለተጠቁት ምግብና ገንዘብ ተሰጥቷል።

ቡሩንዲ፦ በዚያ የሚገኙት ስደተኞች ሕክምናን ጨምሮ ሌሎች እርዳታዎች እየተሰጧቸው ነው።