በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

የፈጠራ ችሎታን የሚያበረታቱ ጨዋታዎች ያላቸው ጥቅም

የፈጠራ ችሎታን የሚያበረታቱ ጨዋታዎች ያላቸው ጥቅም

 “የፈጠራ ችሎታን የሚያበረታቱ ጨዋታዎች” የሚባሉት የማወቅ ጉጉትን የሚቀሰቅሱና በዓይነ ሕሊና የመሳል ችሎታን የሚያጎለብቱ ጨዋታዎች ናቸው። እነዚህ ጨዋታዎች ለልጆች አእምሮ እድገት ይረዳሉ፤ እንዲሁም ክህሎት እንዲያዳብሩ ያግዛሉ።

 ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  •   ሥዕል መሣል

  •   ምግብ ማዘጋጀት

  •   ዕቃቃ መጫወት

  •   መዘመር

  •   መገጣጠም

  •   በቀላሉ ሊገኙ በሚችሉ ቁሳቁሶች መጫወት (እንደ ካርቶን ባለ ነገር እንኳን ተጠቅሞ መጫወት በዓይነ ሕሊና የመሳል ችሎታን ያሳድጋል)

 በብዙ አገሮች ውስጥ የፈጠራ ችሎታን የሚያበረታቱ ጨዋታዎች እየቀሩ መጥተዋል፤ ቁጭ ተብለው በሚታዩ መዝናኛዎች እንዲሁም ለልጆች ተብለው በሚደረጉ ዝግጅቶች ተተክተዋል።

 ይህ ጉዳይ ሊያሳስባችሁ ይገባል?

 ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

  •   የፈጠራ ችሎታን የሚያበረታቱ ጨዋታዎች ለአንድ ልጅ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ለአካላዊና ለአእምሯዊ ጤንነቱ ይጠቅማሉ፤ የፈጠራ ችሎታውን እንዲያሳድግና ለማኅበራዊ ሕይወቱ የሚጠቅሙ ክህሎቶችን እንዲያዳብር ይረዱታል። በተጨማሪም ልጆች ትዕግሥተኛ እንዲሆኑ ውሳኔ የማድረግ ችሎታቸው እንዲዳብር፣ ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩና ከሌሎች ልጆች ጋር ተስማምተው እንዲጫወቱ ይረዷቸዋል። በአጭር አነጋገር እነዚህ ጨዋታዎች ለአዋቂነት ዕድሜ ያዘጋጇቸዋል።

  •   በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ላይ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ጎጂ ሊሆን ይችላል። በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ላይ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ሱስ ሊያስይዝ ይችላል። እንዲህ ያለ ልማድ ባላቸው ልጆች ላይ ከልክ ያለፈ ውፍረትና የኃይለኝነት ባሕርይ ተስተውሏል። ልጆቻቸው አርፈው እንዲቀመጡላቸው ሲሉ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን የመክፈት ልማድ ያላቸው ወላጆች ይህን ጉዳይ ሊያስቡበት ይገባል።

  •   ለልጆች ተብለው በፕሮግራም የሚደረጉ ዝግጅቶች አሉታዊ ጎን አላቸው። እንዲህ ባሉ ዝግጅቶች ላይ፣ ልጆች የወጣላቸውን ፕሮግራም ተከተለው ከአንዱ ጨዋታ ወደ ሌላው ጨዋታ እንዲሄዱ ይጠበቅባቸዋል፤ ይህ ደግሞ የማወቅ ጉጉታቸውን ለማርካትና የፈጠራ ችሎታቸውን ለማዳበር በሚያስችሏቸው ጨዋታዎች ላይ እንደልብ ጊዜ እንዳያሳልፉ ያደርጋቸዋል።

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  •   የፈጠራ ችሎታን የሚያበረታቱ ጨዋታዎች እንዲጫወቱ አጋጣሚ ፍጠሩ። ሁኔታው የሚፈቅድ ከሆነ ልጆቻችሁ ውጭ ወጥተው እንዲጫወቱ አድርጉ፤ ይህም ከተፈጥሮ ጋር እንዲተዋወቁ ይረዳቸዋል። የፈጠራ ችሎታን የሚያዳብሩ ክህሎቶችን እንዲማሩና ለዚህ በሚያግዙ መጫወቻዎች እንዲጫወቱ አጋጣሚ ስጧቸው። a

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጄ የፈጠራ ችሎታን የሚያበረታቱ ጨዋታዎችን በመጫወት የትኞቹን ባሕርያትና ክህሎቶች ሊያዳብር ይችላል? ይህስ ለወደፊት ሕይወቱ የሚጠቅመው እንዴት ነው?

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ . . . ይጠቅማል።”—1 ጢሞቴዎስ 4:8

  •   ስክሪን ላይ በሚያሳልፉት ጊዜ ላይ ገደብ አብጁ። ልጃችሁ አርፎ እንዲቀመጥ ስትሉ ስልክ ወይም ታብሌት ከመስጠታችሁ ወይም ቴሌቪዥን ከመክፈታችሁ በፊት ቆም ብላችሁ አስቡ። የሕፃናት ሐኪሞች፣ ከሁለት ዓመት በታች ላሉ ልጆች እንዲህ ያሉ ነገሮች ፈጽሞ መከፈት እንደሌለባቸው ይመክራሉ፤ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ላሉ ልጆች ደግሞ፣ ስክሪን ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ በቀን ከአንድ ሰዓት መብለጥ እንደሌለበት ይናገራሉ። b

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጄ ስክሪን ላይ የሚያሳልፈውን ጊዜ በተመለከተ ምን ዓይነት ገደብ ባበጅ ጥሩ ነው? ልጄ የሚያየውን ነገር አብሬ ባይ ይሻል ይሆን? ከኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሌላ የተሻለ አማራጭ አለ?

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።”—ኤፌሶን 5:15, 16

  •   ለልጆች ተብለው የሚደረጉ ዝግጅቶችን በጥንቃቄ አስቡባቸው። እርግጥ ነው፣ ልጃችሁ አንድን ክህሎት እንዲያዳብር ወይም በአንድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ላይ ጥሩ ችሎታ እንዲኖረው ይረዱት ይሆናል። ብዙውን ጊዜ እንደሚታየው ግን፣ ልጆች እንዲህ ባሉ እንቅስቃሴዎች መጠመዳቸው ውጥረት ሊፈጥርባቸው ይችላል፤ በልጆቹ ላይ ብቻ ሳይሆን እነሱን በሚወስደውና በሚመልሰው ወላጅ ላይም ውጥረት ሊፈጥር ይችላል። በኤፌሶን 5:15, 16 ላይ ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት የተሰጠን ምክር እዚህ ላይም እንደሚሠራ የታወቀ ነው።

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የልጃችን ፕሮግራም ለልጆች ተብለው በሚዘጋጁ እንቅስቃሴዎች የተጣበበ ነው? ከሆነ ምን ማስተካከያ ማድረግ አለብን?

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10

a ገበያ ላይ ያሉ ብዙ መጫወቻዎች፣ የፈጠራ ችሎታን ለማዳበር የሚያግዙ አይደሉም። ከዚህ በተቃራኒ፣ ቀለል ያሉ መጫወቻዎች ወይም ቁሳቁሶች (ለምሳሌ የሚገጣጠሙ ነገሮች ወይም ካርቶኖች) ልጁ በዓይነ ሕሊናው የመሳል ችሎታውን እንዲጠቀምበት ያግዙታል።

b “ልጆች ስክሪን ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ” የተባለው መዝናኛዎች በማየት የሚያሳልፉት ጊዜ ነው፤ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ከወዳጅ ዘመድ ጋር በመነጋገር ወይም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው መንፈሳዊ ፕሮግራም በመከታተል የሚያሳልፉትን ጊዜ አይጨምርም።