በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ የማቴዎስ መጽሐፍ በአውስትራሊያ ምልክት ቋንቋ በወጣበት ወቅት ወንድሞችና እህቶች ሲያጨበጭቡ። በስተ ቀኝ፦ ወንድም ሂዴዩኪ ሞቶይ የማቴዎስ መጽሐፍ መውጣቱን በአስተርጓሚ እገዛ ሲያበስር

መጋቢት 13, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የማቴዎስ መጽሐፍ በአውስትራሊያ ምልክት ቋንቋ ወጣ

የማቴዎስ መጽሐፍ በአውስትራሊያ ምልክት ቋንቋ ወጣ

መጋቢት 2, 2024 በብሪዝበን፣ አውስትራሊያ በሚገኝ አንድ የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደ ልዩ ስብሰባ ላይ የአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሂዴዩኪ ሞቶይ የማቴዎስ መጽሐፍ በአውስትራሊያ ምልክት ቋንቋ ወይም በአውስላን መውጣቱን አበሰረ። በድምሩ 159 ወንድሞችና እህቶች በፕሮግራሙ ላይ በአካል ተገኝተዋል። በአውስትራሊያ፣ በኒው ዚላንድና በሳሞአ የሚኖሩ ሌሎች 377 ሰዎች ደግሞ ፕሮግራሙን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተከታትለዋል። የማቴዎስ መጽሐፍን ወዲያውኑ ከ​jw.org እና ከ​JW Library Sign Language አፕሊኬሽን ማውረድ እንደሚቻል ተገልጿል።

በአውስትራሊያ፣ በኒው ዚላንድ፣ በሳሞአ እና በቶንጋ የአውስትራሊያ ምልክት ቋንቋን ወይም ከዚያ ጋር በቅርብ የሚዛመድ የምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙ 20,000 ገደማ ሰዎች እንዳሉ ይገመታል። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ አውስትራሊያ ምልክት ቋንቋ መተርጎም የጀመሩት በ2001 ሲሆን በመጀመሪያ የተተረጎመው ጽሑፍ የምትወዱት ሰው ሲሞት የሚለው ብሮሹር ነው። ሚያዝያ 2023 በብሪዝበን የርቀት የትርጉም ቢሮ ተቋቋመ። በዛሬው ጊዜ በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ በሚገኝ አንድ የምልክት ቋንቋ ጉባኤና በ18 የምልክት ቋንቋ ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ ወደ 350 የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች አሉ።

ወደ አውስትራሊያ ምልክት ቋንቋ የተተረጎመው የመጀመሪያው የተሟላ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የማቴዎስ መጽሐፍ ነው። አንዲት እህት ይህን ትርጉም ካገኘች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ በተጠቀመባቸው ቃላት ላይ የሚንጸባረቀው ፍቅርና ደግነት ልቤን በጥልቅ ነክቶታል። የተራራውን ስብከት በአውስትራሊያ ምልክት ቋንቋ ስመለከት ኢየሱስ እኔን በቀጥታ እያነጋገረኝ እንዳለ ሆኖ ተሰማኝ!”

በብሪዝበን በሚገኝ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ የምታገለግል አንዲት መስማት የተሳናት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የማቴዎስ መጽሐፍን በአውስትራሊያ ምልክት ቋንቋ ማግኘቴ የኢየሱስን ባሕርያት በተሻለ ሁኔታ ለመኮረጅና በስብከቱ ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ይረዳኛል። ይሖዋ፣ አመሰግንሃለሁ!”

የማቴዎስ መጽሐፍ በአውስትራሊያ ምልክት ቋንቋ በመውጣቱ በጣም ተደስተናል፤ ይህ መጽሐፍ በርካታ ሰዎች ወደ ሕይወት የሚወስደውን ጠባብ በር እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።​—ማቴዎስ 7:13, 14