በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ታራስ ኩዝዮ እና ባለቤቱ ዳርያ፤ ወንድም ሰርጌ ልዩሊን፣ ወንድም ፕዮተር ዢልትሶቭ

መስከረም 27, 2022 | የታደሰው፦ መጋቢት 22, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና

ወቅታዊ መረጃ—የጥፋተኝነት ብይን ተቀለበሰ | በይሖዋ እርዳታ አሉታዊ ስሜቶችን ማሸነፍ

ወቅታዊ መረጃ—የጥፋተኝነት ብይን ተቀለበሰ | በይሖዋ እርዳታ አሉታዊ ስሜቶችን ማሸነፍ

መጋቢት 21, 2024 የክራይሚያ ሪፑብሊክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በወንድም ታራስ ኩዝዮ እና ባለቤቱ እህት ዳርያ ኩዝዮ እንዲሁም በወንድም ሰርጌ ልዩሊን እና በወንድም ፕዮተር ዢልትሶቭ ላይ የተላለፈውን የጥፋተኝነት ብይን ሽሯል። ወንድሞች ወዲያውኑ ከእስር ተለቀዋል። ክሳቸው በድጋሚ እንዲታይ በክራይሚያ ሪፑብሊክ ወደሚገኘው የያልታ ከተማ ፍርድ ቤት ተመልሷል።

የካቲት 27, 2023 በክራይሚያ ሪፑብሊክ የሚገኘው የያልታ ከተማ ፍርድ ቤት፣ ወንድም ታራስ ኩዝዮ እና ባለቤቱ እህት ዳርያ ኩዝዮ እንዲሁም ወንድም ሰርጌ ልዩሊን እና ወንድም ፕዮተር ዢልትሶቭ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላልፏል። ዳርያ የሦስት ዓመት የገደብ እስራት ተበይኖባታል። በአሁኑ ወቅት ወህኒ አትወርድም። ታራስ የስድስት ዓመት ተኩል እስራት ተፈርዶበታል። ሰርጌ እና ፕዮተር ደግሞ እያንዳንዳቸው የስድስት ዓመት ከአንድ ወር እስራት ተበይኖባቸዋል። ሦስቱም ወንድሞች ከፍርድ ቤት በቀጥታ ወደ ወህኒ ቤት ተወስደዋል።

የክሱ ሂደት

  1. መጋቢት 4, 2021

    ታራስ ‘ለጽንፈኛ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል’ በሚል የወንጀል ክስ ተመሠረተበት

  2. መጋቢት 11, 2021

    የእነ ታራስንና የእነ ሰርጌን ቤት ጨምሮ ዘጠኝ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ተፈተሹ። ታራስ ማረፊያ ቤት እንዲገባ ተደረገ

  3. መጋቢት 12, 2021

    ታራስ ከማረፊያ ቤት ተለቅቆ የቁም እስረኛ ተደረገ፤ ሆኖም ከቤተሰቡ ጋር እንዲኖር አልተፈቀደለትም

  4. ሐምሌ 29, 2021

    በዳሪያ፣ በፕዮተርና በሰርጌ ላይ የወንጀል ክስ ተመሠረተ። ፕዮተር ማረፊያ ቤት እንዲገባ ተደረገ

  5. ሐምሌ 30, 2021

    የሁሉም ክስ በአንድ መዝገብ ተካተተ። ፕዮተር ከማረፊያ ቤት ተለቅቆ የቁም እስረኛ ተደረገ

  6. ነሐሴ 11, 2021

    ሰርጌ በቁጥጥር ሥር ውሎ 800 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ወደሚገኝ ማረፊያ ቤት ተወሰደ። አሥራ ስድስት ሰዓት በፈጀው ጉዞ ላይ እጆቹ ከጭንቅላቱ በላይ ካለ ዘንግ ጋር ታስረው እንዲሁም እግሮቹ ከወንበሩ ጋር ታስረው ነበር

  7. መጋቢት 1, 2022

    ሰርጌ ከማረፊያ ቤት ተለቅቆ የቁም እስረኛ ተደረገ

  8. ሚያዝያ 4, 2022

    ክሱ በፍርድ ቤት መታየት ጀመረ

  9. ሐምሌ 11, 2022

    ፕዮተር፣ ሰርጌና ታራስ ከቁም እስር ነፃ ተደረጉ፤ የጉዞ እገዳ ተጣለባቸው

አጭር መግለጫ

በእስር ቤት፣ በማረፊያ ቤት ወይም በቁም እስር ላይ የሚገኙ ታማኝ ክርስቲያኖች ‘መፈናፈኛ እንዳጡ’ ይሰማቸው ይሆናል፤ ሆኖም ይሖዋ ለስሙ ሲሉ የሚሰደዱ ክርስቲያኖችን ፈጽሞ አይተዋቸውም።—2 ቆሮንቶስ 4:8, 9