በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሩሲያ

በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ—ሩሲያ

በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ—ሩሲያ

በዘመናዊቷ ሩሲያ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳለፉት ታሪክ በጭቆናና በስደት የተሞላ ነው። በ20ኛው መቶ ዘመን የሩሲያ ባለሥልጣናት በእነዚህ ሰላማዊና ሕግ አክባሪ ዜጎች ላይ ብዙ ግፍና እንግልት አድርሰውባቸዋል። የሶቪየት ኅብረት መንግሥት ዓላማ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሶቪየትን ርዕዮተ ዓለም እንዲቀበሉ ማስገደድ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች መያዝ አይፈቀድላቸውም ነበር። ባለሥልጣናቱ ሁልጊዜ በዓይነ ቁራኛ ስለሚከታተሏቸው ሃይማኖታዊ ስብሰባዎቻቸውን በድብቅ ለማካሄድ ተገድደው ነበር። ከተያዙ ዕጣ ፈንታቸው ድብደባና የረጅም ጊዜ እስራት ይሆናል። መንግሥት በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን በግዞት ወደ ሳይቤሪያ ወስዷቸዋል።

በ1991 ግን ሁኔታዎች መለወጥ ጀመሩ፤ የሩሲያ መንግሥት ለይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና የሰጣቸው ሲሆን አምልኳቸውን በነፃነት እንዲያካሂዱ ተፈቀደላቸው። ይሁንና ይህ የሰላም ጊዜ ብዙም አልዘለቀም።

በ2009 የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ “ጽንፈኛ” ተብሎ እንዲፈረጅ የበታች ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ አጸደቀው፤ ከዚያ በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚሰነዘረው ተቃውሞና እገዳ እየተፋፋመ መጣ። ዓመታት ከፈጀ የፍርድ ቤት ሙግት በኋላ ሚያዝያ 2017 የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ተቋማት እንዲፈርሱ ወሰነ፤ የተሰነዘረባቸው ክስ በጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎች ተካፍለዋል የሚል ነበር። የሩሲያ ባለሥልጣናት ወዲያውኑ የሕጋዊ ተቋማቱን ንብረት ወረሱ፣ የይሖዋ ምሥክሮችን የአምልኮ ቦታዎች ዘጉ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ጽሑፎቻቸውን በጽንፈኝነት ፈረጇቸው።

ባለሥልጣናቱ የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ ተቋማት በመዝጋት ብቻ ሳይወሰኑ በግለሰብ ደረጃ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት ማድረሱን ተያይዘውታል። ሕጉን በማጣመም፣ የይሖዋ ምሥክሮች በግለሰብ ደረጃ የሚያካሂዱትን አምልኮ እገዳ ከተደረገበት ድርጅት ጋር እንደመተባበር እየቆጠሩት ነው። ፖሊሶች ቤታቸውን ሰብረው በመግባት እያንገላቷቸውና ከባድ ምርመራ እያደረጉባቸው ነው። ወጣት አረጋዊ፣ ወንድ ሴት ሳይል በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በቁጥጥር ሥር ይውላሉ፣ ወንጀለኛ ተብለው ይፈረድባቸዋል፣ ወህኒ ይጣላሉ አሊያም የቁም እስር ይበየንባቸዋል።

ሚያዝያ 2017 ከተጣለው እገዳ ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በጽንፈኝነት ተወንጅለው ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ተደርገዋል አሊያም እስራት ተፈርዶባቸዋል። እስከ ሚያዝያ 17, 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ በድምሩ 123 የይሖዋ ምሥክሮች እስር ላይ ይገኛሉ።

ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የምታደርሰው ግፍ ተቃውሞ እያስከተለባት ነው

ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የምታደርሰውን የመረረ ስደት እንድታቆም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥያቄ እያቀረበ ነው፤ ባለሥልጣናቱ ግን በጽንፈኝነት እንቅስቃሴ ተካፍለዋል በሚል ውንጀላ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከመፍረድ ወደኋላ አላሉም። በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ታዛቢዎችና ፍርድ ቤቶች የሩሲያ መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እያደረሰ ያለውን የማያባራ ስደት አውግዘዋል።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፦ ሰኔ 7, 2022 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት ማድረሷን የሚያወግዝ ታሪካዊ ውሳኔ አሳለፈ። (Taganrog LRO and Others v. Russia, nos. 32401/10 19 others) ፍርድ ቤቱ ሩሲያ በ2017 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ መጣሏ ተገቢ እንዳልነበር ገልጿል። ፍርድ ቤቱ፣ ሩሲያ “በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተመሠረቱ የወንጀል ክሶችን በሙሉ ለማቋረጥና . . . [እስር ላይ ያሉ] የይሖዋ ምሥክሮችን በሙሉ ለማስለቀቅ አስፈላጊውን እርምጃ” እንድትወስድ ትእዛዝ አስተላልፏል። በተጨማሪም የወረሰቻቸውን ንብረቶች ሁሉ እንድትመልስ ወይም ለንብረቶቹ ካሳ እንዲሆን ከ60 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንድትከፍል እንዲሁም ለአቤቱታ አቅራቢዎቹ የ3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካሳ እንድትከፍል ታዝዛለች።

የአውሮፓ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የላኩት ደብዳቤ፦ መሪያ ፔቺኖቪች ቡሪች ታኅሣሥ 9, 2022 ለሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላኩት ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የሞስኮ የይሖዋ ምሥክሮች እና ሌሎች እንዲሁም ክሩፕኮ እና ሌሎች በተሰኙት የክስ መዝገቦች ላይ እንደተመላከተው አቤቱታ አቅራቢው ሃይማኖታዊ ማኅበር እንዲፈርስ መደረጉን ተከትሎ በእንቅስቃሴዎቹ ላይ እገዳ ተጥሏል፣ ሰላማዊ የሆነ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ተበትኗል እንዲሁም በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከተካፈሉት አንዳንዶቹ ነፃነታቸውን ተነፍገዋል፤ ኮሚቴው ይህን በመመልከት በሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበራት እንቅስቃሴዎች ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ እንዲሁም በእነሱ ላይ የተሰነዘሩ የወንጀል ክሶች በሙሉ እንዲቋረጡ ባለሥልጣናቱን አጥብቆ አሳስቧቸዋል።”

የአውሮፓ ምክር ቤት የሚኒስትሮች ኮሚቴ ውሳኔ፦ የሚኒስትሮች ኮሚቴ መስከረም 2023 ባደረገው ስብሰባ ላይ ይህን መግለጫ አውጥቷል፦ “የሩሲያ ባለሥልጣናት፣ በተለይ የይሖዋ ምሥክር እስረኞችን ከመልቀቅ ጋር በተያያዘ [የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት] በግልጽ ያመላከታቸውን ውሳኔዎች ሙሉ በሙሉ እና ሆን ብለው መጣሳቸው በጣም አሳሳቢ ነው፤ እነዚህ ውሳኔዎች በአባል አገራቱ ስምምነት አንቀጽ 46 እንዲሁም የከሳሽ የታጋንሮግ የይሖዋ ምሥክሮች እና ተከሳሽ ሩሲያ የፍርድ ውሳኔ ላይ የተመሠረቱ ናቸው።” ሩሲያ ውሳኔዎቹን ለመተግበር ፈቃደኛ ባለመሆኗ ኮሚቴው “የፍርድ ጉዳዮቹን ለተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ፣ ለተባበሩት መንግሥታት አግባብ ያልሆነ እስራት አጣሪ ቡድን እንዲሁም በሩሲያ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚደርሰው ስደት ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ሁሉ ለማስተላለፍ ወስኗል፤ ዓላማውም የተጠቀሱት የፍርድ ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።”

በቅርብ ጊዜ የተሰጡ ፍርደ ገምድል ውሳኔዎች

  • ጥር 25, 2024 የ37 ዓመቷ ሶና ኦሎፖቫ ማረሚያ ቤት ውስጥ የሁለት ዓመት የግዳጅ ሥራ ተፈረደባት። የፍርድ ጊዜዋን እስክታጠናቅቅ ድረስ ሰማረ ክልል በሚገኝ ማረሚያ ተቋም ውስጥ መኖር ይጠበቅባታል።

  • ሐምሌ 2018 የታጠቁ ፖሊሶች አንድ ቤት ሰብረው ገቡ፤ ዲሚትሪ እና የሌና ባርማኪን የ90 ዓመት አረጋዊት የሆኑትን የየሌናን አያት ለመንከባከብ በዚህ ቤት አርፈው ነበር። ዲሚትሪ እና የሌና ወደ መኖሪያ ከተማቸው ወደ ቭላዲቮስቶክ ተወሰዱ፤ እዚያም ዲሚትሪ ታሰረ። “የጽንፈኛ ድርጅትን እንቅስቃሴ ማስተባበር” የሚል የወንጀል ክስ ተመሠረተበት። የካቲት 6, 2024 ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በዲሚትሪ ባርማኪን ላይ የተላለፈውን የጥፋተኝነት ብይን አጸናው። የቀረውን የስምንት ዓመት የእስራት ጊዜ እንዲጨርስ ከችሎት ወዲያውኑ ወደ ወህኒ ተወሰደ። የሌናም በእምነቷ ምክንያት የፍርድ ሂደት ላይ ነች።

  • በሰማረ ክልል፣ በቶልያቲ የሚገኘው የሴንትራልኒ አውራጃ ፍርድ ቤት በ53 ዓመቱ አሌክሳንደር ቻጋን ላይ የጥፋተኝነት ብይን አስተላልፏል። ባለትዳር የሆነው አሌክሳንደር የስምንት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል፤ ይህም በይሖዋ ምሥክር ወንዶች ላይ ከተላለፉት ረጅም የእስራት ፍርዶች አንዱ ነው። የካቲት 29, 2024 ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን እንዳስተላለፈ በቀጥታ ወህኒ ወርዷል። በሰማረ ክልል በሚገኘው 4ተኛ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ ነው።

  • በምሥራቃዊ ሳይቤሪያ፣ በኢርኩትስክ ክልል የሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት፣ ዘጠኝ የይሖዋ ምሥክር ወንዶችን በጽንፈኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ብሏል። መጋቢት 5, 2024 ዘጠኙ የይሖዋ ምሥክሮች እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ እስራት ተፈርዶባቸዋል፤ ከእነሱ መካከል የ72 ዓመት አዛውንት ይገኝበታል። የፍርድ ሂደታቸው የጀመረው ጥቅምት 2021 በፖሊሶች ቤታቸው በተፈተሸበት ወቅት ነው። ፍርዱ በተላለፈበት ወቅት ያሮስላቭ ካሊን የተባለው አንደኛው ተከሳሽ ከሁለት ዓመት በላይ ማረፊያ ቤት ቆይቷል። አስከፊ ስለነበረው የእስር ቆይታው ሲገልጽ “ከዚህ የከፋ እስር ቤትና የእስር ሁኔታ ሊኖር አይችልም” ብሏል።

ኢፍትሐዊ እስራትን ለማስቆም የሚደረግ ያልተቋረጠ ጥረት

በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የሩሲያ መንግሥት በእምነት ባልንጀሮቻቸው ላይ እያደረሰ ያለው በደል በጣም ይረብሻቸዋል። በመላው ዓለም ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች እስር ላይ ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በተመለከተ ለሩሲያ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደብዳቤዎች ልከዋል። ለታሰሩት የይሖዋ ምሥክሮች የሚሟገቱት ጠበቃዎች፣ በሁሉም ደረጃ ለሚገኙ የሩሲያ ፍርድ ቤቶች ይግባኝ ብለዋል፤ ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤትም በርካታ ማመልከቻዎችን አስገብተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ እንዲሁም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አግባብ ያልሆነ እስራት አጣሪ ቡድን (ዎርኪንግ ግሩፕ ኦን አርቢትራሪ ዲቴንሽን) ቅሬታቸውን አሰምተዋል። በተጨማሪም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለሚከታተሉ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጉዳዩን ሪፖርት አድርገዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በሩሲያ ባሉ የእምነት አጋሮቻቸው ላይ የሚደርሰው ከባድ ሃይማኖታዊ ስደት እንዲቆም ስለሚፈልጉ በወንድሞቻቸው ላይ ስለሚፈጸመው ግፍ ዓለም እንዲያውቅ ለማድረግ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ።

የጊዜ ሰሌዳ

  1. ሚያዝያ 17, 2024

    በአጠቃላይ 123 የይሖዋ ምሥክሮች እስር ላይ ይገኛሉ።

  2. ጥቅምት 24, 2023

    የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ፣ ከኤሊስታ እና ከአቢንስክ የይሖዋ ምሥክሮች የፍርድ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሁለት መግለጫዎች አውጥቷል። ኮሚቴው በሁለቱም መግለጫዎች ላይ እንዳስቀመጠው የሩሲያ መንግሥት በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 18.1 (“የማሰብ፣ የሕሊናና የሃይማኖት ነፃነት”) እና አንቀጽ 22.1 (“የመሰብሰብ መብት”) ላይ የተጠቀሱትን መብቶች ጥሷል። መግለጫዎቹ እንዳረጋገጡት በይሖዋ ምሥክሮቹ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ላይ ጥላቻንና ዓመፅን የሚያበረታታ ምንም ይዘት የለም።

  3. ሰኔ 7, 2022

    የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ በከሳሽ የታጋንሮግ የይሖዋ ምሥክሮችና ሌሎች እና ተከሳሽ ሩሲያ የክስ መዝገብ ላይ ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የምታደርሰውን እንግልት የሚያወግዝ ታሪካዊ ውሳኔ አሳለፈ።

  4. ጥር 12, 2022

    የሩሲያ መንግሥት የፍትሕ ሚኒስቴር፣ JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ጽንፈኛ ተብለው የተፈረጁ ነገሮችን በያዘው የፌዴራል ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት ወሰነ። ይህ አፕሊኬሽን ሩሲያ ውስጥ ጽንፈኛ ተብሎ የታገደ የመጀመሪያውና ብቸኛው አፕሊኬሽን ነው።

  5. መስከረም 27, 2021

    የሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ፍርድ ቤት JW Library አፕሊኬሽን መታገዱን አስመልክቶ የቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ፤ JW Library አፕሊኬሽን ጽንፈኛ ተብሎ የተፈረጀው እንዲሁም በሩሲያ ፌዴሬሽንና በክራይሚያ አገልግሎት ላይ እንዳይውል የታገደው መጋቢት 31, 2021 ነበር። የፍርድ ቤቱ የመጀመሪያ ውሳኔ አሁኑኑ ተፈጻሚ ይሆናል።

  6. ሚያዝያ 26, 2019

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አግባብ ያልሆነ እስራት አጣሪ ቡድን፣ የዲሚትሪ ሚኻይሎቭ መብት እንደተጣሰ በመግለጽ ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የምታደርሰውን ስደት አወገዘ።

  7. ሚያዝያ 20, 2017

    የሩሲያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራዊ መሥሪያ ቤት እንዲሁም በሩሲያ የሚገኙ 395 ሃይማኖታዊ ተቋማት እንዲፈርሱ ወሰነ።