በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ግንቦት 10, 2022
እስራኤል

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በዘመናዊ ዕብራይስጥ ወጣ

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በዘመናዊ ዕብራይስጥ ወጣ

በቅርቡ በእስራኤል ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ የሚገኙት ሁሉም ጉባኤዎች ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናዊ ዕብራይስጥ እንደወጣና ከግንቦት 2, 2022 ጀምሮ በዲጂታል ፎርማት ማውረድ እንደሚቻል ተነገራቸው። የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ መስከረም 2022 ላይ ይደርሳል።

ይህ እትም በ2020 የወጣውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ከተሻሻለው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ጋር አጣምሮ የያዘ ነው። ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናዊ ዕብራይስጥ በአንድ ጥራዝ ሲወጣ ይህ የመጀመሪያው ነው። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በዘመናዊ ዕብራይስጥ መቀመጡ አንባቢዎች በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ጥንታዊ ጽሑፍ በግልጽ እንዲረዱ ያስችላል፤ ምክንያቱም ዛሬ ያሉት አብዛኞቹ አንባቢዎች ጥንታዊውን ቋንቋ መረዳት አይችሉም።

የትርጉም ቡድኑ አባል የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አንባቢዎች በዘመናዊ ዕብራይስጥ የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን በተለይም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማግኘት በጣም ይቸገራሉ። በመሆኑም ሙሉውን አዲስ ዓለም ትርጉም በማግኘታችን በጣም ተደስተናል፤ ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት እንድንረዳ የሚያግዙ ብዙ ገጽታዎች አሉት፤ በተለይ በርካታ የህዳግ ማጣቀሻዎች ያሉት መሆኑ ግሩም ነው።”

በትርጉም ክፍሉ ውስጥ የሚያገለግል ሌላ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ለዚህ ስጦታ ይሖዋን እናመሰግነዋለን። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ዕብራይስጥ ተናጋሪ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችና ሌሎች ሰዎች ከሰማዩ አባታቸው ጋር የጠበቀና የቀረበ ወዳጅነት አንዲመሠርቱ ይረዳቸዋል።”—ያዕቆብ 4:8