መስከረም 8, 2025
ኤርትራ
ከግራ ወደ ቀኝ፦ እህት ብርኽቲ ሃብተ (84 ዓመት) እና እህት ለተብርሃን ተስፋይ (86 ዓመት)
የኤርትራ መንግሥት ከ80 ዓመት በላይ የሆኑ ሁለት እህቶችን በግፍ ካሰረ አንድ ዓመት ሞላው
ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ 14 የይሖዋ ምሥክሮች ታስረዋል
የዛሬ ዓመት መስከረም ወር ላይ የኤርትራ መንግሥት ሁለት አረጋውያን እህቶችን ማሰሩ ይታወሳል። የ84 ዓመት አረጋዊት የሆኑት እህት ብርኽቲ ሃብተ የታሰሩት መስከረም 27, 2024 ፖሊሶች በእህት ለተብርሃን ተስፋይ ቤት ላይ ድንገተኛ ብርበራ ባደረጉበት ወቅት ነው፤ በዕለቱ በዚህ ቤት ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በሰላም ስብሰባ እያካሄዱ ነበር። ከሦስት ቀናት በኋላ ፖሊሶቹ የ86 ዓመት አረጋዊት ወደሆኑት ወደ እህት ለተብርሃን ተስፋይ ቤት ተመልሰው በመምጣት ይዘዋቸው ሄዱ። አሁን ላይ ሁለቱ እህቶች በዓዲ ኣበይቶ እስር ቤት ይገኛሉ።
ሁለቱም እህቶች ለብዙ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን አገልግለዋል። እህት ለተብርሃን የተጠመቁት በ1957 ሲሆን ከመጀመሪያዎቹ የኤርትራ የይሖዋ ምሥክሮች አንዷ ናቸው። ስምንት ልጆቻቸውም የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ሓዳስ ዘርኢሰናይ የተባለችው አንዷ ልጃቸው በመስከረም 2024ቱ ፍተሻ ላይ በቁጥጥር ሥር ውለው ከታሰሩት አንዷ ነች። የ52 ዓመቷ ሓዳስ አሁን ያለችው ማይ ስርዋ እስር ቤት ውስጥ ነው። እህት ብርኽቲ ደግሞ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክር የሆኑት በ1974 ነው፤ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል።
የ17 ዓመቷ እህት ሲዶን ተኸስተ በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ውስጥ በእስር ላይ ከሚገኙት ሁሉ በዕድሜ ትንሿ ነች
በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ውስጥ 64 የይሖዋ ምሥክሮች በእስር ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል 14 የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ60 በላይ ነው። የ17 ዓመቷ እህት ሲዶን ተኸስተ ከእነሱ መካከል በዕድሜ ትንሿ ስትሆን ከኅዳር 2024 አንስቶ በማይ ስርዋ እስር ቤት ትገኛለች። አንዳቸውም ቢሆኑ በአግባቡ ክስ አልተመሠረተባቸውም እንዲሁም ፍርድ ቤት አልቀረቡም። እስር ቤት ውስጥ ሕመም ሲያጋጥማቸው አስፈላጊውን የሕክምና እርዳታ የሚነፈጉ ከመሆኑም ሌላ ብዙ እንግልት ይፈጸምባቸዋል። ጥር 2025 ከዓዲ ኣበይቶ እስር ቤት የተለቀቀች አንዲት እህት በዚያ ስላለው አስከፊ ሁኔታ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ከባድ ሁኔታ ነው ያለው። እስር ቤቱ በሰው የተጨናነቀ ነው። አረጋውያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ጨምሮ እስረኞቹ የሚተኙባት ቦታ ከ40 እስከ 60 ሴንቲ ሜትር ብትሆን ነው። በጎን በኩል ካልሆነ መተኛት አይቻልም፤ ገልበጥ ማለት ብንፈልግ እንኳ ቦታው ብዙ የሚያላውስ አይደለም። የእስር ቤቱ ኃላፊዎች አረጋውያን ወንድሞቻችንን እንዲህ የሚያንገላቷቸው በሁኔታው ተመርረው አቋማቸውን እንዲያላሉ ለማድረግ ይመስለኛል።”
በርካታ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች፣ እነዚህን አስከፊ ሁኔታዎች ጨምሮ የኤርትራ መንግሥት እየፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳሳሰባቸው እየገለጹ ነው። ለምሳሌ ያህል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሾመው ገለልተኛ አጣሪ ቡድን በኤርትራ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ከገመገመ በኋላ ግንቦት 2025 ለአገሪቱ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል፤ “ከሕግ አግባብ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙ ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ [እንዲፈቱ]” እንዲሁም “ሃይማኖትን መሠረት በማድረግ በግለሰቦች ላይ የሚፈጸም እንግልት [እንዲቆም]” መንግሥትን አሳስቧል። እስካሁን ባለው መረጃ የኤርትራ መንግሥት እንዲህ ላሉ ጥሪዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል፤ የይሖዋ ምሥክሮችን በሃይማኖታቸው ምክንያት ብቻ ማንገላታቱን ቀጥሏል።
በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ውስጥ የታሰሩ ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ 14 ታማኝ ወንድሞችና እህቶች። ላይኛው መደዳ፣ ከግራ ወደ ቀኝ፦ ብርኽቲ ሃብተ፣ 84፤ ኢለን ጐይትኦም፣ 60፤ ገነት ዘርኣይ፣ 67፤ ከሰተብርሃን ንጉሰ፣ 74፤ ህድኣት ገብረህይወት፣ 65፤ ለተብርሃን ተስፋይ፣ 86። ታችኛው መደዳ፣ ከግራ ወደ ቀኝ፦ ተወልደመድህን ሃብተጽዮን፣ 66፤ ሳባ ተኽለ፣ 66፤ ታረቀ ተስፋማርያም፣ 77፤ ተኽለ ዮኣብ፣ 74 እና ባለቤቱ ቅድስቲ ተስፋሚካኤል፣ 71፤ ተስፋይ ክፍላይ፣ 67፤ ተስፋፅዮን ገብረሚካኤል፣ 83፤ ዕቝባ ኣማረ፣ 62
በዓለም ዙሪያ ያለን የይሖዋ ምሥክሮች በኤርትራ በግፍ ታስረው የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲፈቱ እንጸልያለን። ‘የአምላክ መንፈስ ስለሚያርፍባቸው’ እነዚህን ከባድ ፈተናዎች በጽናት እንደሚወጡ እምነታችን ነው።—1 ጴጥሮስ 4:14

