በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ቪልዬን አቫንዬሶቭ ከእስር እንደተፈታ ከባለቤቱ ከስቴላ ጋር

የካቲት 14, 2024
ሩሲያ

የሰባ አንድ ዓመቱ ወንድም ቪልዬን አቫንዬሶቭ ከሩሲያ እስር ቤት ተለቀቀ

የሰባ አንድ ዓመቱ ወንድም ቪልዬን አቫንዬሶቭ ከሩሲያ እስር ቤት ተለቀቀ

የካቲት 9, 2024 ለአምስት ዓመታት ገደማ በእስር የቆየው ወንድም ቪልዬን አቫንዬሶቭ ተፈታ። ቪልዬን ግንቦት 2019 በቁጥጥር ሥር ውሎ ታሰረ። ከዚያም ሐምሌ 29, 2021 የስድስት ዓመት እስራት ተፈረደበት። ማረፊያ ቤት የቆየበት ጊዜ ግምት ውስጥ ስለሚገባ ሙሉ የእስራት ፍርዱን መጨረስ አላስፈለገውም። አርሲን የተባለው ልጁም በቁጥጥር ሥር ውሎ የታሰረው ተመሳሳይ ጊዜ አካባቢ ነው። አርሲን አሁንም ከእስር አልተፈታም።

ቪልዬን ከመፈታቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ባለቤቱ እህት ስቴላ አቫንዬሶቫ እንዲህ ብላ ነበር፦ “ሁኔታው ለሁላችንም ይበልጥ ከብዶን የነበረው ቪልዬን ማረፊያ ቤት እንደገባ ባለው የሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ነው። በጣም ተጨንቄ ነበር። ከቪልዬን ጋር በምንም መንገድ እንድንገናኝ አልተፈቀደልንም፤ በደብዳቤም እንኳ። በዚያ ላይ ደግሞ ባለቤቴም ልጄም ስለታሰሩ ቤተሰባችንን የማስተዳደሩ ጉዳይ አሳስቦኝ ነበር።”

በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥም እንኳ ቪልዬንም ሆነ ስቴላ የይሖዋ ድጋፍ እንዳልተለያቸው አስተውለዋል። ስቴላ አክላ እንዲህ ብላለች፦ “ቪልዬን፣ ለፍርድ ቤት ቀጠሮ ወደ ችሎት በወሰዱት ቁጥር ወንድሞችና እህቶች ሁሌም እዚያ ተሰብስበው ያያል። እንደነገረኝ ከሆነ፣ ይህ ለእሱ የይሖዋን እንክብካቤ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ይሖዋ ለእኔም የሚያስፈልገኝ ነገር እንዲሟላልኝ ያላደረገበት ጊዜ የለም። ይሖዋ የሚታመኑበትን እንደሚደግፍ መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ።”

ቪልዬን እና ስቴላ ዳግም ለመገናኘት በመብቃታቸው እኛም ተደስተናል። ልጃቸውን አርሲንን ጨምሮ በእስር ላይ ያሉ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በጸሎታችን ማሰባችንንም አናቆምም። ይሖዋ ለታማኞቹ ብርሃን፣ አዳኝና ተገን መሆኑን እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት አለን።​—መዝሙር 27:1