የአምላክ ቃል ያለው ኃይል የሂንዱ እምነት በሚከተል ቤተሰብ ውስጥ
ነሐሴ 22, 2005 ሰኞ ዕለት ጠዋት፣ ከቤተሰቤ ጋር ቁርስ ለመብላት ተሰባስበን የነበረበትን ወቅት መቼም ቢሆን አልረሳውም። በአንጎሌ ውስጥ ትልቅ ዕጢ በመገኘቱ በሕይወት የመትረፌ ጉዳይ በጣም አጠያያቂ ሆኖ ነበር። ባለቤቴ ክሪሽና ጸሎት ካቀረበ በኋላ ለቤተሰቦቼ እንዲህ አልኳቸው፦
“ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ወደ ሆስፒታል ልሄድ ነው፤ ቀዶ ጥገናው ለሕይወት የሚያሰጋ ስለሆነ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን የመጣውን ለመቀበል ዝግጁ ሁኑ። ምናልባት አንድ ነገር ቢያጋጥመኝ በሚል ለቀብሬ የሚያስፈልገውን ዝግጅት አድርጌያለሁ። አሁን ይሖዋን እያመለካችሁ ያላችሁ የቤተሰባችን አባላት እባካችሁ ይህን ማድረጋችሁን አታቋርጡ። ሌሎቻችሁ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት እንድትጀምሩ እለምናችኋለሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ፣ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ፍጹም ጤንነት አግኝተው ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም በሚኖሩበት በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ አንድ ዓይነት እምነት ይኖረናል።”
ቀዶ ሕክምናው ከተደረገልኝ በኋላ ስለሆነው ነገር ከመናገሬ በፊት ስለ አስተዳደጌ እንዲሁም እውነተኛውን አምላክ እንዴት እንዳወቅሁ እስቲ ላውጋችሁ።
በሂንዱ ቤተሰብ ውስጥ ማደግ
ቤተሰባችን የሚኖረው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በባሕር ዳርቻ ላይ በምትገኘው ደርባን የተባለች ከተማ ነበር። በእንጨትና በብረት የተሠራው ቤታችን የሚገኘው ከፍታ ቦታ ላይ ሲሆን ዝቅ ብሎ ካለው ዋና መንገድ ወደ ቤታችን ለመድረስ 125 ደረጃዎችን መውጣት ነበረብን። ከዚያም በቁጥቋጦዎች መካከል አቋርጠን አጭር ርቀት ከተጓዝን በኋላ ወደ አንድ የብረት በር እንደርሳለን። ከበሩ አጠገብ አያቴ ያሠራችው ቤተ መቅደስ ይገኛል፤ ውስጡ በሂንዱ አማልክት ሥዕሎችና ምስሎች ተሞልቶ ነበር። አያቴ፣ “የቤተ መቅደስ ልጅ” (በሂንዲ ማንዲር ኪ ባካ) እንደሆንኩና የተወለድኩት በአማልክቶቻችን እርዳታ እንደሆነ ትነግረኝ ነበር። ከዚህ ቤተ መቅደስ ትይዩ የሚገኙትን ቀይ ቀለም ያላቸው የሚያብረቀርቁ ደረጃዎች ከወጣን በኋላ ወደ ቤቱ ዋና በር እንደርሳለን። ቤቱ ትልቅ ሲሆን ረጅም ኮሪደር አለው፤ እንዲሁም የከሰል ምድጃ ያለው ሰፊ ኩሽና እና ሰባት መኝታ ቤቶች አሉት። ግቢያችን ውስጥ ከዋናው ቤት በተጨማሪ አንድ መኝታ ክፍል ያለው ሌላ ቤት አለ። አያቶቼን፣ አባቴን፣ ሦስት ታናናሽ ወንድሞቹን፣ ታናሽ እህቱንና ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ 27 ሆነን በዚህ ግቢ እንኖር ነበር።
እንዲህ ያለው ትልቅ ቤተሰብ የሚያስፈልገውን ማሟላት ቀላል አልነበረም። ሆኖም አብረን መኖራችን ቤተሰባችን ብዙ አስደሳች ትዝታዎች እንዲኖሩት አድርጓል። እናቴ ጋርጊ ዴቪ እና ሦስቱ የአጎቶቼ ሚስቶች የቤቱን ሥራ ተከፋፍለው ይሠራሉ። በየተራ ምግብ ያዘጋጃሉ እንዲሁም ቤቱን ያጸዳሉ። የቤተሰባችን ራስ፣ አያቴ ሲሆን ለመላ ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ምግብ የሚሸምተው እሱ ነበር። በየሳምንቱ ረቡዕ ዕለት አያቶቼ ገበያ ሄደው ለሳምንቱ የሚሆነንን ሥጋ፣ ፍራፍሬና አትክልት ይገዛሉ። እኛም የኮረብታው አናት ላይ በሚገኝ ዛፍ ሥር ቁጭ ብለን ከገበያ እስኪመለሱ እንጠብቃቸዋለን። አያቶቻችን ትላልቅ ዘንቢሎቻቸውን ይዘው ከአውቶቡስ ሲወርዱ ስናይ 125ቱን ደረጃዎች እየተንደረደርን ወርደን የሸመቷቸውን ነገሮች ወደ ቤት በመውሰድ እናግዛቸዋለን።
በአትክልት ቦታችን ትልቅ የዘንባባ ዛፍ የሚገኝ ሲሆን ማይና የተባሉት ወፎች ጎጇቸውን ሠርተውበት ነበር። እነዚህ ወፎች ከወዲያ ወዲህ ሲበሩ እናይ እንዲሁም ሲንጫጩ እንሰማቸው ነበር። አያቴ ዋናው በር ጋ ያለው ደረጃ ላይ ተቀምጣ ወፎቹ የሚያሰሙትን ድምፅ የምትተረጉም በማስመሰል ተረቶችን ትነግረን ነበር። በዚያ ቤት
ስላሳለፍነው ሕይወት ብዙ ጥሩ ትዝታዎች አሉኝ። ሳቃችን፣ ለቅሷችን፣ ጨዋታችን እንዲሁም ያለንን እየተካፈልን እንደ አንድ ትልቅ ቤተሰብ አብረን ያሳለፍናቸው አስደሳች ጊዜያት አይረሱኝም! ከሁሉ በላይ ደግሞ ስለ ፈጣሪያችን ስለ ይሖዋ እና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መማር የጀመርነው በዚህ ቤት በመሆኑ ልዩ ትዝታ አለኝ።ስለ ይሖዋ ከመማራችን በፊት የሂንዱ እምነት ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን በየቀኑ የምናከናውናቸው በርካታ የአምልኮ ሥርዓቶች ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ ለወንድና ለሴት አማልክቶቻችን ክብር ስንል በየተወሰነ ጊዜ ትላልቅ ግብዣዎችን በማዘጋጀት እንግዶችን እንጠራ ነበር። ከእነዚህ ዝግጅቶች በአንዳንዶቹ ላይ አያቴ ሰመመን ውስጥ ገብታ ከመናፍስት ጋር ትነጋገር ነበር፤ ልክ እኩለ ሌሊት ላይ መናፍስቱን ለማስደሰት የእንስሳት መሥዋዕት ይቀርባል። በሌላ በኩል ደግሞ ወንድ አያቴ በአካባቢያችን በሚያከናውነው የበጎ አድራጎት ሥራ የታወቀ ነበር፤ የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን እና የሂንዱ ቤተ መቅደሶችን የሚያሠራ ከመሆኑም ሌላ ለእነዚህ ተቋማት ገንዘብ ይሰጥ ነበር።
ስለ ይሖዋ አወቅን
በ1972 ወንድ አያቴ ባደረበት ሕመም የተነሳ ሕይወቱ አለፈ። ይህ ከሆነ ከጥቂት ወራት በኋላ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ኢንደርቫቲ (ጄን ተብላም ትጠራለች) ለተባለችው የአጎቴ ሚስት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ሰጧት። ጄን የይሖዋ ምሥክሮቹን ወደ ቤት እንዲገቡ ስላልጋበዘቻቸው የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማት። ከዚያ ቀደም የይሖዋ ምሥክሮች ሲመጡ አንቀበላቸውም ነበር። በቀጣዩ ጊዜ ሲመጡ ግን ጄን ወደ ቤት እንዲገቡ ከጋበዘቻቸው በኋላ አጎቴ ከመጠን በላይ ስለሚጠጣ በትዳራቸው ውስጥ ችግር እንደገጠማቸው አጫወተቻቸው። ጎረቤቶቻችንና ዘመዶቻችን አጎቴን እንድትፈታው መክረዋት ነበር። የይሖዋ ምሥክሮቹ ግን አምላክ ለጋብቻ ያለውን አመለካከት ገለጹላት። (ማቴዎስ 19:6) የአጎቴ ሚስት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ምክር እንዲሁም ወደፊት በምድር ላይ የተሻለ ሕይወት እንደሚመጣ የሚገልጸው ተስፋ * በጥልቅ ነካት። ከአጎቴ ጋር የመፋታት ሐሳቧን ትታ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ማጥናት ጀመረች። ጄን ሳሎን ሆና ስታጠና እናቴና ሌሎቹ የአጎቶቼ ሚስቶች በየክፍላቸው ሆነው ውይይቱን ያዳምጡ ነበር።
ከጊዜ በኋላ እናቴና ሁሉም የአጎቶቼ ሚስቶች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ጄን የተማረችውን ትነግረን እንዲሁም ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ * ከተባለው መጽሐፍ ላይ ታሪኮችን እያነበበች ታብራራልን ነበር። አጎቶቼ፣ ሚስቶቻቸው መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑ እንደሆነ ሲያውቁ መቃወም ጀመሩ። እንዲያውም አንደኛው አጎቴ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ጨምሮ ሌሎች ጽሑፎቻችንን በሙሉ ወስዶ አቃጠላቸው። አጎቶቼ ስብሰባ በመሄዳችን ምክንያት ይሰድቡን አልፎ ተርፎም ይመቱን ነበር። እንዲህ የማያደርገው አባቴ ብቻ ነበር፤ ስለ ይሖዋ በመማራችን ተቃውሞን አያውቅም። እናቴም ሆነች ሌሎቹ የአጎቶቼ ሚስቶች በስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውን አላቆሙም፤ አራቱም ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እያደገ ሄደ።
በ1974 ጄን ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች፤ እናቴና ሌሎቹ የአጎቶቼ ሚስቶችም ብዙም ሳይቆይ ተጠመቁ። ከጊዜ በኋላ አያቴ የሂንዱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ማከናወን አቆመች። እኔም ለበርካታ ዓመታት ከእናቴና ከአጎቶቼ ሚስቶች ጋር ሆኜ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ እገኝ ነበር። አንድ ቀን፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ትልቅ ስብሰባ ላይ እያለን ሻሚላ ራምፐርሳድ የተባለች
አንዲት የይሖዋ ምሥክር “አንቺስ የምትጠመቂው መቼ ነው?” አለችኝ። “ማንም መጽሐፍ ቅዱስን አስጠንቶኝ ስለማያውቅ እንዴት መጠመቅ እችላለሁ?” ብዬ መለስኩላት። እሷም ልታስጠናኝ እንደምትችል ነገረችኝ። በቀጣዩ ዓመት በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ ማለትም ታኅሣሥ 16, 1977 ተጠመቅሁ። አብረን እንኖር ከነበርነው 27 የቤተሰባችን አባላት መካከል ከጊዜ በኋላ 18ቱ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ይሁንና ቀዶ ሕክምናውን ባደረግሁበት ወቅት አባቴ ሶኒ ዴቫ የሂንዱ እምነት ተከታይ ነበር።“ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ”
በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኘው ሐሳብ፣ በተለይ በአንጎሌ ውስጥ ትልቅ ዕጢ እንዳለ ከታወቀ በኋላ በጣም አጽናንቶኛል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” በማንኛውም ሰዓት ልትሞቱ እንደምትችሉ ከተነገራችሁ በኋላ “ስለ ምንም ነገር [አለመጨነቅ]” ከባድ ነው። በአንጎሌ ውስጥ ዕጢ እንዳለ መጀመሪያ ሲነገረኝ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፤ ከዚያም ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ “ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም” የሚሰጠውን የመረጋጋት ስሜት አግኝቻለሁ።
ይሖዋ አምላክ በመንገዴ ሁሉ ቀኝ እጄን ይዞ እንደመራኝ ይሰማኛል። (ኢሳይያስ 41:13) ከደም እንድንርቅ የሚያዝዘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ለመታዘዝ ያለኝን ቁርጥ አቋም ለሕክምና ባለሙያዎቹ በድፍረት ለማስረዳት እንድችል ይሖዋ ረድቶኛል። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29) በዚህም ምክንያት የቀዶ ጥገና ሐኪሙም ሆነ ማደንዘዣ የሚሰጠው ባለሙያ ያለ ደም ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ ተስማሙ። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ሐኪሙ፣ ቀዶ ጥገናው በተሳካ ሁኔታ እንደተከናወነና ዕጢው ሙሉ በሙሉ እንደወጣ ገለጸልኝ። እንዲህ ያለ ከባድ የአንጎል ቀዶ ጥገና ከተደረገለት በኋላ እንደ እኔ ቶሎ ያገገመ ታካሚ አይቶ እንደማያውቅም ነገረኝ።
ከሦስት ሳምንት በኋላ አልጋዬ ላይ ሆኜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ቻልኩ። በሰባተኛው ሳምንት መጨረሻ ላይ ደግሞ እንደገና መኪና መንዳት፣ በስብከቱ ሥራ መካፈል እንዲሁም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመርኩ። በወንጌላዊነቱ ሥራ አብረውኝ የሚካፈሉ ክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ላደረጉልኝ ድጋፍ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ምንጊዜም ብቻዬን እንዳልሆን ጥረት የሚያደርጉ ሲሆን ወደ ቤት ስሄድ ይሸኙኝ ነበር። በድምፅ የተቀረጸ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ማዳመጤና በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮሬ ቶሎ እንዳገግም አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይሰማኛል።
ቀዶ ጥገና ካደረግሁ በኋላ አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ መሆኑም አስደስቶኛል። አባቴ በ73 ዓመቱ የተጠመቀ ሲሆን አሁን ይሖዋን በቅንዓት እያገለገለ ነው። ከዘመዶቼ መካከል ከ40 በላይ የሚሆኑት አብረውን ይሖዋን እያመለኩ ነው። በስተግራ በኩል ባለው ዓይኔ በደንብ ማየት የማልችል ከመሆኑም ሌላ የራስ ቅሌ አንድ ላይ የተያያዘው በብረት ነው፤ በመሆኑም ይሖዋ ወደፊት ገነት በሆነች ምድር ላይ “ሁሉንም ነገር አዲስ” የሚያደርግበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።—ራእይ 21:3-5
ይሖዋ፣ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግል አፍቃሪ ባልና በሙሉ ጊዜ ወንጌላዊነት እንድቀጥል የምትረዳኝ ክሊሪስታ የተባለች ቆንጆ ልጅ ስለሰጠኝ ተባርኬያለሁ። ይሖዋ አምላክ የማከናውነውን አገልግሎትም ባርኮልኛል። እስካሁን ድረስ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል በሕይወታቸው ውስጥ እንዲመለከቱ መርዳት ችያለሁ። ከ30 በላይ የሚሆኑት ጥናቶቼ ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ተጠምቀዋል።
ይሖዋ አምላክ፣ በሥቃይ የተሞላውን ይህን ዓለም አስወግዶ ገነት በሆነች ምድር ላይ እንድንኖር የሚያደርግበትን ጊዜ በተስፋ እጠባበቃለሁ።
^ አን.12 አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።
^ አን.13 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።