በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 በእምነታቸው ምሰሏቸው

“ምግባረ መልካም ሴት”

“ምግባረ መልካም ሴት”

ለዓይን ያዝ ማድረግ ጀምሯል። በቤተልሔም ዙሪያ ባሉት ማሳዎች ላይ ሲሠሩ የዋሉ በርካታ ሠራተኞች በአቅራቢያው ባለው ኮረብታ ላይ ጉብ ብላ ወደምትገኘው ትንሽ ከተማ የሚወስደውን መንገድ ተያይዘውታል። ሩት ቀኑን ሙሉ ስትሰበስብ በዋለችው የገብስ ነዶ አጠገብ በርከክ አለች። ከማለዳ ጀምራ ቀኑን ሙሉ ያለ እረፍት ስትለፋ ስለዋለች ሰውነቷ በድካም እንደዛለ ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ መሥራቷን አላቆመችም፤ እህሉን ከአገዳው ለመለየት ስትል በዱላ ወይም በመውቂያ በትር መደብደብ ጀመረች። ሥራው ከባድ ቢሆንም ከጠበቀችው በላይ ማግኘት ችላለች።

ይህች ወጣት መበለት ነገሮች እየተቃኑላት ይሆን? ከአማቷ ከኑኃሚን ጋር ለመሆን የወሰነች ሲሆን ከእሷ ላለመነጠልና የኑኃሚን አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለማምለክ ቆርጣለች። የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት የተነጠቁት ሩትና ኑኃሚን ከሞዓብ ምድር ወደ ቤተልሔም የመጡት አብረው ነው፤ ብዙም ሳይቆይ ሞዓባዊቷ ሩት በይሖዋ ሕግ ውስጥ ከሌላ አገር የመጡ መጻተኞችን ጨምሮ ድሆችን የሚጠቅምና ክብራቸውን የሚጠብቅ ዝግጅት እንዳለ አወቀች። * አሁን ደግሞ ከይሖዋ ሕግ የተማሩ ሕዝቦቹ ባሕርይና ያሳዩዋት ደግነት በሐዘን የተሰበረው ልቧ እንዲጠገን አደረገ።

እንዲህ ዓይነት ደግነት ካሳዩዋት ሰዎች አንዱ ቦዔዝ ነው፤ ቦዔዝ በዕድሜ ጠና ያለ ባለጠጋ ሰው ሲሆን ሩት እየቃረመች ያለችው በእሱ ማሳ ላይ ነው። ዛሬም ልክ እንደ አባት ተንከባክቧታል። ቦዔዝ፣ አረጋዊቷን ኑኃሚንን በመንከባከቧና በእውነተኛው አምላክ በይሖዋ ክንፎች ጥላ ሥር ለመጠለል በመምረጧ ሩትን አመስግኗታል፤ እሷም ቦዔዝ የተናገራቸውን ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት ስታስብ ደስ እንደሚላት የታወቀ ነው።—ሩት 2:11-13

ያም ሆኖ ሩት የወደፊት ሕይወቷ ሳያሳስባት አልቀረም። ድሃ ከመሆኗም ሌላ ባልም ሆነ ልጅ የሌላት የባዕድ አገር ሰው ናት፤ ታዲያ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ራሷንና ኑኃሚንን መደገፍ የምትችለው እንዴት ነው? በቃርሚያ ብቻ ኑሯቸውን መግፋት ይችሉ ይሆን? ደግሞስ እሷ ስታረጅ ማን ይጦራታል? ሩት እንዲህ ያሉ ሐሳቦች ቢያስጨንቋት የሚያስገርም አይሆንም። ከባድ የኢኮኖሚ ችግሮች ባሉበት በዛሬው ጊዜም ብዙዎች ተመሳሳይ ነገሮች ያስጨንቋቸዋል። ሩት፣ እንዲህ ዓይነቶቹን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም እምነቷ የረዳት እንዴት እንደሆነ ማወቃችን ምሳሌዋን መከተል የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች እንዳሉ እንድንገነዘብ ያደርገናል።

 ቤተሰብ የሚያሰኘው ምንድን ነው?

ሩት ለራሷና ለኑኃሚን የሚያስፈልገውን ለማቅረብ በትጋት ትሠራ ነበር

ሩት የቃረመችውን ገብስ ወቅታ ከጨረሰች በኋላ ስትሰፍረው አንድ የኢፍ መስፈሪያ ሆነ፤ አንድ የኢፍ መስፈሪያ 22 ሊትር ያህል ይሆናል። በመሆኑም የሰበሰበችው እህል በአጠቃላይ 14 ኪሎ ግራም ገደማ ሳይሆን አይቀርም! እህሉን በጨርቅ ቋጥራ በጭንቅላቷ በመሸከም ወደ ቤቷ ማዝገም ጀመረች፤ ወደ ቤተልሔም ስትደርስ ጨለምለም ብሎ ነበር።—ሩት 2:17

ኑኃሚን፣ የምትወዳት ምራቷ እንደተመለሰች ስታይ ተደሰተች፤ ሩት ይህን ያህል ገብስ ቃርማ መምጣቷን ስትመለከት ሳትገረም አልቀረችም። ሩት፣ ቦዔዝ ለሠራተኞቹ ካቀረበው ምሳ በልታ የተረፋትን ምግብም አምጥታ ነበር፤ ሁለቱ ሴቶች ይህን ምግብ ተካፍለው ራታቸውን በሉ። ከዚያም ኑኃሚን “ዛሬ የቃረምሽው ከየት ነው? የትስ ቦታ ስትሠሪ ዋልሽ? መልካም ነገር ያደረገልሽ ሰው የተባረከ ይሁን” አለቻት። (ሩት 2:19) ኑኃሚን አስተዋይ ስለነበረች ሩት የተሸከመችውን እህል ስትመለከት ለዚህች ወጣት መበለት ትኩረት የሰጣትና በደግነት ያስተናገዳት ሰው እንዳለ መገንዘብ ችላ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ሁለቱ ሴቶች የጦፈ ጨዋታ ያዙ፤ በዚህ መሃል ሩት ስለ ቦዔዝ ደግነት ለኑኃሚን ነገረቻት። ኑኃሚን በዚህ ተደስታ “በጎነቱን ለሕያዋንም ሆነ ለሙታን ማድረጉን ያልተወ እግዚአብሔር ይባርከው” አለች። (ሩት 2:19, 20) ኑኃሚን፣ ቦዔዝ ደግነት እንዲያሳይ ያነሳሳው ይሖዋ እንደሆነ ተገንዝባ ነበር፤ ይሖዋ አገልጋዮቹ ለጋሶች እንዲሆኑ የሚገፋፋቸው ከመሆኑም ሌላ ሕዝቦቹ ለሚያሳዩት ደግነት ወሮታቸውን እንደሚከፍል ቃል ገብቷል። *ምሳሌ 19:17

ቦዔዝ፣ አጫጆቹ እንዳያስቸግሯት ሲል የቤተሰቡ አባላት የሆኑትን ወጣት ሴቶች እየተከተለች በእሱ እርሻ ላይ ብቻ እንድትቃርም ሩትን መክሯት ነበር፤ ኑኃሚንም ቦዔዝ ያቀረበላትን ሐሳብ እንድትቀበል ሩትን አበረታታቻት። ሩት የተሰጣትን ምክር የተቀበለች ሲሆን ‘ከአማቷ ጋር መኖሯንም ቀጠለች።’ (ሩት 2:22, 23) ይህ ጥቅስ የሩት መለያ የሆነውን ባሕርይ ማለትም ለአማቷ ያላትን ታማኝ ፍቅር ጎላ አድርጎ ይገልጻል። የእሷ ምሳሌነት እኛም ለቤተሰብ ዝግጅት ያለንን አመለካከት እንድንመረምር ሊያነሳሳን ይገባል፤ የቤተሰባችንን አባላት በመደገፍና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በመርዳት ለዚህ ዝግጅት አክብሮት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። ይሖዋ የምናሳየውን ታማኝ ፍቅር ምንጊዜም ይመለከታል።

ሩትና ኑኃሚን እርስ በርስ ይደጋገፉና ይበረታቱ ነበር

ኑኃሚንና ሩት ቤተሰብ ተብለው ሊጠሩ አይችሉም? በአንዳንድ ባሕሎች አንድ ቤተሰብ “እውነተኛ” ቤተሰብ የሚባለው ባልን፣ ሚስትን፣ ልጆችን፣ አያቶችንና የመሳሰሉትን ያቀፈ ከሆነ ብቻ እንደሆነ ይታሰባል። ይሁን እንጂ የይሖዋ አገልጋዮች ልባቸውን ክፍት የሚያደርጉ ከሆነ ከላይ የተጠቀሱት የቤተሰብ አባላት ባልተሟሉበት ትንሽ ቤተሰብ ውስጥም እንኳ መተሳሰብ፣ ደግነትና ፍቅር እንዲሰፍን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ከኑኃሚንና ከሩት ሁኔታ እንገነዘባለን። አንተስ ያለህን ቤተሰብ ታደንቃለህ? ኢየሱስ፣ ቤተሰብ የሌላቸውን ጨምሮ ተከታዮቹ ሁሉ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቤተሰብ እንደሚያገኙ ተናግሯል።—ማርቆስ 10:29, 30

“የመቤዠት ግዴታ ካለባቸው ዘመዶቻችን አንዱ እርሱ ነው”

ሩት የገብስ አዝመራ ከሚሰበሰብበት ከሚያዝያ ወር አንስቶ የስንዴ ምርት እስከሚደርስበት እስከ ሰኔ ድረስ በቦዔዝ እርሻ ላይ መቃረሟን ቀጠለች። ሳምንታት እያለፉ ሲሄዱ ኑኃሚን ለምትወዳት ምራቷ ምን ልታደርግላት እንደምትችል ማሰቧ አልቀረም። በሞዓብ እያሉ ኑኃሚን ለሩት ሌላ ባል ልታገኝላት እንደማትችል ተሰምቷት ነበር። (ሩት 1:11-13) አሁን ግን ሌላ አማራጭ እንዳለ ማሰብ ጀምራለች። ኑኃሚን ወደ ሩት ቀርባ “ልጄ ሆይ፤ የሚመችሽን ቤት እንድፈልግልሽ አይገባኝምን?” አለቻት። (ሩት 3:1) በዚያ ዘመን ወላጆች ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ መፈለጋቸው የተለመደ ሲሆን ሩት ደግሞ ለኑኃሚን እንደ ልጇ ነበረች። በመሆኑም ኑኃሚን ለሩት ‘የሚመቻትን’ ወይም እረፍት የምታገኝበትን ቤት እንደምትፈልግላት ተናገረች፤ ኑኃሚን ይህን ስትል ባል ማግባትና ኑሮ መመሥረት ሊያስገኝ የሚችለውን ጥበቃና የደኅንነት ስሜት መግለጿ ነበር። ይሁን እንጂ ኑኃሚን ምን ልታደርግ ትችላለች?

ሩት ስለ ቦዔዝ ለኑኃሚን መጀመሪያ ስትነግራት ኑኃሚን “ሰውየው እኮ የሥጋ ዘመዳችን ነው፤ የመቤዠት ግዴታ  ካለባቸው ዘመዶቻችን አንዱ እርሱ ነው” ብላት ነበር። (ሩት 2:20) ኑኃሚን ምን ማለቷ ነበር? አምላክ ለእስራኤል የሰጠው ሕግ፣ በድህነትም ሆነ የቤተሰብ አባልን በሞት በማጣት የተነሳ ችግር ላይ የወደቁ ቤተሰቦችን የሚጠቅም ፍቅራዊ ዝግጅት ይዟል። አንዲት ሴት፣ ልጅ ሳትወልድ ባሏ ቢሞት ሐዘኗ የከፋ ይሆናል፤ ምክንያቱም ባሏ ዘር ሳይተካ ስለሞተ ወደፊት በስሙ የሚጠሩ ዘሮች አይኖሩትም። ይሁን እንጂ ይህች ሴት የባሏን ወንድም አግብታ የሟቹን ስም የሚያስጠራና የቤተሰቡን ንብረት የሚወርስ ልጅ ለመውለድ የሚያስችላት ዝግጅት በአምላክ ሕግ ውስጥ ተካትቶ ነበር። *ዘዳግም 25:5-7

ኑኃሚን ከዚህ ዝግጅት ጋር በተያያዘ ምን ለማድረግ እንዳሰበች ለሩት ነገረቻት። ወጣቷ ሩት፣ የአማቷን ሐሳብ አፏን ከፍታ ስታዳምጥ በዓይነ ሕሊናችን መመልከት እንችላለን። የእስራኤላውያን ሕግ አሁንም ቢሆን ለሩት አዲስ ሳይሆንባት አልቀረም፤ ብዙዎቹ ልማዶችም ለእሷ እንግዳ ነበሩ። እንደዚያም ሆኖ ኑኃሚንን በጣም ታከብራት ስለነበረ የነገረቻትን እያንዳንዱን ነገር በጥንቃቄ አዳመጠች። ኑኃሚን እንድታደርግ የጠየቀቻት ነገር ግራ የሚገባ፣ የሚያሳፍር አልፎ ተርፎም ሊያዋርዳት የሚችል ቢመስልም ሩት እንደተባለችው ለማድረግ ተስማማች። “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” በማለት በትሕትና መለሰችላት።—ሩት 3:5

አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች በዕድሜ የሚበልጧቸውና ተሞክሮ ያካበቱ ሰዎች የሚሰጧቸውን ምክር መስማት ይቸግራቸዋል። ወጣቶቹ፣ ትላልቅ ሰዎች እነሱ እያጋጠሟቸው ያሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎችና ችግሮች ሊረዱ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። ሩት በትሕትና ረገድ የተወችው ምሳሌ ግን የሚወዱንና ለእኛ የሚያስቡልን ትላልቅ ሰዎች የሚሰጡንን ጥበብ ያዘለ ምክር መስማት በእጅጉ እንደሚክስ ያሳያል። ይሁን እንጂ የኑኃሚን ምክር ምን ነበር? ደግሞስ ሩት ምክሩን በመቀበሏ ተክሳለች?

 ሩት በአውድማው ላይ

በዚያን ዕለት ምሽት ሩት ወደ አውድማው አመራች፤ አፈሩ በደንብ ተጠቅጥቆ በተዘጋጀው አውድማ ላይ ገበሬዎች እህል እየወቁ ያነፍሳሉ። ገበሬዎች ብዙውን ጊዜ አውድማ እንዲሆን የሚመርጡት ቦታ ከፍ ያለ አካባቢ ወይም ጉብታ ሲሆን ይህን የሚያደርጉት በእነዚህ አካባቢዎች አመሻሹ ላይ የሚኖረው አየር ነፋሻማ ስለሚሆን ነው። ሠራተኞቹ ምርቱን ከገለባውና ከእብቁ ለመለየት ሲሉ በመንሽ እና በላይዳ ወደ ላይ ይበትኑታል፤ እህሉ ክብደት ስላለው ወደ መሬት ሲወድቅ እብቁን ግን ነፋስ ይወስደዋል።

ሩት ሠራተኞቹ ሥራቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ በማትታይበት ቦታ ሆና ጠበቀች። ቦዔዝ ሠራተኞቹ እህሉን እያዘሩ ምርቱን ከገለባው በመለየት አንድ ቦታ ላይ ሲቆልሉ ይከታተላል። ቦዔዝ ራቱን በደንብ ከበላ በኋላ በተቆለለው እህል አጠገብ ተኛ። አውድማ ላይ ማደር የተለመደ ነገር የነበረ ይመስላል፤ ምናልባትም ይህ የሚደረገው ብዙ ጉልበት የፈሰሰበትን ምርት ከሌቦችና ከወንበዴዎች ለመጠበቅ ተብሎ ይሆናል። ሩት፣ ቦዔዝ መተኛቱን ባየች ጊዜ ኑኃሚን የነገረቻትን ነገር የምትፈጽምበት ሰዓት እንደደረሰ ተገነዘበች።

ሩት ቀስ ብላ ወደ ቦዔዝ ተጠጋች፤ ልቧ በኃይል እየደለቀ ነው። ሰውየው ጭልጥ ያለ እንቅልፍ እንደወሰደው ከሁኔታው ማስተዋል ስለቻለች ልክ ኑኃሚን እንደነገረቻት ወደ እሱ ሄዳ እግሩን ገለጠችና ጋደም አለች። ከዚያም የሚሆነውን ትጠብቅ ጀመር። ጊዜው ነጎደ። እነዚያ ጥቂት ሰዓታት ለሩት የዓመታት ያህል ረዝመውባት መሆን አለበት። በመጨረሻም እኩለ ሌሊት አካባቢ ቦዔዝ መገላበጥ ጀመረ። ቅዝቃዜ ስለተሰማው ምናልባትም ለሌሊቱ ቁር የተጋለጠ እግሩን ለመሸፈን ሳይሆን አይቀርም ቀና አለ። በዚህ ጊዜ እግሩ ሥር የተኛ ሰው እንዳለ ታወቀው። ዘገባው “አንዲት ሴት እግርጌው ተኝታ አገኘ!” ይላል።—ሩት 3:8

ቦዔዝ “አንቺ ማነሽ?” ሲል ጠየቀ። ሩትም በፍርሃት ድምጿ እየተንቀጠቀጠ “እኔ አገልጋይህ ሩት ነኝ፤ መቤዠት የሚገባህ ቅርብ የሥጋ ዘመድ አንተ ነህና ልብስህን ጣል አድርግብኝ” ብላ መልስ ሰጠች። (ሩት 3:9) አንዳንድ ዘመናዊ ተንታኞች የሩት ድርጊትና የተናገረችው ነገር በተዘዋዋሪ የቀረበ የፆታ ጥያቄ እንደሆነ ቢገልጹም እነዚህ ግለሰቦች የዘነጓቸው ሁለት እውነታዎች አሉ። አንደኛ፣ ሩት ያደረገችው ነገር በወቅቱ የተለመደ ነበር፤ በዚያ ዘመን ከነበሩት ልማዶች ስለ አብዛኞቹ በዛሬው ጊዜ ያለን እውቀት ውስን ነው። ስለዚህ አድራጎቷን በዛሬው ጊዜ ካለው ወራዳ የሥነ ምግባር ሁኔታ አንጻር መመዘን ስህተት ይሆናል። ሁለተኛ፣ ቦዔዝ ለሩት የሰጣት መልስ በሥነ ምግባር ንጹሕ እንደሆነችና በጣም የሚያስመሰግን ጠባይ እንዳላት ሴት አድርጎ እንደተመለከታት የሚያሳይ ነው።

ሩት ወደ ቦዔዝ የሄደችው በንጹሕ ልብ እና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ዓላማ ነው

ቦዔዝ፣ ሩትን ያናገራት በደግነትና በሚያጽናና መንገድ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክሽ፤ ከዚህ በፊት ካደረግሽው ይልቅ ያሁኑ በጎነትሽ ይበልጣል፤ ባለጠጋም ሆነ ድኻ፣ ወጣት ወንድ ፈልገሽ አልሄድሽምና።” (ሩት 3:10) ቦዔዝ “ከዚህ በፊት ካደረግሽው” ሲል ሩት፣ ኑኃሚንን ተከትላ ወደ እስራኤል በመምጣትና አማቷን በመንከባከብ ያሳየችውን ታማኝ ፍቅር መግለጹ ነው። “ያሁኑ በጎነትሽ” ያለው ደግሞ በዚያ ምሽት ያደረገችውን ነገር ለመጥቀስ ነው። ቦዔዝ እንደ ሩት ያለች ወጣት ሴት ሀብታምም ይሁን ድሃ የፈለገችውን መርጣ ወጣት የሆነ ባል በቀላሉ ማግባት እንደምትችል ተረድቷል። ሩት ግን ለኑኃሚን ብቻ ሳይሆን ለሟቹ የኑኃሚን ባል ጭምር መልካም ማድረግ ፈልጋለች፤ የኑኃሚን ባል የዘር ሐረጉ እንዲቀጥል ማድረግ ስለምትችልበት መንገድ አስባ ነበር። ቦዔዝ፣ ይህች ወጣት በፈጸመችው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ድርጊት ልቡ የተነካው ለምን እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም።

ቦዔዝ በመቀጠል እንዲህ አላት፦ “አሁንም ልጄ ሆይ፤ አትፍሪ፤ የምትጠይቂውን ሁሉ አደርግልሻለሁ፤ አንቺ ምግባረ መልካም ሴት መሆንሽንም የአገሬ ሰው ሁሉ ያውቀዋል” አላት። (ሩት 3:11) ቦዔዝ፣ ሩትን የማግባት አጋጣሚ በማግኘቱ ደስ ብሎታል፤ ምናልባትም እሷን እንዲቤዣት ጥያቄ እንደሚቀርብለት ጠብቆ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ቦዔዝ ጻድቅ ሰው በመሆኑ ስለ ራሱ ፍላጎት ብቻ አላሰበም። ከእሱ ይልቅ ለኑኃሚን ቤተሰብ የሚቀርብና የመቤዠት ግዴታ ያለበት ሌላ ዘመድ ስላለ መጀመሪያ ያንን ሰው ቀርቦ እሷን ለማግባት ፈቃደኛ መሆኑን እንደሚጠይቀው ለሩት ገለጸላት።

ቦዔዝ፣ ሩትን እስኪነጋጋ ድረስ እዚያው እንድትተኛ ከዚያም ጎህ ከመቅደዱ በፊት ተነስታ ማንም ሳያያት ወደ ቤቷ እንድትሄድ ነገራት። ይህን ያለው የእሷም ሆነ የራሱ መልካም ስም እንዳይጎድፍ አስቦ ነው፤ ምክንያቱም  ሰዎች ቢያዩአት ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ነገር እንደተፈጸመ አድርገው በስህተት ሊያስቡ ይችላሉ። ሩት ላቀረበችው ጥያቄ ቦዔዝ በደግነት መልስ ስለሰጣት ጭንቀቷ ቀለል ብሎላት ተመልሳ በስተ ግርጌው ተኛች። ከዚያም ገና በደንብ ሳይነጋ ከእንቅልፏ ተነሳች፤ ከዚያም ቦዔዝ የደረበችውን ልብስ እንድትዘረጋው ከጠየቃት በኋላ ገብስ ሰፍሮ ሰጣት፤ እሷም የተሰጣትን እህል ተሸክማ ወደ ቤተልሔም ተመለሰች።

ሩት፣ በሰው ሁሉ ዘንድ “ምግባረ መልካም ሴት” በመሆኗ እንደምትታወቅ ቦዔዝ የነገራትን መለስ ብላ ስታስብ ምን ያህል ተደስታ ይሆን! ይሖዋን ለማወቅና እሱን ለማገልገል ያላት ጉጉት እንዲህ ያለ መልካም ስም እንድታተርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም ለእሷ ፈጽሞ እንግዳ የሆኑ ልማዶችንና ባሕሎችን ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆን ለኑኃሚንና ለሕዝቧ ታላቅ ደግነትና አሳቢነት አሳይታለች። እኛም ሩትን በእምነቷ የምንመስላት ከሆነ ለሌሎች እንዲሁም ለባሕላቸው ጥልቅ አክብሮት ለማሳየት እንጥራለን። እንዲህ ካደረግን እኛም እንደ ሩት በመልካም ምግባራችን ጥሩ ስም እናተርፋለን።

ለሩት የእረፍት ቦታ ተገኘ

ሩት ቤት ስትደርስ ኑኃሚን “ልጄ፣ አንቺ ማነሽ?” (NW) አለቻት። ምናልባትም ኑኃሚን እንዲህ ብላ የጠየቀቻት በደንብ ስላልነጋ ማንነቷን መለየት አቅቷት ሊሆን ይችላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኑኃሚን፣ ሩት የሚያገባት ሰው አግኝታለች ወይስ እንደ ቀድሞዋ ብቸኛ መበለት ናት የሚለውን ማወቅ ፈልጋ ይሆናል። ሩትም ከቦዔዝ ጋር የተነጋገሩትን በሙሉ ወዲያው ለአማቷ ነገረቻት። በተጨማሪም ቦዔዝ ለኑኃሚን የላከላትን ገብስ ሰጠቻት። *ሩት 3:16, 17

 ብልህ የሆነችው ኑኃሚን፣ በዚያ ቀን ለመቃረም ወደ እርሻው በመሄድ ፈንታ ቤት እንድትውል ሩትን መከረቻት። እንዲሁም “ጕዳዩ ዛሬውኑ እልባት ካላገኘ ሰውየው አያርፍም” የሚል ማረጋገጫ ሰጠቻት።—ሩት 3:18

ኑኃሚን ስለ ቦዔዝ የተናገረችው ነገር ትክክል ነበር። ቦዔዝ፣ አብዛኛውን ጊዜ የከተማዋ ሽማግሌዎች ወደሚሰባሰቡበት ወደ ከተማዋ በር ሄዶ ለኑኃሚን ቤተሰብ የቅርብ ዘመድ የሆነው ሰው እስኪመጣ ድረስ ጠበቀ። ከዚያም ቦዔዝ፣ ሰውየው ሩትን በማግባት ቤተሰቡን የመቤዠት መብት እንዳለው በምሥክሮች ፊት ነገረው። ይሁን እንጂ ሰውየው እንዲህ ማድረግ የራሱን ርስት አደጋ ላይ እንዲጥል ሊያደርገው እንደሚችል በመናገር ለመቤዠት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ገለጸ። ከዚያም ቦዔዝ፣ የኑኃሚን ሟች ባል የሆነውን የአቤሜሌክን ርስት በመግዛትና የአቤሜሌክ ልጅ የመሐሎን ሚስት የነበረችውን ሩትን በማግባት ቤተሰቡን እንደሚቤዥ በከተማዋ በር ባሉት ምሥክሮች ፊት ተናገረ። ቦዔዝ በዚህ መንገድ “የሟቹን ስም በርስቱ ላይ ለማስጠራት” ፈቃደኛ እንደሆነ ገለጸ። (ሩት 4:1-10) ቦዔዝ እውነትም ራስ ወዳድ ያልሆነ ቅን ሰው ነበር።

ቦዔዝ ሩትን አገባት። ዘገባው ከዚያ በኋላ ስለሆነው ነገር ሲገልጽ “እግዚአብሔር እንድትፀንስ አደረጋት፤ ወንድ ልጅም ወለደች” ይላል። የቤተልሔም ሴቶች ኑኃሚንን የመረቋት ሲሆን ሩትንም ከሰባት ወንዶች ልጆች ይልቅ ለኑኃሚን የምትሻል በመሆኗ አሞገሷት። ከጊዜ በኋላም የሩት ልጅ የንጉሥ ዳዊት አያት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሩት 4:11-22) ዳዊት ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት ነው።—ማቴዎስ 1:1 *

ይሖዋ ለሩት የመሲሑ ቅድመ አያት የመሆን መብት በመስጠት ባርኳታል

በእርግጥም ሩትም ሆነች ሕፃኑን እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ ያሳደገችው ኑኃሚን ተባርከዋል። የእነዚህ ሁለት ሴቶች ሕይወት፣ ይሖዋ ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ለማሟላት ደፋ ቀና ለሚሉና ከተመረጡ ሕዝቦቹ ጋር ሆነው በታማኝነት ለሚያገለግሉት ሁሉ ትኩረት እንደሚሰጥ የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። ይሖዋ እንደ ሩት በመልካም ምግባራቸው በእሱ ዘንድ ጥሩ ስም ለሚያተርፉ ታማኝ ሕዝቦቹ ወሮታ ከመክፈል ፈጽሞ ወደኋላ አይልም።

^ አን.4 በሐምሌ 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በእምነታቸው ምሰሏቸው—‘ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ’” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.10 ኑኃሚን እንደገለጸችው ይሖዋ ደግነት የሚያሳየው በሕይወት ላሉት ብቻ ሳይሆን ለሞቱትም ጭምር ነው። ኑኃሚን ባሏንና ሁለቱንም ወንዶች ልጆቿን በሞት አጥታለች። ሩትም ባሏን በሞት ተነጥቃለች። እነዚያ ሟች ሦስት ወንዶች በሁለቱ ሴቶች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደነበራቸው ጥርጥር የለውም። ሟቾቹ፣ ኑኃሚንን እና ሩትን ይወዷቸው ስለነበር እንክብካቤ እንዲደረግላቸው እንደሚፈልጉ የታወቀ ነው፤ በመሆኑም ለእነዚህ ሴቶች የሚደረግ ማናቸውም የደግነት ድርጊት ለሟቾቹ እንደተደረገ የሚቆጠር ነው።

^ አን.15 ከውርስ ጋር በተያያዘ እንደሚደረገው ሁሉ በዚህ ጊዜም ባሏ የሞተባትን ሴት የማግባት መብት በመጀመሪያ ለሟቹ ወንድሞች ይሰጣል፤ እነሱ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ይህ መብት የቅርብ ዘመዱ ለሆነ ወንድ ይተላለፍ ነበር።—ዘኍልቍ 27:5-11

^ አን.28 ቦዔዝ ለሩት ስድስት መስፈሪያ (መለኪያው አልተገለጸም) ገብስ መስጠቱ፣ ከስድስት የሥራ ቀናት በኋላ የሰንበት እረፍት እንደሚኖር ሁሉ ሩትም በመበለትነት ያሳለፈችው የልፋት ዘመን አብቅቶ ባል ማግባትና ኑሮ መመሥረት የሚያመጣውን እረፍት የምታገኝበት ጊዜ እንደቀረበ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ስድስት መስፈሪያ ገብስ (ምናልባትም በአካፋ እየዛቀ) የሰጣት ሩት ልትሸከም የምትችለው ይህን ያህል ብቻ ስለሆነ ሊሆን ይችላል።

^ አን.31 ሩት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ዝርዝር ውስጥ ከተጠቀሱት አራት ሴቶች መካከል አንዷ ናት። ሌላዋ ደግሞ የቦዔዝ እናት የሆነችው ረዓብ ናት። (ማቴዎስ 1:3, 5, 6) እንደ ሩት ሁሉ ረዓብም እስራኤላዊት አልነበረችም።