በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ክርስቲያን” የተባለ ሁሉ ክርስቲያን ነው?

“ክርስቲያን” የተባለ ሁሉ ክርስቲያን ነው?

“ክርስቲያን” የተባለ ሁሉ ክርስቲያን ነው?

በዛሬው ጊዜ ምን ያህል ክርስቲያኖች አሉ? አትላስ ኦቭ ግሎባል ክርስቲያኒቲ የተባለው መጽሐፍ በገለጸው መሠረት በ2010 በመላው ዓለም ወደ 2.3 ቢሊዮን የሚጠጉ ክርስቲያኖች ነበሩ። ይሁንና ይኸው ጽሑፍ እንደሚያመለክተው እነዚህ ክርስቲያኖች ከ41,000 በሚበልጡ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ውስጥ የታቀፉ ሲሆን እያንዳንዱ ቡድን የየራሱ መሠረተ ትምህርትና የሥነ ምግባር ደንብ አለው። ይህን ያህል ብዛት ያላቸው “የክርስትና” ሃይማኖቶች ከመኖራቸው አንጻር አንዳንዶች በሁኔታው ግራ ቢጋቡ፣ አልፎ ተርፎም ተስፋ ቆርጠው የሃይማኖትን ነገር እርግፍ አድርገው ቢተዉት አያስገርምም። እነዚህ ሰዎች፣ ‘ለመሆኑ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ በእርግጥ ክርስቲያኖች ናቸው?’ የሚለው ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይችላል።

እስቲ ጉዳዩን ከሌላ አቅጣጫ እንመልከተው። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ተጓዥ ወደ አንድ አገር ሲገባ ዜግነቱን እንዲናገር ይጠበቅበታል። በተጨማሪም ማንነቱን የሚያረጋግጥ መታወቂያ ወረቀት ምናልባትም ፓስፖርት በማሳየት የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን የሚጠቁም መረጃ ማቅረብ ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በክርስቶስ እንደሚያምን ከመናገር ባለፈ ተጨማሪ መለያ ሊኖረው ይገባል። ይህ መለያ ምንድን ነው?

“ክርስቲያን” የሚለው ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው በ44 ዓ.ም. ገደማ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ “ደቀ መዛሙርቱም በመለኮታዊ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ ‘ክርስቲያኖች’ ተብለው የተጠሩት በአንጾኪያ ነበር” በማለት ዘግቧል። (የሐዋርያት ሥራ 11:26) ክርስቲያኖች ተብለው የተጠሩት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደነበሩ ልብ በል። ይሁን እንጂ አንድን ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሚያስብለው ምንድን ነው? ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲዎሎጂ እንዲህ ይላል፦ “የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ሲባል በሕይወት እስካሉ ድረስ . . . መላ ሕይወትን ያለ ገደብ መሥዋዕት ማድረግ ማለት ነው።” ስለዚህ አንድ ሰው እውነተኛ ክርስቲያን የሚባለው የክርስትና መሥራች የሆነውን የኢየሱስን ትምህርቶችና መመሪያዎች ሙሉ በሙሉ እና ያለ ምንም ገደብ የሚከተል ከሆነ ነው።

በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን እንደሆኑ ከሚናገሩት ብዙ ሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል እንዲህ ዓይነት ሰዎች ማግኘት ይቻላል? ኢየሱስ ራሱ፣ እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ ተለይተው ከሚታወቁበት ምልክት ጋር በተያያዘ ምን ብሏል? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንድትመረምር እናበረታታሃለን። በቀጣዮቹ ርዕሶች ውስጥ የኢየሱስን እውነተኛ ተከታዮች ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉንን እሱ የተናገራቸውን አምስት ነጥቦች እንመረምራለን። እንዲሁም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እነዚህን ብቃቶች እንዴት እንዳሟሉ እንመለከታለን። ከዚያም በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ከሚናገሩት ብዙ ሃይማኖቶች መካከል እነዚህን ብቃቶች እያሟሉ ያሉት እነማን እንደሆኑ ለማየት እንሞክራለን።