በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ይሰበካል’

‘ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ይሰበካል’

 ‘ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ይሰበካል’

“ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”​—ማቴዎስ 24:14

ይህ ምን ማለት ነው? የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ይጓዝ ነበር” ብሏል። (ሉቃስ 8:1) ኢየሱስ ራሱም “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 4:43) ምሥራቹን በከተሞችና በመንደሮች እንዲሰብኩ ደቀ መዛሙርቱን የላካቸው ሲሆን ቆየት ብሎም “እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል።​—የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ ሉቃስ 10:1

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ብቃት አሟልተዋል? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እሱ የነገራቸውን ለመፈጸም ጊዜ አልወሰደባቸውም። “በየቀኑ በቤተ መቅደስም ሆነ ከቤት ወደ ቤት ስለ ክርስቶስ . . . የሚናገረውን ምሥራች ያለማሰለስ ማስተማራቸውንና ማወጃቸውን ቀጠሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 5:42) መስበክ ልዩ ቦታ ላላቸው የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተሰጠ ሥራ አልነበረም። የታሪክ ምሁር የሆነው ኒያንደር እንደሚከተለው ብሏል፦ “ክርስትናን በመቃወም የጻፈው የመጀመሪያ ሰው ይኸውም ሴልሰስ ሸማኔዎች፣ ጫማ ሠሪዎች፣ ቆዳ ፋቂዎች፣ ያልተማሩና ተራ የሆኑ ሰዎች ቀናተኛ የወንጌሉ ሰባኪዎች በመሆናቸው አፊዟል።” ዣን በርናርዲ የቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ታሪክ (እንግሊዝኛ) በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “[ክርስቲያኖች] በየቦታው እየሄዱ ላገኙት ሰው ሁሉ መናገር ነበረባቸው። በአውራ ጎዳናዎችና በከተሞች፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው አደባባዮችና በየቤቱ እየሄዱ ለሚያገኟቸው ሰዎች ሁሉ መናገር ነበረባቸው። ተቀባይነት ቢያገኙም ባያገኙም . . . እስከ ምድር ጫፍ ድረስ መስበክ ነበረባቸው።”

በዛሬው ጊዜ ብቃቱን የሚያሟሉት እነማን ናቸው? የአንግሊካን ቄስ የሆኑት ዴቪድ ዋትሰን “በዛሬው ጊዜ በሰፊው ለሚታየው የመንፈሳዊ ፍላጎት መጥፋት አንዱ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን መስበክና ማስተማርን በቁም ነገር  አለመፈጸሟ ነው” በማለት ጽፈዋል። ሆሴ ሉዊስ ፔሬስ ጉዋዳሉፔ ካቶሊኮች ቤተ ክርስቲያኗን እየተዉ ያሉት ለምንድን ነው? (እንግሊዝኛ) በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ኢቫንጀሊካሎች፣ አድቬንቲስቶችና ሌሎች ሃይማኖቶችም ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሲጽፉ “ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ አይሰብኩም” ብለዋል። የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ግን “ሥርዓት ባለው መንገድ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ይሰብካሉ” በማለት ጽፈዋል።

ካቶ ሱፕሪም ኮርት ሪቪው 2001-2002 በሚለው ጽሑፍ ላይ ጆናታን ተርሌ የሰጡት በእውነታ ላይ የተመሠረተ አስተያየት ትኩረት የሚስብ ነው፤ እንዲህ ብለዋል፦ “ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብታነሱ አብዛኞቹ ሰዎች ወዲያውኑ ወደ አእምሯቸው የሚመጡት በአጉል ሰዓት ቤታችንን የሚያንኳኩት ሰባኪዎች ናቸው። ለይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ፣ እምነታቸውን ለማራመድ ሲሉ ብቻ የሚያደርጉት ሳይሆን ለእምነታቸው አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው።”

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ምልክቶቹን አስተዋልካቸው?

እስከ አሁን ባየናቸው ተከታታይ ርዕሶች ላይ ከተወያየንባቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች አንጻር በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች እነማን ይመስሉሃል? ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ቢኖሩም ኢየሱስ ለተከታዮቹ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል፦ “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ነው።” (ማቴዎስ 7:21) የአብን ፈቃድ እያደረጉ ያሉትን ይኸውም የእውነተኛውን ክርስትና ምልክቶች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያሳዩትን ክርስቲያኖች ለይቶ ማወቅና ከእነሱ ጋር መተባበር በአምላክ መንግሥት ሥር ዘላለማዊ በረከቶችን ለማግኘት ያበቃል። ይህን መጽሔት ያመጡልህን የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡህ እንድትጠይቃቸው እናበረታታሃለን።​—ሉቃስ 4:43