በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘመናችን አዝቴኮች እውነተኛ ክርስትናን ተቀበሉ

የዘመናችን አዝቴኮች እውነተኛ ክርስትናን ተቀበሉ

 የዘመናችን አዝቴኮች እውነተኛ ክርስትናን ተቀበሉ

“ቤተ መቅደሶቹ ፈራርሰው ትቢያና አመድ ሆኑ፤ ጣዖታቱ ተደመሰሱ፤ ቅዱስ መጻሕፍቱንም እሳት በላቸው፤ ይሁን እንጂ የጥንቶቹ አማልክት ከሕንዶቹ ልብ ውስጥ አልወጡም።”​—ላስ አንቲግዋስ ኩልቱራስ ሜኺካናስ (የጥንቶቹ ሜክሲካውያን ባሕል)

የሜክሲኮ ነዋሪዎች የሆኑት አዝቴኮች ወደዚች አገር ፈልሰው የመጡት በ13ኛው መቶ ዘመን ነበር፤ በወቅቱ አነስተኛ ቁጥር የነበራቸው የዚህ ጎሣ አባላት ከጊዜ በኋላ በፔሩ ከነበረው የኢንካዎች ግዛት ጋር የሚመጣጠን ታላቅ ግዛት ለመመሥረት በቅተዋል። በ1521 ቴኖችቲትላንን ስፔናዊው ኸርናንዶ ኮርቴስ ድል አድርጎ ሲቆጣጠር የአዝቴክ ንጉሣዊ አገዛዝ ቢወድቅም የአዝቴኮች ቋንቋ የሆነው ናዋትል ግን ፈጽሞ አልሞተም። * ይህን ቋንቋ፣ ቢያንስ በ15 የሜክሲኮ ግዛቶች የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን ተኩል የአገሬው ተወላጆች አሁንም ድረስ ይጠቀሙበታል። ቫልተር ክሪክበርግ የተባሉት በመግቢያው ላይ ያለውን ሐሳብ የተናገሩት ተመራማሪ እንደገለጹት ይህ ቋንቋ እስካሁን ድረስ አለመጥፋቱ የጥንቶቹ አዝቴኮች አንዳንድ እምነቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከእነዚህ እምነቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

እንግዳ ሆኖም የተለመዱ ባሕሎች

አዝቴኮች በሰፊው የሚታወቁት ሰዎችን መሥዋዕት አድርገው በማቅረባቸው ሳይሆን አይቀርም። ይህ ልማድ የተመሠረተው ፀሐይ የሰዎች ልብና ደም ካልቀረበላት እንደምትሞት በሚገልጸው እምነት ላይ ነው። የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መነኩሴ የሆነው ስፔናዊው ዲዬጎ ዱራን እንደገለጸው ከሆነ በ1487 በቴኖችቲትላን ትልቁ የፒራሚድ ቤተ መቅደስ በተመረቀበት ወቅት በአራት ቀናት ውስጥ ከ80,000 የሚበልጡ ሰዎች መሥዋዕት ተደርገዋል።

ስፔናውያኑ ይህ የአዝቴኮች ልማድ ቢዘገንናቸውም በርካታ የአዝቴክ እምነቶች ከራሳቸው ይኸውም ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነቶች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸው አስገርሟቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አዝቴኮች ከሥርዓተ ቁርባን ጋር የሚመሳሰል ልማድ የነበራቸው ሲሆን በዚህ ሥርዓት ላይ ከበቆሎ የተሠሩ የአማልክቶቻቸውን ምስሎች፣ አንዳንድ ጊዜም መሥዋዕት አድርገው ያቀረቧቸውን ሰዎች ሥጋ ይበሉ ነበር። አዝቴኮች በመስቀል ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን ኃጢአትን የመናዘዝና ሕፃናትን የማጥመቅ ልማድ ነበራቸው። ምናልባትም በካቶሊኮችና በአዝቴኮች መካከል ያለው ከሁሉ ይበልጥ አስገራሚ የሆነው ተመሳሳይነት የድንግል ቶናንጺን አምልኮ ሳይሆን አይቀርም፤ “የአማልክት እናት” እንደሆነች የምትታሰበውን ቶናንጺንን አዝቴኮች ትንሿ እናታችን እያሉ ይጠሯታል።

የናዋትል ቋንቋ ተናጋሪና ካቶሊክ የሆነች ጥቁር የጓዴሎፕ ድንግል፣ አዝቴኮች ቶናንጺንን በሚያመልኩበት ተራራ ላይ ለአንድ የአዝቴክ ሕንድ በ1531 እንደታየች ይታመናል። ይህም አዝቴኮች የካቶሊክን ሃይማኖት ቶሎ እንዲቀበሉ አድርጓቸዋል። የቶናንጺን ቤተ መቅደስ በተመሠረተበት ቦታ ላይ ለዚህች ድንግል ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶላታል። በየዓመቱ ታኅሣሥ 12 ቀን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖተኛ ሜክሲካውያን (አብዛኞቹ የናዋትል ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው) ይህን ቤተ ክርስቲያን ይጎበኙታል።

የናዋትል ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት ማኅበረሰቦች የሚኖሩት ርቀው በሚገኙት ተራሮች ላይ ሲሆን በዚያም ይጠብቁናል ብለው የሚያምኑባቸውን ቅዱሳን ለማክበር በርካታ በዓላትን ያዘጋጃሉ፤ ከእነዚህ  በዓላት አንዳንዶቹ ለቀናት አልፎ ተርፎም ለሳምንታት የሚቆዩ ናቸው። ኤል ኡኔቬርሶ ዴ ሎስ አስቴካስ (የአዝቴኮች ዓለም) የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚገልጸው የአገሬው ተወላጆች “በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለቅዱሳን የሚቀርበውን አምልኮ [ከስፔናዊው ቅኝ ገዥ] ከኮርቴስ ዘመን በፊት ይካሄዱ ከነበሩት ሥርዓቶች ጋር ያያይዟቸዋል።” የናዋትል ሕዝቦች በመናፍስታዊ እምነትም በእጅጉ የተጠላለፉ ናቸው። በሚታመሙበት ጊዜ የማንጻት ሥርዓት ወደሚፈጽሙና የእንስሳት መሥዋዕቶችን ወደሚያቀርቡ ፈዋሾች ይሄዳሉ። ከዚህም በላይ አብዛኛው ሕዝብ ማንበብና መጻፍ አይችልም፤ ብዙዎቹ ስፓንኛም ሆነ የናዋትል ቋንቋን ማንበብ አይችሉም። ባሕላቸውንና ቋንቋቸውን የሙጥኝ ብለው የያዙ ከመሆናቸውም ሌላ በድህነት አረንቋ የተዘፈቁ ስለሆኑ በጥቅሉ ሲታይ ከማኅበረሰቡ ተገልለዋል።

የዘመናችን አዝቴኮች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ደረሳቸው

በሜክሲኮ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለሁሉም ሕዝቦች “የመንግሥቱን ምሥራች” ለማድረስ ለብዙ ዓመታት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። (ማቴዎስ 24:14) በሜክሲኮ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በ2000 ለሁሉም የናዋትል ተናጋሪዎች በራሳቸው ቋንቋ ለመስበክ፣ በስፓንኛ በሚደረጉ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለሚገኙት ደግሞ በቋንቋቸው ጉባኤዎች እንዲቋቋሙላቸው ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በናዋትል ለማዘጋጀት አንድ የትርጉም ቡድን ተቋቋመ። በተጨማሪም የናዋትል ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦችን በራሳቸው ቋንቋ ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ለማስተማር ጥረት ተደርጓል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ቀጥሎ የቀረቡትን ተሞክሮዎች እንመልከት።

የአገሬው ተወላጅ የሆነች አንዲት ሴት ለመጀመሪያ ጊዜ በናዋትል ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ስትሰማ እንደሚከተለው በማለት በደስታ ተናግራለች፦ “ለአሥር ዓመታት በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ የቆየን ቢሆንም ስፓንኛ በደንብ ስለማንችል ስብሰባው ራስ ምታት ይሆንብን ነበር። እውነትን እንደ አዲስ የሰማን ያህል ነው!” የስልሳ ዓመቱ ኽዋን ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ለስምንት ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ያጠና እንዲሁም በስፓንኛ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ የነበረ ቢሆንም ምንም ዓይነት እድገት አላደረገም። መጽሐፍ ቅዱስን በናዋትል ቋንቋ ማጥናት ሲጀምር ግን ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ!

እነዚህ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ብዙዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሰሙት በስፓንኛ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ አልተረዱትም። በየሳምንቱ የሚደረጉትንም ሆነ ትልልቅ ስብሰባዎችን በራሳቸው ቋንቋ መካፈላቸው እንዲሁም በቋንቋቸው ጽሑፎችን ማግኘታቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመረዳትና ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻቸውን ለመገንዘብ አስችሏቸዋል።

መሰናክሎችን መወጣት

የናዋትል ሕዝቦች መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የቻሉት ያለ ምንም እንቅፋት አልነበረም። ለምሳሌ ያህል፣ በሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ላይ እንዲካፈሉ ብዙ ጫና ይደረግባቸው ነበር። በሳን አጉስቲን ኦኣፓን የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ እንዲሰብኩ አልተፈቀደላቸውም ነበር። ይህ የሆነው የይሖዋ ምሥክሮች ስብከት ሕዝቡ ለበዓላቱ ድጋፍ የሚሆን ገንዘብ መስጠት እንዲያቆም ያደርገዋል የሚል ስጋት ስለተፈጠረ ነው። ፍሎራንስዮ እና የናዋትል ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች በስብከት ላይ ሳሉ ከመካከላቸው ሦስቱ ተይዘው ታሰሩ። በ20 ደቂቃ ውስጥ፣ በእነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመምከር ብዙ ሰዎች ተሰባሰቡ።

“እዚያው ሊገድሉን አስበው ነበር” በማለት ፍሎራንስዮ ሁኔታውን ያስታውሳል። “አንዳንዶች ታስረን ወንዝ ውስጥ እንድንጣል ሐሳብ አቅርበው ነበር። የዚያን ዕለት እስር ቤት አሳደሩን። በቀጣዩ ቀን ጠበቃ የሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክርና ሌሎች ሁለት ወንድሞች ሊረዱን መጡ። ሆኖም እነሱንም ወኅኒ ቤት አስገቧቸው። በመጨረሻም ባለሥልጣናቱ ከከተማው እንድንወጣ በማስጠንቀቅ ሁላችንንም ለቀቁን።” እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ቢፈጠርም ከአንድ ዓመት በኋላ በዚያ ቦታ ጉባኤ ተቋቋመ፤ በዚህ ጉባኤ ውስጥ 17 የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ያሉ ሲሆን 50 ያህል ሰዎች በስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ።

ኮኣፓላ በሚባል የናዋትል ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖረውና የይሖዋ ምሥክር የሆነው አልቤርቶ በአካባቢው በሚካሄድ ክብረ በዓል ላይ እንዲካፈል ተጋብዞ ነበር። አልቤርቶ ግብዣውን ስላልተቀበለ ታሰረ። በማኅበረሰቡ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ የተጠራ ሲሆን አንዳንዶች፣ የእሱን ሃይማኖት በመከተል የአካባቢውን ባሕል ለመተው ለሚፈልጉ ሁሉ መቀጣጫ እንዲሆን አልቤርቶ በስቅላት እንዲቀጣ ጫና ለማሳደር ሞከሩ። እሱን ለማስፈታት ጥረት ያደረጉ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮችም ታሰሩ። ሆኖም ለአንድ ሳምንት ያህል የዘለቀው በዓል ሲያበቃ ሁሉም በነፃ ተለቀቁ። ተቃውሞው እየቀጠለ በመሄዱ የከፍተኛ ባለሥልጣናትን እርዳታ  መሻት ግድ ሆነ፤ በመጨረሻም ስደቱን የሚያስቆም መመሪያ ተላለፈ። የሚገርመው ነገር፣ ዋነኛው ተቃዋሚ ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበለ ሲሆን አሁን ተጠምቋል። በዛሬው ጊዜ በዚያ ከተማ አንድ ጉባኤ ተቋቁሟል።

አዝመራው ደርሷል

ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች የናዋትል ሕዝቦች በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ እድገት ሊኖር እንደሚችል ስላስተዋሉ ይህን ቋንቋ እየተማሩ ነው። እርግጥ ይህን ማድረግ ተፈታታኝ ነው። ምክንያቱም የናዋትል ሕዝቦች በጣም ዓይናፋር ከመሆናቸውም ሌላ ከደረሰባቸው በደል የተነሳ በቋንቋቸው ለመናገር አይደፍሩም። ከዚህም በተጨማሪ ቋንቋው ብዙ ቀበሌኛዎች አሉት።

የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነችው ሶኒያ ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመጋፈጥ ያነሳሳትን ምክንያት እንደሚከተለው በማለት ትገልጻለች፦ “ከቤቴ የሁለት ሰዓት መንገድ በሚርቅ ቦታ ላይ በዘበኛ በሚጠበቁ መጠለያዎች ውስጥ የሚኖሩ 6,000 የሚያህሉ ናዋትል ተናጋሪ ሠራተኞች አሉ። እነዚህ ሰዎች ውርደት የደረሰባቸውና ምስኪኖች ናቸው። የናዋትል ሰዎች የባሕላችን መሠረት የሆኑ ኩሩ ሕዝቦች ስለነበሩ ሁኔታቸው በጣም አሳዘነኝ። ለ20 ዓመታት ያህል በስፓንኛ ምሥራቹን ስንሰብክላቸው ብንቆይም ሙሉ በሙሉ የማይረዱት ከመሆኑም ሌላ እምብዛም ፍላጎት አላሳዩም። ይሁን እንጂ ከቋንቋቸው ውስጥ ጥቂት ቃላትን ስማር ከእነሱ ጋር ለመነጋገር አጋጣሚ አገኘሁ። ዙሪያዬን ከበው ያዳምጡኝ ጀመር። ከሴቶቹ አንዷን የናዋትል ቋንቋ የምታስተምረኝ ከሆነ እኔ ደግሞ ማንበብና መጻፍ ላስተምራት እንደምችል ሐሳብ አቀረብኩላት። አሁን በመጠለያዎቹ በሙሉ የምታወቀው ‘ናዋትል የምትናገረው ሴት’ ተብዬ ነው። በአገሬ ውስጥ ሚስዮናዊ እንደሆንኩ ይሰማኛል።” በዛሬው ጊዜ በዚያ አካባቢ አንድ የናዋትል ቋንቋ ጉባኤ ተቋቁሟል።

ማሪሴላ የተባለችው የሙሉ ጊዜ አገልጋይም የናዋትልን ቋንቋ ለመማር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው። መጀመሪያ ላይ ማሪሴላ፣ ፌሊክስ የሚባሉትን የ70 ዓመት አረጋዊ መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናቸው ነበር። ማሪሴላ የናዋትልን ቋንቋ በደንብ እያወቀች ስትሄድ የምታስተምራቸውን ነገር በራሳቸው ቋንቋ ታብራራላቸው ጀመር። ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። እኚህ ሰው “ይሖዋ በናዋትል ቋንቋ ሳናግረው ያዳምጠኛል?” ብለው ሲጠይቋት ማሪሴላ ምን እንደተሰማት መገመት ይቻላል። እኚህ ሰው፣ ይሖዋ ሁሉንም ቋንቋዎች እንደሚያውቅ ሲማሩ በጣም ደስ አላቸው። አረጋዊው ፌሊክስ ምንም እንኳ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ለአንድ ሰዓት ተኩል በእግር መጓዝ ቢኖርባቸውም አዘውትረው የሚሰበሰቡ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ተጠምቀዋል። ማሪሴላ “ለሕዝቦች ሁሉ የሚሰበከውን ምሥራች ከያዘው መልአክ ጋር መተባበር በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ!” ብላለች።​—ራእይ 14:6, 7

በእርግጥም የናዋትል ሕዝቦች ባሉበት ማሳ ‘አዝመራው ነጥቷል።’ (ዮሐንስ 4:35) ይሖዋ አምላክ፣ የዘመናችንን አዝቴኮች ጨምሮ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሕዝቦች የእሱን መንገዶች ለመማር ወደ ተራራው እንዲወጡ መጋበዙን እንዲቀጥል እንጸልያለን።​—ኢሳይያስ 2:2, 3

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ናዋትል ከዩቶ-አዝቴክ ቋንቋዎች አንዱ ነው፤ እንደ ሆፒ፣ ሾሾኒና ከማንቺ ያሉት በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ጎሣዎች የሚነጋገሩባቸው ቋንቋዎችም እዚሁ ምድብ ውስጥ ናቸው። እንደ ቶሜቶ፣ ቾክሌት፣ አቮካዶ እና ካዮቲ ያሉት ብዙ የናዋትል ቃላት እንግሊዝኛ ቋንቋ ውስጥ ገብተዋል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሜክሲኮ ሲቲ

በተለያዩ ክልሎች ያሉ የአዝቴክ ሕዝቦች

150,000

ከ1,000 በታች