በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማያ ሕዝቦች ያገኙት እውነተኛ ነፃነት

የማያ ሕዝቦች ያገኙት እውነተኛ ነፃነት

የማያ ሕዝቦች ያገኙት እውነተኛ ነፃነት

የማያ ሕዝቦች በጥንት ዘመን ባከናወኗቸው ታላላቅ ነገሮች በሰፊው ይታወቃሉ። በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አገር ጎብኚዎች እንደ ቺቼን ኢትሳና ኮባ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙትን አስደናቂ ፒራሚዶች ለማየት በሜክሲኮ ወደምትገኘው የዩካታን ባሕረ ገብ መሬት ይጎርፋሉ። ማያዎች አስገራሚ ከሆነው የምህንድስና ሙያቸው በተጨማሪ በሥነ ፈለክ ምርምር፣ በሒሳብና በሥነ ጽሑፍ ረገድ አስደናቂ ነገሮችን አከናውነዋል። ከዚህም ባሻገር ውስብስብ የሆነውን ሥዕላዊ የአጻጻፍ ስልትና የዜሮን ጽንሰ ሐሳብ አዳብረዋል፤ እንዲሁም 365 ቀናትን የያዘ የቀን መቁጠሪያ አዘጋጅተዋል።

ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው ለየት ያለ ሆኖ እናገኘዋለን። ማያዎች በርካታ አማልክትን የሚያመልኩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የፀሐይ፣ የጨረቃ፣ የዝናብ እና የበቆሎ አምላኮች ይገኙበታል። የሃይማኖት መሪዎቻቸው በኮከብ ቆጠራ የተካኑ ነበሩ። አምልኮታቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ዕጣንና ምስሎችን ይጠቀሙ፣ በገዛ አካላቸው ላይ ጉዳት ያደርሱ ብሎም ደም እስኪፈሳቸው ድረስ ሰውነታቸውን ያቆስሉ የነበረ ሲሆን ሰዎችን በተለይ ደግሞ እስረኞችን፣ ባሪያዎችንና ልጆችን መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር።

ስፔናውያን ወደ አካባቢው መጡ

ስፔናውያን በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የማያ ሕዝቦች ወደሚኖሩበት አካባቢ ሲመጡ የነበረው ሁኔታ ከላይ የተገለጸውን ይመስላል። ስፔናውያኑ ወደዚህ የመጡት ሁለት ዓላማ ይዘው ነበር፤ ይኸውም ምድሪቱን ተቆጣጥረው ሀብቷን ለመውሰድና ሕዝቡን ኋላ ቀር ከሆነው የባዕድ አምልኮ በማላቀቅ የካቶሊክን እምነት እንዲቀበል ለማድረግ ነው። ታዲያ ስፔናውያኑ ለማያዎች በሃይማኖትና በሌሎች ነገሮች ረገድ እውነተኛ ነፃነት አስገኝተውላቸዋል?

የካቶሊክ ቀሳውስትና ሌሎች ስፔናውያን፣ ማያዎች ከበርካታ ዘመናት አንስቶ ጫካን በመመንጠርና በማቃጠል ለእርሻ ይጠቀሙበት የነበረውን መሬት ወሰዱባቸው። ይህም ከፍተኛ ችግር ያስከተለ ከመሆኑም በላይ በመካከላቸው የከረረ ጥላቻ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ስፔናውያኑ በዩካታን ባሕረ ገብ መሬት ለሚኖሩ ሰዎች ብቸኛ የውኃ ምንጭ የሆኑትን ጥልቅ ጉድጓዶችም ተቆጣጥረው ነበር። መንግሥት በነዋሪዎቹ ላይ ከጣለው ከፍተኛ ቀረጥ በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያኒቱ እያንዳንዱ ወንድ 12 ተኩል፣ ሴቶቹ ደግሞ 9 ሪል * በየዓመቱ ቀረጥ እንዲከፍሉ ትዕዛዝ ማውጣቷ ሁኔታውን ይበልጥ አስከፊ አደረገው። ይህ መሆኑ ለስፔናውያን ባለ ርስቶች ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፤ ምክንያቱም እነዚህ ባለ ርስቶች ቤተ ክርስቲያኒቱ የጣለችባቸውን ቀረጥ ለነዋሪዎቹ ከከፈሉላቸው በኋላ ሰዎቹ ዕዳቸውን ከፍለው እስኪጨርሱ ድረስ ከባርነት በማይተናነስ ሁኔታ እንዲያገለግሏቸው ያስገድዷቸው ነበር።

ቀሳውስቱም ቢሆኑ እንደ ጥምቀት፣ ሠርግና ቀብር ለመሳሰሉ አገልግሎቶች ክፍያ ይጠይቁ ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ ከማያዎቹ ከወሰደችው መሬትና ከልዩ ልዩ አገልግሎቶች በምታገኘው ገቢ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ሰው በምትሰበስበው ቀረጥ በልጽጋለች። ገበሬዎቹ አጉል እምነት እንደሚከተሉና የመረዳት ችሎታቸው ዝቅተኛ እንደሆነ ተደርገው ይታዩ ነበር። በመሆኑም ቀሳውስቱና ሥልጣን ያላቸው ሌሎች ሰዎች ማያዎች ሥርዓት እንዲማሩና አጉል እምነት ከመከተል እንዲርቁ ለማድረግ እነሱን መግረፍ ተገቢ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር።

ከጭቆና ለመላቀቅ የተደረገ ጦርነት

ማያዎች መጀመሪያ ላይ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቀረጥ ባለመክፈል፣ ልጆቻቸውን ከሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች በማስወጣት፣ ይከታተሉት የነበረውን መንፈሳዊ ትምህርት በማቆም እንዲሁም በእርሻ ቦታዎች ላይ ለመሥራት ፈቃደኛ ባለመሆን ተቃውሟቸውን ገለጹ። ይህ ግን ሁኔታውን ከማባባስ ውጪ የፈየደው ነገር አልነበረም። ስፔናውያኑ ለ300 ዓመታት ያህል ከገዟቸው በኋላ በመካከላቸው የነበረው ቅራኔ ተካርሮ በ1847 የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደረሰ። በዚህም የተነሳ ማያዎች ከጭቆና ለመላቀቅ ሲሉ “ከነጮቹ” ጋር ለመዋጋት ቆርጠው ተነሱ።

የአርበኞቹ መሪዎች በጦርነቱ ወቅት፣ ‘የሚያወራው መስቀል’ ብለው በሰየሙት ሃይማኖታዊ ምልክት ተጠቅመው ነበር። አንድ ሰው፣ ይህ መስቀል እንደተናገረ በማስመሰል ማያዎች እስከ ሞት ድረስ እንዲዋጉ ያበረታታ ነበር። ጦርነቱ በማያ ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ እልቂት አስከትሎባቸዋል። በ1853 ጦርነቱ ማብቃቱ በይፋ በተገለጸበት ወቅት በዩካታን ከሚኖሩት ማያዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በውጊያው አልቀው ነበር። ያም ሆኖ ለ55 ዓመታት ያህል ግጭቱ አልበረደም ነበር። በመጨረሻም ማያዎች ከስፔናውያኑ የጭቆና ቀንበር መላቀቅ የቻሉ ሲሆን ፍትሐዊ የሆነ የመሬት ክፍፍልም እንዲኖር ተደረገ። ሃይማኖታዊ ነፃነትን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?

እውነተኛ ነፃነት አላገኙም

ስፔናውያኑ ይዘውት የመጡት የካቶሊክ እምነትም ሆነ ከጭቆና ለመላቀቅ የተደረገው ጦርነት ለማያ ሕዝቦች እውነተኛ ነፃነት አላስገኘላቸውም። በዛሬው ጊዜ ማያዎች ስፔናውያን ወደ አካባቢው ከመምጣታቸው በፊት የነበራቸውን ልማድ ከሮም ካቶሊክ ወጎች ጋር አጣምሮ የያዘ እምነት ይከተላሉ።

ዘ ማያስ—3000 ይርስ ኦቭ ሲቪላይዜሽን የተባለው መጽሐፍ በዛሬው ጊዜ ስላሉት ማያዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ማያዎች በአንድ በኩል ጥንት ያመልኳቸው የነበሩትን የተፈጥሮ አማልክት ብሎም የቀድሞ አባቶቻቸውን በሜዳዎችና በተራሮች ላይ እንዲሁም በዋሻዎች ውስጥ ሲያመልኩ . . . በሌላ በኩል ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለቅዱሳን አምልኮ ያቀርባሉ።” ኬትሳልኮዋትል ወይም ኩኩልካን የተባለው አምላክ ከኢየሱስ ጋር፣ የጨረቃዋ አምላክ ደግሞ ከድንግል ማርያም ጋር አንድ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ለሆነው የሴበ ዛፍ የሚቀርበው አምልኮ በመስቀል አምልኮ የተተካ ሲሆን ሰዎችም ዛፍ ይመስል አሁንም ድረስ መስቀሉን ውኃ ያጠጡታል። የሚጠቀሙባቸው መስቀሎች የኢየሱስ ምስል ያለባቸው ሳይሆኑ በሴበ አበባ ያጌጡ ናቸው።

በመጨረሻ እውነተኛ ነፃነት አገኙ!

በቅርብ ዓመታት፣ በሜክሲኮ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለማያ ሕዝቦች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስተማር ሰፊ ዘመቻ አድርገዋል። አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ በተመለከተ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለመርዳት የማያ ሕዝቦች፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተዘጋጁ አሁን እንደምታነበው ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች እንዲደርሷቸው ተደርጓል። ታዲያ ምን ውጤት ተገኘ? ይህ ጽሑፍ በተዘጋጀበት ወቅት በአካባቢው በሚገኙ 241 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚሰበሰቡ 6,600 የሚያህሉ የማያ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የአምላክ መንግሥት ምሥራች አዋጅ ነጋሪዎች ነበሩ። ታዲያ ቀደም ሲል ይከተሏቸው የነበሩትን እምነቶች ትተው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መቀበል ለማያዎች ቀላል ነበር?

ቅን ልብ ያላቸው በርካታ የማያ ሕዝቦች እንዲህ ያለውን እርምጃ መውሰድ ከፍተኛ ትግል ማድረግ ጠይቆባቸዋል። ማርሴሊኖና ባለቤቱ ማርጋሪታ ቀናተኛ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ይሰማቸው ነበር። ለመስቀል ያላቸውን አክብሮት ለማሳየት በየዓመቱ መስቀሉን ከቤተ ክርስቲያን እስከ ቤታቸው ድረስ ተሸክመው ይወስዱታል። እዚያም የእንስሳ መሥዋዕት ያቀርቡና መሥዋዕቱን ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በመሆን ይበሉት ነበር። አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው ካነጋገሯቸው በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። “የምንማረው ነገር እውነት እንደሆነ ቢገባንም ቀደም ሲል እንከተለው የነበረውን እምነት ከተውን መናፍስት ጉዳት ያደርሱብናል ብለን ፈርተን ነበር” በማለት ተናግረዋል። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸውን አላቋረጡም። ማርሴሊኖ እንዲህ ብሏል፦ “ቀስ በቀስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ወደ ልባችን ዘልቆ መግባት ጀመረ። ይህ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርናቸውን ነገሮች ለቤተሰቦቻችንና ለጓደኞቻችን በድፍረት እንድንናገር አስችሎናል። በአንድ ወቅት ባሪያ አድርገውን ከነበሩት አጉል እምነቶች መላቀቅ በመቻላችን ደስተኞች ነን። ቅር የሚለን ነገር ቢኖር ቀደም ብለን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አለመጀመራችን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን አስደናቂ እውነቶች ለሌሎች ለመንገር የቻልነውን ያህል በማድረግ ከዚህ በፊት ያቃጠልነውን ጊዜ ማካካስ እንፈልጋለን።”

የ73 ዓመት አረጋዊ የሆኑት አልፎንሶ ቀናተኛ ካቶሊክ ነበሩ። በሚኖሩበት ከተማ ውስጥ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን ያደራጁ ነበር። በእነዚህ በዓላት ላይ ሥርዓተ ቁርባንና ጭፈራ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በዚያ ለተገኘው ሕዝብ ምግብና መጠጥ ይቀርባል። በተጨማሪም ሰዎች፣ ከኮርማዎች ጋር በመጋጠም ትርዒት ያሳዩ ነበር። አልፎንሶ እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ ክብረ በዓላት ወደመጠናቀቁ ሲቃረቡ የሰከሩ ሰዎች ረብሻ መፍጠራቸው የተለመደ ነው። በዓላቱ ቢያስደስቱኝም ሃይማኖቴ የሆነ ጉድለት እንዳለበት ይሰማኝ ነበር።” አልፎንሶ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ያቀረቡላቸውን ግብዣ ተቀበሉ። የጤንነት ችግር ያለባቸው ቢሆንም በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። በአሁኑ ጊዜ የድሮ ሃይማኖታዊ ልማዶቻቸውን እርግፍ አድርገው የተዉ ሲሆን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ሊጠይቋቸው ለሚመጡ ሰዎች ስለ ይሖዋ የተማሯቸውን ነገሮች ይነግሯቸዋል።

ከላይ የተመለከትነው፣ እውነተኛ ሃይማኖታዊ ነፃነት ካገኙት በርካታ ልበ ቅን የማያ ሕዝቦች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ነው። አዎን፣ በዩካታን የሚገኙትን አስደናቂ ፒራሚዶች የሠሩት የጥንቶቹ ማያዎች ዝርያ አሁንም ድረስ አለ። የሚናገሩት ቋንቋም አንድ ዓይነት ነው። ልክ እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው ብዙዎቹ የሚኖሩት የዘንባባ ክዳን ባላቸው የጭቃ ቤቶች ውስጥ ነው። በቆሎና ጥጥ ለማምረት የሚሆን መሬት የሚያዘጋጁት ልክ እንደጥንቱ ጫካን በመመንጠርና በማቃጠል ነው። በአሁኑ ጊዜ፣ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነት በርካታ ማያዎችን ከሐሰት ሃይማኖትና ከአጉል እምነት ቀንበር አላቋቸዋል። ኢየሱስ፣ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል” በማለት የተናገረውን ሐሳብ እውነተኝነት በራሳቸው ሕይወት ተመልክተዋል።—ዮሐንስ 8:32

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 ሪል የጥንት ስፔናውያን የመገበያያ ገንዘብ ነው።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የጥንቶቹ ማያዎች ተጽዕኖ አሳድረውባቸው የነበሩ አካባቢዎች

የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ

ሜክሲኮ

የዩካታን ባሕረ ገብ መሬት

ቺቼን ኢትሳ

ኮባ

ቤሊዝ

ጓቲማላ

ሆንዱራስ

ኤል ሳልቫዶር

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማያን ታሪክ የሚያሳዩ በቺቼን ኢትሳ የሚገኙ ቅርሶች

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርሴሊኖና ባለቤቱ ማርጋሪታ በዩካታን ስለ አምላክ መንግሥት ሲሰብኩ