በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች ብሉይ ኪዳንን ይቀበላሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ብሉይ ኪዳንን ይቀበላሉ?

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

የይሖዋ ምሥክሮች ብሉይ ኪዳንን ይቀበላሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ የአምላክ ቃል እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱት ከመሆኑም በተጨማሪ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ፈጽሞ የማይነጣጠሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደሆኑ ያምናሉ። ይሁንና ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን በመጀመሪያ የተጻፉት በዕብራይስጥና በግሪክኛ ስለሆነ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች “የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት” እና “የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት” በሚሉት ይበልጥ ተስማሚ የሆኑ ስሞች መጥራትን ይመርጣሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩ አንዳንዶች ብሉይ ኪዳንን አይቀበሉም። እነዚህ ሰዎች በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰው አምላክ እንደ ጦርነትና ግድያ የመሳሰሉ ነገሮችን እንዲሁም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከተገለጸው አፍቃሪና ጥሩ የሆነ አምላክ ጋር የማይስማሙ ሌሎች ድርጊቶችን የፈቀደ ቁጡ አምላክ እንደሆነ ይናገራሉ። ወይም ደግሞ፣ ብሉይ ኪዳን በአብዛኛው የሚናገረው ከአይሁዳውያን ሃይማኖት ጋር ስለተያያዙ ነገሮች ስለሆነ ለክርስቲያኖች እንደማይሠራ ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ በአምላክ ቃል ላይ መጨመርንም ሆነ ከቃሉ ላይ መቀነስን ከሚከለክለው በዘዳግም 12:32 ላይ ከተገለጸው ትእዛዝ አንጻር፣ ከላይ የቀረቡት ሐሳቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ሦስት አራተኛ የሚሆነውን ብሉይ ኪዳንን ላለመቀበል በቂ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ?

በ50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በግሪክ ወደምትገኘው ተሰሎንቄ ሄዶ ነበር። ይህ ሐዋርያ እዚያ በቆየበት ወቅት “ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነርሱ [ከተሰሎንቄ ነዋሪዎች] ጋር ተነጋገረ፤ ክርስቶስ መከራን መቀበል እንዳለበትና ከሙታንም መነሣት እንደሚገባው እያስረዳ [አረጋገጠላቸው]።” (የሐዋርያት ሥራ 17:1-3) ጳውሎስ ከሰበከላቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ክርስትናን የተቀበሉ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ይህ ሐዋርያ እንዲህ ሲል አመስግኗቸዋል፦ “ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ፣ . . . እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ [አልተቀበላችሁትም]።” (1 ተሰሎንቄ 2:13) ጳውሎስ በተሰሎንቄ በነበረበት ጊዜ ከ27ቱ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በወቅቱ ተጽፎ ያለቀው የማቴዎስ ወንጌል ብቻ ይመስላል። በመሆኑም ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ማስረጃ ለማቅረብ የተጠቀመባቸው “ቅዱሳት መጻሕፍት” የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

እንዲያውም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት 320 ጊዜ በቀጥታ የጠቀሱ ሲሆን በብዙ መቶዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ ደግሞ ከእነዚህ መጻሕፍት ላይ የተወሰዱ ሐሳቦችን በተዘዋዋሪ መንገድ አስፍረዋል። እነዚህ ጸሐፊዎች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የጠቀሱት ለምንድን ነው? ምክንያቱም “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል።” (ሮሜ 15:4) በዛሬው ጊዜም ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ የሚቀበሉ ሁሉ በእጅጉ እንደሚጠቀሙ ከዚህ በግልጽ መረዳት ይቻላል።

አምላክ ዓላማውን የሚገልጠው ደረጃ በደረጃ በመሆኑ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ በተጻፉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አማካኝነት ተጨማሪ እውነቶችን ገልጿል። እነዚህ መጻሕፍት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ያላቸውን ጠቀሜታ በምንም ዓይነት አይቀንሱትም። በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት ፕሮፌሰር የሆኑት ኸርበርት ፋርመር፣ የወንጌል ዘገባዎችን ለመረዳት “በጥንት ዘመን በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ከታቀፉት ሕዝቦች ጋር በተያያዘ ስለተፈጸሙት ነገሮች የሚናገረውን በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሰፈረውን ታሪክም ማወቅ” እንዳለብን ገልጸዋል።

የአምላክ ቃል ማሻሻያ አያስፈልገውም። ሆኖም “የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣ ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን ነው።” (ምሳሌ 4:18) አምላክ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዲሆኑ በማድረግ ዓላማው እንዴት እንደሚፈጸም ለማወቅ የሚያስችል ተጨማሪ ብርሃን ፈንጥቋል፤ እንዲህ ማድረጉ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጠቀሜታ እንደሌላቸው የሚያሳይ አይደለም። የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ‘ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው የይሖዋ ቃል’ ክፍል ናቸው።—1 ጴጥሮስ 1:24, 25