በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንጽሕና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ንጽሕና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

 ንጽሕና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

የሰው ዘር በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በወረርሽኝና በቸነፈር ሲሠቃይ ኖሯል። አንዳንድ ሰዎች እነዚህ ነገሮች የፈጣሪ ቁጣ እንደሆኑና አምላክ ክፉ ሰዎችን ለመቅጣት ብሎ እንዳመጣቸው ያስባሉ። ለበርካታ ዘመናት በትዕግሥትና በጥንቃቄ የተደረጉ ሰፊ ጥናቶች ደግሞ ለእነዚህ ወረርሽኞች “ተጠያቂ” የሚሆኑት በዙሪያችን የሚኖሩት ጥቃቅን ፍጥረታት እንደሆኑ አረጋግጠዋል።

አይጦች፣ በረሮዎች፣ ዝንቦችና የወባ ትንኞች በሽታ ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ የሕክምና ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል። በተጨማሪም አብዛኛውን ጊዜ ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ እንዲዛመቱ ምክንያት የሚሆነው ሰዎች ንጽሕናቸውን አለመጠበቃቸው እንደሆነ ደርሰውበታል። እንግዲያው ንጽሕናን መጠበቅ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል።

እርግጥ ነው፣ የንጽሕና ደረጃ እንደየአካባቢው ልማድና እንደየሁኔታው ይለያያል። የቧንቧ ውኃና በቂ የሆነ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር በሌለባቸው አካባቢዎች ንጽሕናን መጠበቅ በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። አምላክ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን፣ ንጽሕናን ለመጠበቅ ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ በነበረበት በምድረ በዳ እየተጓዙ ባለበት ወቅት እንኳ ንጽሕናን የሚመለከቱ መመሪያዎችን ሰጥቷቸዋል።

አምላክ ለንጽሕና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው? ንጽሕናን በተመለከተ ሊኖረን የሚገባው ተገቢ አመለካከትስ ምንድን ነው? አንተም ሆንክ ቤተሰብህ በሽታን ለመከላከል ምን ዓይነት ጥንቃቄዎችን ማድረግ ትችላላችሁ?

በካሜሩን የሚኖረው ማክስ * ከትምህርት ቤት ተለቅቆ ወደ ቤቱ እየሄደ ነው። ማክስ ርቦት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ውኃ ጠምቶታል። ወደ ትንሿ ቤቱ ሲገባ ውሻውን አቅፎ ሰላም ካለው በኋላ ቦርሳውን መመገቢያ ጠረጴዛው ላይ አስቀምጦ ምግብ እስኪቀርብለት ድረስ ቁጭ ብሎ መጠበቅ ጀመረ።

ማዕድ ቤት የነበረችው እናቱ የማክስን መምጣት ስትሰማ ትኩስ ሩዝና ባቄላ ይዛለት መጣች። ሆኖም ማክስ ቦርሳውን ንጹሕ በሆነው ጠረጴዛ ላይ እንዳስቀመጠ ስታይ ፊቷ ተለዋወጠ። ከዚያም ወደ ልጇ ተመለከተችና “ማክስ!” ብላ ስትጠራው ሁኔታው ስለገባው ወዲያው ቦርሳውን ከጠረጴዛው ላይ በማንሳት በፍጥነት እጁን ሊታጠብ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ፣ ሲጠብቅ የነበረውን ምግብ ለመብላት ተመልሶ መጣ። ጥፋተኛ መሆኑን እንደተገነዘበ በሚያሳይ መንገድ “ይቅርታ እማዬ፣ ረስቼው ነው” አለ።

 አሳቢ የሆነች አንዲት እናት ጤናንና ንጽሕናን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ልታደርጋቸው የምትችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እርግጥ የሁሉም የቤተሰቡ አባላት ትብብር ያስፈልጋታል። ከማክስ ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው ንጽሕናን መጠበቅ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግን የሚጠይቅ ከመሆኑም ሌላ ልጆች ሁልጊዜ ማሳሰቢያ ያስፈልጋቸዋል። ይህ ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ሥልጠና መስጠትን ይጠይቃል።

የማክስ እናት ምግብ በተለያዩ መንገዶች ሊበከል እንደሚችል ታውቃለች። ስለዚህ ምግብ ከማቅረቧ በፊት እጆቿን በሚገባ የምትታጠብ ከመሆኑም በላይ ዝንቦች እንዳያርፉበት ምግቡን ትሸፍነዋለች። የሚመገቧቸውን ምግቦች ከድና ስለምታስቀምጥ እንዲሁም ቤቱን በንጽሕና ስለምትይዝ በአይጦችና በበረሮዎች ምክንያት የሚመጡ ችግሮች አያጋጥሟትም ማለት ይቻላል።

የማክስ እናት እንዲህ ያለ ጥንቃቄ የምታደርግበት ዋነኛው ምክንያት አምላክን ማስደሰት ስለምትፈልግ ነው። “መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ቅዱስ ስለሆነ ሕዝቦቹም ቅዱስ መሆን እንዳለባቸው ይናገራል” ስትል ገልጻለች። (1 ጴጥሮስ 1:16) አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ቅዱስ መሆን ሲባል ንጹሕ መሆን ማለት ነው። በመሆኑም ቤቴም ሆነ ቤተሰቦቼ ንጹሕ እንዲሆኑ እፈልጋለሁ። እርግጥ ነው፣ ይህ ሊሆን የቻለው እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ ነው።”

በቤተሰብ መካከል ትብብር መኖሩ አስፈላጊ ነው

የማክስ እናት እንደተናገረችው የቤተሰቡን ንጽሕና ለመጠበቅ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል። አንዳንድ ቤተሰቦች ከንጽሕና ጋር በተያያዘ ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮችና በቤታቸውም ሆነ በግቢያቸው ውስጥ ማሻሻያ ማድረግ ስለሚችሉባቸው መንገዶች በየጊዜው ይወያያሉ። ይህ ደግሞ ቤተሰቡ እንዲቀራረብ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ እያንዳንዱ ግለሰብ የቤተሰቡን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ያለውን ድርሻ እንዲያስታውስ ያስችለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት እናት ለትላልቅ ልጆቿ ከመጸዳጃ ቤት ሲመለሱ፣ እንደ ገንዘብ ያሉ ነገሮችን በእጃቸው ከነኩ እንዲሁም ከምግብ በፊት እጃቸውን መታጠብ ያለባቸው ለምን እንደሆነ ልትነግራቸው ትችላለች። እነሱ ደግሞ በበኩላቸው ታናናሾቻቸው ይህን ጉዳይ በቁም ነገር እንዲመለከቱት ማድረግ ይችላሉ።

ሁሉም የቤተሰቡ አባላት የተለያዩ ሥራዎችን ተከፋፍለው ማከናወን ይችላሉ። ቤቱን በየሳምንቱ ለማጽዳት፣ በዓመት አንዴ ወይም ሁለቴ ደግሞ አጠቃላይ ጽዳት ለማድረግ ይወስኑ ይሆናል። ይሁንና ለአካባቢያችን ንጽሕናም ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ የሆኑት ስቴዋርት ዩዳል ዩናይትድ ስቴትስን አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የምንኖርበት አካባቢ ውበቱን እያጣ፣ መጥፎ ገጽታዎቹ እየበዙና ያሉት ባዶ  ቦታዎች እየጠፉ ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበከለ፣ ሁካታ እየበዛበት ብሎም ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ነው።”

አንተስ በአካባቢህ ስላለው ሁኔታ እንዲህ ይሰማሃል? በድሮ ጊዜ ሕዝቡን ለመቀስቀስ በየጎዳናው እየዞሩ ደወል የሚያሰሙ ሰዎች ነበሩ። በዛሬው ጊዜም በመካከለኛው አፍሪካ በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች ውስጥ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ነዋሪዎቹን፣ ከተማውን እንዲያጸዱ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮችን እንዲጠርጉ፣ ዛፎችን እንዲከረክሙ፣ አረም እንዲነቅሉና ቆሻሻ እንዲያስወግዱ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያሳስቧቸዋል።

ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ አለመቻል በዓለም ዙሪያ እየታየ ያለ ችግር ሲሆን ለበርካታ መንግሥታትም ራስ ምታት ሆኖባቸዋል። አንዳንድ ከተሞች ቆሻሻን ቶሎ ቶሎ ስለማያነሱ በየመንገዱ ላይ የተከማቸ ቆሻሻ ይታያል። እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ የከተማው ነዋሪዎች እርዳታ እንዲያደርጉ ሊጠየቁ ይችላሉ። እንዲህ ላለው ጥሪ በግንባር ቀደምትነት ምላሽ ከሚሰጡና ባለ ሥልጣናት የሚያወጡትን መመሪያ ያለማጉረምረም ከሚታዘዙ ሰዎች መካከል ክርስቲያኖችም ይገኙበታል። (ሮሜ 13:3, 5-7) እውነተኛ ክርስቲያኖች ጥሩ ዜጎች በመሆናቸው በዚህ ረገድ ከተጠየቁትም በላይ ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው። አካባቢያቸውን በንጽሕና የመያዝ ፍላጎት አላቸው እንዲሁም ማሳሰቢያ ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው ተነሳሽነት በጽዳት ሥራ ይካፈላሉ። ንጽሕናን መጠበቅ ጥሩ ሥልጠና የማግኘትና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው የመሆን ጉዳይ እንደሆነ ያውቃሉ። ንጽሕና የሚጀምረው ከእያንዳንዱ ግለሰብ ብሎም ከእያንዳንዱ ቤተሰብ ነው። በቤታችን አካባቢ ከንጽሕና ጋር በተያያዘ ቀላል የሚመስሉ ነገሮችን ማከናወን ጤንነትን ለመጠበቅና አካባቢው እንዲያምር ለማድረግ ያስችላል።

የግል ንጽሕናን መጠበቅ ለምናመልከው አምላክ ክብር ያመጣል

አካላዊ ንጽሕናችንን መጠበቃችን እንዲሁም አለባበሳችን የሚያስከብር መሆኑ የአምልኮታችን ክፍል ሲሆን ሰዎች ከሌሎች የተለየን መሆናችንን በቀላሉ እንዲያስተውሉም ያደርጋቸዋል። አሥራ አምስት የሚሆኑ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ፈረንሳይ ውስጥ በምትገኘው በቱሉዝ ከተማ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ባደረጉት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከተካፈሉ በኋላ ወደ አንድ ምግብ ቤት ጎራ አሉ። ወጣቶቹ ካሉበት አጠገብ ባለው ጠረጴዛ ላይ የነበሩ በዕድሜ የገፉ አንድ ባልና ሚስት ወጣቶቹ እየተንጫጩ ይረብሹናል ብለው አስበው ነበር። ሆኖም ባልና ሚስቱ፣ ጥሩ አለባበስ ያላቸው እነዚህ ወጣቶች ሥርዓታማ በመሆናቸውና ያደርጉ በነበረው ደስ የሚል ጭውውት ተገረሙ። ወጣቶቹ ከምግብ ቤቱ ሊወጡ ሲሉ ባልና ሚስቱ ስለ መልካም ባሕርያቸው ያመሰገኗቸው ከመሆኑም ባሻገር እንዲህ ዓይነቱ በምሳሌነት የሚጠቀስ ባሕርይ በዚህ ዘመን ብዙም እንደማይታይ ለአንዱ ወጣት ነገሩት።

የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮዎችና በውስጡ ያሉትን ማተሚያ ክፍሎች እንዲሁም መኖሪያ ቤቶች የሚጎበኙ ብዙ ሰዎች በእነዚህ ቦታዎች የሚያዩት ንጽሕና ይማርካቸዋል። በዚያ የሚኖሩት ፈቃደኛ ሠራተኞች ንጹሕ ልብስ መልበስ እንዲሁም እጃቸውንና ሰውነታቸውን አዘውትረው መታጠብ ይጠበቅባቸዋል። ዲዮድራንቶችንና ሽቶዎችን መጠቀም አካላዊ ንጽሕናን ላለመጠበቅ ምክንያት አይሆንም። የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆኑት እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ምሽት ላይ ወይም ቅዳሜና እሁድ የአምላክን ቃል ሲሰብኩም ንጹሕ ሆነው መታየታቸው ሰዎች ለመልእክቱ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል።

‘አምላክን ምሰሉ’

ክርስቲያኖች ‘አምላክን እንዲመስሉ’ ተመክረዋል። (ኤፌሶን 5:1) ነቢዩ ኢሳይያስ፣ መላእክት ፈጣሪን “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” በማለት ሲገልጹት የተመለከተውን ራእይ ዘግቧል። (ኢሳይያስ 6:3) ይህ መግለጫ አምላክ በንጽሕናው አቻ እንደሌለው ጎላ አድርጎ ያሳያል። በመሆኑም አምላክ አገልጋዮቹ በሙሉ ቅዱስ ማለትም ንጹሕ እንዲሆኑ እንደሚጠብቅባቸው ሲናገር “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብሏል።—1 ጴጥሮስ 1:16

መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች “ተገቢ የሆነ ልብስ” እንዲለብሱ ያበረታታል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው “የሚያንጸባርቅና ንጹሕ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ” አምላክ ቅዱስ አድርጎ የሚመለከታቸው ሰዎች የሚያከናውኑትን የጽድቅ ሥራ የሚያመለክት መሆኑ ምንም አያስገርምም። (ራእይ 19:8) በአንጻሩ ደግሞ ኃጢአት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙውን ጊዜ በእድፍና በቆሻሻ ተመስሏል።—ምሳሌ 15:26፤ ኢሳይያስ 1:16፤ ያዕቆብ 1:27

በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚኖሩት አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናን ለመጠበቅ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ በሚጠይቅ አካባቢ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ለዘለቄታው የሚወገደው አምላክ ‘ሁሉን ነገር አዲስ በሚያደርግበት’ ጊዜ ነው። (ራእይ 21:5) ይህ ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ ሁሉም ሰው አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናውን ጠብቆ ለዘላለም ይኖራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 ስሙ ተቀይሯል።

 [በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አምላክ ንጹሕ እንድንሆን ይጠብቅብናል

እስራኤላውያን በምድረ በዳ ጉዟቸው ወቅት ዓይነ ምድርን በሚያስወግዱበት ጊዜ ማድረግ ስላለባቸው ነገር ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳግም 23:12-14) በወቅቱ ከነበረው ሕዝብ ብዛት አንጻር ሲታይ ይህን ትእዛዝ መከተል አሰልቺ ሊመስል ይችላል፤ ይሁንና እንደ ታይፎይድና ኮሌራ ያሉ በሽታዎችን ለመከላከል እንደረዳቸው ጥርጥር የለውም።

ሕዝቡ በድን የነካውን ማንኛውንም ነገር እንዲያጥቡ ወይም እንዲያስወግዱ ታዘው ነበር። እስራኤላውያን ይህ ትእዛዝ የተሰጠበትን ምክንያት ላይረዱ ቢችሉም ሕጉን መከተላቸው ከተለያዩ በሽታዎች እንዲጠበቁ ረድቷቸዋል።—ዘሌዋውያን 11:32-38

ካህናቱ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚያከናውኑትን አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት እጃቸውንና እግራቸውን መታጠብ ይጠበቅባቸው ነበር። ለመታጠቢያ የሚሆነውን ውኃ በነሐስ ገንዳው ውስጥ መሙላት ቀላል ባይሆንም መታጠብ ግን የግድ ነበር።—ዘፀአት 30:17-21

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አንድ የሕክምና ባለሙያ የሰጡት ማሳሰቢያ

ውኃ ለሕይወት በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ከተበከለ ግን ለሕመምና ለሞት ሊዳርግ ይችላል። ካሜሩን ውስጥ በሚገኘው በዱዋላ ወደብ የሕክምና ክፍል ኃላፊ የሆኑ ኧምባንጌ ሎቤ የተባሉ ሐኪም ቃለ ምልልስ በተደረገላቸው ወቅት ጠቃሚ የሆኑ አንዳንድ ሐሳቦችን ሰጥተዋል።

“የምትጠጡት ውኃ ንጹሕ መሆኑን ከተጠራጠራችሁ አፍሉት።” ትኩረት ልናደርግበት ስለሚገባው ነገር ሲያስጠነቅቁ “ውኃው ንጹሕ እንዲሆን የሚረዱ የተለያዩ ኬሚካሎችን መጨመር ችግር ባይኖረውም ጥንቃቄ ካልተደረገ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ከመመገባችሁ በፊት እንዲሁም ከመጸዳጃ ቤት ስትወጡ ሁልጊዜ እጃችሁን በውኃና በሳሙና ታጠቡ። ሳሙና መግዛት ያን ያህል ወጪ የሚጠይቅ ስላልሆነ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎችም እንኳ መግዛት ይችላሉ። ልብሳችሁን በየጊዜው እጠቡ፤ የቆዳ በሽታ ካለባችሁ ደግሞ በሙቅ ውኃ ማጠባችሁ ጥሩ ይሆናል።”

ሐኪሙ በመቀጠል እንዲህ ብለዋል፦ “የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ቤታቸውንም ሆነ አካባቢያቸውን በንጽሕና መያዝ አለባቸው። መጸዳጃ ቤቶችና ዕቃ ቤቶች አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት ስለማይሰጣቸው የበረሮና የዝንብ መራቢያ ሊሆኑ ይችላሉ።” ከልጆች ጋር በተያያዘ ያስተዋሉትን አንድ አስፈላጊ ነገር አስመልክተው ሲያስጠነቅቁም እንዲህ ብለዋል፦ “በአካባቢያችሁ በሚገኙ ኩሬዎች ውስጥ ከመታጠብ ተቆጠቡ። ምክንያቱም ኩሬዎች አደገኛ በሆኑ ረቂቅ ነፍሳት የተሞሉ ናቸው። ከመተኛታችሁ በፊት ሁልጊዜ ገላችሁን ታጠቡ እንዲሁም ጥርሳችሁን ፋቁ ወይም ቦርሹ። በተጨማሪም አጎበር ተጠቀሙ።” እነዚህ ሁሉ ማሳሰቢያዎች የያዙትን መልእክት በሚከተለው መንገድ ማጠቃለል ይቻላል፦ ንጽሕናህን እንዴት መጠበቅ እንዳለብህ አስብ እንዲሁም ያሰብካቸውን ነገሮች ተግባራዊ አድርግ፤ እንዲህ ካደረግህ ከንጽሕና ጉድለት ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ችግሮች ራስህን መጠበቅ ትችላለህ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልብስን ማጠብ የቆዳ በሽታዎችን ለመከላከል ይረዳል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች በራሳቸው ተነሳስተው አካባቢያቸውን ያጸዳሉ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሳቢ የሆነች አንዲት እናት የቤተሰቧን ንጽሕና ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ልታደርጋቸው የምትችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ