በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መከራዎችን በጽናት መቋቋማችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት አጠናክሮልናል

መከራዎችን በጽናት መቋቋማችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት አጠናክሮልናል

 መከራዎችን በጽናት መቋቋማችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት አጠናክሮልናል

አዳ ዴሎ ስትሪቶ እንደተናገረችው

የዕለቱን ጥቅስ በማስታወሻ ደብተሬ ላይ ገልብጬ መጨረሴ ነው። ሠላሳ ስድስት ዓመቴ ቢሆንም እነዚያን ጥቂት መስመሮች ለመጻፍ ሁለት ሰዓት ወስዶብኛል። ለምን? ምክንያቱን እናቴ ትነግራችኋለች።—ጆኤል

እኔና ባለቤቴ የይሖዋ ምሥክር የሆንነው በ1968 ነበር። ዴቪድና ማርክ የተባሉ ሁለት ጤነኛ ልጆች የነበሩን ሲሆን በኋላም ጆኤል የተባለው ሦስተኛው ልጃችን ተወለደ። ጆኤል፣ ቤልጅየም ውስጥ ከብራስልስ በስተ ደቡብ 60 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ ቤንሽ የተባለች ከተማ ባለ ሆስፒታል ውስጥ በ1973 ተወለደ። ጆኤል የተወለደው ያለጊዜው ሲሆን በወቅቱ ክብደቱ 1.7 ኪሎ ግራም ብቻ ነበር። ከወለድኩ በኋላ እኔ ከሆስፒታል ስወጣ ጆኤል ግን ክብደቱ እስኪስተካከል ድረስ እዚያው መቆየት ነበረበት።

የተወሰኑ ሳምንታት ቢያልፉም የልጃችን ሁኔታ ባለመሻሻሉ እኔና ባለቤቴ ሉዊጂ ወደ አንድ የሕፃናት ሐኪም ወሰድነው። ዶክተሩ ጆኤልን ከመረመረው በኋላ “በጣም አዝናለሁ፤ ጆኤል የወንድሞቹን በሽታ ሁሉ የተሸከመ ይመስላል” አለን። ለተወሰነ ጊዜ ጸጥታ ሰፈነ። በዚህ ጊዜ ትንሹ ልጃችን ከባድ የጤና ችግር እንዳለበት ተገነዘብኩ። ዶክተሩ ባለቤቴን ለብቻው ወስዶ “ልጃችሁ ትራይሶሚ 21 አለበት” አለው፤ ይህ ሕመም ዳውን ሲንድሮም በመባልም ይታወቃል። *

ሐኪሙ በነገረን ነገር በጣም አዘንን፤ ከዚያም ጆኤልን ሌላ ስፔሻሊስት ሐኪም ጋር ለመውሰድ ወሰንን። ሐኪሙ ሕፃኑን ጆኤልን ለአንድ ሰዓት ያህል በጥንቃቄ መረመረው፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ አንድም ቃል አልተነፈሰም። እኔና ሉዊጂ ጊዜው የዓመት ያህል ረዝሞብን ነበር። በመጨረሻም ሐኪሙ “ልጃችሁ ሁልጊዜ የእናንተ እርዳታ ያስፈልገዋል” አለን። ከዚያም ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ “ለነገሩ ጆኤል የወላጆቹን ፍቅር ስለሚያገኝ ደስተኛ ይሆናል!” አለን። የተደበላለቀ ስሜት ተሰማኝ፤ ጆኤልን በቀስታ ክንዴ ላይ አድርጌ ከታቀፍኩት በኋላ ወደ ቤት ወሰድነው። በወቅቱ ሁለት ወሩ ነበር።

ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና አገልግሎት ብርታት ሰጥተውናል

ጆኤል ከዚያ በኋላ የተደረገለት ምርመራ እንዳሳየው የልቡ መጠን ጤናማ አልነበረም፤ እንዲሁም ከባድ  የሪኬትስ በሽታ ነበረበት። ልቡ በጣም ትልቅ ስለሆነና ሳንባዎቹን ስለሚጫናቸው ጆኤል ለኢንፌክሽን የተጋለጠ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ጆኤል ገና የአራት ወር ሕፃን እያለ የሳንባ ምች ስለያዘው እንደገና ሆስፒታል መግባት ነበረበት፤ በዚያም ከሰው ተገልሎ ለብቻው እንዲተኛ ተደረገ። ጆኤል ሲሠቃይ ማየት ለእኛ ከባድ ነበር። በእጃችን ታቅፈን ብንደባብሰው ደስ ይለን ነበር፤ ሆኖም ለሁለት ወር ከአሥራ አምስት ቀን ያህል እንድንነካው እንኳ አልተፈቀደልንም። በዚህ ጊዜ ውስጥ እኔና ሉዊጂ በጭንቀት ተውጠን የሚሆነውን ከመጠበቅና ከመጸለይ በቀር ልናደርገው የምንችለው አንዳች ነገር አልነበረም።

በእነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት ሁሉ ከሁለቱ ልጆቻችን ጋር በመሆን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችንን አላቋረጥንም፤ በወቅቱ ዴቪድና ማርክ የ6 እና የ3 ዓመት ልጆች ነበሩ። በመንግሥት አዳራሽ ስንሆን በይሖዋ እቅፍ ውስጥ እንዳለን ሆኖ ይሰማን ነበር። በዚያ በምንሆንበት ጊዜ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዙሪያችን ስለሚሆኑ ሸክማችንን በይሖዋ ላይ እንደጣልን ይሰማን ነበር፤ ይህ ደግሞ በተወሰነ መጠን ውስጣችን እንዲረጋጋ አድርጎናል። (መዝ. 55:22) ጆኤልን የሚንከባከቡት ነርሶችም እንኳ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ሚዛናችንን እንድንጠብቅ እንደሚረዳን ማስተዋላቸውን ይነግሩን ነበር።

በእነዚያ ወቅቶች በመስክ አገልግሎት ለመካፈል የሚያስችለኝን ጥንካሬ እንዲሰጠኝም ይሖዋን እለምነው ነበር። ቤት ቁጭ ብዬ ከማልቀስ ይልቅ አምላክ ሕመም የሌለበት ዓለም እንደሚመጣ በሰጠው ተስፋ ላይ ያለኝ እምነት እንዴት ብርታት እንደሰጠኝ ለሌሎች ለመናገር ፈልጌ ነበር። አገልግሎት በወጣሁ ቁጥር ይሖዋ ለጸሎቴ መልስ እንደሰጠኝ ይሰማኝ ነበር።

“ይህ ተአምር ነው!”

በመጨረሻም ጆኤልን ከሆስፒታል ወደ ቤት የወሰድነው ዕለት ምን ያህል ተደስተን እንደነበር መገመት ትችላላችሁ! ይሁንና በማግሥቱ ደስታችን ወደ ሐዘን ተቀየረ። ሕመሙ እየተባባሰ በመሄዱ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ወሰድነው። ሐኪሞቹ ከመረመሩት በኋላ “ጆኤል ከዚህ በኋላ ቢበዛ ስድስት ወር ቢቆይ ነው” አሉን። ከሁለት ወር በኋላ ይኸውም ስምንት ወር ሲሆነው የጆኤል ሁኔታ እየተባባሰ በመሄዱ የሐኪሞቹ ግምት እውን የሚሆን ይመስል ነበር። አንድ ሐኪም “በጣም አዝናለሁ፤ ከዚህ በላይ ምንም ልንረዳው አንችልም” አለን። አክሎም “አሁን ሊረዳው የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው” በማለት ተናገረ።

ጆኤል ወደተኛበት ክፍል ተመለስኩ። ስሜቴ ተደቁሶና ሰውነቴ ዝሎ የነበረ ቢሆንም ከጎኑ ላለመለየት ቆረጥኩ። ሉዊጂ ሁለቱን ልጆቻችንን መንከባከብ ስለነበረበት አንዳንድ እህቶች በየተራ ከእኔ ጋ ይቆዩ ነበር። በዚህ ሁኔታ አንድ ሳምንት አለፈ። ከዚያም በድንገት የጆኤል ልብ መምታት አቆመ። ነርሶቹ እየተሯሯጡ ቢመጡም ምንም ሊያደርጉለት አልቻሉም። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አንደኛዋ ነርስ በቀስታ “አረፈ” አለች። ስቅስቅ ብዬ እያለቀስኩ ከክፍሉ ወጣሁ፤ አቅሜ ሙጥጥ ብሎ ነበር። ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ብሞክርም የሚሰማኝን ሥቃይ ምን ብዬ እንደምገልጽ ጠፋኝ። አሥራ አምስት ደቂቃ ያህል ካለፈ በኋላ አንዲት ነርስ ወደ እኔ እየተጣራች “ጆኤል መተንፈስ ጀምሯል!” አለችኝ። ከዚያም “አሁን መጥተሽ ልታይው ትችያለሽ” በማለት እጄን ይዛ ወደ ክፍሉ ወሰደችኝ። ጆኤል ወዳለበት ክፍል ስገባ ልቡ እንደገና መምታት ጀምሮ ነበር! ወሬው ወዲያውኑ ተዳረሰ። ነርሶችና ሐኪሞች እሱን ለማየት የመጡ ሲሆን ብዙዎቹ “ይህ ተአምር ነው!” በማለት መገረማቸውን ይገልጹ ነበር።

በአራት ዓመቱ አስገራሚ ለውጥ ታየ

ጆኤል ሕፃን እያለ ሐኪሙ “ጆኤል ብዙ ፍቅር ያስፈልገዋል” እያለ በተደጋጋሚ ይነግረን ነበር። እኔና ሉዊጂ፣ ጆኤል ከተወለደ በኋላ ይሖዋ ልዩ ፍቅራዊ እንክብካቤ ስላደረገልን እኛም ልጃችንን በፍቅር ተንከባክበን  ለማሳደግ እንፈልግ ነበር። ጆኤል ምንም ነገር ማድረግ ሲፈልግ የእኛ እርዳታ ያሻው ስለነበር ለእሱ ፍቅር የምናሳይባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩን።

ጆኤል ሰባት ዓመት እስኪሆነው ድረስ ከጤናው ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ተመሳሳይ ነገሮች ያጋጥሙን ነበር። ከጥቅምት እስከ መጋቢት ባሉት ወራት ውስጥ ጤንነቱን የሚያቃውሱ ነገሮች በላይ በላይ ይፈራረቁበት ስለነበር አሁንም አሁንም ሆስፒታል ማመላለስ ግድ ሆኖብን ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ዴቪድና ማርክ ለተባሉት ልጆቼ በተቻለኝ መጠን ጊዜ ለመስጠት እጥር ነበር። እነሱም ጆኤል ለውጥ እንዲያደርግ ለመርዳት የበኩላቸውን ጥረት ያደርጉ የነበረ ሲሆን ይህም አስገራሚ ውጤት አስገኝቷል። ለምሳሌ ብዙ ሐኪሞች ጆኤል ፈጽሞ በእግሩ ሊሄድ እንደማይችል ነግረውን ነበር። ይሁንና ጆኤል የአራት ዓመት ልጅ ሳለ አንድ ቀን ልጃችን ማርክ “ጆኤል ትችላለህ እኮ፣ በል ለእማዬ አሳያት!” አለው። ጆኤል መራመድ ሲጀምር ዓይኔን ማመን አቃተኝ! በዚህ በጣም ስለተደሰትን በቤተሰብ ሆነን ይሖዋን ከልባችን በጸሎት አመሰገንነው። በሌሎች ጊዜያትም ጆኤል በተለያዩ ነገሮች ትንሽም ቢሆን መሻሻል ሲያሳይ ሁልጊዜ አድናቆታችንን እንገልጽለት ነበር።

ከጨቅላነቱ ጀምረን የሰጠነው መንፈሳዊ ሥልጠና ፍሬ አፍርቷል

ጆኤልን በመንግሥት አዳራሽ ወደሚደረጉት ስብሰባዎች በተቻለን መጠን አዘውትረን እንወስደው ነበር። ጀርሞች በቀላሉ ስለሚያሳምሙት የፕላስቲክ መሸፈኛ ባለው ለየት ያለ ጋሪ ውስጥ እናስቀምጠው ነበር። ከጋሪው መውጣት ባይችልም ፕላስቲኩ ውጪውን ስለሚያሳየው ጉባኤ መሄድ ያስደስተው ነበር።

አፍቃሪ የሆኑት ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከጎናችን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጉልን ስለነበር የብርታት ምንጭ ሆነውልናል። አንድ ወንድም በኢሳይያስ 59:1 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ብዙ ጊዜ ያስታውሰን ነበር። ጥቅሱ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፤ ጆሮውም መስማት አልተሳናትም” ይላል። እነዚህ የሚያበረታቱ ቃላት በይሖዋ እንድንታመን ረድተውናል።

ጆኤል እያደገ ሲሄድ ይሖዋን ማገልገል የሕይወቱ ዋነኛ ክፍል እንዲሆን ለማድረግ እንጥር ነበር። ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ለጆኤል ስለ ይሖዋ በመንገር በሰማይ ለሚገኘው አባቱ ፍቅር እንዲያዳብር እንረዳው ነበር። እንዲሁም ለጆኤል የምንሰጠው መንፈሳዊ ሥልጠና ጥሩ ፍሬ እንዲያፈራ በማድረግ ጥረታችንን እንዲባርክልን ይሖዋን እንለምነው ነበር።

ጆኤል በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማካፈል እንደሚያስደስተው ስንመለከት ይሖዋን አመሰገንን። በ14 ዓመቱ ካደረገው ከባድ ቀዶ ሕክምና እያገገመ ሳለ “እማዬ ለሐኪሙ ዘላለም መኖር መጽሐፍ ልስጠው?” ብሎ ሲጠይቀኝ የተሰማኝን ደስታ መግለጽ ያቅተኛል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጆኤል ተጨማሪ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አስፈልጎት ነበር። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ላይተርፍ እንደሚችል እናውቅ ነበር። ጆኤል አብረነው ያዘጋጀነውን ደብዳቤ ቀዶ ሕክምና ከማድረጉ በፊት ለሐኪሞቹ ሰጣቸው። ደብዳቤው ከደም ጋር በተያያዘ ያለውን አቋም የሚገልጽ ነበር። ቀዶ ሕክምናውን የሚያደርግለት ሐኪም “አንተ ትስማማበታለህ?” ብሎ ጠየቀው። ጆኤልም በቁርጠኝነት “አዎን” በማለት መለሰ። ልጃችን በፈጣሪው ላይ በመተማመኑና እሱን ለማስደሰት በመቁረጡ በጣም ኮራንበት። የሆስፒታሉ ሠራተኞች ላደረጉልን ከፍተኛ ትብብር በጣም አመስጋኞች ነን።

 ጆኤል በመንፈሳዊ ያደረገው እድገት

ጆኤል 17 ዓመት ሲሆነው ራሱን ለአምላክ በመወሰን ተጠመቀ። ይህ ፈጽሞ የማይረሳ ቀን ነበር! ጆኤል በመንፈሳዊ ማደጉን ስንመለከት ልባችን በደስታ ተሞላ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ለይሖዋ ያለው ፍቅርና ለእውነት ያለው ቅንዓት ቀዝቅዞ አያውቅም። እንዲያውም ጆኤል ለሚያገኛቸው ሰዎች በሙሉ “እውነት ሕይወቴ ነው!” ብሎ መናገር ይወዳል።

ጆኤል በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ ሲደርስ ማንበብና መጻፍ ቻለ። ይህን ለማድረግ ብርቱ ትግል ማድረግ ጠይቆበታል። አጭር የሆነ አንድ ቃል እንኳ መጻፍ መቻሉን እንደ ትልቅ ድል ይቆጥረው ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በየቀኑ የመጀመሪያ ሥራው ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር ከተባለው ቡክሌት የዕለቱን ጥቅስ ማንበብ ነው። ከዚያም የዕለቱን ጥቅስ በማስታወሻ ደብተሩ ላይ በጥንቃቄ ይገለብጣል፤ በአሁኑ ጊዜ ጥቅሶችን የገለበጠባቸው ብዙ ማስታወሻ ደብተሮች አሉት።

ስብሰባ ባለባቸው ቀናት ጆኤል ወደ አዳራሹ የሚመጡትን በሙሉ ሞቅ ባለ ስሜት መቀበል ስለሚፈልግ ወደ መንግሥት አዳራሹ በጊዜ እንድንሄድ ለማድረግ ይጥራል። በስብሰባ ወቅት ሐሳብ መስጠትና ሠርቶ ማሳያዎች ማቅረብ ያስደስተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በድምፅ ክፍል ያገለግላል፤ እንዲሁም በሌሎች ሥራዎች ይካፈላል። ጤንነቱ በሚፈቅድለት መጠን በየሳምንቱ ከእኛ ጋር በስብከቱ ሥራ ይካፈላል። በ2007 ጆኤል የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ እንደተሾመ የሚገልጽ ማስታወቂያ በጉባኤ ተነገረ። የደስታ እንባ አነባን። ይህ እንዴት ታላቅ በረከት ነው! በእርግጥም ይሖዋ ደግ ነው!

የይሖዋ እጅ አጭር እንዳልሆነች ተመልክተናል

በ1999 ሌላ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጠመን። ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ይነዳ የነበረ አንድ አሽከርካሪ መኪናችንን ሲገጫት ሉዊጂ ከባድ ጉዳት ደረሰበት። አንደኛው እግሩ መቆረጥ የነበረበት ከመሆኑም በላይ አከርካሪው ላይ በተለያየ ጊዜ ከባድ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለታል። በዚህ ጊዜም ቢሆን በይሖዋ በመታመናችን ለአገልጋዮቹ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ የሚሰጠውን ጥንካሬ እንዳገኘን ተሰምቶናል። (ፊልጵ. 4:13) ሉዊጂ የአካል ጉዳተኛ ቢሆንም ነገሮችን በአዎንታዊ መንገድ ለመመልከት እንጥር ነበር። ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ስላልቻለ ጆኤልን ይበልጥ ለመንከባከብ ጊዜ አገኘ። ይህ ደግሞ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተጨማሪ ጊዜ እንዳገኝ አጋጣሚ ከፍቶልኛል። በተጨማሪም ሉዊጂ ለቤተሰባችንም ሆነ ለጉባኤው መንፈሳዊ ፍላጎት የበለጠ ትኩረት መስጠት የቻለ ሲሆን በጉባኤ ውስጥ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል።

ያጋጠሙን ለየት ያሉ ችግሮች ቤተሰባችን ይበልጥ እንዲቀራረብ አድርጓል። ጊዜያት እያለፉ ሲሄዱ ምክንያታዊ መሆን እንዳለብን እንዲሁም የማይሆን ነገር መጠበቅ እንደሌለብን ተምረናል። የተስፋ መቁረጥ ስሜት በሚሰማን ጊዜ ሁሉ የውስጣችንን ገልጠን ለይሖዋ በጸሎት እንነግረዋለን። የሚያሳዝነው ነገር ዴቪድና ማርክ የተባሉት ልጆቻችን ትልቅ ሆነው ከቤት ከወጡ በኋላ ቀስ በቀስ ይሖዋን ማገልገላቸውን አቆሙ። አንድ ቀን ወደ ይሖዋ እንደሚመለሱ ተስፋ እናደርጋለን።—ሉቃስ 15:17-24

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የይሖዋ እርዳታ እንዳልተለየን ያስተዋልን ከመሆኑም ሌላ ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን በእሱ መመካት እንዳለብን ተምረናል። በተለይ በኢሳይያስ 41:13 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በጣም እንወደዋለን፦ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ።” ይሖዋ እጃችንን አጥብቆ እንደሚይዘን ማወቃችን ትልቅ የብርታት ምንጭ ሆኖልናል። በእርግጥም መከራዎችን በጽናት መቋቋማችን በሰማዩ አባታችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት እንዳጠናከረልን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ትራይሶሚ 21 የአእምሮ ዝግመት የሚያስከትል አብሮ የሚወለድ በሽታ ነው። በተፈጥሮ ክሮሞዞሞች የሚቀመጡት ጥንድ ጥንድ ሆነው ነው፤ ትራይሶሚ ኖሯቸው የሚወለዱ ሕፃናት ግን ከጥንዶቹ ክሮሞዞሞች ውስጥ በአንዱ ላይ ተጨማሪ ክሮሞዞም ይኖራቸዋል። ትራይሶሚ 21 የሚከሰተው በ21ኛው ጥንድ ክሮሞዞም ላይ ነው።

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጆኤል ከእናቱ ከአዳ ጋር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳ፣ ጆኤልና ሉዊጂ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጆኤል ወደ መንግሥት አዳራሽ የሚመጡትን ወንድሞችና እህቶች ሞቅ ባለ ስሜት መቀበል ያስደስተዋል