በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወጣቶችይሖዋን ለማገልገል ያላችሁ ፍላጎት እያደገ ይሂድ

እናንት ወጣቶችይሖዋን ለማገልገል ያላችሁ ፍላጎት እያደገ ይሂድ

 እናንት ወጣቶች​—ይሖዋን ለማገልገል ያላችሁ ፍላጎት እያደገ ይሂድ

“በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ።”—መክ. 12:1

1. በእስራኤል ለሚገኙ ልጆች ምን ግብዣ ቀርቦላቸው ነበር?

የይሖዋ ነቢይ የሆነው ሙሴ፣ የዛሬ 3,500 ዓመታት ገደማ የእስራኤልን ካህናትና አለቆች እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ይሰሙና አምላካችሁን እግዚአብሔርን መፍራት ይማሩ ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችን . . . ሰብስብ።” (ዘዳ. 31:12) ለአምልኮ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ የታዘዙት ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች እንደሆኑ ልብ በል። አዎን፣ ትናንሽ ልጆችም እንኳ የይሖዋን መመሪያ እንዲሰሙ፣ እንዲማሩና እንዲከተሉ ይጠበቅባቸው ነበር።

2. ይሖዋ በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች እንደሚያስብ ያሳየው እንዴት ነው?

2 በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ይሖዋ በሕዝቦቹ መካከል ለሚገኙት ወጣቶች እንደሚያስብ አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጉባኤዎች በላካቸው አንዳንድ ደብዳቤዎች ላይ ልጆችን በቀጥታ የሚመለከቱ መመሪያዎችን እንዲያካትት ይሖዋ በመንፈሱ መርቶታል። (ኤፌሶን 6:1ን እና ቆላስይስ 3:20ን አንብብ።) እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ ያደረጉ ክርስቲያን ወጣቶች አፍቃሪ ለሆነው ሰማያዊ አባታቸው ያላቸው አድናቆት እያደገ ከመሄዱም በላይ የይሖዋን በረከት አግኝተዋል።

3. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ወጣቶች አምላክን ለማገልገል እንደሚፈልጉ ያሳዩት እንዴት ነው?

3 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ወጣቶችስ ይሖዋን ለማምለክ እንዲሰበሰቡ ተጋብዘዋል? በሚገባ! ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ እንበረታታ።” (ዕብ. 10:24, 25) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች የሆኑ በርካታ ወጣቶች የጳውሎስን ምክር በተግባር ማዋላቸው ሁሉንም የአምላክ ሕዝቦች ያስደስታቸዋል። ከዚህም በላይ በርካታ ልጆች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከወላጆቻቸው ጋር ሆነው ይሰብካሉ። (ማቴ. 24:14) እንዲሁም በየዓመቱ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ለይሖዋ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ለመግለጽ ራሳቸውን ወስነው ይጠመቃሉ፤ በዚህ መልኩ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸው በረከት አስገኝቶላቸዋል።—ማቴ. 16:24፤ ማር. 10:29, 30

ግብዣውን አሁኑኑ ተቀበሉ

4. ልጆች አምላክ እሱን እንዲያገለግሉ ያቀረበላቸውን ጥሪ መቀበል የሚችሉት በስንት ዓመታቸው ነው?

4 መክብብ 12:1 “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” ይላል። እናንት ልጆች ይሖዋን እንድታመልኩና እንድታገለግሉ የቀረበላችሁን ይህን ሞቅ ያለ ግብዣ ለመቀበል ስንት ዓመት ሊሆናችሁ ይገባል? ቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰነ የዕድሜ ገደብ አላስቀመጡም። በመሆኑም ይሖዋን ለመስማትና ለማገልገል ዕድሜያችሁ ገና እንደሆነ በማሰብ ወደኋላ አትበሉ። ዕድሜያችሁ ምንም ያህል ቢሆን ሳትዘገዩ ለግብዣው ምላሽ እንድትሰጡ ተበረታታችኋል።

5. ወላጆች ልጆቻቸው በመንፈሳዊ እንዲያድጉ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

5 አብዛኞቻችሁ በመንፈሳዊ እንድታድጉ ወላጆቻችሁ ድጋፍ አድርገውላችኋል። በዚህ ረገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው ከጢሞቴዎስ ጋር ትመሳሰላላችሁ። ጢሞቴዎስ ገና ጨቅላ እያለ እናቱ ኤውንቄና አያቱ ሎይድ ቅዱሳን መጻሕፍትን አስተምረውታል። (2 ጢሞ. 3:14, 15) የእናንተም ወላጆች አብረዋችሁ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና በመጸለይ፣ የአምላክ ሕዝቦች ወደሚያደርጓቸው የጉባኤና ትላልቅ ስብሰባዎች ይዘዋችሁ  በመሄድ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት አብረዋችሁ በመካፈል ልክ እንደ ጢሞቴዎስ እያሠለጠኗችሁ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። በእርግጥም እናንተን ስለ አምላክ መንገዶች ማስተማር ወላጆቻችሁ ከይሖዋ የተቀበሉት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ኃላፊነት ነው። ታዲያ ወላጆቻችሁ ለእናንተ ያላቸውን ፍቅርና አሳቢነት ታደንቃላችሁ?—ምሳሌ 23:22

6. (ሀ) በመዝሙር 110:3 መሠረት ይሖዋን የሚያስደስተው ምን ዓይነት አምልኮ ነው? (ለ) ከዚህ ቀጥሎ የትኞቹን ነገሮች እንመረምራለን?

6 እያደጋችሁ ስትሄዱ ደግሞ ልክ እንደ ጢሞቴዎስ እናንተ ራሳችሁ “ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ” እንድታረጋግጡ ይሖዋ ይፈልጋል። (ሮም 12:2) እንዲህ ካደረጋችሁ ጉባኤው በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የምትካፈሉት ወላጆቻችሁ ስለሚጠብቁባችሁ ሳይሆን እናንተ ራሳችሁ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ስለምትፈልጉ ይሆናል። ይሖዋን በፈቃደኝነት ተነሳስታችሁ የምታገለግሉት ከሆነ ይደሰትባችኋል። (መዝ. 110:3) ታዲያ ይሖዋን ለመስማትና መመሪያዎቹን ለመከተል ያላችሁን ፍላጎት ለማሳደግ እንደምትጓጉ ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው? ይህንን ማድረግ የምትችሉባቸውን ሦስት ጠቃሚ መንገዶች ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን። እነዚህም ጥናት፣ ጸሎትና ምግባር ናቸው። እስቲ እነዚህን ነገሮች አንድ በአንድ እንመርምር።

ይሖዋ እውን ሆኖ ይታያችሁ

7. ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት ረገድ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው? እንዲህ እንዲሆን የረዳውስ ምንድን ነው?

7 ይሖዋን የማገልገል ፍላጎታችሁ እያደገ እንዲሄድ እንደምትፈልጉ ማሳየት የምትችሉበት አንዱ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ ነው። የአምላክን ቃል አዘውትራችሁ በማንበብ መንፈሳዊ ፍላጎታችሁን ማርካትና ውድ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት መቅሰም ትችላላችሁ። (ማቴ. 5:3) በዚህ ረገድ ኢየሱስ ምሳሌ ይሆናችኋል። ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ በአንድ ወቅት ወላጆቹ “በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ሲጠይቃቸው አገኙት።” (ሉቃስ 2:44-46) ኢየሱስ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማወቅ ይጓጓ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የአምላክ ቃል እውቀት ነበረው። እንዲህ እንዲሆን የረዳው ምን ነበር? እናቱ ማርያምና አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ምንም ጥርጥር የለውም። ወላጆቹ የአምላክ አገልጋዮች የነበሩ ሲሆን ኢየሱስን ገና ከጨቅላነቱ ጀምሮ ስለ አምላክ አስተምረውታል።—ማቴ. 1:18-20፤ ሉቃስ 2:41, 51

8. (ሀ) ወላጆች ልጆቻቸው ለአምላክ ቃል ፍቅር እንዲያድርባቸው መርዳት መጀመር ያለባቸው መቼ ነው? (ለ) ልጆችን ከጨቅላነታቸው ጀምሮ ማሠልጠን ጠቃሚ እንደሆነ የሚያሳይ የምታውቀው ተሞክሮ ካለ ተናገር።

8 ዛሬም በተመሳሳይ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች፣ ልጆቻቸው ገና ከጨቅላነታቸው ጀምሮ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ጉጉት እንዲያድርባቸው የመርዳትን አስፈላጊነት ይገነዘባሉ። (ዘዳ. 6:6-9) ሩቢ የተባለች አንዲት ክርስቲያን የመጀመሪያ ልጇን ጆሴፍን ከወለደች ብዙም ሳትቆይ ያደረገችው ይህን ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ በየቀኑ ታነብለት ነበር። ልጁ ከፍ እያለ ሲሄድ የተለያዩ ጥቅሶችን በቃሉ እንዲይዝ ረዳችው። ታዲያ ጆሴፍ እንዲህ ዓይነቱን ሥልጠና በማግኘቱ ተጠቅሟል? አፍ ከፈታ ብዙም ሳይቆይ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በራሱ አባባል መተረክ ይችል ነበር። አምስት ዓመት ሲሆነው ደግሞ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ክፍሉን አቀረበ።

9. መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችሁና ባነበባችሁት ላይ ማሰላሰላችሁ የሚጠቅማችሁ እንዴት ነው?

9 እናንት ልጆች፣ መንፈሳዊ እድገታችሁ ቀጣይ እንዲሆን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ልማድ ሊኖራችሁ ይገባል፤ ይህ ልማዳችሁ በወጣትነት ጊዜያችሁም ሆነ ትልቅ ሰው ስትሆኑ መቀጠል ይኖርበታል። (መዝ. 71:17) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እድገት እንድታደርጉ የሚረዳችሁ እንዴት ነው? ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ ምን እንዳለ ልብ በሉ፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተ . . . እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።” (ዮሐ. 17:3) በእርግጥም ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቃችሁ መጠን ይሖዋ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እውን እየሆነላችሁ የሚሄድ ከመሆኑም በላይ ለእሱ ያላችሁ ፍቅር ጥልቅ ይሆናል። (ዕብ. 11:27) እንግዲያው አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በምታነቡበት ጊዜ ሁሉ አጋጣሚውን ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለመማር ተጠቀሙበት። ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ይህ ዘገባ  ይሖዋ እውን እንዲሆንልኝ የሚረዳኝ እንዴት ነው? ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አምላክ እንደሚወደኝና እንደሚያስብልኝ የሚያሳየው እንዴት ነው?’ እንዲህ ባሉ ጥያቄዎች ላይ ጊዜ ወስዳችሁ ማሰላሰላችሁ የይሖዋን አስተሳሰብና ስሜት ለመረዳት ብሎም ከእናንተ የሚፈልገው ምን እንደሆነ ለማወቅ ያስችላችኋል። (ምሳሌ 2:1-5ን አንብብ።) እንዲሁም እንደ ወጣቱ ጢሞቴዎስ ከቅዱሳን መጻሕፍት የተማራችኋቸውን ነገሮች ‘አምናችሁ ለመቀበል’ የሚያስችላችሁ ከመሆኑም በላይ ይሖዋን በፈቃደኝነት ለማገልገል ያነሳሳችኋል።—2 ጢሞ. 3:14

ጸሎት ለይሖዋ ያላችሁ ፍቅር እንዲጠነክር የሚረዳችሁ እንዴት ነው?

10, 11. ጸሎት አምላክን ለማገልገል ያላችሁን ፍላጎት የሚያጠናክርላችሁ እንዴት ነው?

10 ይሖዋን በሙሉ ልባችሁ ለማገልገል ያላችሁን ፍላጎት ማሳደግ የምትችሉበት ሁለተኛው መንገድ ጸሎት ነው። መዝሙር 65:2 “ጸሎትን የምትሰማ ሆይ፤ የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ” ይላል። (መዝ. 65:2) እስራኤላውያን የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝቦች በነበሩበት ጊዜም እንኳ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ የሚመጡ የባዕድ አገር ሰዎች ወደ እሱ መጸለይ ይችሉ ነበር። (1 ነገ. 8:41, 42) አምላክ ፈጽሞ አያዳላም። የአምላክን ትእዛዛት የሚጠብቁ ሰዎች፣ የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሖዋ እንደሚሰማላቸው እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። (ምሳሌ 15:8) መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልጆች ሁሉ” ሲል እናንተን ወጣቶችንም እንደሚጨምር ጥርጥር የለውም።

11 ለማንኛውም እውነተኛ ወዳጅነት መሠረቱ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ እንደሆነ የታወቀ ነው። ሐሳባችሁን፣ ያስጨነቃችሁን ጉዳይና ስሜታችሁን ለምትቀርቡት ጓደኛችሁ ማካፈል እንደሚያስደስታችሁ ግልጽ ነው። በተመሳሳይም ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረብ ለታላቁ ፈጣሪያችሁ ሐሳባችሁን መግለጽ ትችላላችሁ። (ፊልጵ. 4:6, 7) ከምትወዱት ወላጃችሁ ወይም ከቅርብ ጓደኛችሁ ጋር ስታወሩ እንደምታደርጉት ሁሉ ለይሖዋም የልባችሁን አውጥታችሁ ንገሩት። የጸሎታችሁ ይዘት ይሖዋን ምን ያህል እንደምትቀርቡት የሚያሳይ ጉልህ ማስረጃ ነው። ከይሖዋ ጋር ያላችሁ ወዳጅነት ጠንካራ እየሆነ በሄደ መጠን የምታቀርቡት ጸሎትም ይበልጥ ትርጉም ያለው እንደሚሆን ታስተውላላችሁ።

12. (ሀ) ትርጉም ያለው ጸሎት ቃላትን ከመደርደር የበለጠ ነገር ይጨምራል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በእርግጥም ለእናንተ ቅርብ መሆኑን እንድትገነዘቡ የሚረዳችሁ ምንድን ነው?

12 ይሁንና ትርጉም ያለው ጸሎት ማቅረብ ቃላትን ከመደርደር የበለጠ ነገር እንደሚጨምር አስታውሱ። የምታቀርቡት ጸሎት ውስጣዊ ስሜታችሁን የሚገልጽ መሆን አለበት። በጸሎታችሁ ላይ ይሖዋን ከልብ እንደምትወዱት፣ በጥልቅ እንደምታከብሩትና ሙሉ በሙሉ እንደምትተማመኑበት ግለጹ። ይሖዋ ለምታቀርቡት ጸሎት መልስ የሚሰጥበትን መንገድ ስታስተውሉ ይሖዋ “ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ” መሆኑን ከምንጊዜውም የበለጠ በራሳችሁ ሕይወት ትገነዘባላችሁ። (መዝ. 145:18) በእርግጥም ይሖዋ ወደ እናንተ የሚቀርብ ሲሆን ዲያብሎስን ለመቃወም የሚያስችል ጥንካሬ ሊሰጣችሁና በሕይወታችሁ ትክክለኛ ምርጫ እንድታደርጉ ሊረዳችሁ ይችላል።—ያዕቆብ 4:7, 8ን አንብብ።

13. (ሀ) አንዲት እህት ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረቷ የጠቀማት እንዴት ነው? (ለ) ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረታችሁ የእኩዮቻችሁን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚረዳችሁ እንዴት ነው?

13 ሼሪ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረቷ ጥንካሬ የሰጣት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለች በትምህርቷ ጥሩ  ውጤት ስላመጣችና በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በጣም ጎበዝ ስለነበረች ሽልማት አግኝታ ነበር። ትምህርቷን ስትጨርስ ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል የሚያስችላትን የነፃ ትምህርት ዕድል አገኘች። ሼሪ እንዲህ ብላለች፦ “የቀረበልኝ ግብዣ የሚያጓጓ ነበር፤ አሠልጣኞችና አብረውኝ የሚማሩ ልጆችም ባገኘሁት ዕድል እንድጠቀም ከፍተኛ ጫና አድርገውብኝ ነበር።” ይሁንና ሼሪ ተጨማሪ ትምህርት ከተከታተለች አብዛኛውን ጊዜዋን በጥናትና ስፖርታዊ ልምምድ በማድረግ ማሳለፍ ስለሚኖርባት ይሖዋን ለማገልገል በቂ ጊዜ እንደማታገኝ ተገነዘበች። ታዲያ ምን አደረገች? “ወደ ይሖዋ ከጸለይኩ በኋላ የቀረበልኝን የነፃ ትምህርት ዕድል ላለመቀበል ወሰንኩ፤ ከዚያም የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ” ብላለች። ሼሪ ላለፉት አምስት ዓመታት አቅኚ ሆና እያገለገለች ነው። “ምንም የምቆጭበት ነገር የለም” ብላለች። “ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ እንዳደረግሁ ማወቄ እርካታ አስገኝቶልኛል። በእርግጥም የአምላክን መንግሥት ካስቀደማችሁ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።”—ማቴ. 6:33

መልካም ምግባር ‘ልበ ንጹሕ’ መሆናችሁን ያሳያል

14. መልካም ምግባር ማሳየታችሁ በይሖዋ ዘንድ ምን ያስገኝላችኋል?

14 ይሖዋን በፈቃዳችሁ እንደምታገለግሉ ማሳየት የምትችሉበት ሦስተኛው መንገድ ምግባራችሁ ነው። ይሖዋ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነው ለመኖር የሚጥሩ ወጣቶችን ይባርካቸዋል። (መዝሙር 24:3-5ን በ1954 ትርጉም አንብብ።) ወጣቱ ሳሙኤል መጥፎ ሥነ ምግባር የነበራቸውን የሊቀ ካህኑን የዔሊን ልጆች ምሳሌ አልተከተለም። የሳሙኤል መልካም ምግባር ሳይስተዋል አልቀረም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ “ብላቴናውም ሳሙኤል በአካልና በሞገስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት እያደገ ሄደ” ይላል።—1 ሳሙ. 2:26

15. መልካም ምግባር ማሳየታችሁን እንድትቀጥሉ የሚያነሳሷችሁ አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

15 የምንኖርበት ዓለም ራሳቸውን በሚወዱ፣ ትዕቢተኛ በሆኑ፣ ለወላጆቻቸው በማይታዘዙ፣ በማያመሰግኑ፣ ታማኝ ባልሆኑ፣ ጨካኞች በሆኑ፣ በኩራት በተወጠሩና አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን በሚወዱ ሰዎች የተሞላ ነው፤ እነዚህ ባሕርያት ጳውሎስ ከዘረዘራቸው መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1-5) ክፉ በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ ሆናችሁ ሁልጊዜ አርዓያ የሚሆን ምግባር ማሳየት በጣም ከባድ ሊሆንባችሁ ይችላል። ያም ቢሆን ትክክል የሆነውን ነገር ባደረጋችሁና በመጥፎ ምግባር ለመካፈል አሻፈረኝ ባላችሁ ቁጥር ከአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ በተነሳው ጥያቄ ረገድ ከይሖዋ ጎን እንደቆማችሁ ታሳያላችሁ። (ኢዮብ 2:3, 4) በተጨማሪም “ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው፤ ለሚንቁኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችል ዘንድ” በማለት ይሖዋ ላቀረበው ሞቅ ያለ ግብዣ ምላሽ እየሰጣችሁ መሆኑን ማወቃችሁ እርካታ ያስገኝላችኋል። (ምሳሌ 27:11) ከዚህም በላይ የይሖዋን ሞገስ እንዳገኛችሁ ማወቃችሁ እሱን ለማገልገል ያላችሁ ፍላጎት እንዲጨምር ያደርጋል።

16. አንዲት እህት የይሖዋን ልብ ያስደሰተችው እንዴት ነው?

16 ካሮል የተባለች አንዲት ክርስቲያን፣ ተማሪ በነበረችበት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ ትከተል የነበረ ሲሆን መልካም ምግባሯም ሳይስተዋል አላለፈም። ካሮል ምን አጋጠማት? በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናዋ የተነሳ በበዓላትና ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶች ላይ ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኗ የክፍሏ ተማሪዎች ያፌዙባት ነበር። በእነዚህ ወቅቶች እምነቷን ለሌሎች ለማስረዳት አጋጣሚ ያገኘችበት ጊዜ ነበር። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ካሮል፣ አብራት ከተማረች አንዲት ሴት እንዲህ የሚል ካርድ ደረሳት፦ “አንቺን አግኝቼ ለማመስገን ሁልጊዜ እመኝ ነበር። ወጣት ክርስቲያን በነበርሽበት ጊዜ ያሳየሽው መልካም ምግባርና ምሳሌነትሽ እንዲሁም ከበዓላት ጋር በተያያዘ የወሰድሽው ድፍረት የተሞላበት አቋም ሳይስተዋል አልቀረም። መጀመሪያ ያወቅኳት የይሖዋ  ምሥክር አንቺ ነሽ።” የካሮል ምሳሌነት በክፍል ጓደኛዋ ላይ በጎ ተጽዕኖ ስላሳደረ ይህች ሴት ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ይህች ሴት ለካሮል በላከችው ካርድ ላይ እንደጻፈችው የይሖዋ ምሥክር ከሆነች 40 ዓመታት አልፈዋል! እንደ ካሮል ሁሉ በዛሬው ጊዜም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በጥብቅ የምትከተሉ ወጣቶች ቅን የሆኑ ሰዎች ይሖዋን ለማወቅ እንዲነሳሱ ልታደርጉ ትችላላችሁ።

ይሖዋን የሚያወድሱ ወጣቶች

17, 18. (ሀ) በጉባኤህ ስላሉ ወጣቶች ምን ይሰማሃል? (ለ) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወጣቶች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል?

17 በይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ውስጥ የምንገኝ ሁሉ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በእውነተኛው አምልኮ በቅንዓት ሲካፈሉ መመልከት ያስደስተናል! እነዚህ ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብና በመጸለይ እንዲሁም ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር ይሖዋን የማምለክ ፍላጎታቸው እየጨመረ እንዲሄድ ያደርጋሉ። እንደነዚህ ያሉት አርዓያ የሚሆኑ ወጣቶች ለወላጆቻቸውም ሆነ ለሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች የደስታ ምንጭ ናቸው።—ምሳሌ 23:24, 25

18 ታማኝ የሆኑ ወጣቶች ወደፊት ደግሞ ከጥፋት ተርፈው አምላክ ቃል ወደገባላቸው አዲስ ዓለም ከሚገቡት መካከል ይሆናሉ። (ራእይ 7:9, 14) በዚያም ለይሖዋ ያላቸው አድናቆት እያደገ የሚሄድ ሲሆን ማለቂያ የሌለው በረከት ያገኛሉ፤ እንዲሁም ይሖዋን ለዘላለም ማወደስ ይችላሉ።—መዝ. 148:12, 13

ልታብራራ ትችላለህ?

• በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች በእውነተኛው አምልኮ መካፈል የሚችሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

• ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ ጥቅም ለማግኘት ማሰላሰል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ጸሎት ወደ ይሖዋ እንድትቀርብ የሚረዳህ እንዴት ነው?

• አንድ ክርስቲያን መልካም ምግባር ማሳየቱ ምን ውጤት ያስገኛል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ልማድ አለህ?