በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ እንዲጠይቅህ ትፈቅድለታለህ?

ይሖዋ እንዲጠይቅህ ትፈቅድለታለህ?

 ይሖዋ እንዲጠይቅህ ትፈቅድለታለህ?

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጣዊ ስሜታችንንና ዝንባሌያችንን እንድንመረምር የሚያደርጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥያቄዎችን ይዟል። ይሖዋ አምላክ ራሱ አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን ለማስተማር በጥያቄዎች ይጠቀማል። ለአብነት ያህል፣ ቃየን ከመጥፎ ጎዳናው እንዲመለስ ለማስጠንቀቅ ይሖዋ በርካታ ጥያቄዎችን ተጠቅሟል። (ዘፍ. 4:6, 7) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ኢሳይያስን ለተግባር አነሳስተውታል። ይሖዋ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ነቢዩ ኢሳይያስ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” የሚል ምላሽ ሰጠ።—ኢሳ. 6:8

ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስም ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ይጠቀም ነበር። የወንጌል መጻሕፍት ኢየሱስ የተጠቀማቸውን ከ280 የሚበልጡ ጥያቄዎች ዘግበዋል። ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን ዝም ለማሰኘት በጥያቄዎች የተጠቀመባቸው ጊዜያት ቢኖሩም በአብዛኛው ጥያቄዎችን ይጠቀም የነበረው የአድማጮቹን ልብ በመንካት ያሉበትን መንፈሳዊ ሁኔታ ቆም ብለው እንዲመረምሩ ለማነሳሳት ነበር። (ማቴ. 22:41-46፤ ዮሐ. 14:9, 10) በተመሳሳይም ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ 14ቱን የጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎችን ለማሳመን በጥያቄዎች ይጠቀም ነበር። (ሮም 10:13-15) ለምሳሌ፣ ለሮም ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ በርካታ ጥያቄዎችን ይዟል። ጳውሎስ ያቀረባቸው ጥያቄዎች አንባቢዎቹ “የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት” ምን ያህል ጥልቅ መሆኑን እንዲረዱና ለዚህም አድናቆት እንዲያድርባቸው ረድተዋቸዋል።—ሮም 11:33

አንዳንድ ጥያቄዎች የሚቀርቡበት ዓላማ ሰዎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ማድረግ ሲሆን ሌሎች ጥያቄዎች የሚቀርቡት ደግሞ በጉዳዩ ላይ በጥልቅ እንዲያስቡበት ለማነሳሳት ነው። የወንጌል ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ኢየሱስ በአብዛኛው በጥያቄዎች የተጠቀመው የሰዎችን ልብ ለመኮርኮር ነው። በአንድ ወቅት ኢየሱስ “ከፈሪሳውያን እርሾና ከሄሮድስ እርሾ [እንዲጠበቁ]” ይኸውም የእነሱን የግብዝነት አካሄድና የሐሰት ትምህርታቸውን እንዳይከተሉ ደቀ መዛሙርቱን አስጠንቅቋቸው ነበር። (ማር. 8:15፤ ማቴ. 16:12) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ነጥቡ ስላልገባቸው ዳቦ ባለመያዛቸው እርስ በርስ ይከራከሩ ጀመር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በጥያቄ እንዴት እንደተጠቀመ ልብ በል። እንዲህ አላቸው፦ “ዳቦ ባለመያዛችሁ ለምን ትከራከራላችሁ? አሁንም ትርጉሙን አላስተዋላችሁም? ልባችሁ መረዳት ተስኖታል? ‘ዓይን እያላችሁ አታዩም? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙም?’ . . . ታዲያ አሁንም ትርጉሙ አልገባችሁም?” ኢየሱስ እነዚህን ጥያቄዎች ያነሳው ደቀ መዛሙርቱ የንግግሩ ትክክለኛ ትርጉም ምን እንደሆነ እንዲያሰላስሉ ለማነሳሳት ነበር።—ማር. 8:16-21

“እኔ ልጠይቅህ”

ይሖዋ አምላክ የአገልጋዩን የኢዮብን አመለካከት ለማስተካከል በጥያቄዎች ተጠቅሟል። ይሖዋ በርካታ ጥያቄዎችን በመጠቀም ኢዮብ ከፈጣሪው ጋር ሲወዳደር ኢምንት መሆኑን አስተምሮታል። (ኢዮብ ከምዕ. 38-41) ይሖዋ ላነሳቸው ጥያቄዎች ኢዮብ መልስ እንዲሰጠው ጠብቆ ነበር? ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው እንደዚያ ያሰበ አይመስልም። “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ?” እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ዓላማቸው የኢዮብን ሐሳብና ስሜት መኮርኮር ነበር። ኢዮብ እንዲህ ያሉ ከባድ የሆኑ ጥያቄዎችን ከሰማ በኋላ አንደበት አልነበረውም። “ምን እመልስልሃለሁ? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ” ከማለት ውጪ መልስ አልነበረውም። (ኢዮብ 38:4፤ 40:4) ኢዮብ ነጥቡ ስለገባው ራሱን ዝቅ አደረገ። ይሁንና የይሖዋ ዓላማ ኢዮብን ትሕትና ማስተማር ብቻ አልነበረም። የኢዮብን አስተሳሰብም አስተካክሎታል። በምን መንገድ?

ኢዮብ “ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን” ሰው የነበረ ቢሆንም ከተናገራቸው አንዳንድ ነገሮች ለመመልከት እንደሚቻለው የተሳሳተ አመለካከት ነበረው፤ ኢዮብ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ [በማድረጉ]” ኤሊሁ በገሠጸው ወቅት ኤሊሁ የተናገረው ነገር ኢዮብ የተሳሳተ አመለካከት እንደነበረው ይጠቁማል። (ኢዮብ 1:8፤ 32:2፤ 33:8-12) በዚህም ምክንያት ይሖዋ ያነሳቸው ጥያቄዎች የኢዮብን  አስተሳሰብም አስተካክለውታል። አምላክ በአውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ኢዮብን እንዲህ አለው፦ “ዕውቀት በጐደለው ቃል፣ ዕቅዴን የሚያጨልም ይህ ማን ነው? እስቲ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤ እኔ ልጠይቅህ፣ አንተም መልስልኝ።” (ኢዮብ 38:1-3) ከዚያም ይሖዋ በጥያቄዎች በመጠቀም አስደናቂ በሆኑት የፍጥረት ሥራዎቹ ላይ የተንጸባረቀውን ወሰን የሌለውን ጥበቡንና ኃይሉን እንዲያስተውል ኢዮብን ረድቶታል። ኢዮብ ይህንን እውቀት ማግኘቱ በይሖዋ ፍርድና ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንዲተማመን ረድቶታል። በእርግጥም ኢዮብ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ የመጠየቅ አጋጣሚ ማግኘቱ በጣም አስደናቂ ነገር ነው!

ይሖዋ እንዲጠይቀን እንደምንፈልግ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

እኛስ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝገበው ከሚገኙት ጥያቄዎች ጥቅም ማግኘት እንችላለን? አዎን፣ እንችላለን። እነዚህን ጥያቄዎች በምናነብበት ጊዜ ቆም ብለን ማሰባችን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት ሊያስገኝልን ይችላል። የአምላክ ቃል ኃይል እንዲኖረው ካደረጉት ነገሮች አንዱ ውስጣችን ድረስ ሰርስረው የሚገቡ ጥያቄዎችን መያዙ ነው። በእርግጥም “የአምላክ ቃል . . . ኃይለኛ ነው፤ . . . የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።” (ዕብ. 4:12) ይሁን እንጂ ከአምላክ ቃል የተሟላ ጥቅም ለማግኘት በውስጡ የሚገኙትን ጥያቄዎች ይሖዋ በቀጥታ ለእኛ እንዳቀረባቸው አድርገን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። (ሮም 15:4) እስቲ እንዲህ ለማድረግ የሚረዱንን አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት።

“የምድር ሁሉ ዳኛ በቅን አይፈርድምን?” (ዘፍ. 18:25) አብርሃም ይህንን ጥያቄ ለይሖዋ ያቀረበው አምላክ በሰዶምና በገሞራ ላይ በፈረደበት ወቅት ነበር፤ አብርሃም ይህን ያለው ከይሖዋ መልስ ጠብቆ አልነበረም። ይሖዋ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር በመግደል ፍትሕ የጎደለው እርምጃ ይወስዳል ብሎ ማመን ለአብርሃም ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር። አብርሃም ያነሳው ጥያቄ በይሖዋ ጽድቅ ላይ ጥልቅ እምነት እንደነበረው ያሳያል።

ዛሬም አንዳንዶች ይሖዋ ወደፊት ከሚወስደው የፍርድ እርምጃ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ለምሳሌ ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት ወይም ትንሣኤ የሚያገኙት እነማን ስለመሆናቸው ግምታዊ ሐሳብ ይሰነዝሩ ይሆናል። እንዲህ ያሉት ሐሳቦች እንዲረብሹን ከመፍቀድ ይልቅ አብርሃም ያነሳውን ጥያቄ ማስታወስ እንችላለን። አብርሃም እንዳደረገው እኛም በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ ደግ እንደሆነ ማወቃችን እንዲሁም ፍትሐዊና ምሕረት የሚንጸባረቅበት እርምጃ እንደሚወስድ ሙሉ በሙሉ መተማመናችን አላስፈላጊ በሆነ ጉዳይ ላይ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ከማባከን እንዲሁም እምነታችንን ከማዳከም ብሎም የማይረባ ክርክር ውስጥ ከመግባት ይጠብቀናል።

“ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ይኖራል?” (ማቴ. 6:27) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጨምሮ ያዳምጡት ለነበሩ በርካታ ሰዎች ይህን ጥያቄ ያቀረበው ይሖዋ ፍቅራዊ እርዳታ እንደሚያደርግላቸው በመተማመን ራሳቸውን ለእሱ አደራ መስጠት እንደሚያስፈልጋቸው ለማጉላት ነበር። በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ስለምንኖር  ብዙ የሚያስጨንቁን ነገሮች ቢፈጠሩም በእነዚህ ነገሮች ላይ ማተኮራችን ሕይወታችንን ሊያራዝምልን ወይም የተሻለ ሕይወት እንድንመራ ሊረዳን አይችልም።

ስለ ራሳችን ወይም ስለምንወዳቸው ሰዎች በምንጨነቅበት ጊዜ ሁሉ ኢየሱስ ያነሳውን ጥያቄ ማስታወሳችን ስለምንጨነቅባቸው ነገሮች ተገቢ አመለካከት እንድንይዝ ሊረዳን ይችላል። አእምሯችን፣ ስሜታችንና አካላችን እንዲዝል የሚያደርገውን ጭንቀትና አሉታዊ ሐሳብ ለማስወገድ ይረዳናል። ኢየሱስ እንዳረጋገጠልን የሰማይ ወፎችን የሚመግበውና የሜዳ ተክሎችን የሚያለብሰው በሰማይ ያለው አባታችን የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሚገባ ያውቃል።—ማቴ. 6:26-34

“ለመሆኑ ልብሱ ሳይቃጠል፣ በጕያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን?” (ምሳሌ 6:27) የምሳሌ መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ምዕራፎች አንድ አባት ለልጁ የሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር ይዘዋል። ከላይ የተጠቀሰው ጥያቄ ምንዝር መፈጸም የሚያስከትለውን መራራ ውጤት ያሳያል። (ምሳሌ 6:29) ሌሎችን የማሽኮርመም አዝማሚያ እንዳለን ወይም የተሳሳተ የፆታ ምኞት በአእምሯችን እንደምናስተናግድ ከተገነዘብን ከላይ ያለው ጥያቄ እንደ ማስጠንቀቂያ ደወል ሊያነቃን ይገባል። በዚህ ጥያቄ ላይ የተገለጸው መሠረታዊ ሥርዓት አንድ ሰው ማንኛውንም ጥበብ የጎደለው እርምጃ ለመውሰድ በሚፈተንበት ጊዜም ሊጠቅመው ይችላል። ይህ ጥያቄ፣ ‘የዘራኸውን ታጭዳለህ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እውነተኝነት በጉልህ የሚያሳይ አይደለም?—ገላ. 6:7

“በሌላው ሰው የቤት አገልጋይ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?” (ሮም 14:4) ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ጉባኤዎች ውስጥ የተነሱትን ችግሮች ጠቅሷል። ክርስቲያኖች የተለያየ ዓይነት ባሕልና አስተዳደግ ስለነበራቸው አንዳንዶች የእምነት ባልንጀሮቻቸው በሚያደርጓቸው ውሳኔዎችና በሚወስዷቸው እርምጃዎች ላይ የመፍረድ አዝማሚያ ነበራቸው። ጳውሎስ ያነሳው ጥያቄ፣ አንዳቸው ሌላውን መቀበል እንዳለባቸው እንዲሁም ፍርድ መስጠትን ለይሖዋ መተው እንደሚገባቸው አስታውሷቸዋል።

ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋ ሕዝቦች አስተዳደጋቸውና የኑሯቸው ሁኔታ የተለያየ ነው። ያም ቢሆን ይሖዋ ሁላችንንም በማሰባሰብ በዋጋ የማይተመን አንድነት እንዲኖረን አድርጓል። እኛስ ለዚህ አንድነት አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው? አንድ ወንድም ሕሊናው ፈቅዶለት የወሰደውን እርምጃ ለመንቀፍ የምንቸኩል ከሆነ ጳውሎስ ከላይ ያነሳውን ጥያቄ ራሳችንን መጠየቃችን ምንኛ የተገባ ነው!

ጥያቄዎች ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ይረዱናል

ከላይ የተመለከትናቸው ጥቂት ምሳሌዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ጥያቄዎች ኃይል እንዳላቸው ያሳያሉ። በእያንዳንዱ ጥያቄ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ መመርመራችን ነጥቡን በራሳችን ሕይወት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳናል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ሌሎች ጠቃሚ ጥያቄዎችም እንዳሉ እናስተውላለን።—በገጽ 14 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ውስጣችንን ሰርስረው የሚገቡ ጥያቄዎች በጥልቅ እንዲነኩን መፍቀዳችን አእምሯችንንና ልባችንን ከይሖዋ የጽድቅ መንገዶች ጋር ለማስማማት ይረዳናል። ኢዮብ ይሖዋ ጥያቄዎችን ካቀረበለት በኋላ “ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤ አሁን ግን ዐይኔ አየችህ” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 42:5) አዎ፣ ኢዮብ ይሖዋ በፊቱ እንዳለ ሆኖ እስኪሰማው ድረስ ይበልጥ እውን ሆኖለት ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት የተናገረው ሐሳብ በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት ጥያቄዎች ተጠቅመን ራሳችንን መመርመራችን ያለውን ጥቅም ያጎላል። (ያዕ. 4:8) ጥያቄዎችን ጨምሮ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች በሙሉ በመንፈሳዊ እንድናድግና ይሖዋን ከምንጊዜውም የበለጠ በግልጽ ‘ማየት’ እንድንችል እንዲረዱን እንፍቀድ!

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከዚህ በታች የቀረቡትን ጥያቄዎች ራስህን መጠየቅህ ይሖዋ ለነገሮች ያለው ዓይነት አመለካከት እንድታዳብር የሚረዳህ እንዴት ነው?

▪ “ ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣ በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን?”—1 ሳሙ. 15:22

▪ “ ዐይንንስ የሠራ እርሱ አያይምን?”—መዝ. 94:9

▪ “ ሰዎችስ ለራሳቸው ክብር መፈለጋቸው ያስከብራቸዋል?”—ምሳሌ 25:27 NW

▪ “ በውኑ ልትቈጣ ይገባሃልን?”—ዮናስ 4:4

▪ “ አንድ ሰው ዓለሙን ሁሉ የራሱ ቢያደርግ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?”—ማቴ. 16:26

▪ “ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?”—ሮም 8:35

▪ “ ያልተቀበልከው ምን ነገር አለህ?”—1 ቆሮ. 4:7

▪ “ ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ያገናኘዋል?”—2 ቆሮ. 6:14

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ ይሖዋ ካቀረበለት ጥያቄዎች ምን ትምህርት አግኝቷል?