በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወጣቶች መንፈሳዊ እድገት እያደረጋችሁ ነውን?

እናንት ወጣቶች መንፈሳዊ እድገት እያደረጋችሁ ነውን?

እናንት ወጣቶች መንፈሳዊ እድገት እያደረጋችሁ ነውን?

ሂዴኦ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የነበረበትን ጊዜ መለስ ብሎ ሲያስታውስ እንዲህ ይላል:- “በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ብገኝም ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት ግን አልነበረኝም። የምፈልገው አብረውኝ በሚማሩት ልጆች ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍና ከሴት ጓደኛ ጋር መታየት ነበር። ይህ ነው የምለው ግብም ሆነ መንፈሳዊ እድገት የማድረግ ፍላጎት አልነበረኝም።” ልክ እንደ ሂዴኦ ሁሉ በርካታ ወጣቶችም ጠቃሚ የሆኑ ግቦች ላይ የመድረስ ወይም እድገት የማድረግ ፍላጎት ሳይኖራቸው እንዲያው ለይስሙላ ያህል በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ይመላለሳሉ።

ወጣት ከሆንክ አንተም በስፖርት ወይም በአንድ ዓይነት የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ እንቅስቃሴ መካፈል ያስደስትህ ይሆናል። መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ግን የዚያን ያህል ቀልብህን አይስቡት ይሆናል። መንፈሳዊ ግቦችን በማውጣት ደስታ ማግኘት ይቻላል? “የእግዚአብሔር ሥርዐት የታመነ ነው፤ አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል . . . የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፣ ዐይንን ያበራል” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት ልብ በል። (መዝሙር 19:7, 8 አ.መ.ት) የአምላክ ቃል ‘አላዋቂው’ ወይም ተሞክሮ የሚጎድለው በጥበብ እንዲመላለስ በማድረግ ‘ዓይኖቹ እንዲበሩ’ ያደርጋል። በእርግጥም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ልትደሰት ትችላለህ። ሆኖም እንደዚህ ዓይነት ዝንባሌ እንድታዳብር ምን ሊረዳህ ይችላል? በቅድሚያ ልትወስደው የሚገባህ እርምጃስ ምንድን ነው?

አምላክን የማገልገል ፍላጎት አዳብር

በመጀመሪያ አምላክን የማገልገል ፍላጎት መኮትኮት ያስፈልግሃል። የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ወጣቱ ኢዮስያስ ያደረገውን ተመልከት። የይሖዋን ሕግ የያዘው መጽሐፍ በቤተ መቅደሱ በተገኘ ጊዜ ኢዮስያስ መጽሐፉ እንዲነበብለት አደረገ። ከዚያም በሰማው ነገር በጥልቅ በመነካቱ “ከእስራኤል ልጆች ምድር ሁሉ ርኩሱን ሁሉ አስወገደ።” (2 ዜና መዋዕል 34:14-21, 33) ኢዮስያስ የአምላክ ቃል ሲነበብ መስማቱ እውነተኛውን አምልኮ በማስፋፋት በኩል የበለጠ ተሳትፎ እንዲያደርግ አነሳስቶታል።

አንተም መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ በማንበብና ባነበብከው ላይ በማሰላሰል ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት ልትኮተኩት ትችላለህ። ሂዴኦ አምላክን የማገልገል ፍላጎት እንዲያዳብር የረዳው ይህ ነው። ሂዴኦ በዕድሜ ከእሱ ከሚበልጥ ከአንድ አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ከሆነ የይሖዋ ምሥክር ጋር የቅርብ ወዳጅነት መሠረተ። አቅኚው ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከመሆኑም በላይ የተማረውን በሕይወቱ ተግባራዊ ለማድረግ ይጥር ነበር። ሂዴኦ በአቅኚው ምሳሌነት በጣም ስለተበረታታ እሱም መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናትና የተማረውን ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ፤ ይህም አምላክንና ሌሎች ሰዎችን የማገልገል ጠንካራ ፍላጎት እንዲያዳብር ረዳው። መንፈሳዊ እድገት ማድረጉ ሕይወቱ ትርጉም ያለው እንዲሆንለት ረድቶታል።

ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ አምላክን የማገልገል ፍላጎት ሊያዳብሩ ይችላሉ። ታካሂሮ እንዲህ ይላል:- “ልተኛ አልጋ ላይ ከወጣሁ በኋላ የዕለቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን እንዳላደረግሁ ትዝ ሲለኝ ከተኛሁበት እነሳና አነባለሁ። ይህም ይሖዋ እንደሚመራኝ ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጎኛል። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቤ መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ ከፍተኛ እገዛ አድርጎልኛል። በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ተሳትፎ ለማድረግ ስለፈለግሁ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። በዚህ አገልግሎት ከፍተኛ ደስታ አግኝቻለሁ።”

መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ በተጨማሪ ይሖዋን የማወደስ ልባዊ ፍላጎት ለማዳበር ምን ሊረዳህ ይችላል? ቶሞሂሮ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተማረው ከእናቱ ነው። እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ ባሳየን ፍቅርና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በጥልቅ የተነካሁት በ19 ዓመቴ ሕይወት ዓላማ አለው የተባለውን መጽሐፍ በግሌ ካጠናሁ በኋላ ነበር። አምላክ ላሳየን ፍቅር ያደረብኝ አድናቆት በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ተሳትፎ እንዳደርግ አነሳሳኝ።” (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) እንደ ቶሞሂሮ ሁሉ ሌሎች በርካታ ወጣቶችም ትጋት የተሞላበት የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረጋቸው መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።

እንደዚህ አድርገህም እንኳን ይሖዋን ለማገልገል የሚገፋፋ ልባዊ ፍላጎት ማዳበር ቢሳንህስ? እርዳታ ማግኘት የምትችልበት መንገድ ይኖር ይሆን? ሐዋርያው ጳውሎስ “መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 2:13) ይሖዋ እንዲረዳህ በጸሎት ከጠየቅኸው መንፈስ ቅዱሱን አብዝቶ በመስጠት ‘ለማድረግ’ ብቻ ሳይሆን ‘ለመፈለግም’ የሚገፋፋ ኃይል ይሰጥሃል። ይህም ማለት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በይሖዋ አገልግሎት የምትችለውን ያህል ለማድረግ እንድትነሳሳ ያበረታሃል እንዲሁም በመንፈሳዊ እንድታድግ ይረዳሃል። እንግዲያው በይሖዋ ኃይል በመታመን ልብህን አጠንክር!

ለራስህ ግብ አውጣ

ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ መንገድ ለማገልገል ልባዊ ፍላጎት ካዳበርህ በኋላ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንድትችል ለራስህ ግቦች ማውጣት ይኖርብሃል። ማና የተባለች አንዲት ክርስቲያን ወጣት እንዲህ ብላለች:- “ግብ ማውጣቴ በጣም ጠቅሞኛል። በመንፈሳዊ ሁኔታ ከማሽቆልቆል ይልቅ በድፍረት ወደፊት እንድራመድ አስችሎኛል። ግቤን በአእምሮዬ ይዤ ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠኝ አጥብቄ ጸለይኩ፤ በመሆኑም ትኩረቴ በሌሎች ነገሮች ሳይወሰድ እድገት ማድረግ ችያለሁ።”

የምታወጣቸው ግቦች ምክንያታዊና ሊደረስባቸው የሚቻል መሆን አለባቸው። በየዕለቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ምዕራፍ ማንበብ እንደ ምክንያታዊ ግብ ሊቆጠር ይችላል። ምርምር የማድረግ ፕሮግራምም ልታወጣ ትችላለህ። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ከመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) ላይ “ይሖዋ” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር “በስማቸው የተዘረዘሩ ባሕርያት” (“Qualities by Name”) በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር የተዘረዘሩትን ባሕርያት ማጥናት ትችላለህ። በዚህ ርዕስ ሥር 40 የሚያክሉ ባሕርያት ተዘርዝረዋል። ወይም በታኅሣሥ 15 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ በሚወጣው የርዕስ ማውጫ ላይ “ይሖዋ” በሚለው ርዕስ ሥር ያሉትን ሐሳቦች መመልከት ትችላለህ። በእነዚህ ባሕርያት ላይ ምርምር ማድረግህ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ እንደሚረዳህና እሱን ለማገልገል እንደሚያነሳሳህ ምንም ጥርጥር የለውም። ልትደርስባቸው ከምትችላቸው ሌሎች ግቦች መካከል አድማጮች ተሳትፎ እንዲያደርጉ በሚጋብዙ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ቢያንስ አንድ ጊዜ ሐሳብ መስጠት፣ በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ቢያንስ ከአንድ ሰው ጋር ቀረብ ብለህ ለመጨዋወት መሞከር እንዲሁም ወደ ይሖዋ ሳትጸልይና ስለ እርሱ ለሌሎች ሳትመሰክር አንድም ቀን እንዳያልፍ መጣር ይገኙበታል።

በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ገና አልተመዘገብህ ከሆነ ይህ ልትደርስበት የምትችል ጥሩ ግብ ነው። ለሕዝብ በሚሰጠው ምስክርነት መካፈል ጀምረሃል? አልጀመርክ ከሆነ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ጥረት ልታደርግ ትችላለህ። ቀጣዩ እርምጃ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ስለመሠረትከው ዝምድና በጥልቅ ማሰብና ከዚያም ራስህን ለእሱ መወሰን ይሆናል። ብዙ ወጣቶች ከዚህ ውሳኔያቸው ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ሲሉ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል ግብ ያወጣሉ።

ግብ ማውጣት ጥሩ ነገር ቢሆንም የፉክክር መንፈስ እንዳታዳብር መጠንቀቅ ይኖርብሃል። በምታከናውነው ነገር የበለጠ ደስታ ማግኘት የምትችለው ራስህን ከሌሎች ጋር የማታወዳድር ከሆነ ነው።​—⁠ገላትያ 5:26፤ 6:4

ምናልባት ተሞክሮ እንደሚጎድልህና በዚህም የተነሳ ምክንያታዊ የሆኑ ግቦችን ማውጣት እንደሚያስቸግርህ ይሰማህ ይሆናል። ከሆነ “ጆሮህን አዘንብለህ የጠቢባንን ቃላት ስማ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመከተል የወላጆችህን ወይም የሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖችን እርዳታ ጠይቅ። (ምሳሌ 22:17) እርግጥ ነው፣ ወላጆችህም ሆኑ ሌሎች ሰዎች በሚያወጡልህ ግቦች ረገድ ምክንያታዊ ሊሆኑና ግብህ ላይ ለመድረስ በምታደርገው ጥረትም ሊያበረታቱህ ይገባል። ወጣቶች ሌሎች ሰዎች ያወጡላቸው ግቦች ላይ እንዲደርሱ ግፊት እንደሚደረግባቸው ሆኖ ከተሰማቸው ደስታቸውን ሊያጡና ግብ የማውጣቱም ዓላማ ሊበላሽ ይችላል። አንዲት ወጣት ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ገጥሟት ነበር። እንዲህ ትላለች:- “ወላጆቼ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ማቅረብ፣ በመስክ አገልግሎት መካፈል፣ መጠመቅና ከዚያም አቅኚ መሆን የመሳሰሉትን ተከታታይና በርካታ ግቦችን አውጥተውልኝ ነበር። እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት አደርግ ነበር። አንዱ ግብ ላይ ስደርስ ወላጆቼ ያደረግሁትን ጥረት ከማድነቅ ይልቅ ሌላ ግብ ያወጡልኝና እዚያ ግብ ላይ እንድደርስ ይጠብቁብኝ ነበር። በመሆኑም ሁልጊዜ ግፊት እንደሚደረግብኝ ሆኖ ይሰማኝ ነበር። ሁኔታው አድካሚ ሆኖብኝ ስለነበር ባገኘሁት ስኬት አልደሰትም ነበር።” ስህተቱ ምኑ ላይ ነው? ያወጡላት ግቦች በሙሉ ምክንያታዊ ቢሆኑም ግቦቹ ግን የራሷ አልነበሩም። ጥረትህ እንዲሳካ በራስህ ተነሳሽነት ግቦች የማውጣት ፍላጎት ማዳበር ይኖርብሃል!

ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ምሳሌ አድርገህ ተመልከት። ወደ ምድር ሲመጣ አባቱ ምን እንዲያደርግ እንደሚፈልግበት ያውቅ ነበር። የይሖዋን ፈቃድ መፈጸም አባቱ ለእርሱ ያስቀመጠለት ግብ ብቻ ሳይሆን ሊያከናውነው የሚገባ ተልዕኮ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ የተሰጠውን ሥራ የተመለከተው እንዴት ነበር? “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:34) ኢየሱስ የይሖዋን ፈቃድ መፈጸምና አባቱ የሚጠብቅበትን ነገር ማድረግ ያስደስተው ነበር። ኢየሱስ እንዲያከናውነው የሚጠበቅበትን ሥራ በመፈጸም ደስታና እርካታ አግኝቷል፤ ሥራው ለእርሱ እንደ ምግብ ሆኖለት ነበር። (ዕብራውያን 10:5-10) አንተም ወላጆችህ እንድታከናውን የሚፈልጉብህን ነገር ለማከናወን ከልብህ ከተነሳሳህ በሥራህ ደስታ ልታገኝ ትችላለህ።

መልካም ሥራ ለመሥራት አትታክት

አንድ ጊዜ ግብ ካወጣህ ግብህ ላይ ለመድረስ ትጋት የተሞላበት ጥረት አድርግ። ገላትያ 6:9 “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት” ይላል። በራስህ ጥንካሬና ችሎታ አትታመን። እንቅፋቶች ሊያጋጥሙህና አልፎ አልፎም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊያድርብህ ይችላል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “በመንገድህ ሁሉ [አምላክን] እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” በማለት ያበረታታናል። (ምሳሌ 3:6) መንፈሳዊ ግቦችህ ላይ ለመድረስ በምትጥርበት ጊዜ ይሖዋ ይደግፍሃል።

በእርግጥም ይሖዋን ለማገልገል ልባዊ ፍላጎት በማዳበርና መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ በመጣጣር “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ” ማድረግ ትችላለህ። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) ይህም አምላክን በማገልገል ትርጉም ያለው ሕይወት እንድትመራ ያስችልሃል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ባነበብከው ላይ ማሰላሰል ይሖዋን የማገልገል ውስጣዊ ፍላጎት እንድታዳብር ይረዳሃል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ አባቱ የሚጠብቅበትን ፈጽሟል