ሳፋንን እና ቤተሰቡን ታውቃቸዋለህ?
ሳፋንን እና ቤተሰቡን ታውቃቸዋለህ?
መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ሳፋንና አንዳንድ የቤተሰቡ አባላት የተጠቀሱባቸውን ቦታዎች አስተውለሃል? እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ምንስ አድርገዋል? ከእነርሱ ምን ልንማር እንችላለን?
መጽሐፍ ቅዱስ “የሜሶላምን ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን” ኢዮስያስ በ642 ከዘአበ እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ከማቋቋሙ ጋር አያይዞ ይጠቅሰዋል። (2 ነገሥት 22:3) ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ እስከጠፋችበት ጊዜ ድረስ ባለው 36 ዓመት ውስጥ አኪቃም፣ ኤልዓሣ፣ ገማርያና ያእዛንያ ስለተባሉ አራት ልጆቹ እንዲሁም ሚክያስና ጎዶልያስ ስለተባሉ ሁለት የልጅ ልጆቹ ተጠቅሶ እናገኛለን። (ሠንጠረዡን ተመልከት።) “የሳፋን ቤተሰብ ከንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ተማረኩበት ጊዜ ድረስ [በይሁዳ መንግሥት ውስጥ] የንጉሡ ጸሐፊ ከመሆን አንስቶ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።” ሲል ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ ይገልጻል። ስለ ሳፋን እና ስለ ቤተሰቡ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ማንበባችን ነቢዩ ኤርምያስንና የይሖዋን እውነተኛ አምልኮ በመደገፍ ረገድ ያበረከቱትን ድርሻ እንድናስተውል ይረዳናል።
ሳፋን እውነተኛውን አምልኮ ደግፏል
በ642 ከዘአበ ንጉሥ ኢዮስያስ የ25 ዓመት ወጣት ሳለ ሳፋን የንጉሡ ጸሐፊና ገልባጭ ሆኖ ያገለግል ነበር። (ኤርምያስ 36:10) ይህ ሥራው ምንን ያካትት ነበር? ከላይ ያየነው የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው የንጉሡ ጸሐፊ የሆነ ሰው የገንዘብ ነክ ጉዳዮች ኃላፊና የንጉሡ አማካሪ ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑም በላይ ጥሩ የዲፕሎማሲ ችሎታ ያለውና ከውጪ አገሮች ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶች በቂ ልምድ ያካበተ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕጎችንና የንግድ ስምምነቶችን ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆን ይጠበቅበት ነበር።
ወጣቱ ኢዮስያስ ‘የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ የጀመረው’ ከአሥር ዓመት በፊት ነበር። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሳፋን ኢዮስያስን በዕድሜ ብዙ ይበልጠው ስለነበር ኢዮስያስ እውነተኛውን አምልኮ እንደገና ለማቋቋም ባደረገው የመጀመሪያ ዘመቻ ላይ ሊደግፈውና የአምልኮ ጉዳዮችን በተመለከተ ጥሩ ምክር ሊሰጠው የሚችል ሰው ነበር። a—2 ዜና መዋዕል 34:1-8
በቤተ መቅደሱ ጥገና ወቅት ‘የሕጉ መጽሐፍ’ የተገኘ ሲሆን ሳፋን “በንጉሡ ፊት አነበበው።” ኢዮስያስም በሕጉ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን ሲሰማ በጣም ስለደነገጠ የተጻፈው ነገር ምን እንደሚያመለክት ይሖዋን ጠይቃ እንድትነግራቸው ወደ ነቢይቱ ሕልዳና የታመኑ መልእክተኞችን ላከ። ንጉሡ ወደ ሕልዳና ከላካቸው መልእክተኞች መካከል ሳፋንና የሳፋን ልጅ አኪቃም ይገኙበታል። ይህም ንጉሡ ምን ያህል እንደሚተማመንባቸው ያሳያል።—2 ነገሥት 22:8-14፤ 2 ዜና መዋዕል 34:14-22
በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ አባት ወይም አያት ተደርጎ የተገለጸው ሳፋን ራሱ ያደረገውን ነገር አስመልክቶ በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ ተጽፎ የምናገኘው እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው። የሳፋን ልጅ ከነቢዩ ከኤርምያስ ጋር ይቀራረብ ነበር።
አኪቃምና ጎዶልያስ
ቀደም ሲል እንዳየነው የሳፋን ልጅ አኪቃም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው ወደ ነቢይቱ ሕልዳና ከተላኩት
መልእክተኞች መካከል እሱም እንደሚገኝ በሚገልጸው ዘገባ ውስጥ ነው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ምንም እንኳ አኪቃም ምን ዓይነት ማዕረግ እንደነበረው በዕብራይስጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ባይጠቀስም ከፍተኛ ቦታ እንደነበረው ግልጽ ነው” በማለት ይገልጻል።ይህ ከሆነ ከ15 ዓመታት በኋላ የኤርምያስን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ተከሰተ። ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ሊያጠፋ መሆኑን ለሕዝቡ ሲያስጠነቅቅ “ካህናትና ነቢያት ሕዝብም ሁሉ:- ሞትን ትሞታለህ . . . ብለው ያዙት።” ከዚያስ ውጤቱ ምን ሆነ? ዘገባው እንዲህ ሲል ይቀጥላል:- “በሕዝቡ እጅ እንዳይሰጥና እንዳይገድሉት የሳፋን ልጅ የአኪቃም እጅ ከኤርምያስ ጋር ነበረች።” (ኤርምያስ 26:1-24) ይህ ምን ያመለክታል? ዘ አንኮር ባይብል ዲክሽነሪ “ይህ አጋጣሚ አኪቃም ሥልጣኑን መጠቀሙን ብቻ ሳይሆን ልክ እንደሌሎቹ የሳፋን ቤተሰቦች ሁሉ ለኤርምያስ ብዙ መልካም ነገር ያደርግ እንደነበር ይጠቁማል” ሲል ይገልጻል።
ባቢሎናውያን በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምን አውድመው ሕዝቦቿን በምርኮ ከወሰዱ ከ20 ዓመታት በኋላ የአኪቃም ልጅ የሆነው የሳፋን የልጅ ልጅ ጎዶልያስ በቀሩት አይሁዳውያን ላይ ገዢ ሆኖ ተሾሞ ነበር። ልክ እንደሌሎቹ የሳፋን ቤተሰቦች ሁሉ ጎዶልያስም ለኤርምያስ መልካም ነገር ያደርግለት ይሆን? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ኤርምያስም የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ ምጽጳ ሄደ፣ ከእርሱም ጋር በአገሩ ውስጥ በቀሩት ሕዝብ መካከል ተቀመጠ።” በጥቂት ወራት ውስጥ ጎዶልያስ የተገደለ ሲሆን የተቀሩት አይሁዳውያንም ኤርምያስን ወደ ግብጽ ይዘውት ሄዱ።—ኤርምያስ 40:5-7፤ 41:1, 2፤ 43:4-7
ገማርያና ሚክያስ
የሳፋን ልጅ ገማርያና የልጅ ልጁ ሚክያስ በኤርምያስ ምዕራፍ 36 ላይ በተገለጸው ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ይህም የሆነው ንጉሥ ኢዮአቄም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት በ624 ከዘአበ ገደማ ነበር። የኤርምያስ ጸሐፊ ባሮክ የኤርምያስን ቃል በእግዚአብሔር ቤት “በሳፋን ልጅ በገማርያ ጓዳ” ጮክ ብሎ አነበበው። በዚህ አማካኝነት ‘የሳፋንም ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመጽሐፉ ለመስማት ችሏል።’—ኤርምያስ 36:9-11
ሚክያስ ለአባቱ እንዲሁም ለሌሎቹ መኳንንት በሙሉ ስለ ጥቅልሉ ሲነግራቸው ሁሉም ምን እንደሚል ለማወቅ ጓጉ። ከሰሙት በኋላ ምን አደረጉ? “ቃሉንም ሁሉ በሰሙ ጊዜ ፈርተው እርስ በእርሳቸው ተመካከሩ፣ ባሮክንም:- ይህን ቃል ሁሉ በእርግጥ ለንጉሡ እንናገራለን አሉት።” ሆኖም ንጉሡን ከማናገራቸው በፊት ባሮክን “አንተና ኤርምያስ ሂዱ፣ ተሸሸጉ፣ ወዴትም እንደ ሆናችሁ ማንም አይወቅ አሉት።”—ኤርምያስ 36:12-19
የፈሩት አልቀረም ንጉሡ በጥቅልሉ ውስጥ ያለውን ኤርምያስ 36:21-25) ጀረማያ አን አርኪኦሎጂካል ከምፓንየን የተባለው መጽሐፍ “ኤርምያስ በንጉሡ በኢዮአቄም ቤተ መንግሥት በነበረበት ወቅት ገማርያ በጣም ይረዳው ነበር” በማለት ይገልጻል።
መልእክት በመቃወም ጥቅልሉን አንድ በአንድ አቃጠለው። የሳፋንን ልጅ ገማርያን ጨምሮ አንዳንድ መኳንንት “ክርታሱን እንዳያቃጥል ንጉሡን ለመኑት፣ እርሱ ግን አልሰማቸውም።” (ኤልዓሣና ያዕዛንያ
በ617 ከዘአበ ባቢሎን የይሁዳን ግዛት ተቆጣጠረች። ነቢዩ ሕዝቅኤልን ጨምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አይሁዳውያንን “አለቆቹንም ሁሉ፣ ጽኑዓን ኃያላኑንም ሁሉ፣ ጠራቢዎቹንም ሁሉ፣ ብረት ሠራተኞቹን ሁሉ” በግዞት ወሰዱ። ባቢሎናውያን ሴዴቅያስ የሚል ስም የሰጡት ማታንያ አዲስ እንደራሴ ንጉሥ በመሆን ተሾመ። (2 ነገሥት 24:12-17) በኋላም ሴዴቅያስ የሳፋንን ልጅ ኤልዓሣን ጨምሮ ወደ ባቢሎን መልእክተኞችን ላከ። ኤርምያስም በግዞት ላሉት አይሁዳውያን ከይሖዋ የተላከውን ጠቃሚ መልእክት የያዘ ደብዳቤ ለኤልዓሣ በአደራ ሰጠው።—ኤርምያስ 29:1-3
የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው ሳፋን፣ ሦስቱ ልጆቹና ሁለቱ የልጅ ልጆቹ ሥልጣናቸውን እውነተኛውን አምልኮም ሆነ ታማኙን ኤርምያስን ለመደገፍ ተጠቅመውበታል። የሳፋን ልጅ የሆነው ያእዛንያስ? ሌሎቹ የሳፋን ቤተሰቦች ካደረጉት በተቃራኒ በግልጽ ጣዖት አምላኪ ሆኗል። ሕዝቅኤል ወደ ባቢሎን በግዞት በሄደ በስድስተኛው ዓመት ወይም በ612 ከዘአበ ገደማ 70 ሰዎች በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ ለጣዖት ሲያጥኑ በራእይ ተመልክቷል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል በስም የተጠቀሰው ያእዛንያ ብቻ መሆኑ የቡድኑ ዋና መሪ እንደነበር የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። (ሕዝቅኤል 8:1, 9-12) ፈሪሃ አምላክ ባለው ቤተሰብ ውስጥ ማደግ በራሱ አንድን ልጅ ታማኝ የይሖዋ አምላኪ እንደማያደርገው የያእዛንያ ምሳሌ ያሳያል። እያንዳንዱ ሰው ለሚያደርገው ነገር በኃላፊነት ይጠየቃል።—2 ቆሮንቶስ 5:10
የሳፋንና የቤተሰቡ ታሪክ
ሳፋንና ቤተሰቡ በኢየሩሳሌም በኃላፊነት ቦታዎች ላይ ይሠሩ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ሰነዶች ሕጋዊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በሰነዶቹ ላይ ማኅተም ማድረግ የተለመደ ነበር። ማኅተሞቹ የሚሠሩት ከከበሩ ድንጋዮች፣ ከብረት፣ ከዝሆን ጥርስ እንዲሁም ከመስታወት የነበረ ሲሆን ብዙውን ጊዜ በማኅተሙ ላይ የባለቤቱ ስም፣ የአባቱ ስምና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ማዕረጉ ይቀረጽ ነበር።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የዕብራውያን ማኅተሞች
ያረፉባቸው ሸክላዎች ተገኝተዋል። የዕብራውያን ጥንታዊ ጽሑፎች ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ናማን አቬጋድ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናውቃቸውን ሰዎች ስም በእነዚህ ማኅተሞች ላይ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ነገር ላይ በዕብራይስጥ ቋንቋ ተቀርጾ አናገኝም።” ሳፋን ወይም ቤተሰቡ ይጠቀምበት የነበረ ማኅተም ተገኝቷልን? አዎን፣ በገጽ 19 እና 20 ላይ በሚታየው ማኅተም ላይ የሳፋንና የልጁ የገማርያ ስም አለ።ምሁራን የአራቱን የሳፋን ቤተሰብ አባላት ማለትም የሳፋንን አባት የኤዜልያስን፣ የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን፣ የሳፋንን ልጅ የገማርያን እና “የቤቱ አለቃ” እንደሆነ ተደርጎ የተጠቀሰውን የጎዶልያስን ስሞች የያዙ ማኅተሞች አሉ የሚል ግምት አላቸው። ምንም እንኳ አራተኛው ማኅተም የጎዶልያስ አባት የሆነውን የአኪቃምን ስም የያዘ ባይሆንም ማኅተሙ የሳፋን የልጅ ልጅ የሆነው የጎዶልያስ እንደሆነ ይታመናል። በማኅተሙ ላይ የተጻፈው ማዕረጉ በግዛቱ ከነበሩት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ እንደነበረ ይጠቁማል።
ከሳፋንና ከቤተሰቡ ምን እንማራለን?
የነበራቸውን ከፍ ያለ ሥልጣን ታማኙን ኤርምያስንና እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ በመጠቀም ረገድ ሳፋንና ቤተሰቡ ግሩም ምሳሌዎች ናቸው! እኛም ብንሆን ያለንን ሃብትና ሥልጣን የይሖዋን ድርጅትና የእምነት አጋሮቻችንን ለመርዳት ልንጠቀምበት እንችላለን።
መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ከማንበባችንም በተጨማሪ በጥልቀት ምርምር በማድረግ ሳፋንንና ቤተሰቡን ስለመሳሰሉ በድሮ ዘመን ይኖሩ ስለነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ማወቃችን እምነታችንን ይገነባልናል። ምሳሌነታቸውን ልንኮርጅ ከምንችላቸው ‘እንደ ደመና ያሉ ምሥክሮች’ መካከል ናቸው።—ዕብራውያን 12:1
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢዮስያስ 25 ዓመት ገደማ ሲሆነው የሳፋን ልጅ አኪቃም ትልቅ ሰው የነበረ መሆኑ ሳፋን ከኢዮስያስ በጣም ይበልጥ እንደነበረ ያሳያል።—2 ነገሥት 22:1-3, 11-14
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሕልዳና—ተደማጭነት ያገኘች ነቢይት
ንጉሥ ኢዮስያስ በቤተ መቅደሱ የተገኘው ‘የሕግ መጽሐፍ’ ሲነበብ ከሰማ በኋላ ሳፋንንና ሌሎች አራት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ስለ መጽሐፉ “እግዚአብሔርን ጠይቁ” ብሎ አዘዛቸው። (2 ነገሥት 22:8-20) የተላኩት ሰዎች መልስ ከየት ሊያገኙ ይችላሉ? በወቅቱ ኤርምያስ ምናልባትም ናሆምና ዘካርያስ እንዲሁም ሌሎች ነቢያትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በይሁዳ የነበሩ ቢሆንም ልዑካኑ ቀርበው ለመጠየቅ የመረጡት ሕልዳናን ነበር።
ጀሩሳሌም—አን አርኪኦሎጂካል ባዮግራፊ የተባለው መጽሐፍ “በዚህ ታሪክ ውስጥ የሚታይ አንድ አስገራሚ ነገር ቢኖር ወንዶች የሕጉ ጥቅልል ምን እንደሚል ለማወቅ ወደ አንዲት ሴት መሄዳቸው ተገቢ ያልሆነ ነገር እንደሆነ የተሰማው ማንም ሰው አለመኖሩ ነው። ነቢይቱ የጌታን ቃል ስትነግራቸው ያለምንም ማንገራገር ተቀብለዋታል። ብዙውን ጊዜ በጥንት እስራኤል ዘመን ሴቶች ያበረክቱት የነበረውን ድርሻ የሚያጠኑ ምሁራን ይህን ታሪክ እምብዛም ትኩረት ሳይሰጡት አልፈዋል። በእርግጥም መልእክቱ ከይሖዋ የመጣ ነበር።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የሳፋን የዘር ሐረግ
ሜሶላም
↓
ኤዜልያስ
↓
ሳፋን
↓ ↓ ↓ ↓
አኪቃም ኤልዓሣ ገማርያ ያእዛንያ
↓ ↓
ጎዶልያስ ሚክያስ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገማርያና ሌሎች ሰዎች ኢዮአቄም ጥቅልሉን ከኤርምያስ ወስዶ እንዳያቃጥለው ለመኑት
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያእዛንያ የሳፋን ቤተሰብ አባል ቢሆንም ጣዖት ሲያመልክ በራእይ ታይቷል
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Courtesy Israel Antiquities Authority
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Courtesy Israel Antiquities Authority